1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 23 2012

የኮሮና ወረርሽኝ የኢትዮጵን ምርጫ ከማራዘም ባሻገር በገዢው ብልፅግና ፓርቲና የአገሪቱ የፖለቲካ ልሒቃን መካከል የነበረውን መቃቃር እንደገና አካሮታል። በምርጫው እጣ ፈንታ ላይ መስማማት የተሳናቸው ልሒቃን እየተወዛገቡ ነው።የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት በኮሮና ሳቢያ በታቀደለት ጊዜ አይካሔድም የተባለው ምርጫ የቀሰቀሰውን ውዝግብ ይቃኛል

https://p.dw.com/p/3beWJ
Symbolbild Apps Facebook, Google und Google + Anwendungen
ምስል Imago Images/P. Szyza

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ሐሙስ ለነሐሴ ታቅዶ የነበረውን ምርጫ ማካሔድ የማይችልበትን ምክንያት ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ካስረዳ በኋላ የአገሪቱን ከፍተኛ ሥልጣን የያዙት ሕግ አውጪዎች የሕግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን እንዲመረምር አዘዋል። በምክር ቤቱ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ፣ ስልጠናና ስምሪት ፣ የመራጮች ትምህርት እና ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ስርጭት በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መከናወን እንዳልቻሉ አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው  የውሳኔ ሐሳብ በሶስት ተቃዉሞ ፣በሰባት ድምጸ-ተዓቅቦና በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ መሰረት ጉዳዩ ለሕግ ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መመራቱ አንድ ተቃውሞ አስራ ስምንት ድምተ-ተኣቅቦ ገጥሞታል። 
ጉዳዩ በተለያየ ጽንፍ ለቆሙ ኢትዮጵያውያን አከራካሪ ሆኖ ይታያል። አሸንዳ ቀደም የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ «በወቅቱ ምርጫው ይካሄድልን፤ የተቃዋሚ ፖርቲዎች በሚወዳደሩበት አካባቢ ኃላፊነት ወስደው እንዲሰሩ ይደረግ» የሚል አስተያየት ምክር ቤቱ ውሳኔውን ይፋ ባደረገበት የፌስቡክ ገፁ አስፍረዋል። እኚሁ ግለሰብ «ልብ በሉ:- ወረርሽኙ የጤና ሙያተኞች የሚሰጡትን [ምክር] ተግባራዊ በማደረግ መቆጣጠር ይቻላል። ስለዚህ ምርጫው የግድ መደረግ አለበት። በመረጥንው፤ ያስተዳድረናል በምንለው ነው መመራት ያለብን» ብለዋል። «መጀመሪያ በሽታውን እንከላከል። ምርጫው ይደርሳል፤ የት ይሄድብናል? በዚህ ሰዓት ስለ ምርጫ ማውራቱ ተገቢ አይመስለኝም» የሚል አስተያየት የጻፉት ደግሞ ሰብለ ግርማ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው። 

የኢትዮጵያ መንግሥት አራቱ አማራጮች 

የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ምርጫውን በተመለከተ አራት የመፍትሔ ሐሳቦች አስቀምጧል። እነሱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ፤ ሕገ-መንግሥቱን ማሻሻል እና የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ ናቸው። ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ  ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ጉምቱዎቹ የፖለቲካ ሰዎች በተገኙበት በአራቱ አማራጮች ላይ ከትናንት በስቲያ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ማብራሪያ ሰጥተዋል። 
አራቱም አማራጮች በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዘንድ አከራካሪ ሆነው ይታያሉ። የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግግረስ አባል የሆኑት ጀዋር መሐመድ በፌስቡክ ገጻቸው «አራቱም አማራጮች አያዋጡም። ህጋዊ መሰረት የላቸውም። መፍትሄው ህጋዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ስምምነት መፍጠር ነው» በማለት የዐቢይ መንግሥት ባስቀመጣቸው አማራጮች እንደማይስማሙ ገልጸዋል።

Äthiopien Addis Abeba Oppositionsführer Jawar Mohammed
ጀዋር መሐመድ የመንግሥትን አራት አማራጮች ተቃውመዋልምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

