1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙኒኩ የፀጥታ ጉባኤ

ሰኞ፣ የካቲት 9 2012

«ዓለም በጣም አደገኛ እና ብዙ ጊዜ ሕግ አልባ እየሆነች ነዉ። ምዕራቡ ደግሞ የማንነት ቀዉስ የተጠናወተዉ መስሏል። እየቀነሰ የመጣዉ የዓለም ምዕራባዊ የመሆን ዝንባሌ ብቻ ሳይሆን ምዕራቡ ራሱ ምዕራባዊ መሆኑ እያሽቆለቆለ ነዉ።---»

https://p.dw.com/p/3XuLs
MSC München John Kerry
ምስል picture-alliance/dpa/A.Vitvitsky

የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤና «የምዕራቡ ምርጡ» እሳቤ


እንደ ሐገር መሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈሉት የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚየር ዜሌንስኪ እንደ መሪ አምረርዉ ሩሲያን ወቅሰዉ፣ እንደ ድሮ ቀልደኛ አሹፈዉ-ጉባኤተኞችን አሳቁበት።የሞስኮ፣ ቤጂንግ፣የቴሕራን እና የዋሽግተን ባላንጦች ለ56ኛ ጊዜ ተወጋግዘዉ፣ ለዘመናት በፀና ትብብር የተወደጁት የአዉሮጳና የአሜሪካ ተወካዮች ተወራረፉበት።ለዓለም ሠላም መከበር፣ለሰብአዊ መብት፣ ለተፈጥሮ ሐብት መጠበቅ የሚከራከሩ ወገኖች የጉባኤተኞችን መርሕ ተቃወሙበት። የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ። የጉባኤዉ ምንነት፣ የጉባኤተኞች መልዕክትና የዓለም እዉነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነው።
                               
በመሪዎች ቀልደዉ፣ስቀዉ-አስቀዉ፣ከመሪ ጋር ተፎካክረዉ አምና ግንቦት መሪ የሆኑት ቮሎድሚየር ዜሌንስኪይ እንደ ቀልደኛነታቸዉ ዘመን አሹፈዉ የአዳራሹን ጭፍግ ዓየር ላፍታ በፈገግታ ገፈፉት።ቅዳሜ።ነገሩ እንዲሕ ነዉ።የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ባየሪሸር ሆፍ ከተባለዉ ትልቅ ሆቴል ትልቅ አዳራሽ ጎን ከተለጠፈችዉ ትንሽ አዳራሽ ለታደሙት ጉባኤተኞች ንግግር ለማድረግ ወደ መድረኩ ወጡ።ወጣቱ መሪ እንደ ቀልደኛ ከለመዱት መድረክ ሲደርሱ ግን ማይክራፎን የለም።አስተናጋጆቹን ጠየቁ።
 «ማክራፎን ማግኘት እችላለሁ።» መለሱም።«እንዲሁም መናገር እችላለሁ።
ዜሌንስኪ ቀልደኛም ሆኑ ፖለቲከኛ፣ ሞስኮዎች ግላሲኖስትና ፔሬስትሮይካን ዘምረዉ የፈረካከስዋት የቀድሞዋ ኃያል፤ ግዙፍ፤ ሰፊ ሐገር የሶቭየትሕብረት ፍርካሽ የአንዷ ዉጤት ናቸዉ።በ1990ዎቹ መጀመሪያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሶቭየቶች ሲፈረካከሱ፣ በርሊኖች ግንብ ፈርክሰዉ አንድ ሆኑ።
የመኖች የሰሜን ደቡብ፣ የካፒታሊስት-ሶሻሊስት ክፍፍላቸዉን በጦርም፣ በሴራም፣ በፍላጎትም ንደዉ አንድ ሲሆኑ፣ አዲስ አበቦች የሌኒን ሐዉልትን ገንድሰዉ የኤርትራን መሸረፍ አብስረዉ ወይም አርድተዉ ቀሪዋ ኢትዮጵያ በጎሳ የመሰነጣጠቅዋን መሰረት ጣሉ።

ሞስኮ፣ በርሊን፣ አደን-ሰነዓ ና አዲስአባባ  የሆነዉ የአድነት-ክፍፍል ተቃራኒ እዉነት አድርጋዊዎች አንድ የሚመስሉበት የጋራ ነገር ነበር። «ምዕራቡ ምርጡ-West is best»ን ካንጀትም ሆነ ካንገት ማቀንቀናቸዉ።ከርዕዮተ ዓለም እስከ ምጣኔ ሐብት መርሕ፣ ከፊልም እስከ ፋሽን ሌላዉ ቀርቶ ከዉበት እስከ ቅባት የምዕራቡ ዓለም አስተምሕሮ በሰፊዉ በሚለፈፍ፣ በሚዘመርበት በዚያ ዘመን ሌላ ባይ ከነር እሱ በርግጥ በአራዶቹ አገላለፅ «ፋራ» ነበር።

