1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሐምሌ 23 2013

«በርካታ ባለ ድል አትሌቶች የነበራትና ያላትን ሀገራችን ለተሳትፎ ብቻ በሚመስል መልኩ በአንድ ተወካይ በመክፈቻው እለት ስትታይ ሀገሬን በመድረኩ ያሳነሷት፣ ያዋረዷትም መሠለኝ ነገር ግን ሀገራችን ሀገር ነችና ጥቂት ስግብግቦች በፈጠሩት ስህተት ሀገራችን አታንስም በመድረኩ  ሁሌም እንደምትደምቀው በጀግኖቿ ዛሬም በውጤት ትደምቃለች ።» ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3yHWd
 Olympia I Schwimmen I Yusra Mardini von IOC Flüchtlingsteam
ምስል David J. Phillip/AP/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን በቶክዮ ኦሎምፒክ የመክፈቻ ስነስረዓት በኦሎምፒክ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሁለት ሰዎች መወከሏ በኦሎምፒክ ጫወታዎች በተለይም በአትሌቲክስ ስሟ ገኖ የሚታወቀውን ኢትዮጵያን የሚመጥን አይደለም ሲሉ በርካቶች ሀዘናቸውን ሲገልጡ ተሰምተዋል። በርካቶች ደግሞ ከክስተቱ ጋር የተያያዙ አስተያየቶችን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲቀባበሉት ተስተውሏል። ላለፉት ስምንት ወራት በትግራይ ክልል በፌዴራል መንግስት እና በትግራይ አማጽያን መካከል  ሲደረግ የነበረው ጦርነት አሁን መልኩን ቀይሯል። የፌዴራሉ መንግስት የተናጥል የተኩስ አቁም አድርጎ ትግራይን ለቆ ከወጣ በኋላ የትግራይ አማጽያን ክልሉን ከመቆጣጠር አልፈው በአጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች የተወሰኑ አካካቢዎችን መቆጣጠራቸውን እያስታወቁ ነው። ይህንኑ ተከትሎ በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘው ነዋሪ በየከተሞች በነቂስ ወጥቶ አማጽያኑን የሚያወግዝ እና የመከላከያ ሰራዊቱን ደግሞ የሚደግፍ ሰልፍ እያደረገ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ተ,ፈጥሯል። በዚህም የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተስተጓጉሏል፤ በተፈጠረው ጭጋጋማ አየር የከተማዋ ዕለታዊ የትራፊክ እንቅስቃሴንም አስተጓጉሏል። በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የማህበራዊ ትስስር ተጠቃሚዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ሲያጋሩ ቆይተዋል። በዛሬው የማህበራዊ መገናና ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችንም በእነዚሁ ሶስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አተኩረን የተሰጡ አስተያየቶችን መራርጠን ይዘን ቀርበናል ታምራት ዲንሳ ነኝ ።
መሸጋገሪያ 
በኮሮና ወረርሽን ምክንያት ለአንድ ዓመት ተገፍቶ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው  የቶክዮ ኦሎሚፒክ ከተጀመረ አንድ ሳምንት አስቆጥሯል። በኮሮና ወረርሽን የምትናጠው የቶክዮ ከተማ በጥብቅ የኮሮና ቁጥጥር እንግዶቿን ስትቀበል ሰንብታለች። የቶክዮ ኦሎምፒክ የመክፈቻ ስነስረአቱ ከመከናወኑ አስቀድሞ በመወዳደርያ መንደሮች በኮሮና ተሐዋሲ የተያዘ ሰው መገኘቱን ጨምሮ በርካታ ዜናዎች ተሰምተዋል። ይህም ቶክዮ ቀድሞውኑ የተዘጋጀችበትን ጥብቅ የኮሮና መከላከል እና ቁጥጥር እንድታጠብቅ አስገድዷታል። በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቶክዮ ኦሎምፒክ የመክፈቻ ስነስረዓት ባለፈው ዓርብ ሲጀመር ኢትዮጵያውያንን ያስደነገጠ ክስተት ተፈጥሯል። ኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ጫወታዎች ላይ መሳተፍ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በመክፈቻ ስነስረዓት ላይ የሚታደሙ ልዑካን ኢትዮጵያን በሚገልጽ አቀራረብ በስነ ስረዓቱ ላይ ይታደሙ ነበር ፤ በዘንድሮው የቶክዮው ኦሎምፒክ ሁለት ሰዎች ብቻ ኢትዮጵያን ወክለው በአደባባይ ሲያልፉ ታይተዋል። ለክስተቱ የቡድኑ  አባላት አርፍደው ወደ ስነስረአቱ ቦታ መምጣታቸው እንደምክንያት ቢገለጽም ነገር ግን በሆነው ነገር ብዙዎች ቁጣቸውን ገልጸዋል ፤ አስተያየትም ሰጥተውበታል።። 
