1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምርጫ አስተባባሪ አስተያየት

ረቡዕ፣ ኅዳር 10 2012

ከጥዋት ጀምሮ ህዝቡ ያው በምርጫ ጣቢያ እየተገኘ ድምጹን እየሰጠ ነው ያለው። ወጣቱ አለ፣ ነዋሪው ህዝብ አለ፣ እኔ እንኳ አሁን ያለሁበት ጣቢያ ላይ በስፋት ተሰልፈው በትዕግስት እየተጠባበቀ ድምጹን እየሰጠ ይገኛል።”

https://p.dw.com/p/3TPxt
Äthiopien: Sidama stimmen über Autonomie ab
ምስል Reuters/T. Negeri

የሃዋሳ ከተማ እና አካባቢዋ የምርጫ አስተባባሪ

የሲዳማ ዞን በክልል ደረጃ ይደራጅ አልያም ቀደም ሲል በነበረበት የደቡብ ክልል ስር የዞን አስተዳደር ሆኖ ይቀጥል በሚለው ላይ ለመወሰን በዞኑ ሲካሄድ የዋለው የድምጽ አሰጣጥ እንደተጠናቀቀ ጊዜያዊ ውጤት በየምርጫ ጣቢያው እንደሚገለጽ የሃዋሳ ከተማ እና አካባቢዋ የምርጫ አስተባባሪ ተናገሩ።  

የሲዳማ ዞን በክልል ደረጃ ይደራጅ አልያም ቀደም ሲል በነበረበት የደቡብ ክልል ስር የዞን አስተዳደር ሆኖ ይቀጥል በሚለው ላይ ለመወሰን የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች ዛሬ ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ ድምጻቸውን ሲሰጡ ውለዋል።
ይኽ ዜና እስከ ተጠናከረበት ሰዓት ድረስ በዞኑ አብዛኞቹ አካባቢዎች የድምጽ አሰጣጥ ስነ-ሥረዓቱ ተጠናቆ በየምርጫ ጣቢያው የድምጽ ቆጠራ መጀመሩን ከድምጽ መስጫ ጣቢያ አካባቢዎች የሚወጡ መረጃዎች እያመለከቱ ነው።
በሃዋሳ ከተማ ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ በነበረው የድምጽ አሰጣጥ ስነ-ሥረዓት ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡት የከተማዋ ነዋሪዎች ረዣዥም ሰልፎችን በትዕግስት በመጠበቅ ድምጽ ሲሰጡ እንደነበር የሃዋሳ ከተማ እና አካባቢዋ የምርጫ አስተባባሪ ወይዘሮ ሙሉ እመቤት አንዳርጌ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።
“ከጥዋት ጀምሮ ህዝቡ ያው በምርጫ ጣቢያ እየተገኘ ድምጹን እየሰጠ ነው ያለው። ወጣቱ አለ፣ ነዋሪው ህዝብ አለ፣ እኔ እንኳ አሁን ያለሁበት ጣቢያ ላይ በስፋት ተሰልፈው በትዕግስት እየተጠባበቀ ድምጹን እየሰጠ ይገኛል።”
የድምጽ አሰጣጥ ስነ-ሥረዓቱ መጠናቀቁን ተከትሎም በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከአስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ የድምጽ ቆጠራ ተከናውኖ ጊዜያዊ ውጤቱ በየምርጫ ጣቢያው እንደሚገለጽ ወይዘሮ ሙሉ እመቤት አስረድተዋል።
“ምርጫ ቦርዱ እንግዲህ በምርጫ ጣቢያ የተሰጠውን ድምጽ የመደመር ስራ ተሰርቶ ይፋ የሚደረግበት ጊዜ ላይ ይፋ ይደረጋል። በየጣቢያው ግን በዛሬው ዕለት ከቆጠራ በኋላ ድምጹ ይገለጻል ማለት ነው።”
በሲዳማ ዞን ውስጥ ባሉ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የተሰጠው ድምጽ የብሄራዊ የምርጫ ቦርድ በቀጣይ በሚወስነው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት አጠቃላይ ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግ ወይዘሮ ሙሉ እመቤት በአጭሩ ተናግረዋል።
“እርሱን ቦርዱ በሚያስቀምጠው ጊዜ ነው የሚገለጸው።”  
በሃዋሳ ከተማ አንዳንድ የምረጫ ጣቢያዎች በድምጽ ሰጪዎች መጨናነቃቸውን ተከትሎ የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ በተከናወነባቸው 195 የምርጫ ጣቢያዎች  30 የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መጨመራቸውን የከተማዋ የምርጫ አስተባባሪዎች ለዶይቸ ቬለ አስረድተዋል።
በሲዳማ ዞን በአንድ የምርጫ ጣቢያ የድምጽ ሰጪዎችን ሰልፍ በማስተባበር ሽፋን ከመራጮች ጋር ወደ ምስጢር ክፍል ተከትሎ በመግባት ፣ በማስፈራራት ፣ የሚመርጡትን ምልክት በማየት ፣ ምልክት እንዲቀይሩ በመንገር የምርጫ ሂደቱን ሲያስተጓጉል ነበር የተባለ ግለሰብ በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ማጣራት እየተደረገበት መሆኑን የብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ከሰዓት በኋላ ላይ ዐስታውቋል።

 

ታምራት ዲንሳ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