1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራባዉያን እና የሩስያ ዉዝግብ

ሐሙስ፣ መስከረም 19 2015

ሰባተኛ ወሩን የያዘው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትና በዚህም ምክኒያት በምዕራባውያንና ሩሲያ መካከል የተፈጠረው የኢኮኖሚና፣ ዲፕሎማሲ ጦርነት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ ይህ ፍጥጫና አለመግባባት ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ክመቼውም ግዜ አሁን አሳስቢ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/4HXJy
Ukraine | Krieg | Scheinreferenden
ምስል Privat

ሩስያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ሊጣል ነዉ

ሰባተኛ ወሩን የያዘው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትና በዚህም ምክኒያት በምዕራባውያንና ሩሲያ መካከል የተፈጠረው የኢኮኖሚና፣ ዲፕሎማሲ ጦርነት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ ይህ  ፍጥጫና አለመግባባት ወዴት  ሊያመራ እንደሚችል ክመቼውም ግዜ አሁን አሳስቢ ሆኗል።

ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ሩሲያ በህግ ማስከበር ሰበብ ወደ ዩክሬን ዘልቃ ጦርነት ከከፍተች ወዲህ፤ የአውሮፓ ህብረት፤ አሜሪካና የሰባቱ ባለጸጋ አገሮች፤ በሩሲያ ላይ በርካታ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ እርምጃዎችን የወሰሰዱ ሲህን፤ ለዩክሬን ደግሞ በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብና የወታደራዊ ትጥቅ እርዳታ ለግሰዋል። በተለይ የአውሮፓ ህብረትና አባል አገሮቹ ለዩክሬን በገፍ ከሚያቀርቡት ወታደራዊና የገንዘብ እርዳታ በተጨማሪ፤ ሩሲያ ጦርነቱን እንድታቆም ለማስገደድ እስካሁን ሰባት ዙር የማዕቀብ ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል።

Ukraine | Krieg | Scheinreferenden
ምስል ITAR-TASS/IMAGO

ሆኖም ግን ጦርነቱ ሊቆም ወይም ሊያበቃ ቀርቶ እንደውም ወደ ሌላ ግን ከፍተኛ ደረጃ እየገባና ማብቂያ ግዜውም  እየተራዘመ እንደሆነ ነው አሁን በተጨባጭ እየታየ ያለው። ባለፈው ሳምንት ደግሞ በሩሲያ በተያዙት፤ በዶኔስክ፤ ሉሃንስክ፤ ዛፖሪዛሂያና ክሄርሶን ግዛቶች፤ ህዝበ ውሳኔ ተካሂዶ ድምጽ ከሰጠው ህዝብ ከ87 ከመቶ በላይ ከሩሲያ ጋር ለመቀልቀል መወሰኑ እተገለጸነው። ፕሬዚዳንት ፑቲን በነገው ዕለት ለፓርማቸው በሚያደርጉት ንግግርም በህዝበ ውሳኔው ውጤት መሰረት እነዚህ ግዛቶች የሩሲያ አካል መሆናቸውን ያበስራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአውሮፓ ህብረትና ምዕራባውያን ባጠቃላይ ግን፤ የህዝበ ውሳኔውን ሂደትና ውጤቱን ቀድመው በማውገዝ፤ እርምጃው የፕሬዝዳንት ፑቲንን ጦረኝነትና የመስፋፋት ፍላጎት የሚያረጋግጥ ነው በማለት በሩሲያ ላይ ተጨማሪ የማዕቀብና ሌሎች እርምጃዎችን እንደሚወስዱ እየገለጹ ነው። የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝድንት ወይዘሮ ኡርሱላ ቮንዴርሌየን፤ ፕሬዝዳንት ፑቲን የሚወስዷቸው እርምጃዎች እያካሂዱት ያለውን ህገወጥ ጦርነት እየገፉበት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፤ በማለት ትናንት አዲስ የማዕቀብ ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።ማዕቀቡ ፕሬዝዳንት ፕቲን በዩክሬን ግዛቶች ላካሂዱት ህገወጥ ህዝበ ውሳኔ፤ ጦርነቱን ለማስቀጠል ለተጠባብቂ ሀይላቸው ላደረጉት ጥሪና የኒውክለር ጦር መሳሪያ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ላሰሙት ዛቻ አጸፋ ነው ተብሏል። ወይዘሮ ቮንዴር ለየን የዚህን ማዕቀብ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት  ስገልጹም፤ “በዩክሬን የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ ተብየና ውጤቱን  አንቀበለውም። ክሬምሊን ይህን በማድረጉ ዋጋ እንዲከፍል ለማድረግ  ቁርጠኞች ነን፤ በማለት ፕሬዝደንት ፑቲን እነዚህን እርምጃዎች በመውሰድ በዩክሬን ላይ እየፈጸሙት ያለውን ህገ ወጥ ድርጊት የቀጠሉበት መሆኑን አረጋግጠዋል ብለዋል።

