1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ነሐሴ 13 2014

የአዲስ አበባ ከተማ የወሰን አከላለል፣የመንግስት የሰላም የድርድር ምክረ ሃሳብ እና የህወሃት ክስ እንዲሁም በደቡብ ክልል የተነሳው የክልልነት ጥያቄ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በዚሀ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርከት ያሉ አእስተያየቶች የተሰጡባቸው ጉዳዮች ናቸው።

https://p.dw.com/p/4FlGu
Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance

የነሀሴ 13 ቀን 2014 ዓም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት


 የአዲስ አበባ ከተማ የወሰን አከላለል፣የመንግስት የሰላም የድርድር ምክረ ሃሳብ እና የህወሃት የክስ መግለጫ እንዲሁም በደቡብ ክልል የተነሳው የክልልነት ጥያቄ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በዛሬው ዝግጅታችን የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው። 
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኦሮሚያ ክልል መካከል   የአስተዳደር ወሰን ስምምነት ተደርሰ መባሉ  በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ያነጋገረው ጉዳይ ጉዳይ ነው።
ለሰባት ዓመታት በጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሲሰራበት የቆየ ነው የተባለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮምያ ክልል  የአስተዳደራዊ ወሰን ጉዳይ በዚህ ሳምንት እልባት ያገኘው፤በኢትዮጵያ ህገመንግስት እና በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር መሰረት ነው ተብሏል።  ያለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2014 ዓ/ም  ይፋ የተደረገው ይህ የወሰን ማካለል ስራ ሁለቱ አስተዳደሮች ሰሞኑን ከህብረተሰብ ተወካዮች  ጋር ከተወያዩ በኋላ ውጤቱ ይፋ መደረጉም ተገልጿል፡፡
 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ፤በኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካላት የጋራ ስምምነት ጉዳዩ መፈታቱን «ታሪካዊ» የወሰን ማካለሉን ስራም «ስኬታማ» ብለውታል፡፡
ይህንን ተከትሎ አዲስ አበራ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ «ከሰባቱ የጥናት አመታት ውስጥ ለሁለት ቀን እንኳን የነዋሪውን ፍላጎት ለመረዳት እና ለማወያየት አለመቻሉ እኮ ሌላ ዜና መሆን ይችላል ጎበዝ። የተካለለው መሬት ሰው የማይኖርበት ምድረ በዳ አስመሰላችሁት እኮ።»ብለዋል።
ጥላሁን ምትኩ  በበኩላቸው «የጀሞ 2 እና የቱሉዲምቱ ነዋሪዎች/በወሰን ማካለሉ ወደ ኦሮሚያ ክልል የተካተቱትን ማለታቸው ነው/ ማህበራዊና ኢኮኖሚ ትስስራቸው ከማን ጋር ነው?» ሲሉ ጠይቀዋል። ፉአድ ከማል «እኛ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ብንሆን ወይም በፊንፍኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ስርም ብንካተት ዋናው ፍላጎታችን ሰላም እና ጥሩ የሆነ አገልግሎት ማግኘት ነው።»ብለዋል።
