1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሐምሌ 16 2013

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ታዬ ደንደዓ አሜሪካ ለኢትዮጵያ በዕርዳታ በሰጠችው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ላይ በጻፉት አስተያየት መነጋገሪያ ሆነዋል። ዘጠኝ ወራት ሊሞላው የሚንደረደረው የሰሜኑ ውጊያ ተሳታፊዎች ብዛት እየጨመረ ሲሔድ የጦርነትን አስቀያሚነት እየነቀሱ እንዲቆም የሚወተውቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች አሉ

https://p.dw.com/p/3xvxN
USA | Coronavirus | Impstoff von Johnson & Johnson
ምስል Michael M. Santiago/Getty Images

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ታዬ ደንደዓ በግል የፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ሳምንቱን መነጋገሪያ ሆነው ቆይተዋል። አቶ ታዬ "ለጥንቃቄ ያክል" ብለው በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጻቸው ያሰፈሩት ጽሁፍ አሜሪካንን በብርቱ የሚወቅስ ነው።

"አሜሪካ የኢትዮጵያውያንን ምርጫ በማጣጣል በመዋጮ ስም ተላላኪ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ለመሾም ጡረተኛ ፖለቲከኞችን እያሰባሰበች ትገኛለች፤ የህዳሴ ግድብን እንዳንሞላ ከጠላቶቻችን ጋር ወግናለች" የሚል ውንጀላ ያቀረቡት ፖለቲከኛው፤ ልዕለ ኃያሏ አገር ከኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት ውጊያ የገጠመውን ህውሓት "በሞራል እና በቁሳቁስ" መደገፏን፤ "በኢትዮጵያ ውስጥ የወረዳና የቀበሌ ድንበሮችን ለመወሰን" መከጀሏን እየጠቀሱ ክሳቸውን ያጠናክራሉ። 

አቶ ታዬ እንደሚሉት አሜሪካ ለኢትዮጵያ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት በእርዳታ ለመስጠት የወሰነችው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይዞታል የሚሉትን ቂም ለማረሳሳት ነው። ከዚህ አመክንዮ እየተነሱ አቶ ታዬ "የኢትዮጵያዉያንን ምርጫ እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማያከብር ሀገር ለምን እርዳታ ይሰጠናል?" እያሉ ይጠይቃሉ።

"ሚዲያችንስ እርዳታ መቀበላችንን እንደ ታላቅ ድል ለምን ይዘግባል? እኛስ ለምን ከጠላታችን እጅ እርዳታ እንቀበላለን?" የሚሉት አቶ ታዬ ገፋ አድርገው "ክትባቱ ራሱ ኮሮናን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት የማዕከላዊ የስለላ ኤጀንሲ (CIA) ሴራ አለመሆኑንስ በምን እናዉቃለን?" እያሉ የሴራ ትንታኔ ያቀርባሉ። ወትሮም አወዛጋቢ አስተያየቶች በመስጠት የሚታወቁት አቶ ታዬ እንዲያውም "በኔ እምነት ከሞራልና ከጤና አኳያ ክትባቱን አለመቀበል ይበጀናል" እስከ ማለት ደርሰዋል።

Äthiopien Addis Ababa | Lia Tadesse Gesundheitsministerin
የጤና ምኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ "የኢትዮጵያ መንግሥት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት የአሜሪካ መንግስት ከመጀመሪያው ጀምሮ በአጋርነት ሲደግፍ የቆየ መሆኑን፤ አሁንም ወረርሽኙ እያደረሰ ያለውን ጫና ለመቋቋም ትብብሩን አጠናክሮ በመቀጠል ይህን የክትባት ድጋፍ በማድረጉ ምስጋናቸውን" እንዳቀረቡ መስሪያ ቤታቸው በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

ይኸ ፖለቲካ እና የኮሮናን ክትባት ጉዳይ ያቆራኘ አወዛጋቢ አስተያየት በአቶ ታዬ የፌስቡክ ገጽ የሰፈረው ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር። ይኸ ማለት ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መንግሥት እርዳታ የተሰጣትን 453 ሺህ 600 የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮቪድ-19 ክትባቶች ከተረከበች በኋላ መሆኑ ነው። 