Livestream MSC 2020

የምዕራብ ምስራቆች ፍጥጫ በናረበት በ1963 የተጀመረዉ የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ፣ መስራቾቹ እንደሚሉት የተከፋፈለችዉ ዓለም እንደ 1930ዎቹ ማብቂያ ከአዉዳሚ ጦርነት እንዳትገባ ለመከላከል ፖለቲከኞች፣ዲፕሎማቶችና ሙሕራን እንዲመክሩበት ታስቦ ነዉ።ጉባኤዉ የምዕራቦች መርሕ የሚጫነዉ፣የምዕራብ ፖለቲከኛ፣ ዲፕሎማትና ሙሕራን የሚበዙበት በመሆኑ ምዕራቡ ዓለም ለሚከተለዉ መርሕ መጠናከር በዉጤቱም ለኮሚኒዝም ዉድቀት፣ ምዕራቡ ምርጡን ላስዘመረዉ ለወጥም አስተዋፅኦ ማድረጉ በርግጥ አላነጋገረም።
ካለፈዉ አርብ እስከ ትናንት የመከረዉ 56ኛ ጉባኤ፣ ከዓብይ ርዕሱ፣ እስከ ዐብይ ተሳታፊዎቹ የነገሩን ግን ምዕራቡ የሚመረጥበት ዘመን ከመጨረሻዉ መጀመሪያ መድረሱን ጠቋሚ ነዉ።ሶቭየቶችን፣ ዩጎዝላቪያዎችን፣ ቼኮዝላቪያን ፈረካክሶ፣ ኢትዮጵያን ገምሶ፣ የመኖች፣ ጀርመኖችን አዋሕዶ ኮሚኒዝምን በተለይ አዉሮጳና አፍሪቃ ላይ ሙሉ በሙሉ የቀበረዉ የምዕራቦቹ የጋራና ሁለንተናዊ ግፊት ነበር።
የሙኒኩ ጉባኤ ዋና አዘጋጅ ቮልፍጋንግ ኢሽንገር ለጉባኤተኞች እንደነገሩት ምዕራቡ የዓለምን የዓለም የመሪነት ስልጣን ወይም ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ በተረከበ በ30ኛ ዓመቱ አመራሩ ወደፍፃሜዉ የተቃረበዉ በሌሎች ግፊት ሳይሆን የምዕራቡ አንድነት ክፉኛ በመሸርሸሩ ነዉ።
 

Wolfgang Ischinger Sicherheitskonferenz
ምስል Ren Ke/dpa/picture-alliance

«ዓለም በጣም አደገኛ እና ብዙ ጊዜ ሕግ አልባ እየሆነች ነዉ።ምዕራቡ ደግሞ የማንነት ቀዉስ የተጠናወተዉ መስሏል።እየቀነሰ የመጣዉ የዓለም ምዕራባዊ የመሆን ዝንባሌ ብቻ ሳይሆን ምዕራቡ ራሱ ምዕራባዊ መሆኑ እያሽቆለቆለ ነዉ።የዘንድሮዉ የ2020 የሙኒክ ጉባኤያችን ዘገባ በአርቴፊሻል ቃላት እንዲሰየም ያደረግነዉም ለዚሕ ነዉ።ስያሜዉ «ምዕራባዊነትን የቀነሰ» WESTLESSNESS የሚል ነዉ።»

የ35 ሐገራት ርዕሳነ ብሔራትና መራሕያነ መንግስታት ተካፍለዉበታል።ከሰባ የሚበልጡ መንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ድርጆች ባለስስልጣናት፣ ፌስቡኩን የመሳሳሉ ኩባንዮች ባለቤቶች፣ ዲፕሎማቶችና አጥኚዎች ተካፍለዉበታል።በድምሩ አምስት መቶ ግድም።

የሊቢያ እና ሳሕል የተባለዉ አካባቢ ሰላምና ፀጥታ ጉባተኞች ከተነጋገሩባቸዉ ርዕሶች አንዱ ነዉ።ስለአፍሪቃ በመከረዉ ጉባኤ ላይ አንድም አፍሪቃዊ መሪ አለመገኘቱ እንጂ ድንቁ።አፍሪቃዉያን መሪዎች በጉባኤዉ አለመካፈላቸዉ ምዕራባዊነት በቀነሰበት ዘመን ከምዕራቦች ጉያ የመዉጣታቸዉ ምልክት ይሁን አይሁን በዉል አልታወቀም። 
የጀርመኑ ፕሬዝደንት ፍራንክ-ቫልተር ሽታይማየር ባለፈዉ አርብ ጉባኤዉን በይፋ ሲከፍቱ እንዳሉት ግን ለምዕራቦች አንድነት መሸርሸር ተጠያቂዉ የአፍሪቃዉያን ማመንታት፣ የሩቁ ጫና ሳይሆን የዶናልድ ትራምፕዋ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።

