1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምርጫው ቀን መራዘም፣ በዐባይ ግድብ የግብፅ አዲሱ አቋም

ዓርብ፣ ግንቦት 13 2013

ባሳለፍነው ሳምንት በርከት ያሉ ርዕሰ ጉዳዮች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ሆነዋል። የስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ መራዘም እና በዐባይ ግድብ ሙሉት ላይ ግብጽ ያንጸባረቀችው አዲስ አቋም በተመለከተ ከተሰጡት አስተያየቶች የመራረጥነውን ለዕለቱ አጠናቅረናል።

https://p.dw.com/p/3tmaC
Facebook User Symbolbild
ምስል Reuters/D. Ruvic

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በያዝነው ግንቦት ወር ማለቂያ እንደሚካሄድ የተጠበቀው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሳምንታት መገፋቱ የተነገረው ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ነበር። የምርጫ ቦድር መረጃውን ይፋ እንዳደረገ በርካቶች በማኅበራዊ መገናኛው አስተያየታቸውን በየፈርጁ ሲገልጹ ተስተውሏል። ቢብ ማርሊ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ «ትክክለኛ ርምጃ ነው፣ ብዙ የሚቀድም ነገር አላት ሀገሪቱ።» በማለት ውሳኔውን በአዎንታነት ሲቀበሉ ፤ ጥሌ ዘሚግራ የተባሉት ሌላኛው የፌስቡክ ተጠቃሚም «አሁን ኢትዮጵያ የሚያሳስባት ምርጫ አይደለም፤ ሰላም እንጂ።» በማለት ድጋፋቸውን ገልጸዋል። ቄሮ ባራና በበኩላቸው፤ «አማራጭ ያልቀረበበት ምርጫ ስለሆነ በዚህም ሆነ በዚህ ብዙም አያስገኝም። ሀገር ሰላም ይሁን እንጂ ስለምርጫው አይሞቀኝ አይበርደኝ።» ነው የሚሉት። ጆሴ ዮሴፍ ፤ «መራዘሙ አግባብነት የለውም። በማለት ይቃወማሉ፤ ናሆም ናሆምም በተመሳሳይ፤ «ከዚህ ሁሉ ቢቀር አይሻልም?» ባይ ናቸው። ዘላለም አሳአ «ምንድነው አርዝመው አርዝመው ሰማይ ሊያደርሱ ነው እንዴ? ወይስ የምርጫ ቦርዱ ሠራተኞች አልወደዱም?» በማለት ይጠይቃሉ። በአፍሪቃው ቀንድ የሚካሄዱ ምርጫዎችን አስመልክቶ አሜሪካ ሁለት አቋም አላት የሚሉት ደግሞ ሁሴን ናቸው በትዊተር፤ «አሜሪካ፤ የሶማሊያ ምርጫ በምንም ዓይነት መልኩ መራዘም የለበትም።፤ አሁንም አሜሪካ ብሔራዊ መግባባት ላይ ሳይደረስ ምርጫ በኢትዮጵያ መደረግ የለበትም።» በማለት የተለያየ ያሉትን ምርጫን የተመለከተ የዩናይትድ ስቴትስን አቋም ለማሳየት ሞክረዋል። ትዕግስት እንዲሁ በትዊተር የኢትዮጵያን የምርጫ መራዘም ከኤርትራ ይዞታ ጋር ለንጽጽር አቅርበዋል፤ «አስቂኝ ዕውነታ» ያሉት ትዕግስት፣ «ከ30 ዓመታት በኋላም ኤርትራ የሽግግር መንግሥት ነው ያላት፤ ኢትዮጵያም ለመጪዎቹ ሦስት እና አራት አስርት ዓመታት ምርጫውን መግፋት ብትቀጥልበት አትገረሙ።» ትናንት ሐሙስ ከቀትር በኋላ ምርጫው የሚካሄድበት ቀን ተቆርጦ ይፋ ሆኗል። ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ እንደገለጸው ምርጫው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ,ም ይካሄዳል ተብሏል። አቢስ አርሳቢስ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «ይኼን ምርጫ እኮ መከራውን አበላችሁት» ብለው ሲቆረቆሩ፤ ቢኒት ኤ ሀሰን በበኩላቸው፤ «ገፍታችሁ ገፍታችሁ ሰኔ 14 አደረሳችሁት? ጊዜው ከሄደ አይቀር ለሐምሌ ይሁንልን፤ የሰኔን ወር አናምነውም። እንደውም ከውኃ ሙሌቱ በኋላ ቢሆን ተመራጭ ነው።» የሚል አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

Symbolbild Social Media
ምስል DW/S. Leidel
Äthiopien NEBE Amhara Büro
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

