1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ መጋቢት 4 2012

በኦኤምኤን የተላለፈዉ ንግግር ፣የፕሬስ ኤጀንሲ የተሳሳተ ምስልና፤ጥቃት በህክምና ባለሙያዎት ላይ የዚህ ሳምንት ርዕስ ነዉ ። ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ በአዳማ ከተማ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ባዘጋጀዉና በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ በቀጥታ የተላለፈዉ ንግግር፣ የፕሬስ ኤጀንሲ የተሳሳተ ምስል መለጠፉ ብዙ አስተያየቶች አሰናዝሮአል።

https://p.dw.com/p/3ZOYl
Symbolbild Twitter
ምስል Imago/xim.gs

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት


 በእነዋሪ ከተማ ነጻ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በሄደ ቡድን ላይ ጥቃት ደረሰ መባሉ በዚህ ሳምንት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ያነጋገሩ ጉዳዮች ነበሩ።
ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ በአዳማ ከተማ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ባዘጋጀዉ መድረክና በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ  የተላለፈዉ የአንዲት ተሳታፊ ወጣት  ንግግር በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ ብዙ አነጋግሯል።ንግግሩ በኦሮምኛ ቋንቋ የተደረገ ቢሆንም  የንግግሩ ትርጉም «የኦሮሞ ብሄር አባላት ከሌላ ብሄር አትጋቡ»የሚል ይዘት አለዉ በሚልም  በማህበራዊ መገናና ዘዴዎች በእጅጉ ተሰራጭቷል።ይህንን ተከትሎ ም አዲስ አብርሃም የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ «ተጋብቶ፣ተዋልዶና ተዛምዶ ለዘመናት ለኖረዉ  የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ንግግር አሳዛኝ ነዉ»ሲሉ፤ አሌክስ አልክስ በሚል ስም ደግሞ «ችግሩ የልጅቷ አይደለም። ይህች ወጣት የተሰበከላትን ጥላቻ ፊት ለፊት በየዋህነት ተናገረችዉ እንጅ።ጥፋቱ የፖለቲከኞቹ ነዉ።»ብለዋል በዚሁ በፌስ ቡክ።«በመድረክ ከተነገረዉ ይልቅ ጉዳዩን በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የምታራግቡ ሰዎች የበለጠ ጥላቻን እየዘራችሁ መሆናችሁንስ አዉቃችሁታል?በማለት የጠየቁት ደግሞ በዳዳ ስሜ ናቸዉ። አልፊያ ከድር ደግሞ «ማንም ሰዉ የመሰለዉን የመናገር መብት አለዉ።የመናገር ነፃነትን ማንም ሰዉ ሊገድብ አይገባም»ብለዋል። ሀሰን ረጃ ግን «ነፃነት ግን ሃላፊነትንም ይጨምራል።አንድ ሰዉ በነጻነት የመናገር መብቱን ሲጠቀም የሌላዉን መብት መንካት የለበትም።»ሲሉ የላይኛዉን አስተያየት ተቃዉመዋል። ኦስማን አብሽር ደግሞ« የኛ ችግር አዋቂውም አላዋቂውም በተናገረ ቁጥር ማስጮሃችንና ማስተጋባታችን ነዉ። እንሰልጥን አስተማሪ እንጂ ገፊ አንሁን።ስው በተሳሳተ ቁጥር ከአጥፊው በበለጠ አጥፊ መሆን ይብቃ።» ብለዋል።በፀሎት በፀሎት ደግሞ «ፖለቲካዉ ከርስት ወደ ሚስት ተሸጋጋረ ማለት ነዉ?»ሲሉ  ሳምራዊት አዱኛ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ደግሞ 