ሳንቾ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት «በሉ በነካ እጃችሁ በሶማሌ እና በኦሮሚያ፣ በአፋር እና በሶማሌ በአማራ እና በትግራይ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች ያሉትን የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ በአስቸኳይ ፍቱ።» የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ቸልሲ የኔሰው በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት «ማን ከማን ነው ስምምነቱ? ሁለት የተለያዩ አካላት ተሰብስበው ሲስማሙ ኖሮ፤ መስማማት ላይ ደረሱ ይባል ነበር። ሁለቱም የኦሮሚያ ብልፅግና ሰዎች ናቸው።በአካል ሁለት በግብር አንድ የሆኑ ስለዚህ ቢስማሙም አይገርመንም። » ብለዋል። ገላና ኑሬሳ «የትም ክልል ከየትኛውም ብሄር ይወለዱ በከፍተኛ አመራሮቻችን መካከል ያለውን መደማመጥ እና መግባባት ግልፅ ያደረገ መልካም ተግባር ።»የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል።
ስዩም ክፍሌ ደግሞ «ሰፊው ሕዝብ የአዲስ አበባ ሳይመክርበት የኦሮሞ ብልፅግና ሁለት አባላት እርስ በርሳቸው መረካከባቸው ትክክል ነው?» በማለት ጠይቀዋል።
ጀሚ ደስ ነስ በሚል ስም «ነገሩ በሁለት ማሊያ ለአንድ ቡድን እንደመጫወት ነው።» ሲሉ፤ ሮዛ ሮዛ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «ወደዛም ቢሄድ የራሳቸው ሀብት ወደዚህም ቢመጣ የራሳቸው ሀብት ስለዚህ ለአስተዳደር አስከ አመቸ ድረስ አንደፈለገ ቢሆን ምንም ችግር የለውም ምክንያቱም ሁለቱም የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ናቸው።»ብለዋል።
አሰግድ  አድማሱ ገብረማርያም «ያለ ኢትዮጵያ ሙሉ ብሄር ብሄረሰቦች እውቅና የኢትዮጵያ ዋና ከተማን የአዲስ አበባን የድንበር ወሰን ማስፋፋትና ማካለል በከንቲባዋና በኦሮሚያ ክልል መንግስት ብቻ የሚወሰን አይደለም።»የሚልአስተያየት ሰጥተዋል።
ባዬ ዳዲ «ጥሩ ውሳኔ ነው።የኦሮሞ አርሶ አደር ተፈናቅሎ የሰፋች ከተማ ነች።ስለዚህ ቦታው ለባለቤቱ መመለስ አለበት።»ብለዋል።
መዓዛ የማርያም የተባሉ አስተያየት ሰጪ «ከአዲስ አበባ የተወሰዱም ሆነ የተጨመሩ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች በወሰን ማካለሉ የሚያገኙት ጥቅም እና ጉዳት ምንድነው?የማካለሉ ውሳኔ የገበሬዎቹን ጉዳትስ ይመልሳል ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል።«እስኪ ጥቅሙን አስረዱኝ።በሰላም የሚኖረውን ህዝብ አንዴ እዚህ ነህ ሌላ ጌዜ እዚያ ነህ እያሉ ከማንገላታት በቀር። » ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የመሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ በየትኛውም ጊዜ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለውይይት ዝግጁ መሆኑን እንዲሁም ጦርነትን በዘላቂነት ለማስቀረት የተከስ አቁም እንዲደረግ እቅድ መያዙን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ሰሞኑን ገለጿል።የሰላም አማራጭ አብይ  ኮሚቴው በበኩሉ ለሰሜኑ ግጭት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት የሚወስድ እና ለቀጣይ ውይይቶች መሰረት የሚጥል የሰላም  የድርድር ምክረ ሃሳብ ማፅደቁ ተነግሯል።
በሌላ በኩል  ህወሀት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ  በተለያዩ ግንባሮች በከባድ መሳሪያ የታገዘ  ጥቃት በሰራዊቴ ላይ  ፈፅሟል ሲል የፌደራል መንግስቱን በመውቀስ ላይ ነው።