የጤና ምኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ "የኢትዮጵያ መንግሥት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት የአሜሪካ መንግስት ከመጀመሪያው ጀምሮ በአጋርነት ሲደግፍ የቆየ መሆኑን፤ አሁንም ወረርሽኙ እያደረሰ ያለውን ጫና ለመቋቋም ትብብሩን አጠናክሮ በመቀጠል ይህን የክትባት ድጋፍ በማድረጉ ምስጋናቸውን" እንዳቀረቡ መስሪያ ቤታቸው በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።

በጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት የአሜሪካ መንግስት በአጠቃላይ ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው 1.2 ሚሊዮን ዶዝ የጆንሰንና ጆንሰን ክትባት ለኢትዮጵያ ለመለገስ ቃል የገባ ሲሆን የተቀረው በቀጣዮቹ 2 ሳምንታት ውስጥ ለኢትዮጵያ ይደርሳል። 

አቶ ታዬ በፌስቡክ ገጻቸው ያሰፈሩት ጽሁፍ እስከ ትናንት ሐሙስ ሐምሌ 15 ቀን 20113 ዓ.ም. ድረስ ብቻ ከ9 ሺሕ በላይ ሰዎች የወደዱት ሲሆን ከአንድ ሺሕ ጊዜ በላይ ተጋርቷል። ይኸው አወዛጋቢ አስተያየት ከ1 ሺሕ 700 በላይ አስተያየቶች ተሰጥቶታል።  

USA | Coronavirus | Impstoff von Johnson & Johnson
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መንግሥት እርዳታ የተሰጣትን 453 ሺህ 600 የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮቪድ-19 ክትባቶች ተረክባለችምስል Mary Altaffer/AP Photo/picture alliance

ንብረት አዳሙ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "እውነት ለመናገር ክትባቱ አያስፈልግም። ስለተከተብን አይደለም ያለነው በእግዚአብሔር ቸርነት እንጂ ክትባት አንፈልግም" የሚል አስተያየት አስፍረዋል። ዘሪሁን ታምሩ ደግሞ "ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳል። ክትባቱ በጤና ባለሞያዎች የተረጋገጠ ከሆነ ብንጠቀመው ጥሩ ነው። ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል" ብለዋል። 

ሰና አብዲሳ "አንድ ትልቅ የመንግስት ባለስልጣን የኮቪድ-19 ክትባት ላይ ላይ ይኼን ያክል ጥርጣሬ ካለው ህዝብ እንዴት አምኖ ልከተብ ይችላል?" በማለት ጠይቀዋል። በቄ አኬ "መከተብ አለመከተብ የሰው ምርጫ ነው። ግን አሁን አንተ መረጠን ለምትለው ህዝብ እየዘገብክ ያለኸው ለተከተበው ድንጋጤን፤ ላልተከተበው ግራ ማጋባትን፤ መከተብ ለሚፈልገው ጭንቀትን ነው። ሊያውም ምንም የጤና እውቀት ሳይኖርህ" ሲሉ ነቅፈዋቸዋል። ድሪብሳ ጀቤሳ "ልብ በሉ አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለ ስልጣን ለህዝቡ አትከተቡ ብሎ መልክት ስያስተላልፍ። ጤና ምንስትሯ ደግሞ መጥታ ተከተቡ ትበል ወይስ ትተው? ጉድ እኮ ነው" ሲሉ የሚፈጠረውን ግራ መጋባት ጠቆም ያረገ አስተያየት ጣል አድርገዋል። 

ያሬድ እስጢፋኖስ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ አቶ ታዬ ባቀረቧቸው ውንጀላዎች ላይ ያነጣጠሩ አምስት ምላሾች በተራ ቁጥር ቅደም ተከተል ሰጥተው ጽፈዋል። በአንደኛ "ምርጫው አግላይ (ኢፍትሃዊ) ነበር። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ መርጧል ማለት አይቻልም።" ሁለተኛ "የአሜሪካ ችግር ከናንተ እንጂ ከኢትዮጵይ ህዝብ ጋር አይደለም" ሶስተኛ "እኛ ካድሬዎች መሬት እየቸበቸብን እና በሌብነት ገንዘብ እናገኛለን እና ምዕራባውያን ኢትዮጵያን አይርዱ ማለት ለህዝብ አለማሰብ ነው" የሚሉት አቶ ያሬድ በአራተኛ ደረጃ በሰጡት አስተያየት "ለተራ የፖለቲካ ጥቅም ህዝቡ የ ኮቪድ-19 ክትባት እንዳይወስድ መቀስቀስ አስነዋሪ ነው" ሲሉ ነቅፈዋል።  በአምስተኛ ተራ ቁጥር ባስቀመጡት አስተያየት ደግሞ "የባይደን አስተዳደር ግድቡን በተመለከተ ከግብፅ ጎን አልቆመም። በእርግጥ የትራምፕ አስተዳደር ግድቡን በተመለከተ ለግብፅ ያደላ ሲሆን የትግራዩን ጦርነት በተመለከተ ግን ከአብይ ጎን ቆሞ ነበር" ብለዋል።
ኢሳቅ እሸቱ በበኩላቸው "የመንግሥት ትላልቅ ባለሥልጣናት በዚህ ቋንቋ የሚነጋገሩ ከሆነ የአገሪቱ ዲፕሎማሲ በእርግጥም አደጋ ውስጥ ነው" ሐሳብ እንደገባቸው የሚጠቁም አስተያየት ጣል አድርገዋል። 

