1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሰኔ 25 2013

የኢትዮጵያ ጦር ከትግራይ ለቆ ወጥቶ አማጽያኑ መቐለ እና ሌሎች በክልሉ የሚገኙ ከተሞችን መቆጣጠር ከጀመሩ በኋላ በአንድ በኩል የአሸናፊነት ደስታ፣ በሌላ በኩል ቁጭት፣ግራ መጋባት እና ሥጋት የተንጸባረቀባቸው መልዕክቶች በማኅበራዊ ድረ-ገጾች እየተዘዋወሩ ነው።

https://p.dw.com/p/3vwsD
Äthiopien | Jubel beim Einmarsch der TDF in Mekelle
ምስል DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ተንበርክከው ደስታቸውን የሚገልጹ እናቶች፣ በወጣቶች ትከሻ ላይ ተቀምጠው ኤኬ 47 ተብሎ የሚጠራውን ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ በእጃቸው ከፍ አድርገው የያዙ ታጣቂዎች፣ ደስታቸውን ለመግለጽ የሞተር እና የመኪና ጥሩምባ እያሰሙ በሽሬ እና በመቐለ ከተሞች የሚዘዋወሩ ሰዎችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች በብዛት ታይተዋል። ፍትሐዊ ኅሩይ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደስታቸውን የሚገልጹ ሰዎች የሚያሳዩ ፎቶግራፎች አጋርተው "የሕዝቤ ያለፉት ስምንት ወራት መከራ በማብቃቱ ደስተኛ ነኝ። የትግራይ መከላከያ ኃይል ሁሉንም አሳክቶታል" ሲሉ ጽፈዋል። 

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስለ ጦርነቱ እና የደረሰበት ደረጃ በተመለከተ የሰሯቸውን ዘገባዎች እያጋሩ የትግራይ አማፂ  ኃይሎች ውጊያውን ማሸነፋቸውን ለማሳየት የሚጥሩም አሉ። ሰለሞን ነጋሽ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ "የኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የርስ በርስ ጦርነት ታሪክ ሲፃፍ የሰኔ አውደውጊያዎች ከቅርብ  አመታት ታላላቅ የአማጽያን ድሎች አንዱ ሆነው ይቆጠራሉ" በማለት የብሪታኒያው ዘ-ኤኮኖሚስት መጽሔት የፃፈውን ዘገባ ማጋራታቸው በምሳሌነት የሚቀርብ ነው። 

በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ ምክትላቸው ፈትለወርቅ ገብረእግዚዓብሔር እና ሌላው የፓርቲው ከፍተኛ ባለሥልጣን ዓለም ገብረዋሕድ የፓርቲያቸውን መዝሙር ሲዘምሩ የሚያሳይ የተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች ሲዘዋወሩ ታይተዋል። ደደቢት ሚዲያ የተባለ የትዊተር ገጽ ከተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የተወሰደ ፎቶ በማጋራት "የተመረጠው የትግራይ መንግሥት በይፋ ወደ ቦታው ተመልሷል" የሚል አረፍተ-ነገር ጽፏል። ሰይፈስላሴ ገብረ መስቀል የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ትናንት ሐሙስ " ደብረጺ ወደ መቐለ ተመልሰዋል፤ የትግራይ አመራር ወደ መቐለ ተመልሷል" ብለዋል።  በዶክተር ደብረ ጽዮን የሚመራው የክልሉ መንግሥት ዋና መቀመጫው ከሆነችው መቐለ ለቆ የወጣው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሕዳር ወር ከተማዋን ሲቆጣጠር ነበር። 

Äthiopien | Jubel beim Einmarsch der TDF in Mekelle
በማኅበራዊ ድረ ገፆች አማጺያን ወደ ትግራይ ከተሞች ሲገቡ ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ የወጡ በርካታ ሰዎች የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ታይተዋል።ምስል DW

በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ስም ባለፈው ሰኞ የወጣ የተባለ መግለጫ ደስታ ሐይለስላሴ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ አጋርተዋል። መግለጫው "የትግራይ መከላከያ ኃይል" የሚል ስም የተሰጠው ታጣቂ የመቐለ ከተማን መቆጣጠሩን እና  የተመረጠው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ወደ ቦታው መመለሱን ያትታል። ድምጺ ወያነ በተባለው ጣቢያ የፌስቡክ ገጽ ጭምር በተሰራጨው መግለጫ "የትግራይ ህዝብ እንደ አንድ ሰው ሆኖ በመታገሉ መብቱን ማረጋገጥ ጀምሯል። ሁሉ ነገረ የሚቻለው ጀግና ሰራዊታችን ባስመዘገበውና እያስመዝገበ ባለው ተአማራዊ ድል እንኳን ደስ ያለን መልእክት ስናስተላልፍ የትግላችን ውጤት እና ህዝባዊ ትግላችን በህዝባችን ምልአተ ተጋድሎ ታጅቦ እነሆ እንደ ዓላማችን እና ቃላችን ደመኛ ጠላቶቻችን የረገጡት የትግራይ መሬት መቀበርያቸው እንጂ መፈንጪያቸው እንደማትሆን በተግባር አሳይተናቸዋል" ይላል። 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰራዊት ግንባታ ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ግን "አሸባሪው ህወሓት ሥጋት ከሚሆንበት ደረጃ ወጥቷል። ትርጉም ያለው ኢትዮጵያን ሊያሰጋ የሚችል ነገር ሊያደርግ አይችልም" ሲሉ ጦሩ ትግራይን ለቆ የወጣበትን ምክንያት ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል። 

ሙሉነህ ኢዮኤል "የአብይ መንግስ ከዚህ በኋላ በትግራይ ውስጥ ስለሚሆነው ነገር አይመለከተኝም ማለቱን ተከትሎ ብዙ የመንግስት ቀለብተኞች ትግራይ ትገንጠል እያሉ ናቸው። አንዳንዶቹ ትግራይ ትገንጠል ያሉበትን ጽሁፍ ሲያጠቃልሉ "ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!" ይላሉ። ከአንዱ በቀር ለዘላለም የሚኖር ነገር እንደሌለ ባምንም "እስከወዲያኛው ትክረም" ማለት ነው ብዬ ስለማምን እኔም ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር እላለሁ። የእኔ ኢትዮጵያ ግን ትግራይን ትጨምራለች። ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ካለ ተጋሩነትን ይጨምራል። ተጋሩነትን፣ ሲዳማነትን፣ ሶማሌነትን ካልጨመረ ኢትዮጵያዊነት ምንድነው? ኢትዮጵያዊነት ካልሆነ በስተቀር ሙስጠፋንና ኦባንግን ምን አንድ ያደርጋቸዋል? ኢትዮጵያን እያፈረሱ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ማለት ድንቁርና ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል?" የሚል ጽፉፍ በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።

Der Tag in Bildern | Addis Ababa, Äthiopien | Pressekonferenz Armee und Außenministerium
ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ "አሸባሪው ህወሓት ሥጋት ከሚሆንበት ደረጃ ወጥቷል። ትርጉም ያለው ኢትዮጵያን ሊያሰጋ የሚችል ነገር ሊያደርግ አይችልም" ሲሉ ጦሩ ትግራይን ለቆ የወጣበትን ምክንያት ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ አብራርተዋልምስል Minasse Wondimu Hailu/Anadolu/picture alliance

ደረጄ ገረፋ ቱሉ ደግሞ "ጦርነቱ ዛሬ ካልቆመ ከዚህ በፊት ከነበረውም በላይ ቀውስ ያስከትላል" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። "ይኸ ጦርነት አሁን የፌደራል መንግስት በወሰደው መነሳሳት በሰላም ካላለቀ መቼም የማያልቅ እና አስጠሊታ ጦርነት ይሆናል" የሚሉት ደረጀ ሁኔታው የከፋ ሊሆን ይችላል የሚሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዘር በማድረግ አቅርበዋል። "ጦርነቱ የኢትዮጵያ መንግስት ሰራዊት አሁን አፈግፍጎ በሰፈረበት በአፋር ፣በአማራ አዋሳኝ ትግራይ አካባቢዎች፣ በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ ይሆናል። ይኸ አከባቢ ደግሞ የራሱ የተለየ ባህሪያት አሉት። ይህ አካባቢ በአብዛኛው ሜዳማ ነው። ተራራማ አከባቢዎች የሉትም ሳይሆን በአንፃራዊነት ከሌላኛው አከባቢ አንፃር ማለቴ ነው። ይህ አከባቢ የህዝብ አሰፋፈሩ መንግስት አሁን ለቆ ከወጣበት አከባቢ ህዝብ ይለያያል። ስለዚህ በዚህ አከባቢ የሚደረገው ጦርነት ከበፊቱም በላይ እጅግ አደገኛ እና አሰልቺ ይሆናል" ብለዋል። 

