1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ኅዳር 4 2013

ጥቅምት 24 ቀን ዕኩለ ለሊት ገደማ በትግራይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ልዩ ኃይል ጥቃት እንደደረሰበት ከተገለጸ በኋላ የተፋፋመው «ውጊያ» በማኅበራዊ ድረ-ገፆችም በርትቷል። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል ደጋፊዎች አንዳቸው በሌላቸው የበላይነት ለማግኘት በማኅበራዊ ድረ ገፆች ይተጋተሉ።

https://p.dw.com/p/3lGmk
Äthiopien Gondar | Amhara Miliz
ምስል Eduardo Soteras/AFP

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

«ሬሳ በሬሳ እየተከመረ
አውላላ ሜዳ ላይ እንደተዘረረ
ህዝቤ ተጠያቂው ማን ነው? ይልልኛል
እኔስ የጨነቀኝ 
የሟችን ቤተሰብ ማን ያረዳልኛል?»

ይኸ ትዕግስት ሸዋረጋ የተባሉ ኢትዮጵያዊት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በትግራይ መስተዳድር መካከል የተቀሰቀሰው ውጊያ የሚያስከትለው ዳፋ፣ በዜጎች ዘንድ የፈጠረውን ሥጋት ለማሳየት በትዊተር ያጋሩት ግጥም ነው። 

«ልቤ ለብዙ ደስተኛ ዓመታት ለኖርኩባት ለኢትዮጵያ እና ለትግራይ እየተሰበረ ነው። እባካችሁ ጦር በሚሰብቁ የትዊተር መልዕክቶቻችሁ ከፍ ብለው እንዲሰሙ በመፈለግ ጎትታችሁ አታስገቡኝ። አላደርገውም። ውይይት እና ሰላም ነው የሚያስፈልገው» የሚል መልዕክት በትዊተር ያሰፈሩት ደግሞ ፕሮፌሰር ላውራ ሐሞንድ ናቸው።

የለንደን ዓለም አቀፍ የልማት ማዕከልን በኃላፊነት የሚመሩት ላውራ ያስተላለፉት መልዕክት ትዊተር እና ፌስቡክን በመሳሰሉ ማሕበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የበረታው ውዝግብ በግለሰቦች ላይ የፈጠረውን ስሜት ለማሳየት ኹነኛ ምሳሌ ነው። 

ፌስቡክ እና ትዊተር እንደ ጦር አውድማ 

Symbolbild Apps Facebook, Google und Google + Anwendungen
ምስል Imago Images/P. Szyza

«ሕወሐት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል» የሚለው መረጃ ጥቅምት 24 ቀን መጀመሪያ የተሰማው በጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፌስቡክ ገጽ በኩል ነበር። ጠቅላይ ምኒስትሩ በማለዳ በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት «የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል» ከ20 ዓመታት በላይ በክልሉ የሠፈረውን ጦር «ሕወሐት እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ ሀገር ሠራዊት ቆጥሮ፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷል። በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል» ብለዋል። 
ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ በሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጽሟል ያሉት ጥቃት በርካታ ሰዎችን አስቆጥቷል። «ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመው ክህደት እጅግ ዘግናኝ ሰቅጣጭ፣ ጆሮን ጪው የሚያደርግ የአረመኔ አረመኔነት ጥግ የታየበት አሳፋሪ ድርጊት ነው።» ሲሉ ዳንኤል ዲሳሳ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ጽፈዋል። 

ጌታሁን ሔራሞ በበኩላቸው «ቃታው የተሳበው በሰሜን ዕዝ ላይ ብቻ አይደለም፣ በመላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ላይ እንጂ! የአንድን ፓርቲ ሳይሆን የሀገር ውክልናን ባነገበውና በሀገራዊ ግዳጅ ላይ በተሰማራው የሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰው ጥቃት ዝርዝሩ ይፋ ሲደረግ በኢትዮጵያ ታሪክ በጥቁር ነጥብነት ዝንተዓለም ሲታወስ ይኖራል። ይህ እኩይ ተግባር የሕወሓት ተስፋ መቁረጥ ጎልቶ የወጣበት የአጥፍቶ መጥፋት አረመኔያዊ እርምጃ ነው፣ ዋጋ ይከፈልበታል» ብለዋል። 

