1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮምያ ክልል ጥሪ፤ልደቱ ምን እያሉ ነዉ፤ የትግራይ ፖለቲከኞች ቅሬታ፤ የዶቼ ቬለ 70ኛ ዓመት

ዓርብ፣ ግንቦት 4 2015

የኦሮምያ ክልል መንግሥት በክልሉ ለሚደረገዉ የሰላም ጥረት ድጋፍ መጠየቁ፤ ስድስት ወራት የሞሉት የፕሪቶርያ ስምምነት አተገባበር ፍጥነት ይጎድለዋል መባሉ፤ ጉምቱዉ ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌዉ ወደ ሃገር ቤት ሊመለሱ መሆኑ እንዲሁም በ 32 ቋንቋዎች የሚራጨዉ ዶቼ ቬለ 70ኛ ዓመቱን እያከበረ መሆኑ በተሰኙ ርዕሶች ስር የተሰጡ ርዕሶችን ጨምቀን ይዘናል።

https://p.dw.com/p/4REXd
Festakt DW Deutsche Welle 70-jähriges Bestehen
የዶቼ ቬለ 70ኛ ዓመትምስል Jörg Carstensen/dpa/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የኦሮምያ ክልል ጥሪ፤ ልደቱ ምን እያሉ ነዉ? የትግራይ ፖለቲከኞች ቅሬታ፤ የዶቼ ቬለ 70ኛ ዓመት

የኦሮምያ ክልል መንግሥት በክልሉ ለሚደረገዉ የሰላም ጥረት ድጋፍ መጠየቁ፤ ስድስት ወራት የሞሉት የፕሪቶርያ ስምምነት አተገባበር ፍጥነት ይጎድለዋል መባሉ፤ ጉምቱዉ ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌዉ ወደ ሃገር ቤት ሊመለሱ መሆኑ እንዲሁም በ 32 ቋንቋዎች የሚራጨዉ ዶቼ ቬለ 70ኛ ዓመቱን እያከበረ መሆኑ በተሰኙ ርዕሶች ስር የተሰጡ ርዕሶችን ጨምቀን ይዘናል።   

በኦሮሚያ ክልል ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ሁሉም ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ላለፉት አራት ዓመታት ተንሰራፎ የቀጠለውን የሰላም እጦት ከምንጩ ለማድረቅ በመንግስትና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል የነበረው ድርድር በተፈለገው ፍጥነት የተቋጨ አይመስልም፡፡ የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ሰሞኑን በሰጠዉ መግለጫ በክልሉ የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላም ለመፍታት መንግስት ቁርጠኛ ነዉ ብሏል፡፡

Communication Bureau Press
ኃይሉ አዱኛ፤ የኦሮምያ ክልል ቃል አቀባይ ምስል Seyoum Getu/DW

ደጀኔ ዘዉዴ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ „ ቅድሚያ ለሰላም። ክፉዎች ሰላም የላቸውምና፤ ለሰላም ሲባል የሚከፈለው ዋጋ ሁሉ መከፈል ግድ ይላል። በሕግና በሕግ” ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል። ምስር ሙላቱ የተባሉ ሌላዉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ „ እንዲህ በቀላሉ ይቋጫል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው! ረፈደ እኮ! ስንት ባንክ ሲዘረፍ፤ ዘርን መሰረት አድርጎ የተፈናቀለው፤ የሞተውስ ቁጥር አለው? በሚዲያ ከማዉራት በቀር ምን ፍትህ ወረደ!መግደል መሸነፍ ነው! ተብሎ ነበር። ነገም ይቀጥላል። የማፈለገዉ ተሰጥቶ የወገኖቻችን ስቃይ ባቆመ! ፍርዱን ለፈጣሪ ትተን!” ሲሉ በቃል አጋኖ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

አባተ ፉላስ ኬልቻ የተባሉ የፊስ ቡክ ተከታታይ ”በኦሮሚያም ሆነ በሌላ ክልል ሰላም ለማወረድ ከመግለጫዎች በተጨማሪ ተጨባጭ እርምጃ ተወስዶ እንደሆነ እንወቀው። ይህ በራሱ ተሰፋ እና መረጋጋት ያመጣል„ ሲሉ አስተያየት አስቀምጠዋል።  ዳንኤል ፀሐይ ግርማ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ „ የሀገራችን የሠላም ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ነው። በዚህ  ኢኮኖሚያችን በየአቅጣጫው ጥይት እንደ አሸዋ እየተተኮሠ የባሰ መከራ ውስጥ አየገባን ነው። ሀይ ባይ ጠፋ? አገሬ ሠላምሽን ፈጣሪ ይመልስልሽ።” ብለዋል።

አብዱ ሰላሜ የተባሉ አስተያየት ሰጭ፤ „ማንኛውም የኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን በተለያየ ሁኔታ ሲጨፈጨፍ መንግስት ለዚህ ድርጊት መከላከል ቀርቶ ቁጭቱን ወይም ሀዘኑን እንኳን ሲገልፅ አይተን አናውቅም። መንግስት በዚች ሀገር ህዝቦቿን ሣይሆን ምድሯን ብቻ የሚፈልግ ይመስላል።” ብለዋል።  