ካሳሁን ይልማ በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት ፤ «የምወድሽ ደራርቱ ፣ ደሩኮ ከልብ አዝኛለሁ ።  አንቺ እያለሽ እነ አቤ ቢቂላ ባነገሱን ምድረ ጃፓን / ቶክዮ እንደዚህ ለምን አነስን ? ኦሎምፒክ እኮ ከውጤት በላይ ሀገራዊ ውክልና ነው። » ብለዋል። 
ኢትዮ ቤዛ በሚል ስም ትዊተር ላይ በሰፈረ ጽሁፍ ደግሞ «150 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎበት የሄደው የኦሎምፒክ ቡድን ከውድድሩ ጋር ተያያዥነት የሌላቸው 30 ግለሰቦች ሙሉ ወጭያቸው ተሸፍኖ እና የኪስ 3,500 ዶላር ተሰጥቷቸው እንዲሄዱ መደረጉ ተጋልጧል። ለውርደታችን መንስኤው የቴክኒክ ሰዎች መቅረታቸው ነው።»  ሲሉ 
አብዱራህማን የተባሉ ደግሞ «የመክፈቻ ስነስረዓቱ ላይ ከሌሎች ሃገራት በተለየ ኢትዮጵያ በሁለት ሰው ብቻ መታየቷ አስገርሞኛል ። ለመሆኑ አትሌቶቹን ምን በላቸው? » ሲሉ የጠየቁበትን አስተያየት በትዊተር አስፍረዋል። 
ይስሃቅ ካሳ ደግሞ በፌስ ቡክ ባሰፈሩት አስተያየታቸው እንዲህ ብለዋል። «ስለተወካዮቻችን ውርደት ለምን አትነግሩንምከ 86 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች ያሏት ሀገራችን በታላቁ የኦሎምፒክ ውድድር ስመጥር እና አንጋፋ የነፃነት ተምሳሌት የሆኑ እንደነ አበበ ቢቂላ ምሩጽ ይፍጠር ማሞ ወልዴ ደራርቱ ቱሉ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ባለ ድል አትሌቶች የነበራትና ያላትን ሀገራችን ለተሳትፎ ብቻ በሚመስል መልኩ በአንድ ተወካይ በመክፈቻው እለት ስትታይ ሀገሬን በመድረኩ ያሳነሷት መሰለኝ ያዋረዷትም መሠለኝ ነገር ግን ሀገራችን ሀገር ነችና ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ነችና ጥቂት ስግብግብ ና ሌቦች በፈጠሩት ስህተት ሀገራችን አታንስም አትኮስስም በመድረኩ  ሁሌም እንደምትደምቀው በጀግኖቿ ዛሬም በውጤት ትደምቃለች ።» ብለዋል።
ወደ ሁለተኛው ርዕሰጉዳያችን ስንሸጋገር 
 የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት እና አጋር የክልል ኃይሎች ከትግራይ አማጽያን ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ሰሞኑን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚደረጉ ህወሃትን የሚቀወሙ እና የመከላከያ ሰራዊቱን የሚደግፉ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው። ከሰልፉ ባሻገር ህወሃትን ለመዋጋት በርካታ ወጣቶች ከየአካባቢው ወደ ጦር ግንባር እየተሸኙ ነው። ያለፉትን ስምንት ወራት በትግራይ ክልል ሲደረግ የነበረው ጦርነት አሁን ከትግራይ ክልል ውች ወደ አማራ እና የአፋር ክልሎች ተስፋፍቷል። የፌዴራሉ መንግስት በተናጥል የተኩስ አቁም አድርጌያለሁ ቢልም ከሰላም ይልቅ ወደ ለየለት ጦርነት ማምራቱን የሚያመለክቱ የክተት ጥሪዎች ሲስተጋቡ ተስተውለዋል። ይህንኑ የሰሞንኛ ጉዳይ በርካቶች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየታቸውን እንዲያጋሩ ካደረጉ ጉዳዮች አንደኛው አድርጎታል። ደጀኔ አድማሱ በፌስ ቡክ ባሰፈሩት አስተያየት «ጦርነቱ ማን ከማን ጋር እንደሆነ ግራ ያጋባል ይልቁንስ ተረጋግቶ ማሰብ ያስፈልጋል! ሕወሓትም ይሁን መንግስት ከሁለቱም በኩል የሚረግፈው አንድ ወገን እንጂ የውጪ ጠላት የለም! በዚህም 1ኛ መንግስት ለምን እንደሚዋጋ ማወቅ እና ማንን እንደሚወጋ ለይቶ ማስቀመጥ 2ኛ ሕወሓት ለምን እንደምትዋጋ ማንን እንደምትዋጋ ለይታ ማወቅ የግድ ነው ። ሕወሓት ውጊያዋ ከሕዝብ ጋር ከሆነ አማራን እና አፋርን ጨርሳ ካልሆነ ኦሮምያ መግባት አትችልም ይሄንን አውቃ ትግሏን በረድ ብታረገው እና መፍትሄ ቢፈለግ መልካም ነው ።» ብለዋል። 