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት እስካሁን የክልሉ ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ፈጸሙት የተባለውን ጥቃት በይፋ አላስተባበለም። ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጥቅምት 27 በፌስቡክ ገጹ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል «የፌደራሉ ኃይል በሰሜን ዕዝ ወረራ ተፈፀመ ሲል ተሰምቷል። የሰሜን ዕዝ በሁሉም ጉዳዮች ከትግራይ ህዝብ ጋር በመተባበር ሲሰራ የቆየ ኃይል ነው።» ማለታቸውን አስፍሯል። 

በዚሁ የህወሓት ጽሁፍ ደብረጽዮን «ከሰሜን ዕዝ ጋር በሰራነው ሥራ ራሳችንን ለመከላከል እንድንጠቀምበት የሚያስችል ሁኔታ ፈጥሯል። በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ያለ የጦር መሣርያ ለትግራይ ህዝብ ደህንነት እንዲውል፣ ለራሱ እንዲከላከልበትና እንዲጠቀምበት መጠቀም ጀምረናል። ወደፊትም እንጠቀምበታለን» ማለታቸው ሰፍሯል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትጥቅ እንዴት በክልሉ መንግሥት እጅ እንደገባ ግን የተገለጸ ነገር የለም።

በቅርቡ ወደ ጦሩ ተመልሰው ሥራ የጀመሩት ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ በኢትዮጵያ ጦር አባላት ላይ ተፈጽሟል ያሉት ጥቃት በተመለከተ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ውዝግቡ ተካሯል። ሌተናል ጀነራል ባጫ የጦሩ አዛዦች መታገታቸውን ወታደሮችም የራዲዮ ግንኙነት እንዲቋረጥ ተደርጎ በትግራይ ኃይሎች «የእኛ መንግሥት የተመረጠ መንግሥት ነው። ያዲስ አበባ መንግሥት የተመረጠ መንግሥት ስላልሆነ ፈርሷል» መባላቸውን አስረድተዋል። ከሰሜን ዕዝ የተለያዩ ክፍለ ጦሮች መካከል አንዱ የሆነው አራተኛ ድጋፍ ሰጪ ብርጌድ አባላት በትግራይ ኃይሎች ተከበው ከተታኮሱ በኋላ በርካቶች መገደላቸውን፤ አስከሬናቸው ሳይቀበር ሜዳ ላይ መጣሉንም ተናግረዋል። 

አሉላ ሰለሞን በፌስቡክ ባሰፈሩት ጽሑፍ የሌተናል ጀነራል ባጫ ማብራሪያ ከተሰማ በኋላ «በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል መከላከያ አሰማርተህ «እምቢ ለመብቴ» ያለን ህዝብ ስትጨፈጭፍ ከርመህ ስታበቃ አሁን ከውጭ ኃይል ጭምር በመተባበር በህዝብ ላይ የከፈትከውን ወረራ እና ያወጅከውን ጦርነት ምክንያታዊ ለማድረግ «ሠራዊቱ ታረደ.. እራቁቱ ወጣ» የሚል የለማጆች አስቂኝ ፕሮፖጋንዳ» በማለት ተችተዋል። 

ማይካድራ

በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሱዳን እና ኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ማይካድራ የተባለች አነስተኛ ከተማ ከ500 በላይ ሰዎች በትግራይ ልዩ ኃይል ተገድለዋል መባሉ ሌላ ሐዘንም ንዴትም የፈጠረ ጉዳይ ነው። እጅግ በርካታ የተገደሉ ሰዎች አስከሬኖች ቅጠልን ጨምሮ የተለያየ መሸፈኛ ጣል ተደርጎባቸው ለቀብር ሲጓዙ የሚያሳዩ ምስሎች በፌስቡክ እና በትዊተር ተዘዋውረዋል።