Äthiopien Kindeya Gebrehiwot
ምስል Million Hailesilassie/DW
 Addis Ababa City
ምስል Seyoum Getu/DW
Äthiopien | Parlamentswahl | Adanech Abebe
ምስል Solomon Muchie/DW

መንግስት በበኩሉ በሕወሃት ላይ አንዳችም ጥቃት አልተፈጸመም ክሱ ከሰላም ንግግር ለመሸሽ ነው በማለት ውንጀላውን አጣጥሎታል።  
ይህንን የሁለቱን ወገኖች የእርስ በእርስ መወነጃጀል እና ውዝግብ ተከትሎ ፤ዳግማዊ ክበበው «ሰላም ሳትሰጡን የሰላም አማራጭ የሰላም ሚኒስቴር እያላችሁ በዚህ ተላላ ህዝብ ላይ የምተሳለቁት ነገር መቼ ነው የሚያበቃው?»ሲሉ፤ ጥላሁን ደሱ «በዚህ ጊዜ ለሀገራችን ሠላም ነዉ የሚያስፈልጋት ከጦርነት ምንም አይገኝም።»የሚል ሀሳብ ሰጥተዋል። ሻላ ቶማስ ደግሞ «ሰላምን ማን ይጠላል። ግን ከልብ ካልሆነ ምን ዋጋ አለው።»ብለዋል።
«እባካችሁ ህወሃትም ሆነ ፌደራል መንግስቱ የሰላም ድርድሩን ከልብ አስቡበት።ከልብ ካዘኑ እንባ አይገድም ይባላል።ሰላሙን ከልብ የምትፈልጉት ከሆነ መንገድ አይጠፋም።እባካችሁ በረሀብም በጦርነትም የሚያልቀው ህዝብ ያሳዝናችሁ።» ያሉት ደግሞ ዘቢባ ፍቅር የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው። 
የሻነው አይቸህ «ለምንድን ነው ሁልጊዜ የህዝብን ሰላም የምትነሱት?»ሲሉ ጠይቀዋል። ተሻለ ተሰማ  «ይህችን የመገዳደል ጠኔዋ የማያበቃ ሀገር ።ኢትዮጵያ የሚታረቅም የሚያስታርቅም ክብር የማይሰጥበት ሀገር ነች ።መገፋፋት ብቻ።» ብለዋል።ብሌን አሌክሳንድሮ ደግሞ «ሳታማሃኝ ብላኝ አሉ፣በቃ አሁን ጦርነት ልትጀምሩ ነዉ ማለት ነዉ ። የፈረደበት ወጣት ይሞታል።የፈረደባት እናት ታልቅሳለች።ያሳዝናል።»ብለዋል። «ሰላም ወርዶ እፎይ ልንል ነው። ስንል ሌላ ጋሬጣ ባታመጡብን ምናለ።»ያሉት ደግሞ ዓለም ታደሰ ናቸው።
ሌላው በዚህ ሳምንት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተንሸራሸረው ጉዳይ በደቡብ ክልል የተነሳውን የክልልነት ጥያቄ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ማግኘቱ ነበር።
የፌዴሬሽን ምክር በትናንትናው ዕለት እንዳስታወቀው  በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ስር የነበሩ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል እንዲደራጁ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ወስኗል።
በውሳኔው መሰረት አዲስ ክልል የሚመሰርቱት የወላይታ ፣ የጋሞ ፣ የጎፋ ፣ የደቡብ ኦሞ ፣ የጌዴኦ እና የኮንሶ ዞኖች  እንዲሁም የደራሼ ፣ የአማሮ ፣ የቡርጂ ፣ የአሌ  እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ናቸው። ቀሪዎቹ የሀድያ ፣ የሀላባ ፣ የከንባታ ጠንባሮ ፣ የጉራጌ  እና የስልጤ ዞኖች  እንዲሁም የየም ልዩ ወረዳ በነባሩ ክልል ይቀጥላሉ በማለት ገልጿል።
