1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሐምሌ 9 2013

የአለማጣና የኮረም ከተሞች በህወሃት  ሀይሎች እንደገና ተያዘ መባል፤በኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የወጣው የታዳጊ ህፃናት ወታደሮች ምስል እና lበትግራዩ ቀውስ የአሜሪካ መንግስት መግለጫ በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ  በርከት ያሉ አስተያየቶች የተሰጡባቸው ናቸው።

https://p.dw.com/p/3waXd
Logos App Twitter Facebook Google
ምስል picture-alliance/xim.gs

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት


የአለማጣና የኮረም ከተሞች በህወሃት  ሀይሎች እንደገና ተያዘ መባል፤በኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የወጣው የታዳጊ ህፃናት ወታደሮች ምስል እና በቀጠለው የፌደራል መንግስቱና የህወሃት  ፍጥጫ የአሜሪካ መንግስት  መግለጫ በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ  በርከት ያሉ አስተያየቶች የተሰጡባቸው ናቸው።
 መንግስት ወሰድኩት ባለው የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት በመጠኑም ቢሆን ጋብ ያለ የመሰለው የህወሃትና የፌደራል መንግስቱ ግጭት በዚህ ሳምንት ግን  እንደገና አገርሽቷል።ይህም አንዳች መነጋገሪያ ለማያጣው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ  መወያያ ሆኖ ነው የሰነበተው። 
በሳምንቱ መጀመሪያ  የኮረምና የአለማጣ ከተሞችን የህወሀት ሀይሎች መቆጣጠራቸው መሰማቱን ተከትሎ፤ የአማራ ክልል መንግስት  በክልሉ   የሕልዉና ስጋት መደቀኑን  ገልጾ፤ ይህንን ለመቀልበስ የክተት አዋጅ ሲያውጅ፤ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ  በበኩላቸው ፤ ግጭት ላለማባባስና ለሕዝቡ የእርሻ ወቅት ፋታ ለመስጠት እንዲሁም የእርዳታ አቅርቦቱ ያለ ሰበብ እንዲከናወን ሲባል  በትግራይ በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ  የተናጠል የተኩስ አቁም መደረጉን ገልፀው፤ ነገር ግን ለሕዝባችን ስንል የከፈልነው ዋጋ «ባልገባቸው» ባሏቸው ሀይሎች  ውጤት አለማምጣቱን ገልፀዋል። ህዝቡ ከሀሰተኛ መረጃ ራሱን ይጠብቅም ብለዋል።የሀገር መከላከያ ሚንስቴር  የሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ለመገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫም  ህዝቡ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል ።
ይህንን ተከትሎ የከተሞቹ መያዝ  አንዳንዶችን ሲያስፈነድቅ አንዳንዶች ደግሞ መንግስትን ወቅሰዋል።
ምህረት ሀጎስ «ከዚህ በኋላ አራት ኪሎ ጠብቁን ።»ሲሉ  «እንግዲህ ዕቅዳችሁን በዝርዝር ንገሩንና ከመንግስት ይልቅ እናንተን መስማት ነው። ወይ ነዶ።» ብለዋል ሰላማዊት ታደሰ። ማለደ ግርማይ የተባሉ አስተያየት ሰጪ  ደግሞ ለትግራይ ገበሬ የተኩስ አቁም ያደረገ መንግስት የአማራን ገበሬ ለጦርነት መቀስቀሱ ይገርማል።የአማራ ገበሬ አይርስም ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል።
የሹሜ ጣሴ በበኩላቸው «ድልም አሸናፊም የሌለበት የእርስ በእርስ ጦርነት ምን ይጠቅማል።»ሲሉ፤ ዳግማዊ አዲስ ደግሞ ««መንግስት አሸባሪ ብሎ የፈረጀውን ድርጅት ለአማራ ክልል ህዝብና መንግስት አስረክቦ የምን ዳር ዳሩን መዞር ነው።»በማለት ፅፈዋል።
