1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ መጋቢት 3 2013

በትግራይ የተፈጸሙ ግድያዎችን የሚያሳዩ ናቸው የተባሉ ቪዲዮዎች ሐዘን እና ቁጭት ካዘሉ አስተያየቶች ጋር በማኅበራዊ ድረገፆች እየተዘዋወሩ ነው። በሆሮ ጉዱሩ በታጣቂዎች የተፈጸመው ግድያም ሌላ ቁጣ ጭሯል። የአቶ ልደቱ አያሌው ከፖለቲካ ገለል ለማለት ያሳለፉት ውሳኔ እና ተክለ ስብዕናቸው ለአድናቂዎቻቸውም ሆነ ተቺዎቻቸው መነጋገሪያ ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/3qVLW
Symbolbild Apps Facebook und Google Anwendungen
ምስል picture-alliance/dpa/S. Stache

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን በሳምንቱ መገባደጃ 22 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ለበርካታ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች ሐዘን፣ ቁጭት እና ቁጣን ፈጥሯል። የአካባቢው ነዋሪዎች ዶይቼ ቬለን ጨምሮ ለተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች እንደተናገሩት ጥቃቱ ያነጣጠረው በአካባቢው በሚኖሩ የአማራ ብሔር አባላት ላይ ነው። የአይን እማኞች እንደሚሉት በአበደንጎሮ ወረዳ ደቢስ በተባለ ቦታ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ቤተˉክርስቲያን ባመሩበት ታጣቂዎች ከገደሏቸው ሰዎች መካከል ሕፃናት እና ሽማግሌዎች ጭምር ይገኙበታል። በማኅበራዊ ድረ ገፆች በጨርቅ ተጠቅልለው ለቀብር የተዘጋጁ በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች አስከሬኖች ናቸው የተባሉ ፎቶግራፎች ተሰራጭተዋል።

ገበያው መንግሥት የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "ደቡብ ሱዳናውያን እና ሶሪያውያን ተከብረው በሚኖሩባት ኢትዮጵያ አማራ እየታደነ ይታረዳል፤ በሞቱ የሚያዝንለት እንኳ የለም፤ የአማራ ሞት ለዜና እንኳ አይበቃም" ሲሉ ጽፈዋል። ጥላሁን መልኬ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ትግራይ፣ ወለጋ እና መተከልን ጠቅሰው "እስከመቼ ከንፈራችንን መጠን ዝም...? እንዲህ እየተጫረሰን... እያለቅን... እንዲህ እየሆንን? ስቃይ ቆጠራ... አንዳችን በሌላችን ሃዘን እየተሳለቅን? መፍትሄ አጥተን ዝም?" የሚል መልዕክት አስፍረዋል።

ዮሐንስ ቲ ደጉ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "ወለጋ ላይ ሰዎች የጥይት መለማመጃ እየሆኑ ነው። ሞታቸው የአዘቦት ዜና ሆኗል። ዜናው ማንንም አይጎረብጥም። ማንም በጉዳዩ አይሞቀውም፥ አይበርደውም። ሞታቸው የብሔር ካባ ለብሷል። በሞታቸው የሚደነግጥ የለም። ወለጋ ላይ የሚረግፉ ሰዎች ለሞት እጅ መንሻ የተሰጡ ሆነዋል። እነሱን እንደፍጥርጥርህ አድርጋቸው፥ እኛ ጋር አትድረስ ይመስላል። በአራቱም አቅጣጫ ኢትዮጵያን የሚለበልባት የዕልቂት እሳት ቤታችን ይደርሳል። ያኔ ማንም ለማንም አይደርስም" በማለት ጽፈዋል።

በጥቃቱ የብልጽግና ፓርቲ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ከፍተኛ ፖለቲከኞች ወቀሳ እና ክስ ቀርቦባቸዋል። ይታያል ዋለልኝ "የኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን ግድያዎች አሁንም አላባሩም። የተጠና እና ቅንጅት እንዳለው ለማወቅ አይከብድም። ነዋሪዎች ተደራጅተው ራሳቸውን ነቅተው እየጠበቁ ቆይተው ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ተደርገው ይሄው በግላጭ ተገደሉ" ብለዋል።

ወቀሳ እና ትችቱ የአማራ ብሔርን ወክለው የብልጽግና ፓርቲ አባል የሆኑ ፖለቲከኞችም አልቀረላቸውም። ሐመሩ ሐ ዋሸራ የሚል የፌስቡክ ስም የሚጠቀሙ አንድ ሰው "አማራ ብልፅግና ሌላው ቢቀር ዘር ጭፍጨፋውን ለማውገዝ መሽኮርመም ነበረበት?" ሲሉ ጠይቀዋል።

