1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሜቲዎሮሎጂ የዝናብ ይዘት ትንበያ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 7 2011

የክረምት ወቅት ነው በኢትዮጵያ፤ ክረምት ሲባል ቅዝቃዜ፣ ዝናቡ ብሎም ጎርፍ አብሮ ይታሰባል። የዘንድሮው የክረምት ወቅት ከመደበኛው ያልተለየ የዝናብ መጠን እንዳለው ነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሜቲዎሮሎጂ  ኤጀንሲ የሚገልጸው። ከባድ ጎርፍ ሆነ መሬት መንሸራተትን ሊያስከትል የሚችል አስጊ የዝናብ መጠን ይኖራል ብሎም እንደማይጠበቅ አክሎ አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/3NptJ
Symbolbild Düngemitteleinsatz Afrika
ምስል AFP/Getty Images

«ከመደበኛው ያልተናነሰ የዝናብ ሁኔታ ነው ያለው»

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መባቻ ገደማ በምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ ቱሉ ጎላ ቀበሌ ደርሶ ከ20 ሰዎች በላይ ሕይወት የቀጠፈውን፤ ከብቶችን ገድሎ ንብረትም ያወደመውን የመሬት መንሸራተት ምክንያት በማድረግ ክስተቱ በየትኛው የሀገሪቱ ክፍል ይበልጥ ስጋት ነው፤ መንስኤውስ በሚል ባለሙያዎችን ያነጋገርንበትን ጥንቅር ማቅረባችን ይታወስ ይሆናል።  በወቅቱ ያነጋገርናቸው ምሁራን የመሬት መንሸራተት በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚከሰት መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል። እነሱ እንደሚሉት የተፈጥሮ ክስተትን የሚመለከተው አብዛኛውን ጊዜ ከመሬት መንቀጥቀጥ ጋር የሚገናኘው ነው። ሌላው ደግሞ በደን ተሸፍኖ የኖረ መሬት ድንገት ሲራቆት እና ከባድ ዝናብ ሲያገኘውም የመሬት መንሸራተት እንደሚያጋጥም አስረድተዋል። ዘንድሮስ?  የዚህ ዓመት የክረምት ወቅት የዝናብ ይዞታ እንዴት ነው ስንል የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አህመዲን አብዱልከሪምን ጠየቅን።

«በነሐሴ ወር ከሌሎቹ ወራት የተሻለ የዝናብ መጠን እና ስርጭት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚገኝበት ወር ነው። ከዚህ አንጻር ጎርፍ የማስከተል ወይም ደግሞ ከባድ ዝናብ የሚጠበቅባቸው አካባቢዎች ተለይተው ተቀምጠዋል።»

ክረምቱ ከገባ ወዲህ በሐምሌ ወር አጋማሽ በደቡብ ክል ባስኬቶ ወረዳ የመሬት መንሸራተት ተከስቶ መንገድ መዝጋቱ ተሰምቷል። ውሎ አድሮም የተዘጋውን መንገድ ለመክፈት ሥራ መጀመሩ ተነግሯል። በክረምት ወቅት ብዙ ዝናብ ከሚያገኙ አካባቢዎች አንዱ አዲስ አበባ እና አካባቢው ነው። ለመሆኑ አዲስ አበባ እና አካባቢው የመሬት መንሸራተት ያሰጋው ይሆን? የሜቲሪዎሎጂ ኤጀንሲውስ በዚህ ላይ ያስተላለፈው ማሳሰቢያ ይኖር ይሆን?

Erdrutsch Äthiopien Oromia Region West Arsi Zone
ባለፈው ዓመት በምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ የደረሰው የመሬት መንሸራተት ምስል West Arsi Zone Government Communication Affairs Office

«አዲስ አበባ አካባቢ ከባድ ዝናብም ባይዘንብ እንኳን መሬቱ አስፓልት በመሆኑ ወደመሬቱ የመግባት ዕድል ስለሌለው ከተለያየ ቦታ የሚሰባሰበው ወደወንዝ የመቀየር ዕድል እንዳለው፤ ጎርፍ ሊሆን እንደሚችል ነው መረጃ የሰጠነው። መሬት መንሸራተት የሚባለው እኛ በዚያ አግባብም መረጃ አልሰጠንም። ጎርፍ የመከሰት ዕድል አለው ነው።»

ኢትዮጵያ ውስጥ የመሬት መንሸራተት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ያለባቸው አካባቢዎችን የሚዘረዝሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት እና የአፍሪቃ አደጋ መከላከል ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዘውዱ እሸቱ አዲስ አበባ እና ማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል ከዚህ ውጭ መሆኑን ይናገራሉ።