አወል አብዱ በበኩላቸው «ከሀሰተኛ መረጃ ራሳችሁን ጠብቁ ብለዋል።መንግስት ትክክለኛውን መረጃ በጊዜ ካልሰጠን ምን እናድርግ ታዲያ።»ሲሉ፤ መሳፍንት ተፈራ ደግሞ «ምንም ቢሆን መሬት ላይ ያለውን እውነታ ቦታው ላይ ካሉት ወታደሮች በላይ ከተማ ውስጥ ተቀምጦ ፌስቡክ ላይ የሚጽፍ ሰው ሊያውቅ አይችልም። እና  እባካችሁ ቢያንስ በዚህ ጉዳይ የአላዋቂ ትንታኔ ይቅርብን»በማለት ፤ የሌ/ጄ ባጫን «ወታደራዊ ሥራ በውትድርና ባለሙያዎች እንጂ፣ በአክቲቪስቶች የሚመራ አይደለም።" የሚለውን ሀሳብ አጠናክረዋል። ታደለች መኩሪያ  የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ «እውነት ነው።ጦር ከፈታዉ ወሬ የፈታዉ እንዳይህን ጥንቃቄው ወሳኝ ነዉ።»ብለዋል።
አሚራ ኢዛ «ህዝቡ ኑሮ ተወዶበት በልቶ ማደር አቅቶታል እናንተ ደግሞ ጦርነት ታውጃላችሁ። እስቲ ስከን ብለን ወደ ውይይት። ጦርነት ለማንም አይበጅም።»ነው ያሉት። መንግስት በትናንትናዉ ዕለት ከተሞቹን «መልሼ ተቆጣጥሬያለሁ» ማለቱን የሰሙት »ሮማን ፍሪድ ደግሞ «እኔን የጨነቀኝ ጨዋታው እግር ኳስ ይመስል ስንት ዓመት ይሆን ተቆጣጠሩ ተቆጣጠርን የምንለው።የሰው ህይወት እየጠፋ ደም እየፈሰሰ ነው።የሚለቁትም የሚያስለቅቁትም። መቋጫው መቼ ይሆን? »በማለት ፅፈዋል።
ሌላው በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ  የሆነው ጉዳይ ፤የህወሃት ኃይሎች የፌደራል  መንግሥቱን  ጦር ከትግራይ ያስወጡበት መንገድ  በሚል  የአሜሪካው ኒው ዮርክ ታይምስ  ሰሞኑን ይዞት በወጣው  ዘገባ  የጦር መሳሪያ የታጠቁ ታዳጊዎች ምስል መታየቱ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም   ኒውዮርክ ታይምስ እና አሶሼትድ ፕሬስ በዘገባዎቻቸው ላይ ህወሓት ህጻናትን ለውትድርና መጠቀሙን አሞካሽተው ማቅረባቸው የሚያሳዝን ነው ሲሉ፤ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።የኢትዮጵያ የሴቶች የህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚንስቴርም የዓለም አቀፉ ማህበረስብ ሁኔታውን እንዲያወግዝ መጠየቁን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።ይህንን ተከትሎ፤ ራሄል ራሄሎ የተባሉ አስተያየት ሰጪ «አሜሪካ ዲሞክራሲን እኮ እሷ በፈለገችው መንገድ ነዉ ምትተረጉመው። እነሱ ሲፈልጉ ትክክል ነዉ ።ሳይፈልጉ ወላጅ ልጁን መቅጣት እንኳን ትልቅ ወንጀል ይሆናል። መንግስት ለአሜሪካ የሚይጎበድድበት ምክንያት አይታየኝም። ለአገሪቱ የሚጠቅማትን መንገድ ብቻ መከተል አለበት። »ሲሉ፤ ሀርያ መኮንን ደግሞ «እግዚአብሔር ልቦና ይስጣቸው። ህጻናትን በዚህ ሁኔታ ማየት እጅግ በጣም ያማል»ብለዋል።
ስንዱ ጓል ወየንቲ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ግን ነገሩ የተዋጠላቸው አይመስሉም «ከመቸ ጀምራችሁ ነው ስለትግራይ ልጆች ተቆርቋሪ የሆናችሁ። የደርግ ርዝራዞች ከሚጨፍጭፋቸው ከአባታቸው ጋር ወደ ትግል መቀላቀል ይሻላቸዋል።»ሲሉ፤
 ኪሮስ ግርማይ ደግሞ « የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈፅሙባቸው ህፃናት አይደሉም።ዛሬ ሃገራቸውን ከወራሪ ሲከላከሉ  ለነፃነታቸው ጦር ሲይዙ ግን ለነሱ ህፃናት ናቸው።ያዝኑላቸዋል ምን አይነት አመለካከት ነው?»ብለዋል።
ዓለም በቀለ በበኩላቸው «ማንም ያድርገው ማን ልጆች በሚቦርቁበት ዕድሜ የጦር መሳሪያ አሸክሞ ማንገላታትም፣ መደፈርም መገደልም የለባቸውም።ሁሉም መወገዝ አለበት። የመብት ጥሰት ስለደረሰባቸው  ወታደር ይሁኑ ማለት አሳዛኝ መከራከሪያ ነው።ጌታ ልቡና ይስጠን።»ብለዋል
 ታሪኩ ማሞ ደግሞ  «ጦርነት በየትኛውም አለም ቅዱስ ሆኖ አያውቅም። ግን በግፍ የመጣን ጥቃት ለመመከት እድሜና ጾታ ቦታ የላቸውም። »ሲሉ፤
ረሂማ ቃሲም «  ኢትዮጵያ ፈርማ ያጸደቀችው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽን፤ አገራት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች በጦርነት ውስጥ ተሳታፊ አለመሆናውን ማረጋገጥ አለባቸው ይላል።»ታዲያ ይህ ለመቼ ነው የሚሰራው?።»በማለት  የላይኛውን አስተያየት ነቅፈዋል።
