1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሐምሌ 2 2013

«ጀግና ማለት እንደ አበበች ጎበና የዘር ልዩነትንና የግል ፍላጎትን የተሻገረ ሰውን ብቻ ማዕከል ያደረገ ሰብዓዊነት ነው።እንደ አለመታደል ሆኖ እኛ ሀገር ግን ጀግና የሚኮነው ወንድም ወንድሙን ገድሎ ነው።እባካችሁ ቢያንስ ለክብራቸው የሚመጥን ሀውልት ይሰራላቸው።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/3wHH2
Facebook Group Schriftzug
ምስል Richard Drew/AP/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት


 የደግነትና የሰብዓዊነት ምልክት የሆኑት የዶክተር አበበች ጎበና ከዚህ ዓለም በሞት መለየት፤የቀጠለው የህወሃትና የፌደራል መንግስቱ ውዝግብ እንዲሁም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ሙሌት በዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የምንዳስሳቸው ጉዳዮች ናቸው።
ከ40 ዓመታት በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናትን ተንከባክበው ለቁምነገር ያበቁትና አፍሪካዊቷ ማዘር ትሬዛ በሚል ስም የሚታወቁት የበርካቶች እናት ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና  ያለፈው እሁድ ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ/ም  የህልፈታቸው ዜና ከተሰማ ጀምሮ በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ጥልቅ ሀዘናቸውን ሲገልፁ ነው የሰነበቱት።
ዓለም ገብሩ የተባሉ አስተያየት ሰጪ « የብዙዎች እናት ክብርት አበበች ጎበና ! እናትነትዎ በልጆችዎ ብቻ ሳይሆን በትዉልድ ሲከበር.፣ሲዘከር ይኖራል። ላደረጉት መልካም ተግባር እናመሰግናለን!!! ነፍስዎም በሰላም ትረፍ» ሲሉ፤ ዙፋን ያለው ደግሞ «-ዘር ሳይቆጥሩ ብሄር ሳይጠይቁ መጠጊያ ያጡ ህፃናትን የሰበሰቡ የሰብዓዊነትና የርህራሄ ተምሳሌትና የተግባር ባለቤት! ነፍስ ይማር!»ብለዋል።
መሰረት ሀይሉ በበኩላቸው «ጀግና ማለት እንደ አበበች ጎበና የዘር ልዩነትንና የግል ፍላጎትን የተሻገረ ሰውን ብቻ ማዕከል ያደረገ ሰብዓዊነት ነው።እንደ አለመታደል ሆኖ ግን እኛ ሀገር ጀግና የሚኮነው ወንድም ወንድሙን ገድሎ ነው።እባካችሁ ቢያንስ ለክብራቸው የሚመጥን ሀውልት ይሰራላቸው።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ሰውኛ በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «በህይወት ዘመናቸው የተጠየፉትን ዘረኝነት አበበች  ከዚህ ናት ከዚያ ናት እያላችሁ አስከሬናቸውን ወደ ዘር ቋት ለመጨመር የምትታገሉ ሰዎች እያየሁ ስለሆነ፤ እባካችሁ ንጹህ ነብሳቸውን አታቆሽሿት።»ይላል።
ኩሩ አለማየሁ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «ሳይማሩ ይህን የእውቀት ርህራሄ የሰጣቸው በህይወት ዘመናቸው እግዚአብሄርንም ሰውንም ሳያሳዝኑ ወደ ዘላለም ቤታቸው በክብር ሄደዋል። ነብሳቸው ከቅዱሳን ጎን ትረፍ።ዛሬ ላይ  ተማርን የምንል ሰዎች በዘር ተቧድነን አየተገዳደልንና አንዱ አባራሪ ሌላው ተባራሪ ሆነን እየኖርን ነው።ያልተማሩ ወገኖቻችን ያቆዩያትን ሀገር ተማርን ያልን ሰዎች እየከፋፈልናት እንገኛለን ።ያሳዝናል።»ብለዋል።
ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ደግሞ «ሀገር ሆነው የኖሩ እናት!« ካሉ በኋላ፤«ስራዎ ለምንዱባን ህይወት ሆኗል:: በርካቶች አርአያዎትን ተከትለዋል።የሀገር እናት ነበሩና ታሪክዎ የሀገር ታሪክ ሆኖ ይኖራል።እናታችን አግዚአብሔር ነፍስዎን በአፀደ ገነት ያሳርፋት!»በማለት ፅፈዋል።