ደረጀ "አሁን ለሰላም የተከፈተውን በር ካልተጠቀምን ጦርነቱ ሊጠናቀቅ የሚችለው አንደኛው ሌላኛውን ሲያሸንፍ ነው" የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ረዘም ባለ የፌስቡክ ሐተታቸው "ሁሉም ወገን ልብ ገዝቶ፤ ስሜትን ዋጥ አድርጎ ወደ ኋላ ከማሰብ የወደፊቱን አስቀድሞ ይኸንን አጋጣሚ ወደ ተሻለ የሰላም ንግግር ለመቀየር ጥረት ማድረግ አለበት። ይኸንን የሰላም በር ዛሬ የማንጠቀም ከሆነ፤ ልክ እስከዛሬ እንዳደረግነው የአጥፍቶ ማጥፋት ውስጥ ራሳችንን መክተት እና በየቀኑ ራሳችንን መግደል ነው" የሚል ሥጋት የተጫነው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
"ከባሰ እልቂት የመዳን መንገድ ሲመጣ የትምክህትንና የሽንፈትን ነጋሪት ጉሰማ ማቆም ነው የሚበጀን። ሰላምን ማምጣት፣ ሰውነትን አለማፍረስ፣ የፈረሰውን መጠገን፣ ክብር ለተሞላ ሰዋዊ ህይወት መቆምና መልፋት ነው ብዬ ነው የማምነው" የሚሉት ደግሞ ሱራፌል ወንድሙ ናቸው። ሱራፌል በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ "ጀግንነት ምንድን ነው? ሰብአዊነትን ካላከመ፣ ስለሰብአዊነት መኖር ካልሆነ? ብለን ካልጠየቅን ወደፊትም መጠፋፋት እጣችን ሆኖ ይቀጥላል" እያሉ ያስጠነቅቃሉ።

"እስኪ በጥቂት ጊዜ ከብዙ ጥፋት በዃላ እያገኘን ያለነውን አጋጣሚ ለዘለቄታው ለመዳን እንጠቀምበት። እከሌ ከእከሌ፣ እገሊት ከእገሊት ሳንባባል ሁላችንም ይህንን ጊዜ የመተካከሚያ፣ የዘለቄታ አብሮነት ማምጫ፣ በአለም ፊት በሆነው ባልሆነው የምንነካከስበት፣ በቁስም በመንፈስም ድህነት የምንደቅበት ሳይሆን በጋራ ህብረት ሰዋዊ ክብራችንን የምንቀዳጅበት ለማድረግ እንጠቀምበት። የምናገኛቸውን አጋጣሚዎች ለበቀል ሳይሆን ፍቅር ለማብቀል እንጠቀምባቸው። ስንት እድሎች አመለጡን? እንዲያመልጡን አደረግን? መቼ ይሆን ስለ ልጆቻችን የምናስበው? መቼ ይሆን ለልጆቻችን መከራን ሳይሆን ፍቅርን፤ ሰላምን እና ሃብትን ይበልጡን ደግሞ በማህበራዊ ፍትህ የበለፀገ ሰብአዊነትን አውርሰን ለማለፍ የምንሰናዳው?" እያሉ ይጠይቃሉ። "ይህንን ጊዜና ስፍራ የምንቆዝምበት፥ ራሳችንን ቆም ብለን የምናስተውልበት የጥሞና ፋታ እናድርገው። በገቢር የምንተጋገዝበት፣ ደም የምናደርቅበት ያጠሩንን ድንበሮች የምንሻገርበት እናድርገው" እያሉ ይማጸናሉ።