ሸጋው ተክሌ «አንድ አካል ሌለውን አካል በጠላትነት መፈረጅ መብቱ ወይም ፍላጎቱ ቢሆንም የህፃናትን አዕምሮ መርዞ ለሞት ማዘጋጀት ከሰውነት ባህሪ የወጣ ነው።እኩይ ድርጊት ነው። ህፃናት ይኑሩ ፣ይደጉ ፣ይማሩ ይወቁ፣ አድገው ያገናዝቡ ፣ሙሉ ሰው ይሁኑ።  ህፃናቱን ወደ እሳት የምታሰማራ ቀድመህ እራስህንና ልጅህን አሰማራ ያኔ ስሜቱን ትረዳዋለህ። አምላክ ሆይ ህፃናትን ታደግ».ብለዋል።
« እኔን የገረመኝ ለሰብዓዊ መብት እንቆረቆራለን የሚሉት የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ነገሩን ባላዬና ባልሰማ ማለፋቸው ነው።» ያሉት ደግሞ ባንቺ ሁሉቃ ናቸው። 
የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ከትግራዩ ግጭት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰት አሳስቦኛል በሚል ለተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቷል መባሉ  ሌላው በዚህ ሳምንት አነጋጋሪው ጉዳይ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ  የሕብረቱን የውሳኔ ሃሳብ ጊዜውን ያልጠበቀ እና በፖለቲካ ፍላጎት የተላለፈ ነው ሲል ተቃውሟል።
የአሜሪካ መንግስት በተናጠል ባወጣው መግለጫም  የትግራይ ቀውስ አሳስቦኛል ሲል ገልጿል። ይህንን ተከትሎ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል።
በልሁ ሀይልዬ «አሜሪካ በሰብዓዊ መብት ትከሰው ከነበረው ህወሃት ጋር እንዲህ በፍቅር የወደቀችበትን ምክንያት ባስብ ባስብ ሊገባኝ አልቻለም።» ሲሉ፤
ዊንታና በሚልስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«በትግራይ ይህ ሁሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰ አሜሪካ እንድትደግፋችሁ ትፈልጋላችሁ ?»ይላል።
ክንዱ ሙሀመድ በበኩላቸው «አሜሪካ ህወሃትን የምትደግፈው ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ተቆርቁራ ነው ብዬ አላስብም።ምናልባት ኢትዮጵያን በማፍረስ ለግብፅ ውለታ ለመዋል ይሆናል።»ብለዋል። «የአሜሪካ መንግስትንና የአውሮፓ ህብረትን  ከመውቀሳችን በፊት የራሳችን መንግስት የቤት ስራውን ሰርቷል ወይ ?ብሎ መጠየቅ የተሻለ ነው።»ያሉት ደግሞ ሰርኬ ደበላ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
አስማማው ገብረእግዚያብሄር በበኩላቸው «በእርዳታና በብድር የምትኖርን ሀገር  እንደፈልግን እናዛለን ቢሉ ምን ይገርማል።»በማለት አስተያየታቸውን አስፍረዋል።
«ድሃ ክብር የለውም ያለው ማነው? የሀገር ሉዓላዊነትን ለዕርዳታ አሳልፎ መስጠት ውርደት ነው።እንዲህ የሚያስብ ትውልድ መፈጠሩ ያሳዝናል።»በማለት አስተያየት የሰጡት ወርቁ  ዳባ ናቸው።«ኢትዮጵያውያን ለምንድን ነው የምእራቡን አለም ሙገሳና አድናቆት የምንፈልገው?ግልጽ ነው በድህነታችን ስለሚንቁን የኛ ጉዳይ ምናቸውም አይደለም። አርፈን አንድነታችንን ብናጠናክር ይሻላል።ያሉት ደግሞ ፈረደ ዘገዬ  ናቸው።
ማህሌት ስዩም ደግሞ «እርስ በርሳችን የማንደማመጥ።በ21ኛው ክፍለ ዘመን በቃላት ተነጋጋግረን መስማማት አቅቶን በጠመንጃ አፈሙዝ የምንነጋገር ታዲያ ቢንቁን ምን ይገርማል።እንደ እብድ ገላጋይ ሁሉም ድንጋይ የሚያቀብል ከሆነና እኛ ካልተስማማን ለእነሱ ምቹ ሆነን ተገኝተናልና መፍትሄ ከምዕራባውያን ከመጠበቅ በቀር ምን እናደርጋለን።»በማለት በቁጭት ፅፈዋል።

Äthiopien Tigray-Krise | Soldaten TPLF
ምስል Ben Curtis/AP/picture alliance
Äthiopien | Jubel beim Einmarsch der TDF in Mekelle
ምስል DW
Äthiopien | Mai Aini Flüchtlingscamp
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images

ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