ይህንን ተከትሎ መስኩድ ረሽድ የተባሉት አስተያየት ሰጪ «ፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ- መንግስቱ የበላይ ጠባቂ ነው። ህዝቦች የሉዓላዊ መብት ባለቤቶች ናቸው። ፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ-መንግስቱን አክብሮ ያስከብር!»ሲሉ ሀዋ ነኝ በሚል ስም ደግሞ «በቅርቡ 12ኛ ክልል እንጠብቅ ማለት ነው።»ብለዋል። ደሳለኝ ሌጋሞ «ውሳኔው በጣም አሪፍ ነው።» ካሉ በኋላ ምክር ቤጤ ጨምረዋል።«አሁን መንግስት በውስጡ ያሉትን በሁለት ቢላዋ የሚበሉትን ከላይ እስከ ታች ያሉትን አመራሮችንና ኃላፊዎችን ማጥራት አለበት።እራስ ወዳዶች በዝተዋል።»ሲሉ፤ገዱ ዱዴ ደግሞ «የሕዝብ ጥያቄ በሕገመንግስቱ መሠረት ሳይሆን በፌደሬሽኑ ምክርቤት ፍላጎት ብቻ እንደሚወሰን አይተናል። ጉራጌ ዞን ክልል ልሁን ብሎ የጠየቀዉ ጥያቄ ሕገመንግስቱ ን መሠረት ባላደረገ መልኩ ምላሽ አግኝቷል።»ሲሉ ቅሬታቸውን አስፍረዋል። ዋቢ ስሀለ ገብሬ «የጉራጌ ህዝብ ጥያቄ በህገ- መንግስቱ መሰረት ብቻ ይመለስ‼መንግስት እራሱ ያላከበረውን ህገ- መንግስት ነገ ለማስከበር ስለሚቸግር ማስተዋል ያስፈልጋል።»ብለዋል። 
ሳላዲን ሁሴን«እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ነው» ብለውታል  ውሳኔውን። አያይዘውም መንግስት ክላስተርን እምቢ የምትሉ ከሆነ ከነባሩ ተቀላቀል የሚል እሳቤ ይዞ በ6 ዞኖችና በተቀሩት ልዩ ወረዳዎች ሪፍረንዳም ለማካሄድ ሀ ብሎ ጀምራል።ይህ ደግም አንዳችም ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም ። ውጤቱም የጊዜና የኢኮኖሚ ኪሳራ ነው።»በማለት ገልፀዋል። «መንግስት ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብትን በትኩረት መመለሱ የሚደነቅ ነው።»ያሉት ደግሞ ወርቃየሁ አስረስ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው። ቸርነት ፈቀደ በበኩላቸው «ትልቁን ደቡብ አፍርሶ ትንሹን ደቡብ መመስረት በራሱ የእጅ አዙር ክላስተር ነው!!!»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
መሳይ ታደሰ«ክልል መሆንን የመጨረሻ ግብ አድርጎ ለሚቆጥር ማህበረሰብ ህዝበ ዉሳኔ ማካሄድ ሀብትና ጉልበትን ከማባከን በስተቀር ምንም ጥቅም የለዉም።እባካችሁ ጌቶች እያስተዋልን እንጂ።»ሲሉ፤  አብርሃም አብርሃም በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «ጉራጌ ክልል ለማግኘት የግድ የሰው ደም ማፍሰስ አለበት? »ይላል። ሙሉ ሸዋ ጫላ ደግሞ «የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ይቀጥላል መፍትሄውም ክልልማድረግ ብቻ ነው።የሚገርመው ነገር በዚህ ፍጥነት ኮማንድ ፓስቱ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ነው ሰላማዊ ለሆነው የጉራጌ ህዝብ ይሄ አይመጥነውም።»ብለዋል። ሜሪ ተካ በበኩላቸው «ህገ መንግስቱ እስካልተሻረ ድረስ የጉራጌ ህገ መንግስታዊ ጥያቄ መመለስ ያለበት በህገ መንግስቱ መሠረት ብቻ ነው።»ሲሉ፤ 
ቢተው ብርሃኑ ደግሞ ውሳኔውም ጥያቄውም  የተዋጠላቸው አይመስሉም «በጣም ያሳዝናል አንዲት ኢትዮጵያ ብለዉ ስንቶች የታገሉላትን እና የሞቱላትን ሀገር እንዲህ እንደ ዋዛ በቀላሉ የክልል ጥያቄ፣ የዞን ጥያቄ፣ የወረዳ ጥያቄ እየሉ ማፈራረስ።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። 

House of federation, Addis Abeba, Ethiopia
ምስል House of federation Ethiopia

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