አሰፋ ሮባ ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ናቸው፤ «ጥሩ ጊዜ ነው፤ ከዚህ በላይ ወደክረምቱ መግፋቱ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አስቸጋሪ ስለሚሆን።» ሰይድ መሐመድ እንዲህ አሉ፤ «በኢትዮጵያውያን የተመረጠ ሕጋዊ መንግሥት እንፈልጋለን። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በበርካታ አቅጣጫዎች ተግዳሮት ውስጥ ናት፤ የወደፊቱ ከብልጽግና ጋር ብሩህ ነው።» ደምሴ ተመስገን «ወሬ ብቻ » በማለት ነው አስተያየታቸውን የጀመሩት፤ «ኢትዮጵያ ውስጥ በየቀኑ የሚፈጠሩ ችግሮች ተረጋግተው ምርጫ እንካሂዳለን ብለንካሰብን ተሳስተናል። እነዚህ ችግሮች የሚቆሙ ሳይሆኑ ባህሪያቸውን ቀይረው ሲፈልግ ብሔር ተኮር፤ አለያም ሃይማኖት ተኮር ሆኖ ይከሰታል። ይሁን እንጂ ሁሉ መቆም የሚችለው ምርጫ ተደርጎ ያለፈው አልፎ የወደቀው ደግሞ ተስፋ ሲቆርጥ ብቻ ነው።» ባይ ናቸው። ቴዎድሮስ ጉልማ ደግሞ፤ «ሰኔ 14 እኮ ሰኞ ቀን ነው የሚውለው፤ እሱ ደግሞ የሥራ ቀን ነው፤ ሥራ ይዘጋል?» ሲሉ ጠይቀዋል። እንደእሳቸው ሁሉ ብዙዎች ቀኑ የሥራ ቀን መሆኑን አስታወሰዋል። ደጀኔ አወቀ ደግሞ ሰግተዋል፣ «ወይ ይሄ ሰኔ ደግሞ ዞሮ መጣ?» ነው ያሉት። ሌሎችም ከዚህ ቀደም በሰኔ 15 እና 16 የተከሰቱ ድንገቴዎችን በማስታወስ ምርጫው በሰኔ ባይሆን አይነት አስተያየት ሰጥተዋል። ምርጫውን ለማካሄድ በሚከናወኑ ሂደቶች በሥራ የተሳተፉ ወገኖች ክፍያን በማንሳትም ጥያቄ የሰነዘሩ ጥቂት አይደሉም።  እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት 36,2 ሚሊየን መራጮች መመዝገባቸውን መገናኛ ብዙሃን ጠቁመዋል። ምርጫው የመራጮች ምዝገባ በተጠናቀቀባቸው ቦታዎች ብቻ እንደሚካሄድ ነው የተገለጸው።