ሚሚ ኤፍሬም "ክትባት መከተብ ወይም ያለመከተብ የራስ ምርጫ ሆኖ ሳለ ከአንድ ባለስልጣን እንዲህ አይነት መልእክት ለህዝብ ማስተላለፍ ምን ይባላል?? ለፖለቲካ ብላችሁ ህዝቡን አታስጨርሱ ባካችሁ።" በማለት ምክር ሰጥተዋል። 

Äthiopien I Situation in Tigray
ሁሉም በየፊናቸው በሚቆጣጠሯቸው መገናኛ ብዙኃን እና ፌስቡክ እና ትዊተርን በመሳሰሉ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የበላይነታቸውን ለማሳየት ይታትራሉ። በርካታ መረጃዎች ያሰራጫሉ። የዛኑ ያክል የጦርነትን አስቀያሚነት እየነቀሱ እንዲቆም የሚወተውቱም አሉ። ምስል Ben Curtis/AP/picture alliance

ነገረ ጦርነት

ስምንት ወራት አገባዶ ዘጠነኛ ወር ሊሞላው በሚንደረደረው የህውሓት እና የፌድራል መንግሥት ጦርነት የተሳታፊዎቹን ብዛት እና ያዳረሰውን ቦታ እያሰፋ ሲሄድ ይታያል። ውጊያው ግን በጦር አውድማዎች ብቻ አይደለም። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጭምር እንጂ። ሁሉም በየፊናቸው በሚቆጣጠሯቸው መገናኛ ብዙኃን እና ፌስቡክ እና ትዊተርን በመሳሰሉ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የበላይነታቸውን ለማሳየት ይታትራሉ። በርካታ መረጃዎች ያሰራጫሉ። የዛኑ ያክል የጦርነትን አስቀያሚነት እየነቀሱ እንዲቆም የሚወተውቱም አሉ። 

አቡታ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ "ይጮሀሉ፣ ይጨፍራሉ። የጦርነት ውጤት የሚያብሰለስላት እናት ግን ትተክዛለች። ጦርነት አይተን ሲያልቅ የምንረሳው የሆሊውድ ፊልም አይደለም። ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፤ ብዙ ጠባሳ ትቶ ያልፋል...በቃችሁ ይበለን" በማለት ጽፈዋል።

ቀይ ቀበሮ በሚል ስም ትዊተር የሚጠቀሙ ግለሰብ ደግሞ "መነጋገሩ የተሻለ መሆኑን "መረዳት" አለባቸው አለብን። ጦርነት የሰውን ህይወት ይቀጥፋል፤ ንብረትን ያወድሟል። ስለዚህ መነገሩ ወደፊት እንጅ ወደኋላ አይጎትተንም" ብለዋል። 