«እንግዲህ ምንድነው አሁን ክረምት ላይ ከዝናቡ ጋር ተያይዞ የመሬት መንሸራተት ሊመጣ የሚችለው ትልቅ መንገድ በሚሠራበት ጊዜ መሬቱን ይቆፍሩታል ያኔ የበለጠ ይቆስል እና በዚያ ውስጥ ውኃ ሰርስሮ ሲገባ ስለሚያለያየው የመንሸራተት አጋጣሚው ሊኖር ይችላል። ግን በዚህ በአዲስ አበባ ዙሪያ ማዕከላዊው ደጋማ አካባቢ የጠበቀ መሬት ምንም መንሸራተት የሚኖር አይመስለኝም።»

በተለይ የአንድ አካባቢ መሬት እና አፈር በተለያዩ ምክንያቶች እረፍት ሲያጣ ያልተገመተ ክስተት ሊከት እንደሚችል ባለሙያው አሳስበዋል። አንዳንድ ወገኖች የክረምቱ ቅዝቃዜ መጠንከሩን ሲናገሩ ይደመጣል። በብሔራዊ ሜቲሪዎሎጂ ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በበኩላቸው የዘንድሮው ክረምት ከወትሮ የተለየ ቅዝቃዜ  መከሰቱን የሚያመለክት ነገር እንዳልታየበት ነው የገለፁልን። በክረምቱ ወቅት ዝናብ በየጊዜው የሚያገኙ አካባቢዎችም ዘንድሮ የተሻለ እርጥበት እንዳለም አንስተዋል። ዝናብ እንደመኖሩም ያጋጠመው የጎርፍ አደጋ የከፋ የሚባል እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

Überflutung inSüd- Gondar
በደቡብ ጎንደር ዞን በርካታ ቀበሌዎችን ያጥለቀለቀው ጎርፍ ምስል Biruk Teshome

በነገራችን ላይ ደቡብ ጎንደር ዞን የርብ ወንዝ ሞልቶ በርካታ ቀበሌዎችን በጎርፍ አጥለቅልቆ በሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱ ተሰምቷል። መኖሪያ ቤቶችም በውኃው መከበባቸውን የሚያሳዩ ፎቶዎች ከአካቢው ወጥተዋል። ሜቲሪዎሎጂ ኤጀንሲ በድረገፁ ያወጣው መረጃ ባለፈው ሐምሌ ወር በምዕራብ፣ ሰሜን እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች የዝናቡ ፍሰት 80 ሚሊ ሜትር መሆኑ የርጥበቱም ልክ 60 በመቶ መድረሱን ያመለክታል። ምንም እንኳን የዝናቡ መጠን መደበኛ ነው ቢባልም ድርቀት የሚያሰጋቸው አካባቢዎች መኖራቸው ሲነገር ሰንብቷል እና ስለዚህ የሚሉን ካለ አቶ አህመዲንን ጠይቀናቸዋል።

«እንግዲህ የዝናብ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል በሚል የተለዩ ቦታዎች፣ ወይም ደግሞ በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ እና ከመደበኛ በታች ሊከሰትባቸው ይችላል ተብለው የተለዩ አካባቢዎች አሉ። ሰሜን እና ሰሜን ምሥራቅ ትግራይን ጨምሮ እና አፋር ያው በመደበኛ ሁኔታ የሚያገኙትን ያው ዘግይቶ የሚያገኙበት ከዚያ ደግሞ ቀድሞ የሚወጣበት ሁኔታ «በፊትም በመደበኛ እንደዚያ ነው የሚያገኙት» ወደ ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢ ደግሞ የመቆራረጥ ሁኔታ እንዳለ ነው።»

አክለውም ስለክረምቱ ቀጣይ ይዞታም ሆነ የመውጫ ጊዜ የሚያመላክት ትንበያ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ወደሌሎች ሃገራት ስንመለከት ደግሞ ሕንድ፣ ቻይና እና ማያንማር ከሰሞኑ ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ የመሬት መንሸራተት እንዳስከተለባቸው እናያለን። ሕንድ በስምንት ግዛቶቿ 80 የመሬት መንሸራተት አጋጥሞ 42 ሰዎች ሞተዋል። የባቡር እና የተሽከርካሪዎች እንዲሁም የአውሮፕላን መጓጓዣዎችን አስተጓጉሏል።  ደቡብ ምሥራቅ ቻይና ውስጥ ተመሳሳይ አደጋ 28 ገድሏል፤ 20 ሰዎች የገቡበት አልታወቀም። ከአንድ ሚሊየን በላይ ሕዝብ አፈናቋሏል። የመሬት መንሸራተት ጎርፍ ባጥለቀለቃት ማያንማር 52 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