«እንግዲህ ዶክተር ጌዲዎንን ጨምሮ መፍትሄ ለማቅረብ የተሳተፉ የህግ ባለሞያዎች እና በጉዳዩ ላይ የፃፉ የተለያዩ ሰዎችን ሀሳብ ተከታትለናል - አሁን ካለው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የተሻሉ የተባሉት የህገመንግስት ትርጓሜ እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ናቸው» የሚሉት ደግሞ ዮናታን ተስፋዬ  ናቸው።  ዮናታን በግል የፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት አጭር ፅሁፍ «ሁለቱ አማራጮች ከተጋረጠብን የወረርሽኝ ፈተና እና ቀጣይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖው አንፃር ቀጣይነት የሚኖረው እና የተሻለ የመፈፀም አቅም ያለው መንግስት እንዲኖረን እድል የሚሰጡ ናቸው» ብለዋል።  

የአገሪቱ «ሕገ-መንግስትም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ሕጎች ምርጫ ስለማራዘምም ሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የአስፈጻሚውን ስልጣን ማራዘም የሚቻልበት ግልጽ ድንጋጌ የለም» ያለው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በበኩሉ ብሔራዊ የአንድነትና ጊዜያዊ መንግስት እንዲቋቋም፤ የሕገ መንግሥቱ 15 አንቀጾችም እንዲሻሻሉ በፌስቡክ ባሰራጨው መግለጫ ጠይቋል። ንቅናቄው በፌስቡክ ባሰራጨው መግለጫ አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን፣ የክልል መንግሥታት እንዲፈርሱ ጭምር ጠይቋል። 

ልደቱ አያሌው እና ይልቃል ጌትነት ሚመሯቸውን ጨምሮ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተው አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት በበኩሉ ኢትዮጵያ «በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ሆና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ግን የስልጣን ዘመኑን በሕገ-ወጥ መንገድ ለማራዘም» እየሞከረ ነው ሲል ወንጅሏል። በአባል ፓርቲዎቹ የፌስቡክ ገፅ በተሰራጨው መረጃ «ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ ለአንድም ቀን በስልጣን ላይ የሚገኘውን መንግስት ዕድሜ ለማራዘም የሚያስችል ምንም ዓይነት ድንጋጌ በአገራችን ሕገ-መንግስት ውስጥ የለም» የሚል ሐሳብ ሰፍሯል። «ብልፅግና ፓርቲ እንዲህ ዓይነት ሕገ-መንግስታዊ ቀውስ እንዲከሰት ምክንያት የሆኑትን የሕገ-መንግስቱን አርቃቂዎች እና ለሕገ-መንግስቱ ክፍተት መታየት ምክንያት የሆነውን ኮሮና ቫይረስን “ከመርገም” ውጭ በሕጋዊ መንገድ የስልጣን ዘመኑን ለአንድም ቀን የሚያራዝምበት ምንም ዓይነት መብትና ስልጣን በሕገ-መንግስቱ አልተሰጠውም» ብሏል። 

ዳሳ ቡልቻ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ የዐቢይ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ አሁን አገሪቱ ለገጠማት ቀውስ እንደ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ ማስቀመጡ ተገቢ አይደለም የሚል ዕምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ዳሳ በግል የፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት አጭር ጽሁፍ «ሕገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ የሚለው አማራጭ ተግበራዊ እንደምታው ካልተፈራ በስተቀር በሀሳብ ደረጃ ዋነኛ አማራጭ ሊሆን ይችላል» ብለዋል። የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚለው አራተኛው ሐሳብ «ቀላሉ አማራጭ ቢመስልም ብዙ የሚያከራክር ይመስለኛል። ከቀረበው ገለፃም ብዙ ያልጠሩ ጉዳዮች አሉበት። የትኛው አንቀፅ ነው የሚተረጎመው? ትርጉም ያስፈለገው ለምንድን ነው? ግልጽ ስላልሆ ወይስ አወዛጋቢ ስለሆነ? ወይስ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት? በትርጉም ብቻ ያን ሁሉ  ክፍተት በመሙላት ጥያቄዎቹን ሁሉ መመለስስ ይቻል ይሆን? በትርጉም ተሳቦ ሕገ-መንግስት መፃፍስ አይሆንምን? ብዙ ጥያቄዎች የያስነሳል» ይላሉ ዳሳ። 

Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)
ህወሓት ምርጫው ሊካሔድ ይገባል በሚል አቋሙ እንደጸና ነው

የህወሓት መንገድ እና የትግራይ ምርጫ

የምርጫ ጉዳይ ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ ከብልጽግና ሰዎች የገባውን መቃቃር እንደገና እንዲያገረሽ አድርጎታል። ህወሓት በሳምንቱ መጀመሪያ በምርጫ ላይ ያለውን አቋም በድጋሚ ያረጋገጠበትን ጽሁፍ በፌስቡክ አጋርቶ ነበር። ይኸው ጽሁፍ ወይን ከተባለ የህወሓት የንድፈ ሓሳብ መፅሔት የሕዳር 2012 ዓ.ም ዕትም ተወስዶ በድጋሚ በፌስቡክ ተቀንጭቦ የቀረበ ቢሆንም በማኅበራዊ ድረ ገፆች የመነታረኪያ ጉዳይ ከመሆን ያገደው ነገር አልነበረም። 

ይኸው ጽሁፍ «ምርጫ ከተራዘመ ሊፈጠር የሚችለው የቅቡልነት ችግር ለመፍታት፤ በትግራይ ደህንነትና ህልውና ላይ ፅኑ አቋም ካላቸው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ምርጫ ማካሄድ ጨምሮ በአንፃራዊነት የተሟላ መንግስታዊ ቁመና ያነፀች፡ በአንፃራዊነት ራሷን የቻለች ክልል (Defacto state) እንድትሆን የሚያስችል ስራዎች መከወን ይገባል። ይኽን በሚመለከት መንግስት ከተጋሩ (የትግራይ ተወላጆች) ምሁራንና ተመራማሪዎች በመሆን የተጀመሩ ጥናቶች ወደ ተግባር የሚውሉበት ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል» የሚል ነበር። የትግራይ ክልል ኮምኒኬሽን ቢሮ ሐላፊ ወይዘሮ ሊያ ካሳ ባለፈው ሳምንት ምርጫው ሊካሔድ እንደሚገባ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የኮሮና ወረርሽኝ የሚኖረውን ተፅዕኖ እንደማይዘነጉ የተናገሩት ወይዘሮ ሊያ ኢትዮጵያ «በየትኛውም አስከፊ [ኹኔታ] ውስጥ ብትሆን እንኳ» ምርጫ የማካሔድ ልምድ እንዳላት ገልጸው ነበር። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ የፌስቡክ ገጽ ˮየሚገርም ኢ- ሕገ መንግስታዊ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ በትግራይ ክልል አመራሮች ብቻ ተናፈሰ ˮ የሚል ጽሁፍ ሰፍሯል። ይኸው ጽሁፍ እንደሚለው «በሕገ-መንግስቱ የምርጫ የሕግ ጉዳይ የፌዴራል መንግስቱ ስልጣን ስለ መሆኑ በአንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 15 ተደነገጎ እያለ እንዲሁም ምርጫን በክልልም ሆነ በፌደራል ብቸኛ አስፈፃሚ አካል በሕገ-መንግስቱ በአንቀጽ 102 የተቋቋመው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሆኖ ሳለ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 8 የፌዴራሉ መንግሥትና የክልሎች ሥልጣን በሕገ-መንግሥት መወሰኑ፤ ለፌዴራሉ መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች መከበር እንዳለበት፤ ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣን በፌዴራሉ መንግሥት መከበር እንዳለበት በተደነገገበት፤ የትግራይ ክልል አመራሮች ምርጫውን በራሳችን እናካሂዳለን ያሉት እኛ የማናውቀው ሌላ የተፃፈ ወይም ያልተፃፈ ሕገ መንግስት ኢትዮጵያ አላት እንዴ?» በማለት ይጠይቃል። 

በትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ስም የተከፈተ የፌስቡክ ገፅ "ሕገ–መንግስቱ ያለ ምንም ቅደመ–ሁኔታና ምክንያት በየአምስት ዓመቱ ምርጫን ማካሄድ ግዴታ መሆኑ ደንግጎ ሲያበቃ በሕዝብ ጫንቃ ላይ አስገድደው ለመንገስ ሲሉ ቀደው እየጣሉት ስለ ሕገ-መንግስት ጥሰት ሲያወሩ ትንሽ ሀፍረት የላቸውም እንዴ?» በማለት የአቶ ተስፋዬ ዳባን ሐሳብ የሚያጣጥል ጽሁፍ ሰፍሯል። ጸሐፊው «እስኪ አሁን እኝህ ሰው ስለ የተኛው ሕገ-መንግስት ነው የሚያወሩት? ሕገ መንግስቱ አለ ብለው ቢያስቡ ራሱ እስኪ አንቀፅ 39 አንብበው ለመረዳት ይሞክሩ። ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አነሰ ቢባል የፈለጉትን መንግስትና አመራር ከመምረጥ ነው የሚጀምረው። ለመምረጥ ነፃነት የሌለው ህዝብ ስለ ራሱን በራሱ የማስተዳር መብት ሊታሰብ አይችልም። አንድ ህዝብ መሪዎቹን ለመምረጥ ቢፈልግ "ሕገ-መንግስቱ አይፈቅድልህም" የሚባልበት አገር በዓለም ውስጥ ለማየት በቅተናል» ብለዋል። 

ታዲ ሐላኬ የተባሉ የፌስቡክ ለአቶ ተስፋዬ ዳባ በፃፉት የፌስቡክ መልዕክት «የትግራይ ክልል መከራከሪያ አሳማኝ ህገ-መንግስታዊ መሰረት ባይኖረውም፣ እናንተም በተሻለ አቋም ላይ ያላችሁ አይመስለኝም። ምርጫን ማካሄድ የፌደራል መንግስት ስልጣን ቢሆንም፤ ምርጫን ከአምስት አመቱ ገደብ የማስተላለፍ ስልጣን የለውም። አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ሕገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ወይም የህግ ትርጓሜ የሚባሉት ህጋዊነት እና ቅቡልነት የላቸውም። የፌደራል መንግስት እና ገዢው ፓርቲ ያለ ክልሎች እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይሁንታ ህግን አወላግዶም ሆነ ጠባብ ቀዳዳን (loophole) ፈልጎ፤ ምርጫን ከቀነ ገደቡ ቢያሳልፍ ሕገ-ወጥ መንግስት ነው የሚሆነው። ያንን ካደረጋችሁ የትግራይ ክልልም ከህግ ማዕቀፍ ውጪ ምርጫን ቢያካሂድ ለመጠየቅ የሚያስችል ህጋዊም ሆነ ሞራላዊ መሰረት አይኖራችሁም። የፌደራል መንግስት እራሱ ህግ እየጣሰ በክሎችን ሆነ በዜጎች ላይ ህግ ማስከበር አይችልም» ብለዋል። «አሁን ለተጋረጠብን ህገ-መንግስታዊ ቀውስ በክልልም ሆነ ፌዴራል ደረጃ ህጋዊ መፍትሄ የለም። ያለው አማራጭ ፖሊቲካዊ መፍትሄ ማበጀት ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ማዶ ለማዶ ቆሞ መጯጯህ እና ጦር መስበቅ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስቦ መደራደር ነው የሚያዋጣው» የሚል ጥቆማ ታዲ ሐላኬ ሰጥተዋል። 

የትግራይ ልጅ ወይም ሰን ኦፍ ትግራይ የሚል መጠሪያ የሚጠቀሙ ግለሰብ በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት "ክልሎች ያለ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ የሚያካሄዱት ምርጫ ተቀባይነት አይኖረውም" የሚለው ክርክር፣ ክልሎችን ለማስፈራራት የተፈጠረ፣ ተቀባይነትም፣ ሕጋዊ መሠረትም የሌለው ስንኩል ሃሳብ ነው" ብለዋል።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