«ዓለም አቀፍ ትብብርን፣ የዓለም ሰላምን ወደማስከበር ከፍ ከማድረግ አላማችን ከዓመት ዓመት እየተንሸራተትን ነዉ።የታላላቅ ኃይላት ፉክክር በዘመናችን የስልታዊ ጉዳይ የጥናት ወረቀቶችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ያለዉን ተቸባጭ እዉነታ ጭምር እያንፀባረቀ ነዉ።የቅርብ ተባባሪያችን፣ የዩናይትድ ስቴትስ የወቅቱ አስተዳደር፣ የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ የሚለዉን ሐሳብ ራሱን ዉቅድቅ ያደረገዉ መስሏል።ሁሉም የየራሱን (መርሕ) በተናጥል መወሰን ይችል ይመስል።»
የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፒዮ በመስተዳድራቸዉ ላይ የሚሰነዘረዉን ወቀሳና ትችት አጣጥለዉ ነዉ የነቀፉት።ፖፒዮ፣ ፕሬዝደንት ትራምፕ ስልጣን ከያዙበት ከ2017 ጀምሮ እስከ ዘንድሮዉ እስከ ፕሬዝደንት ሽታይንማየር ድረስ ስለመስተዳድራቸዉ የተሰነዘሩ አስተያየቶችን እየጠቀሱ፣ እየነቀፉም ምዕራቡ ዛሬም «እያሸነፈ ነዉ» ይላሉ።
«የመጨረሻዉ (አስተያየት) ትናንት የተሰጠ ነዉ።እጠቅሳለሁ፤«ዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብን ዉቅድ እያደረገች ነዉ።» የጥቅሱ መጨረሻ።ዛሬ ጠዋት እዚሕ የተገኘሁት ዕዉነቱን ልነግራችሁ ነዉ።እነዚያ መግለጫዎች በየትኛዉም መንገድ ተጨባጭ አይደሉም፣ ወይም እዉነታዉን እያንፀባርቁም። የአትላንቲክ ማዶ-ለማዶ ትብብር ሞቷል የሚለዉ አባባል በጣም የተጋነነ መሆኑን በደስታ እነግራችኋለሁ።ምዕራቡ እያሸነፈ ነዉ። እኛ በጋራ እያሸነፍን ነዉ።በጋራ እያደረግነዉ ነዉ።»
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ የትራምፕን መስተዳድር በመዉቀስ  ከጀርመኑ ፕሬዝደንትም ጠንከር ያለ መልዕክት ነዉ ያስተላለፉት። አዉሮጳ እራሷን ችላ ዘለግ ላለ ጊዜ የሚፀና ስልት መንደፍ እንደሚገባት ማክሮ የአዉሮጳ ወዳጆቻቸዉን አሳስበዋል።
«የመደራደር ነፃነት እንኳን ከሌለን፣ የዉጪ መርሐችን ተዓማኒነት ሊኖረዉ አይችልም።የዩናይትድ ስቴትስ ታናሽ ወዳጆች መሆንም አንችልም።ምክንያቱም የተለያየ አመለካከት አለንና። ይሕን ደግሞ መቀበል አለብን። ስለኢራን የተለያየ አመለካከት አለን።የገንዘብ፣ የምጣኔ ሐብት እና ወታደራዊ ስልት ከሌለን ትክክለኛ የዉጪ መርሕ ሊኖረን አይችልም።»   
ለሩሲያ፣ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ጀምሮ ባንድ አብረዉ የሚተገትጓት የአትላንቲክ ማዶ ለማዶ ጥብቅ ወዳጆች መቃቃር፣ ከሰማይ እንደወረደ መና የሚቆጠር ነዉ። አንጋፋዉ የሩሲያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ አጋጣሚዉን ለመጠቀም ሁለቴ ማሰብ አላስፍለጋቸዉም።የሩሲያዉ ዲፕሎማት እሁለት ከተገመሱት የሐገራቸዉ ነባር ጠላቶች ማንን ደግፈዉ ማንን እንደሚወቅሱም ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።
«የመተማመን ቀዉስ ስር እየሰደደ ነዉ። በተለይ በአዉሮጳ ጉዳይ ዉጥረቱ እየተባባሰ ነዉ።የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ወታደራዊ መዋቅር ወደ ምስራቅ እየተስፋፋ ነዉ። ወታደራዊ ልምምዶች ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ እየተጠናከሩ ነዉ። ወታደራዊ በጀት እያሻቃበ ነዉ።ይህ ሁሉ መተማመንን እያሳጣ ነዉ። የቀዝቃዛዉ ጦርነት ዓይነት ፍጥጫ በጦር መሳሪያ ጭምር እየተጠናከረ ነዉ።»