Äthiopien Addis Abeba | Lidetu Ayalew, äthiopischer Politiker
አቶ ልደቱ አያሌዉ ምን እያሉ ነዉ?ምስል privat

ሲሳይ ከፍ ያለዉ ለገሠ  „ እንተባበር ” ሲሉ ነዉ አጠር አድርገዉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋl፤ እንተባበር ።  እዉቁ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌዉ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ማስታወቃቸዉ ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ ዜጎችን ያነጋገር ጉዳይ ሆኖ ነዉ የሰነበተዉ። የኢትዮጵያ መንግስት ለሕክምና ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙትን አቶ ልደቱ አያሌዉን ጨምሮ 11 ሰዎችን «የሽብር ፕሮፓጋንዳ በመንዛት፣ የክልልና የፌደራል መንግስትን በኃይል ለመጣል በማሴር ወንጅሏቸዋል። ዶቼ ቬለ ከቀናት በፊት ያነጋገራቸዉ አቶ ልደቱ አያሌዉ እንደሚሉት፤ መንግስት ያወጀብኝን የአሸባሪነት ክስ በአካል ተገኝቼ ለመሟገት እና የሚመጣዉን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።

አባተ የተባሉ አስተያየት ሰጭ አሁንም „አቶ ልደቱ፤ ጥሩ ርምጃ ነዉ። እንደ አንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ፤ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እና ህልውናን ለማስከበር ያደረከዉ ርምጃ ተቀባይነት ያለዉ ነው!” ሲሉ አስተያየት ጽፈዋል። ወርቅነሽ ተካ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይም ተመሳሳይ አስተያየት ነዉ የሰጡት„ የአቶ ልደቱ ጥሩ ውሳኔ ነው ደግሞ ምንም አይሆንም” ብለዋል።

ሃሰን ጀማል  የተባሉ ሌላዉ የፌስቡክ ተጠቃሚ „አቶ ልደቱ ሌሎች ከሀገር ለመውጣት በሚጠሩት ጊዜ ይህን መወሰነህ ቂርጠኝነት ይጠይቃል። ትክክለኛ ውሳኔ ነው። ” ብለዋል። አብዱ ሞጋ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ „የሄደዉ ለህክምና ነበር። እሱ ግን የሰራውን ያዉቀዋል። ስለዚህ መጥቶ የሚገባውን መዉሰድ ነዉ። ሌላ ነገር ምንም አያስፈልግም”  ሲሉ ጽፈዋል።

ጀማል ያንል የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ „አቶ ልደቱ የሀሳብ ትግል ነው የሚያራምደው መንግስት ተቀብሎ ካሰረው ያው ተሸናፊነቱን ያረጋግጣል” ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። ቀስተ ደመና ሰባት ነዉ የሚል በፌስቡክ ላይ ስያሜ ያላቸዉ ተከታታይ „ጉራ ብቻ። ብለዋል ጉራ ብቻ ዐብይ ነው ችላ ችላ ብሎ እንዲህ የሚያስደርገን ሲሉ ጽፈዋል። ይህሳቅ አዳን የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ „በህግ የምያምን ሁሉ እንደ ልደቱ መሆን አለበት” ይላሉ። 

ይፀደዉ ፀጋዬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ„ ለእውነተኛ ትግል የሚችሉትን ማድረግ አስተማሪና የሚያበረታታ ቢሆንም በእኛ ሀገር ሁኔታ ግን አስቸጋሪ ያደርገዋል ! ምክንያቱም መንግትን መተቸት ተቃዋሚ መሆን ወንጀል ከተባለ ሰነባብቷል።  ለማንኛውም ሁሉን የምናየው ይሆናል። ፍትህ ግን ይኖር ይሆን ? አይ ሀገሬ ሲሉ አስተያየታቸዉን በጥያቄ ደምድመዋል። አቶ ልደቱ አያሌዉ ወደ አዲስ አበባ ከማቅናታቸዉ በፊት ህዝባዊ ዉይይት ሲሉ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የጠሩት ስብሰባ የፊታችን እሁድ እንደሚካሄድ ማስታወቅያዉ በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ተሰራጭቷል።

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት የተካሄደዉን  ደምአፋሳሽ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ስድስት ወራት አልፈዉታል። በትግራይ የሚገኙ ፖለቲከኞች የስምምነቱን ተግባራዊነት በአዎንታ ቢቀበሉትም በርካታ በፍጥነት መፈፀም ይገባቸው የነበሩ ተግባራት እስካሁን ተዘንግተዋል ሲሉ ቅሪታቸዉን አሰምተዋል።  ጦርነቱ ያስከተላቸው ችግሮችን በቶሎ አለመፈታት፥ በተለይም በትግራይ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ እንዲቀጥል አድርጎታል ሲሉ በትግራይ የሚገኙ አንዳንድ ፖለቲከኞች ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