App-Icons von Facebook und WhatsApp
ምስል picture-alliance/dpa/F. Hörhager

ከወደ ትግራይ ወጣ የተባለው ቪዲዮ

በትግራይ ተፈጽመዋል የተባሉ ግድያዎችን ያሳያሉ የተባሉ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ድረ-ገፆች እየተዘዋወሩ ነው። ከተንቀሳቃሽ ምስሎቹ መካከል በአንዱ አስከሬኖች ወደ ገደል ሲወረወሩ ይታያል። ይኸ 54 ሰከንዶች ገደማ የሚረዝም ቪዲዮ ከአክሱም ከተማ በስተ-ምስራቅ ማሕበረ ደጎ አዴት በተባለ ቦታ የተፈጸመ ኩነትን ያሳያል ሲሉ ምስሉን ያሰራጩ የማኅበራዊ ድረ-ገፆች ተጠቃሚዎች ጽፈዋል። በምስሉ አንድ ሰው "ግደለው" የሚል ትዕዛዝ ሲሰጥ ይደመጣል። ትዕዛዙን ተከትሉ በምስሉ የሚታይ የወታደር መለዮ የለበሰ ግለሰብ ጥይት ይተኩሳል። አስከሬኖችም ወደ ገደል እየተገፉ ሲጣሉ ይታያል። ዶይቼ ቬለ የቪዲዮውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ አልቻለም። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ግን እንደየአሰላለፋቸው ምስሉን መሠረት አድርገው ሐሳባቸውን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል። 

ፍሰሐ ታደሰ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "ይኸ የኢትዮጵያ ጦር መለዮ የለበሱ ወታደሮች ወጣቶችን እየገደሉ ወደ ገደል ሲወረውሩ የሚያሳይ ቪዲዮ በጣም ይረብሻል" ብለዋል። 

ኃይለ ስላሴ አምሐ "መተኛት አልቻልኩም። ላለፉት አራት ወራት በትግራይ የጅምላ ግድያ እየተፈጸመ እንደሆነ አውቃለሁ። እንዲህ አይነት ኩነቶችን በቪዲዮ መመልከት ግን የተለየ ነው። የተወሰኑ የኢትዮጵያ ጦር ወታደሮች ጥቂት ቀጫጭን ወጣቶችን ከበቡ፤ ከመኃላቸው መካከለኛ ወታደራዊ አዛዦች ይመስላሉ። ሴት ወታደሮችም አሉበት። የተረጋጉ ናቸው። ይሳሳቃሉ፤ የቀላለዳሉ። ምንም ሥጋት አይሰማቸውም። አንዳንዶቹ ይቀርፃሉ። እነዚህን ልጆች በርካታ ነገር ማድረግ ይችላሉ። ሊያስሯቸው ይችላሉ። ሊመቷቸው ይችላሉ። ነገር ግን ወደ ገደል አፋፍ ወስደው ገደሏቸው። ሬሳቸውን ወደ ገደል ጣሉ" ሲሉ ጽፈዋል።

ያሬድ ከበደ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "የሞተን ሰው ወደ ገደል መወርወር የጭካኔ ጣርያ" ሲሉ ጽፈዋል። ያሬድ "አሁንም ከትግራይ ክልል የሚለቀቁ ቪዲዮዎች አላለቁም። ሰው ሆኖ መፈጠር ያስፈራል፤ አብሶ ሴቶች ላይ የተፈፀመው የእንስሳት ተግባር ይዘገንናል" በማለት አክለዋል። 

"የትኛውም ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚዘዋወሩ ፎቶና ቪዲዮ ትክክለኛነታቸውን ሳናረጋግጥ መደምደሚያ ላይ ከመድረስ ብንቆጠብ ጥሩ ይመስለኛል። እኔ እንደተረዳሁት ጉዳዩ እውነቱን የማውጣት ሳይሆን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ውድድር(በመንግስትም ጭምር) ነው የተያዘው። ለምሳሌ የዛሬው ቪዲዮ በጣም አንገት ያሚስደፋ፣ ኢትዮጵያዊ መሆንን ያስረግማል" ያሉት ደግሞ በፌስቡክ ሞገስ ዘውዱ ናቸው።

ሞገስ "ነገር ግን ቪድዮውን በትኩረት የተመለከተ ሰው አንድ ነገር ያስተውላል።የሚያወራው ልጅ በቦታው ሳይኖር ቪዲዮው ላይ ድምፁን እያስገባ የሚተርክ( narrator) ነው። ይሄ ለጥርጣሬ አንድ በር ይከፍታል። ሲቀጥል እንዲህ ዓይነት ቪዲዮ የቀረፀ ሰው ጉዳዩ ከባድ ወንጀል መሆኑን እያወቀ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያጋራበት ምንም ምክንያት የለውም። ምናልባት ምስሉን የቀረፀው ሌላ ሰው ቢሆን እንኳን፤ በዚያ ሁኔታ ከሰዎቹ ጋር እየተነጋገረ ቪዲዮ የሚቀርፅበት አጋጣሚ አይኖርም" በማለት ጥርጣሪያቸውን አስፍረዋል።