ከወትሮዉ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሐብት ፉክክር በተጨማሪ አዉሮጶች የሩሲያ ጋስ ወደ ግዛታቸዉ የሚፈስበት ረጅም ቧምባ ለመዘርጋት ከሩሲያ ጋር ያደረጉት ስምምነትም ዋሽግተኖችን አስቆጥቷል።የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ መስተዳድር «ስትሪም 2»  በተባለዉ የጋስ መስመር ግንባታ ላይ በሚሳተፉ ኩባንዮች ላይ ማዕቀብ ለመጣል ዝቷልም። ዛቻዉ ባለፉት 2 ዓመታት በኢራን፣ በዓለም የተፈጥሮ ጥበቃ ስምምነት እና በንግድ ሰበብ የሚወዛገቡትን የአትላንቲክ ማዶ ለማዶ ወዳጆችን ጥብቅ ትብብር ይበልጥ እያመነመነዉ ነዉ።
ከግዙፍ ሆቴል ዉጪ የተሰለፉት የመብት፣ የፍትሕ፣ የእኩልነትና የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች ግን ምዕራብን ከምሥራቅ፣ አዉሮጳን ከአሜሪካ ሳይለዩ ሁሉንም አወገዙ-ለሶስት ቀን።
«በዚሕ ጉባኤ የሚታየዉን የኔቶን መርሕን ለመቃወም ነዉ የተሰለፍነዉ። ለጦር ኃይል ተጨማሪ ገንዘብ የማዉጣቱ ፖለቲካዊ እሳቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ነዉ። ለማሕበራዊ መስኮች፣ ለጤና፣ለትምሕርትና ለመሳሰሉት ገንዘብ ከመመደብ ይልቅ ሁል ጊዜ ፀጥታ፣ፀጥታ፣ፀጥታ ብቻ ነዉ የሚባለዉ።»
ካዳራሹ ዉስጥ የታደሙት ከዉጪ የተሰለፉትን ሰዎች ጩኸት መስማታቸዉ ጥርጥር የለዉም። ሰሙት እንጂ ግን አልተቀበሉትም።ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ዓለምን የሚዘዉረዉ የምዕራቡ ዓለም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊና ባሕላዊ አስተሳሰብ የአደባባይ ተቃዉሞ ተለይቶት አያዉቅም። ይሁንና አሁን ፈተና የገጠመዉ ከአደባባይ ሰልፈኞች፣ በአስተሳሰቡ አራማጆች መካከል ከተፈጠረዉ ክፍፍል ወይም ከነባር ተቀናቃኛቸዉ ከሩሲያ ብቻ አይደለም።ከእስያ ጭምር እንጂ።
በቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ወቅት የምዕራባዉያን «ተመፅዋች» የነበሩት ቻይና እና ሕንድ ዛሬ ከምዕራቦች ጋር «ትከሻ እየተለካኩ» ነዉ። የዛሬ አስር ዓመት ግድም መካከለኛ ገቢ የነበረዉ የእስያ ሕዝብ 500 ሚሊዮን አይሞላም ነበር።ዘንድሮ ከ1.75 ቢሊዮን በልጧል። የእስያ በተለይም የቻይና እና የሕንድ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት በእስካሁን ፍጥነቱ ቀጠለ-የምጣኔ ሐብት ተንታኞች እንደሚሉት፣ ከ2050 በኋላ ቻይኖች አሜሪካን፣ ሕንዶች የቀድሞ ቅኝ ገዢያቸዉ ብሪታንያን የማይበልጡበት ምክንያት አይኖርም። ያኔስ «East is best» ይባል ይሆን-በቻይንኛ። የሚኖሩ ያስቡበት።

Deutschland Münchener Sicherheitskonferenz | Polizei
ምስል picture-alliance/ZUMAPRESS/S. Babbar
Münchner Sicherheitskonferenz
ምስል picture-alliance/dpa/M. Dalder
München MSC US-Außenminister Mike Pompeo
ምስል AFP/A. Caballero-Reynolds

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