Äthiopien Premierminister Treffen mit Führern von Tigray
የፕሪቶርያ ስምምነት እና ተግባራዊነቱምስል Ethiopian Broadcasting Corporation

መስፍን ያዘዉ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ „የፕሪቶርያው ስምምነት እኮ ሁለቱም የጦርነቱ ወንጀለኞች ከተጠያቃነት ለማምለጥ የዙየዱት መፍትሔያቸው ነው” ሲሉ ጽፈዋል። ኢብራሂም አብዱ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ „ የሰላም ስምምነቱ ንፋስ ሳይገባው የተፈጠሩ ክፍተቶችን ቶሎ መሸፈን ያስፈልጋል። ስምምነቱ ያለፈውን ጠባሳ ባያድነውም የወደፊቱን ሰላም ለማስፈን ፈር ቀዳጅ ይሆናል። ወደኋላ እያየን ግባችንን ማስተጉዋጎል የለብንም።” ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

ሙለር ኃይሉ የተባሉ ሌላዉ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ „ የትግራይ ግዛቶችን የማያስመልስ ስምምነትን የሚቀበል ትግራዋይ የለም ፡፡” ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። ታድዮስ ገብሩ ወሉ የተባሉ በአስተያየታቸዉ „ሁሉም ፖለቲከኞቾ ህዝብ ያስጨረሱ ስለሆኑ ስለነሱ የሚያገባን ነገር የለም”  ብለዋል። አዲልሃ ብርኃን በበኩላቸዉ „በስምምነቱ መሰረት የትግራይ ህዝብ ችግር በተቻለ ፍጥነት ሊፈታለት ይገባል” ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር ግንቦት 3፣ 1953 በራዲዮ አጭር ሞገድ ማሰራጨት የጀመረዉ ዶቸ ቬለ ዛሬ ከዓለም ትላልቅ ማሰራጪያ ጣቢያዎች አንዱ ነዉ። የጀርመኑ ዓለም አቀፍ ማሰራጪያ ጣቢያ በአሁኑ ወቅት አማርኛን ጨምሮ በ32 ቋንቋዎች፣ በራዲዮ፣በቴሌቪዥን እና በተለያዩ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትኩስ፣ ሚዛናዊና ገለልተኛ መረጃዎችን በቀን 24 ሰዓት፣ በሳምንት ሰባት ቀን ያሰራጫል። ዶቸ ቬለ እዚህ  የደረሰዉ በጋዜጠኞቹና ባልደረቦቹ ላይ የሚደርስ ጥቃት፣ወከባ እስራትና ዘለፋን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎችን፣ የፕሬስ ነፃነት አፈናዎችን ተጋፍጦ ነዉ። 

70 Jahre DW
በ 32 ቋንቋዎች የሚያሰራጨዉ ዶቼ ቬለ 70 ኛ ዓመቱን እያከበረ ነዉምስል Ronka Oberhammer/DW

ጀማል ሃሰን የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ „በአሁኑ ጊዜ ምርጥ እና ታዓማኒ የሆነ ሚድያ ከተቋሙ DW Amharic ወይም የአማረኛዉ ዝግጅት ክፍል ነዉ። ዶቼ ቬለ ምርጫዎቼ ናችሁ ብለዋል።”  አባተ ፉላስ ከልቻ የተባሉ የፊስቡክ ተከታታይ እባካችሁ አፋን ኦሮሞን 33ኛ ቋንቋ አድርጉ። እንዴት ይህ የአፍሪቃ ቀንድ ታላቅ ሕዝብ ቋንቋ ገለል ይደረጋል? ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። አሊ አህመድ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ ፤ ጋዜጠኞችን የሚፈራ መንግሥት በእራሱ እምነተ የሌለዉ መንግስት ነዉ። ዶቼዎች ጥሩ እየሰራችሁ ነዉ።  ቀጥሉ  በርቱልን  ብለዋል። 

ሊዲዛ ሃበሻ፤ በኔ እይታ የጋዜጠኝነት ሞያ በጣም ድንቅ፤ ብዙ መስዋዕትነት እሚከፈልበት፤ ከባድ ሚዛን የሆነ ሞያ ነው። ወደ ኢትዮጵያ ጠቅላላ አፍሪቃ ላይ ስንመጣ ባለስልጣናት በሞያው ባለቤቶች ላይ በሚያደርጉት ተፅዕኖ ምክንያት ሞያውን ትውልድ እንዲሸሸው ያደርጋል፤ብለዋል። የጣቢያዉ የበላይ ኃላፊ ፒተር ሊምቡርግ በጀርመን ፓርላማ ተገኝተዉ የጣብያዉን 70ኛ ዓመት አክብረዋል። ንግግርም አድርገዋል።

የዶቼ ቬለ ተከታታዮች በ 32 የተለያዩ ቋንቋዎች ለሚሰራጨዉ ለዶቼ ቬለ 70ኛ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ። 

ሙሉዉን ዝግጅቱን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