 አህመዱላሂ አህመዱላሂ ደግሞ  «እኔ እሚገርመኝ ይህ ሁሉ ብሄር እያወገዘው እያየ ሕወሃት ምን ለመሆን ማንንሥ ለመግዛት ነው አራት ኪሎ ልግባ እሚለው ?» በማለት ጠይቀዋል። 
የሐበሻ ልጅ የሐበሻ ልጅ በሚል የሰፈረ ጥያቄያዊ አስተያየት ደግሞ «ስልታዊ ማፈግፈግ ነው እየተባለ ከተሞችን እየለቀቁ ስለሚወጡ ነው ድጋፉ? »ይላል። 
ዕጸገነት ገዛኸኝ በፌስ ቡክ ባሰፈሩት አስተያየታቸው «ሀገር እና  ድንበርን ከጠላት ለመከላከል መዝመት መልካም ሆኖ ሳለ እርስ በርስ መገዳደላችን ደግሞ ልብ ያደማል እግዚያብሄር በቃ ይበልና ጥላቻን በፍቅር ይቀይርልን። »ብለዋል። 
ብሩክ ለገሰ በየከተማው የሚደረገውን ሕወሃትን የማውገዝ ሰልፍ አስመልክተው ባሰፈሩት አስተያየታቸው «እንኳን በሰልፍ በምክር ቤት ተወገዘ እኮ ግን ምንም መፍትሄ አላመጣም ። መፍትሄው መዝመት እና ወንጀለኞችን ይዞ ለህግ ማቅረብ ሲቻል ብቻ ነው።» ብለዋል
አብዱ የተባሉ አስተያየት ሰጬ ደግሞ «ህዝቡን ሰልፍ ሚያስወጡ ካድሬዎች እኮ እልም ያሉ ጁንታ ናቸው ፤ ሕወሓት አራት ኪሎ እያለች እጅ እና ጓንት ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ናቸው ።» 
ሲሉ ፍርዴ ዘገየ የተባሉ አስተያየት ሰጭ መፍትሔ ያሉትን ሃሳብ ባሰፈሩት አስተያየታቸው 
«ከዚህም ከዚያም የሚያልቀው ወገን ነው መንግስት ግን ከዚህ ቦኋላ ለምን ለድርድር ቀድሚያ አይሰጥም ሃገሪቷ ወደማትወጣው ቀውስ እያመራች ነው» ብለዋል።
ሰሞኑን የአዲስ አበባ ሰማይ ከባድ ጭጋግ አልብሶታል። ጭጋጉ ወደ ቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚመጡ አውሮፕላኖችን ወደ ሌሎች አውሮፕላን ማረፊያ እንዲያርፉ ከማስገደድ ባሻገር በከተማዋ የትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። ጭጋጋማ አየሩ በርግጥ በአየር ሁኔታ ትንበያ መሰረት ተጠባቂ እንደሆነ የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጄንሲ አስታውቋል። እንደዚያም ሆኖ ግን  ርዕሰ ጉዳዩ በርካቶችን አነጋግሯል። ከብዙዎቹ ጥቂቱን ለመመልከት ያህል ናትናኤል ቴዎድሮስ የጭጋጋማውን አየር ክብደት ለመግለጽ ባሰፈሩት አስተያየት «አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ ፎቆች ውስጥ ስገባ አውሮፕላን የተሳፈርኩ ያህል ይሰማኛል ብለዋል።» ማርኪ ማርክ የተባሉ በትዊተር ባሰፈሩት አስተያየት በአዲስ አበባ መጥፎ የአየር ሁኔታ በመከሰቱ ከዋሽንግተን ዳላስ የተነሳው አውሮፕላናችን ናይሮቢ ለማረፍ ተገዷል፤ ከእኛም በኋላ የመጣው ድሪም ላይነር በተመሳሳይ ናይሮቢ አርፏል። ይህ ለእኔ በጣም አስገራሚ ነው።» ብለዋል። ሸዋነሽ አለሜ ባሰፉርት አስተያየት « የሰሞኑ ጭጋጋማ አየር በርግጥ ለሀገራችን እንግዳ ነው። በመካከለኛው ምስራቅ በቆየሁባቸው ግዜያት ግን በተደጋጋሚ ተመልክቼዋለሁ ፤ በተለይ በተሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱም ሆነ በእግር የሚጓዙ ሰዎች ጥንቃቄ ካላደረጉ የከፋ አደጋ ሊከሰት ይችላል ።» ብለዋል።
ሱልጣን ከበደ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ደግሞ እንዲህ ከበድ ያለ ጭጋጋማ አየር እንደሚከሰት ሜትሮሎጂ አስቀድሞ የጥንቃቄ መልዕክት ማስተላለፍ ነበረበት ፤ በአየር ጉዞም ሆነ በከተማ ውስጥ እንቅስቃሴ በርካታ የተስተጓጎሉ ሰዎች ስላሉ ።» ብለዋል ። እንግዲህ አድማጮቻችን እናም በሶስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አ,ተኩረን ያሰናዳነው የዕለቱ የማህበራዊ መገናና ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችንም በዚሁ ተጠናቋል ጤና ይስጥልን።
 

Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek
Äthiopien |  Demonstration von Unterstützern des Staudammprojekt GERD
ምስል Seyoum Getu/DW
Äthiopien Bahir Dar | Kundgebung für Defence Force
ምስል Alemnew Mekonnen/DW