Social Media Twitter Logo Symbolbild
ምስል picture alliance/ANP

ኢትዮጵያ በዐባይ ወንዝ ላይ በገነባችው ግድብ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት እንዳይከናወን የተለያዩ ምክንያቶችና ጥያቄዎችን ስታነሳ የከረመችው ግብጽ ከሰሞኑ አቋሟን ቀይራ ብቅ ብላለች። የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ባደረጉት ቃለመጠይቅ ኢትዮጵያ በቀጣይ ወራት ግድቡን ለመሙላት የምታደርገው እንቅስቃሴ በግብጾች የውኃ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አይኖረውም በማለት ነው ለዜጎቻቸው በአስዋን ግድብ ውስጥ በቂ የውኃ ክምችት መኖሩን ማረጋገጣቸው ተዘግቧል። ይኽን መሰሉ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስተያየት የተሰማው ኢትዮጵያ በመጪው የክረምት ዝናብ ወቅት ሁለተኛውን የግድቡን ሙሌት ለማካሄድ መዘጋጀቷን አጽንኦት ሰጥታ በይፋ መግለጽ በጀመረችበት በዚህ ወቅት በመሆኑ በርካታ የማኅበራዊ መገናኛው ተጠቃሚዎች በጥርጣሬ የተመለከቱት ይመስላል። አሳብነህ ደምል በፌስቡክ፤ «አይ ይች ሀገር የሆነ ያሰበችውማ ነገር አለ ማለት ነው። በየትኛው ሰዓት ጊዜ እና ቦታ እና ኢትዮጵያውያን ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል።» ሲሉ፤  ፀጋ ሥላሴ ከበደ በበኩላቸው፤ «ማዘናጊያ ነው።» ይላሉ። በላቸው በየነ፣ «አሁን ነው ጥበቃውን ማጠናከር፤ መዘናጋት አያስፈልግም።» በማለት መክረዋል። ተሾመ መሐመድ ጃርሶም ጠያቂ ናቸው፤ «ግብጽ ወደቀልቧ መመለሷ ጥሩ ነው። ነገር ግን ምን አስባ ነው? መንግሥታችን ጠንቀቅ ማለት ይበጃል!» ትሩሲል በትዊተር፤ «ይኽ ማስጠንቀቂያ ነው! ኢትዮጵያ ታጠቅ እና ራስሽን ተከላከይ። አንድ መጥፎ ነገር ሲያስቡ ጥርጣሬን የሚያስከትል እንዲህ ያለ ያልተጠበቀ ነገር ያደርጋሉ። ዐቢይ አህመድ አንድ ርምጃ ቅደምና ታዋቂ ሰዎችን ከመግደል አንስቶ የህዳሴ ግድቡን ኢላማ እስከማድረግ ድረስ አማራጮችን በሙሉ ዝጋባቸው። ማንኛውም ነገር ሊከሰት ይችላል!» በማለት ማሳሰቢያቸውን አስተላልፈዋል።  ሰሎሞን ተስፋዬም እንዲሁ፤ «ልናምናቸው አይገባም!» ነው የሚሉት። ከስጋቱና ጥርጣሬው ባሻገር ግብጽ ከዚህ የተሻለ ምርጫ የላትም ያሉም አልጠፉም፤ ኢንድሪስ አህመድ፤ «እንዲህ እያሉ ህዝባቸውን ቢያጽናኑ ይሻላቸዋል፤ ከኢትዮጵያ ጋር እሰጥ አገባ አያዋጣም።» ሲሉ ግዛቸው ግርማ በበኩላቸው፤ «ጉዳዩ ሞቷል፤ ከፕሮጀክቱ አካባቢ የመጣ መረጃ እንደሚያሳየው ሁለተኛው ሙሉት መጠናቀቁ ገብቷቸዋል። መሬት ላይ ያለውን እውነታ ከመቀበል ውጭ ሌላ ዕድል የላቸውም።» ባይናቸው። ዘሪሁን መሐመድ ደግሞ፤ «ፅናትና ጥንካሬ ካለህ ዓለም ያከብርሃል። ልፍስፍስና በቀላሉ ተጠምዛዥ ከሆንክ ሁሉም ይንቅሃል።» ነው የሚሉት። የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሉ የተባለው ቀድሞም ከኢትዮጵያ በኩል ሲነገር ነበር የሚሉት ኢዮብ ወንድሙ በትዊተር፤ «ይኽን ነበር ስንል የነበረው። ቅናትና ስስት ካልሆነ በቀር ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀሟ የማንምም ፍላጎት አይጎዳም። ግድቡን ሙሉ! ሌላም ግድብ ገንቡ!» በማለት መክረዋል መክረዋል። እንዲህ ያለው አዎንታዊ ሃሳብ በጣም አስፈላጊ ነው የሚሉት ፖቨርቲ ሶሉሽን የሚል ስም ያላቸው የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው፤ «እንዲህ ያለው አዎንታዊ ሃሳብ ለትብብር በጣም አስፈላጊ እና የዐባይ ወንዝን ፍሰትም የሚያጠናክር ነው። ኢትዮጵያ የውኃው ምንጭ ናት እንደመሆኗ የዝናብ ውኃን በተሳካ መንገድ ማከማቸትና ፍሰቱን መጨመር ያስፈልጋታል።» ረቡማ ደጀኔም፤ «ሁለተኛው የግድቡ ሙሌት ብቻ ሳይሆን ታላቁ የህዳሴ ግድብም በራሱ ለግብጽ ሕዝብ የሚያመጣው ጉዳት የለም። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለዐባይ ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ጥቅምና ዕድሎችን ነው የሚያመጣው። ሀቅ 101፤ ኢትዮጵያ ፈጽሞ የምትቃወመው ጉዳዩን ፓለቲካዊ የሚያደርግ ያረጀውን አካሄድና ውጤት አልባ አቀራረብን ነው። የተስፋ ፕሮጀክት።» ሲሉ ሃሳባቸውን በትዊተር አጋርተዋል። ማሩ ግን እጅግም በአዲሱ የግብጽ አቋም አልተደሰቱም፤ «ለበርካታ ዓመታት ሃገራችንን ለማተራመሥ ከሠሩ በኋላ እንዲህ ያለውን ጭፈራ አንፈልገውም። ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ርምጃዎችን መከተል አትፈልግም። የእናንተ መሪ የጋዳፊን መመሪያ ነው የሚከተሉት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከመገንባት ይልቅ በርካታ እስርቤቶችን ይሠራሉ። ከአረቡ አብዮት የተሳሳተ ትምህርት ነው የቀሰሙት።» እማማ ኢትዮጵያ ደግሞ፤ «ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር መሳፈጧን ለጊዜ ያረገበች ይመስላል። ቢሆንም ልንተኛላት አያስፈልግም። በአንድነታችን ጠንክረን ፍንክች ማለት የለብንም የዘመናችን አደዋ አባይ ላይ ነው።» በዚሁ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጥንቅር አበቃ።

Äthiopien Luftbild Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
ምስል DW/Negassa Desalegen
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