ላለፉት ስምንት ወራት ከህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ  ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት  ከትግራይ ክልል ሠራዊቱን በማስወጣት ሰብአዊነትን መሠረት ያደረገ ያለውን የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ገልጾ ነበር።መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔውን ይፋ ካደረገ ከቀናት በኋላ ምላሽ የሰጠው ህወሓት ለተኩስ አቁሙ ተግባራዊነት ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሟሉ ጠይቋል። ይህም  የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን በእጅጉ አነጋግሯል።
ተስፋ ሀጎስ  የተባሉ አስተያየት ሰጪ «ህጋዊ መንግስታችን ወደ መቀሌ ተመልሷልና ገና ብዙ ጥያቄ ይቀርባል።»ሲሉ 
አይናለም  ሀይሌ በበኩላቸው«ለትግራይ ህዝብ የሚያስቡ ከሆነ  ያለ ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁመው ለዕርዳታ ስራው ቅድሚያ ቢሰጡ የተሻለ ነበር።»ብለዋል።
የቸልሲ ነኝ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«መንግስትን ለመውጋት የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ፤ ኢንተርኔት የሚጠይቅ ቅንጡ ድርጅት እንደ ህወሃት አላየሁም ።»ይላል። «በጀት ይለቀቅ ብለዋል።ገንዘብ ሰጥቶ ራሱን የሚያስወጋ መንግስት ካለ እንግዲህ እናያለና።»ያሉት ደግሞ አሌክስ አብርሃም ናቸው።ሀና ያደታ ደግሞ «እኔ በበኩሌ መንግስትም ይሁን ህወሃት በየ ፊናቸው መፎከሩን ትተው ለሀገርና ለህዝብ ሲሉ  ወደ ቀልባቸው ቢመለሱ መልካም ነው ።»ብለዋል።
ከዚሁ ከትግራዩ ቀውስ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ላላቸው አካላት ከአዲስ አበባ የሚነሳ የበረራ ፍቃድ መስጠቱን ማስታወቁ፤ በዚህ ሳምንት ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር።
ሳላዲን አህመድ«የመንግስት ፈቃድ ጥሩ ጅምር ነው ገና ብዙ ሰብዓዊ እርምጃ ይጠበቃል።»ሲሉ፤
ማርታ በየነ ደግሞ «መንግስት ወዶ ሳይሆን ተገዶ ነው»ብለዋል። ሰሚራ ሀጂ በበኩላቸው «ተገዶም ይሁን  ወዶ  ዋናው ለተቸገሩ ሰዎች ዕርዳታ እንዲደርስ መንገድ መፈቀዱ  ነው።እንዲህ ያለው ጀብደኝነት ምስኪኑን የትግራይ ህዝብ እየጎዳ ነው።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
የሱነህ ወልዴ ደግሞ«ከዚሕ ቀደም በእርዳታ ሰበብ ጦር መሳሪያ ሲያጓጉዙ ተደርሶባቸዋል። ያለን መንግስት አሁን ደግሞ ለእርዳታ በረራ ፈቅጃለሁ ይላል።ጎበዝ ግራ ተጋባን እኮ።»ሲሉ፤ 
ሰናይት አማረ ደግሞ «ዱቄት የተባለው ህወሃት ከተሰበሰበ ወዲህ እኮ መንግስትን ማመን ቀብሮ ነው። ብለናል ።»ሲሉ፤ 
ማርቆስ ገለቱ በበኩላቸው «መንግስት በረራ ከፈቀደ፤ ቀጥሎ ለሚሆነው ነገር መዘጋጀት አለበት።በመንግስት ስህተት ድሃው ዋጋ እየከፈለ ነው።» በማለት ፅፈዋል። ኪያ ኪያ በሚል የፌስቡክ የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«ከመብረሩ በፊት ጥብቅ ፍተሻ ይደረጋል ይመስለኛል።ግን ፈታሹስ ቢሆን ማን ከማን ጋር እንደቆመ ለማወቅ የተቸገርንበት ጊዜ ነው።»ይላል።