ሙክታሮቪች ኦስማኖቫ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ "የመከላከያ ስምን እንዲያጠፋ የታሰበ አሰቃቂ ቪዲዮ" ብለውታል። ሙክታሮቪች "የህወሓትን ታሪካዊ ሸፍጥ የምናቅ፤ ህይወቱን ለማትረፍ የሚያደርገውን የምናቅ፤ ጁንታው በሀገር መከላከያ ዩኒፎርም ትልቅ ድራማ ሰርቶ ለቆልናል። የማናቸውም መልክ እንዳይታይ አድርጎ፣ መልዕክቱ ደጋፊ ለማብዛት የተደረገ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ነው። ሀውዜንም እንዲህ ነው የተደረገው። ይህ የጦርነት ነገር የለበትም። ይህ ዜጎችን ጁንታው ገድሎ የሰራው ነው። የሰውን አዕምሮ እንዲረብሽ አድርገው ያቀናበሩት ነው" ብለዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ያለው ነገር የለም።

የልደቱ አያሌው መንገድ

Äthiopien Pressekonferenz EDP in Addis Abeba
ምስል DW/G. Tedla

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መሥራች እና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ልደቱ አያሌው በልብ ሕመም ሳቢያ ከፖለቲካ ገለል ማለታቸውን ያስታወቁትም በዚሁ በመገባደድ ላይ በሚገኘው ሳምንት ነው። የልብ ሕመም እንዳለባቸው የገለጹት ልደቱ " ከሐኪም ጋር ባደረግሁት ምክክር ለሕመሜ አስተማማኝ ሕክምና እስካገኝ ድረስ በአካሌም ሆነ በአዕምሮዬ ላይ ምንም ዓይነት ጫናና ውጥረት የሚፈጥር ሥራ እንዳልሠራና በቂ ረፍት እንዲኖረኝ ከባድ ማስጠንቀቂያና ምክር ተሰጥቶኛል" ብለዋል።

ሕክምና እንዳያገኙ በመንግሥት መከልከላቸውን የገለጹት ልደቱ በማኅበራዊ ድረ ገፆች በስፋት በተሰራጨ መሰናበቻቸው "ተገቢውን የሕክምና ዕርዳታ አግኝቼ ጤናዬ እስኪመለስ ድረስ በሕይወት የመሰንበት ዕድሌን ለመሞከር ስል ከማንኛውም ዓይነት የትግል እንቅስቃሴ (ገንዘብ ወይም ምክር ከማዋጣት ባለፈ) ራሴን ለጊዜው ለማቀብ የተገደድኩ ስለመሆኑ በከፍተኛ ቁጭትና ሐዘን እገልጻለሁ" ሲሉ ውሳኔያቸውን ይፋ አድርገዋል። በዚሁ ጽሁፋቸው አሳሳቢ ያሏቸውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግሮች ዘርዘር አድርገው አቅርበዋል። መንግሥት እና የብልጽግና ፓርቲን ሸንቁጠዋል።

ውሳኔያቸው እና ተክለ ስብዕናቸው ለአድናቂዎቻቸውም ሆነ ተቺዎቻቸው መነጋገሪያ ሆነዋል። አንዳርጌ ጫኔ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "ውጭ ሆኖ `ተናግሬ ነበር´ ለማለት ከሆነ፦ የምትነግረንን 100% ባትነግረን ይሻለኛል። ሰው ማለት ሃገሩን የሚወድና የፓለቲካ ልዩነት ቢኖረውም እንኳ ሃሳቡን ለሃገሩ መፃዒ ዕጣ ሲል ከእልህና ከንዴት ራሱን በመቆጣጠር የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ሲገባ ከበር ውጭ ቁሞ `ብየ ነበር ተናግሬ ነበር´ ለማለት መዘጋጀት ነውር ነው" ብለዋል።

"ወንድማለም ያንተ ትልቁ ችግር ከሰው አይምሮ በላይ መፍጠንህና ትክክለኛ ለኢትዮጵያ ሀሳቢ መሆኑ ነው። አንተን የሚረዳህ ይህ መንጋ ዛሬ አይደለም እንደ ግሪክ ፈላስፋዎች ካለፍክ በኋላ ነው።አዝናለሁ እግዚአብሔር ጤናህን ይስጥህ" ያሉት ደግሞ ናትናኤል ሞላ ናቸው።

በአማን ቄርሎስ ደግሞ "እኛ ኢትዮጵያውያን ዋና ችግራችን በጅምላ የምንፈርድ እና ምክንያታዊ አለመሆናችን እንጂ በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ አንተ ከወሳኝ ሚዛናዊ ሰዎች መካከል አንዱ ነህ። ነገር ግን በ1997 ምርጫ በተፈጠረ ሴራ የተወሰነ ህዝብ እምነት ነስቷል። ሆኖም ግን በዋና ዋና ሀገራዊ እና መንግስታዊ ጉዳዮች ዙርያ ብዙ ጠቃሚ ሀሳቦችን እያቀረብክና ተፅእኖ እየፈጠርክ እንደመጣህ ደግሞ የምናምን ሰዎች አለን። አሁን የወሰንከው ውሳኔ እንደ ግል ትክክል ቢሆንም እንደ ሀገር ግን በፖለቲካው ዙርያ ትልቅ ክፍተት እንደሚፈጥር የግል እምነቴ ነው" የሚል አስተያየት አስፍረዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