ጌትነት ቢ የተባሉ ሰው የሟቾች አስከሬኖች የተሰበሰቡበትን ምስል አስደግፈው «ትህነግ ማይካድራ ላይ ምንም የማያውቁ ነዋሪዎችና የቀን ሠራተኞችን ገድሏል። የሟቾቹ ቁጥር ከ500 በላይ ነው። በጦርነት የተሸነፈው ትህነግ ንጹህንን ወደ መግደል ተሸጋግሯል» ሲሉ ጽፈዋል። 

ሰናይት ሰናይ በትዊተር «ማይካድራ ያሳብዳል! የሚፈልጉት በቀልን ነው። ኢትዮጵያ ላይ ሁሉ እርስ በእርስ ጦርነት እንዲሆን ይፈልጋሉ። አደራ! በቀል ህውሃትን ይጠቀማል እንጂ አይጎዳውም። በግፍ የሞቱትን ነፍስ ይማርልን።  የትግራይን ህዝብ አትንኩ፤ ህውሃት ግን? ያለቀ ጉዳይ ነው» ብለዋል። 

በጦርነቱ የተገደሉ እና የቆሰሉ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር እስካሁን በግልጽ አይታወቅም። በሺሕዎች የሚቆጠሩ ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት አስታውቋል። የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በመቆራረጣቸው ከትግራይ ውጪ የሚኖሩ የቤተሰቦቻቸውን ኹኔታ ለማወቅ መቸገራቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። 

ፊልሞና የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ «እናቴን እና ዕድሜዋ እየገፋ የሔደውን አያቴን ሳላናግር የቆየሁበት ረዥም ጊዜ ይኸ ሳይሆን አይቀርም። መቼ እንደማናግራቸው፣ እስከዚያ ጊዜ አያቴ በሕይወት ለመቆየቷ ምንም አላውቅም። በሕይወቷ በርካታ ጦርነቶች ተመልክታለች። መጠጊያ ፍለጋ በኤርትራ እና በትግራይ በርካታ ኪሎ ሜትሮች ተጉዛለች።» የሚል መልዕክት አስፍረዋል። ፊልሞና እንዳሉት ይኸ «ሊደገም አይገባም።» እንደ ፊልሞና ሁሉ በርካቶች የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል የገቡበት ውጊያ በፍጹም አስፈላጊ አይደለም እያሉ ይሞግታሉ። 

Unruhen in Äthiopien
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ጦርነት አንሻም

ፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሐ በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት «በኢትዮጵያ እየተፈጠረ ያለው ነገር እጅግ አሳዛኝ ነው። ሁለቱም ወገኖች ያለ ርሕራሔ ከሚያቀርቧቸው ቁጥሮች ጀርባ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ይገኛሉ። ሰብዓዊው ቀውስ እየበረታ ነው። በማኅበራዊ ድረ ገፆች የሚታየው ጥላቻ እና ጀብደኝነት ሕመም እና ክፍፍሉን ይበልጥ እያባባሰው ነው። ጦርነት አሸናፊ የለውም ተራፊ እንጂ።» ብለዋል። 

ሰልማን አል ፋሪስ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ «በሃገራችን አሁን የሚታየው ጦርነት ሰፊ የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ባላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መሃል እየተደረገ ያለ ጦርነት እየሆነ መጥቷል። የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት በፖለቲካዊ ሃሳብ የበላይነት እንጂ በጦር ሜዳ አይፈታም። ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ግፋ በለው ከሚሉ ፖለቲከኞች፣ በደርግ ግዜ ምርኮኛ ከነበሩ ወታደሮች እና ፖለቲካውን ወደ ሐይማኖት ተቋማት ለመውሰድ ከሚዳዱ አማካሪዎቹ እጅ ወጥቶ ፖለቲካውን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ቢያመጣው ሀገሪቷን ከመበታተን የድናታል።» ሲሉ ጽፈዋል። 