Ukraine | Krieg | Wolodymyr Selenskyj | Telefonat mit Joe Biden
ምስል Sarsenov Daniiar/Ukraine Presidency/Planet Pix/ZUMAPRESS/picture alliance

በህብረቱ በኩል የቀረበው ማዕቀብ በሩሲያ ነዳጅ ዋጋ ላይና ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ  ውጠቶችንና  የመለዋወጫ ዕቃውችን የሚያጠቃልል እንደሆነና፤ ይህም በርክታ ቢሊዮን ዶላር ሩሲያን እንደሚያሳጣት ተገልጿል። በተጨማሪም የአሁኑ ማዕቀብ የውሮፓ ዜግነት ያላቸውንና በሩሲያ ካምፓኒዎች በህላፊነት ወይም በቦርድ አባልነት የሚሰሩትን ግለሰቦችንም እንደሚያጠቃልል ተጠቅሷል። የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ሚስተር ጆሴፕ ቦሪየል ይህንን ሲያብራሩ “በአሁኑ ማዕቀብ ሊሎችን ቁልፍ ተዋናያንን ወይም ሰራተኖችንም  እንጨምራለን። እነዚህ ሰራተኖች ደግሞ ሩሲያኖች ብቻ ሳይሆኑ የህብረቱ አባል አገሮች ዜጎች ሆነው ማዕቀቦቹ የተፈለገውን ውጤት እንዳያመጡ ሩሲያን የሚያግዙ ናቸው” ብለዋል። ይህ አዲሱ በሩሲያ ላይ ሊወሰን የታቀደው ማዕቀብ ተግባራዊ እንዲሆን ግን  በ27ቱ አባል አገሮች መጽደቅ ይኖርበታል። ይህ ደግሞ በተለይ በአሁኑ አዳዲስ በማዕቀቦች ላይ ጥያቄ የሚያነሱ አባል መንግስታት ብቅ እያሉ ባለበት ወቅት ቀላል እንደማይሆን ነው የሚገመተው።

EU Josep Borrell
ምስል John Thys/AFP/Getty Images

ህዝበ ውሳኔውና ውጤቱ ግን ፕሬዝዳንት ፑቲን እነዚህን ግዛቶች የሩሲያ አካል ለማድረግና የሚያክሂዱት ጦርነትም የአገራቸውን ዳር ደንበር ለማስጠበቅ የሚደርጉት ህጋዊ ጦርነት እንደሆነ አድርገው ለመከራከር  ይጠቀሙበታል እየተባለ ነው። ከዚህ አንጻር አንዳንድ የፖለቲካ ተንትኖችና ታዛቢዎች፤ ይህ የሩሲያና ምዕራባውያን እሰጥ አገባና መካረር ፤ ዩክሬንን ፈጽሞ እያወደመ ያለውንና በአውሮፓም ከፍተኛ የኢኮኖሚ መናጋትና  የኑሮ ውድነት የፈጠረውን ጦርነት፤ እንዲቆም ሳይሆን  ይልቁንም እንዳያብሰውና እንዳያሰፋው ያሰጋል በማለት ስጋታቸውን እየገለጹ ነው ።

ገበያው ንጉሴ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