ሐብትሽ ዶ ይልማ በፌስቡክ ገፃቸው "ጦርነት አስከፊ ነው፤ ጦርነት ውጤቱ አምሮ አያውቅም፤ ጦርነት ገዳይም ተገዳይም አለው፤ ለሚሞትበት ወገን ሃዘኑ ቁጭቱ የዘላለም ነው። ጦርነት ውድ ነው። መሳሪያው፣ ዩኒፎርሙ፣ ቀለቡ የሚያወድመው ነገር ብዙ ነው... ጦርነት አይተን ሲያልቅ የምንረሳው የሆሊውድ ፊልም አይደለም" ሲሉ ጽፈዋል። ጦርነት "ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፤ ብዙ ጠባሳ ትቶ ያልፋል... በዚ ዘመን ማንም ጦርነትን የመጀመርያ አማራጭ ሊያደርግ አይገባም ነበር፤ እንዳለመታደል ሆኖ ጦርነት ያንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ስላልሆነ... አንዱ አልፈልግም ጦርነት ይቅር ቢልም በሌላው ተንኳሽነት ጦርነት ይገባል" ይላሉ ሐብትሽ። "ስግብግብነት፤ ግትርነት፤ ሰጥቶ መቀበል እያቃተና የስልጣን ጥም ገደብ እያጣ ዘንድሮም በ21ኛው ክፈለ-ዘመን ብዙ ተምረን፤ ብዙ አይተን፤ የጦርነትን አስከፊነትም በሚገባ አውቀን ይሄው እርስ በእርስ እንዋጋለን...  እግዚአብሔር በቃችሁ ይበለን፤ ለሃገራችን ሰላም ያምጣልን። የመስማማት፣ የመነጋገር፣ የመተውን የመደራደር፤ ቆም ብሎ የማሰብያ ልብ ይስጥልን።  ሃገራችን ኢትዮጵያውያን ሰላም ያድርግልን! ሌላ ምን ይባላል?" በማለት አብቅተዋል። 

Äthiopien Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌትን ማጠናቀቋን ይፋ ስታደርግ በርካቶች ደስታቸውን ፌስቡክ እና ትዊተርን በመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲገልጹ ታይተዋል። ምስል AFP/Maxar Tech

የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት

ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌትን ማጠናቀቋን ይፋ ስታደርግ በርካቶች ደስታቸውን ፌስቡክ እና ትዊተርን በመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲገልጹ ታይተዋል። ለኃይል ማመንጫ የሚያገለግሉ ሁለት ተርባይኖች ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገው የውኃ መጠን በታላቁ የኅዳሴ ግድብ መጠራቀሙን የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ምኒስትሩ ስለሺ በቀለ በትዊተር ገጻቸው ባለፈው ሰኞ ይፋ አድርገዋል። "ሁለቱ ተርባይኖች ኃይል እንዲያመነጩ ብርቱ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ያንን በቅርብ ወራት በማጠናቀቅ ልፋታችንን ውጤት ላይ እናደርሳለን" ብለዋል።

ግድቡ ሰባት ጊዜ የሚሞላ ነው። ኢትዮጵያ ከሱዳን እና ግብጽ በምታደርገው ድርድር በውኃ ሙሌት ሒደቱም ሆነ በግድቡ አስተዳደር ላይ እስካሁን ከሥምምነት አልደረሱም። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የግድቡ የውኃ ሙሌት "በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ ችግር ስለማይፈጥር ስጋት አይግባችሁ። ግድቡ እውነተኛ ሀብት ሆኖ የጋራ ዕድገትና ትብብር መለያ ሆኖ ይቀጥላል" የሚል መልዕክት ያዘለ ደብዳቤ በአረብኛ ጽፈው በትዊተር አሰራጭተዋል። በርካታ ኢትዮጵያውያንም ሲቀባበሉት ታይቷል። 

የውኃ ጠብታ በሚል ስም ትዊተር የሚጠቀሙ ግለሰብ "ሁላችንም ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ ያለን!  ይህ ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ ሙሌት ከድህነት ለመውጣትና ወደ ብልጽግና ለማምራት ፈር ቀዳጅ ጎህ ነው" ብለዋል። ከድር አብዱሌ ደግሞ "የሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍላጎት የህዳሴ ግድብ ስራ አልቆ የህዝቡን ሰቆቃ ሲቀረፍ [ማየት] ብቻ ነው" በማለት ከውኃ ሙሌቱ ባሻገር በተጨባጭ በአገሪቱ ሕዝብ ኑሮ ላይ ለውጥ እንደሚጠበቅ የሚጠቁም አስተያየት አስፍረዋል። 

ወንድወሰን መንግሥቱ በበኩላቸው "የህዳሴው ግድብ ሙሌት አኩርቶናል። ጉጉታችን የ65 ሚሊዮን ወገኖቻችን ብርሃን ማግኘትና የተሻለ ህይወት ኖረው ማየት ነው። ጉዟችን ግን ከዛም ያልፋል፤ ኢትዮጵያ ተግዳሮት ቢኖርባትም ሁሉንም ተቋቁማ ወደ ከፍታዋ ትደርሳለች። ዕድሜ ለቁርጠኛ ልጆቿ!" ብለዋል። 

እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