ኢብራሒም ዋዚር «ጦርነቱ ማለቁ አይቀርም ያልቃል። መሪዎቹም ደግሞ በመጨረሻ ሰላም ይባባላሉ። እናት ደግሞ የሞተው ልጇ ይመጣል ብላ ትጠብቃለች። ሚስት ደግሞ የምትወደው ባሏ ይመጣል ብላ ትጠብቃለች። ልጆቹም የሚወዱት አባታቸው ይመጣል ብለው ይጠብቁታል። ጦርነት ክቡር የሰው ልጅ ህይወት ነው ሚወስደው ። ለመሪዎች አሪፍ እና ቀለል ያለ ጨዋታ ነው፤ ለህዝቦች ግን ትልቅ ጠባሳ ነው» ሲሉ ዳፋው በማን ላይ እንደሚበረታ በፌስቡክ ባሰፈሩት ጽሑፍ ጠቆም አድርገዋል። 

Karte Äthiopien Region Tigray DE

አቡ ሲትራ ደግሞ «ብቻዬን እስክቀር ጦርነት እቃወማለሁ። ጦርነት አልደግፍም። በተለይ የእርስ በርስ ጦርነትን፦ ምክንያቱም በጦርነት የሚጎዳው ምንም የማያውቅ ምስኪን ሕዝብ ስለሆነ። ይህን በማድረግ ሕሊናዬ ሰላም ያገኛል» ብለዋል። 

አማኑኤል ገብረ መድሕን «የዛሬዋን ቀን ትረግማታለህ» የሚል ርዕስ ያለው ጽሁፍ በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል። አማኑኤል «ዛሬ ቁጭ ብለህ በማኅበራዊ ድረገፆች ላይ ፃፍ፣ ተሳደብ፣ ቀስቅስ፣ ሰዎችን አጋጭ፣ በሆነው ባልሆነው፤ በረባው ባልረባው ተባላ ...ነገ ያለህበት ስፍራ ሲተራመስ -- ኔትዎርኩ ሲዘጋ፤ መብራቱ ሲጠፋ፤ ውሀው ሲቋረጥ፤ የምትበላው ስታጣ፤ ገንዘብ በኪስህ ሞልቶ ለሻይ እንኳን ከቤትህ ለመውጣት ሲያቅትህ የት እንደምትገባ ግራ ይገባሀል። ዛሬ ያቀለልካት ሰላም ደም እምባ ብታለቅስ መልሰህ አታገኛትም። ዛሬማ ሰላም ነው ፎክር እንጂ...የቤትህ አናት ላይ ሲተኮስ፤ የቦንብ ናዳው ሲወርድ፤ ሰው ወጥቶ ሲቀር ስትሰማ፤ ሕጻናት ሲረግፉ ስታይ፤ ህዝብ እየተሰደደ የበረሀ ሲሳይ ሲሆን፥ ባሕር ውስጥ ሰጥሞ ሲቀር ስታይ ... የዛሬዋን ቀን ትረግማታለህ። ምነው ጌታ ባልፈጠርከኝ ትላለህ። ብቻህን ያለወንድም፤ ያለእናት አባት፤ ያለዘመድ ስትቀር መፈጠርህን ትጠላለህ። ዛሬ ያቀለልካትን ሰላም ደም እምባ ብታለቅስ መልሰህ አታገኛትም። ዛሬማ ሰላም ነው ፎክር...አቅራራ...ህዝብ ቀስቅስ...ተነሳ በለው፣ ግደለው በል! የለኮስከው እሳት አመድ ሲያደርግህ የሰላምን ዋጋ ያን ጊዜ ትረዳዋለህ!» ሲሉ እየተሳለቁ ያስጠነቅቃሉ። 

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