አበበ ታደሰ ደግሞ «ከፓለቲካ ሰብአዊነት ስለሚቀድም ውሳኔው ግድ ነው ።በነገራችል ላይ የሀገራችን ነገር ውሃ ቅዳ ውሃ መልሱ መች ይሆን የሚያበቃው? በማለት ሀሳባቸውን በጥያቄ ቋጭተዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ውሃ ሙሌት መጀመሩን ከተገለፀ ካለፈው ሰኞ ወዲህ በርካታ ኢትዮጵያውያን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ደስታቸውን ሲገልፁ ታይተዋል። በአንፃሩ  ግብፅና ሱዳን የግድቡን ሁለተኛ ሙሌት በመቃወም በሀገራቱ መካከል አሳሪ ስምምነት እንዲደረግ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤትን ሲወተውቱ ቆይተዋል። ኢትዮጵያ በበኩሏ የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የሚታየው በፀጥታው ምክር ቤት ሳይሆን በአፍሪካ ህብረት መሆኑን ስትገልፅ ቆይታለች።የአረብ ሊግም ግድቡን በተመለከተ የሚያደርገውን ያልተገባ ያለችውን ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበለው ለፀታው ምክር ቤት አመልክታለች። ይሁን እንጅ የፀጥታው ምክር ቤት ትናንት ማምሻውን ባካሄደው ስብሰባ የህዳሴው ግድብ ድርድር በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ሊቀጥል እንደሚገባ አባላቱ ገልፀዋል።
አለም ጣሰው «ዜናው ለኢትዮጵያዉያን ብስራት ለግብፃውያን ደግሞ መርዶ ነው።»ሲሉ፤
ዳንኤል ላንዴቦ«የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊያን ይፈታል የሚለው ሐሳብ ትክክለኛው ነው።የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ ነው የሚያምረው።»ሲሉ።
ማህሌት በላይ ደግሞ«የአፍሪቃ ህብረት ከችግር ተላቆ መቼ ነው ችግር ፈቶ የሚያውቀው።»ብለዋል።
ናቡቴ ነኝ የተባሉ አስተያየት ሰጪ  ደግሞ« የግብፅን ቀሚስ ለብሰው የሚያለቅሱ ሰዎች እያየን ነው  ።»በማለት ፈገግታ ካለው ምስል ጋር ምላሽ ሰጥተዋል። ሃምዛ ሰኢድ ደግሞ «ግድቡ የታችኞቹን ሀገራት አለመጉዳቱ ተደጋግሞ እየተገለፀ ነው። እነዚህ ሰዎች ግን ምን አድርጉ ነው የሚሉን? የገባው ካለ ያስረዳኝ።» ሲሉ ግራ መጋባታቸውን አስፍረዋል።
ያሬድ አጥላው ደግሞ« የአረብ ሊግ የአፍሪካን ጉዳይ ለአፍሪካ ትቶ ለምን የራሱን ችግር አይፈታም። የየመን፣የሊቢያንና የሶርያ ጉዳይ እኮ የአረብ ሊግ ጉዳይ ነዉ።ወይስ እነዚህ ሀገራት አፍሪካ ዉስጥ ተካለዋል?።» ሲሉ ጠይቀዋል። 
ቢላል ዳሪ ደግሞ «ግብፅና ሱዳን ለህዝቦቻቸው አሥበው ሳይሆን የዓባይን ጉዳይ የሥልጣን  ማራዘሚያ አድርገው እያተጠቀሙበት ነው።  በአፍሪካዊነታቸውም  ሙሉ እምነት ያላቸው አይመስለኝም።በተለይ መሪዎቹ።»የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል። 
ሶሎሞን ሙሉጌታ በበኩላቸው « እነሱ እየዞሩ እኛን ማሳጣታቸውን መቼም አያቆሙም። እኛም ሪባን መቁረጣችን እንዲሁ። ህዝቡ እና እግዚአብሔር ከእውነት ጋር ናቸው። መተባበር አለብን ።ኢትዮጵያ ታሸንፋለች።»ብለዋል።
 «በትክክል ይሄንን እጅ ጥምዘዛ ማስቆም የሚቻለው ስንተባበርና የኛን አቋም ለዓለም ማስረዳት ስንችል ነው።»ያሉት ደግሞ  አዶቴ ሄማ  ናቸው።
 

Karte Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre DE
Äthiopien Tigray-Krise | Soldaten TPLF
ምስል Ben Curtis/AP/picture alliance
Äthiopien | Beisetzung Abebech Gobena
ምስል Seyoum Getu/DW

ፀሐይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