«ለመሆኑ እኛ ሴቶች ችግራችን ይህ ነዉን? ለወሊድ ጤና ጣቢያ በማጣት እናት ሳትገላገል ህይወቷ በሚያልፍባት ሀገር ፣ አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት አሁንም ድረስ ፈተና በሆኑባት ሀገር፣ የድሃ ድሃ ሆነዉ ጎዳና ላይ ልጅ የሚያሳድጉ እናቶች ባሉባት ሀገር፣ በሴቶች ቀን ይህ  መወራት ነበረበት? ሲሉ ጠይቀዋል።
«ሰዉ እንዴት በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን እንዲህ ያብዳል።ሰዉ  በዘሩ በቋንቋዉና በደሙ ምክንያት መጥፎ ወይም ጥሩ ሊሆን አይችልም።መጥፎም ጥሩም ሊያደርገዉ የሚችለዉ የራሱ የግለሰቡ ስብዕና ብቻ ነዉ። ደግሞስ ሰዉ ወዶና ፈቅዶ የተወለደበት ብሄር አለ?ፈጣሪ ልቦና ይስጠን »ያሉት ደግሞ መገርሳ ዳባ ናቸዉ።
 ደራሲ  ህይወት እምሻው በትእዛዝ አልተጣመርንም፣ በትእዛዝ አንለያይም! በሚል ርዕስ ተከታዩን መልዕክት አስፍራለች።«ለአራት አመታት ፍቅረኛዬ የነበረው፣ አዲሳባ ተወልዶ ያደገው ባለቤቴ አያቱ ስላሳደጉትና በእርሳቸው ስለሚጠራ ኦሮሞ እንደሆነ ያወቅኩት በሰርጌ ቀን ነው።» ካለች በኃላ የእርሷንና የባለቤቷን ቤተሰቦች የጋብቻ ጥምረት በሚከተለዉ መልኩ በፌስቡክ ገጿ አስፍራዋለች።
«ቆይቶ የባሌ እማማ እና አባባ እንዴት እንደተገናኙ ሰማሁ፡፡ አባባ ከአምቦ አዲስ አበባ መጥተው ቤት ይከራያሉ፡፡ ቤቱን ከመከራየታቸው ከአዲሱ ቤታቸው በላይ ቀልባቸው በማን ይሰረቃል? በአከራያቸው ሴት ልጅ፣ የዛሬዋ እማማ ተፋቀሩ። ተጋቡ። የእኔን ባል ጨምሮ አምስት ወለዱ። ከበዱ።የእኔ እማማ እና አባባ ደግሞ እንዴት ተናኙ? እሷ ከደምቢዶሎ ፣ እሱ ደግሞ ከመንዝ ለትምህርት ደብረብርሃን ኮሌጅ ሲሄዱ። ተፋቀሩ።ተጋቡ። እኔን ጨምሮ ስድስት ወለዱ።ከበዱ።በቃ የእኛ እና የሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ታሪክ እና ኑሮ ይሄው ነው። በትእዛዝ አልተጣመርንም፣ በትእዛዝ አንለያይም።የተጋባነው ስለተፋቀርን ነው። ዛሬም አብረን የምንኖረውም እስካሁን ስለምንፋቀር ነው።የመጋባታችን እና አብሮ የመኖራችን ምክንያት ፍቅር ብቻ ስለሆነ በመንገዳችን ሁሉ አዛዣችን ፍቅር ነው» በማለት ፅሁፏን ቋጭታለች።
በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የተላለፈዉን  ንግግር ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለሀገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሃን  እንገለጹት፥ በህዝባዊ መድረኮችና መገናኛ ብዙሃን በኩል የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች በሃገር አንድነትና አብሮነት ላይ አደጋ የሚደቅኑ በመሆናቸዉ በዚህ  በመሰል ድርጊት በሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመገናኛ ብዙሃን ላይ ተገቢና ተመጣጣኝ ዕርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል ሲሉ አስታውቀዋል።መግለጫዉን ተከትሎ
 ማርክ ኪንግ በሚል የፌስቡክ ስም «የጥላቻ ንግግርን ሁሉም ሊጠላው ይገባል። የጥቂት ሰዎች ግዴታና ሃላፊነት ሊሆንም አይገባም።»ብለዋል።ሀብቱ አሰፋ «ሕግ መውጣት፣ መግለጫ፣ ማሳሰቢያ፣ ማስታወቂያና ማሰጠንቀቂያ! መች ነው ወደ ሥራ የምትገቡት?»ሲሉ።
ካሳሁን መለሰ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይም « ዜጎች ሲገደሉ እርምጃ እንወስዳለን፤ባንክ ሲዘረፍ እርምጃ እንወስዳለን።ይሄ ሕግን ማስከበር ይጀመራል እየተባለ ሳይጀመር አለቀ እኮ ጃል።» ሲሉ መግለጫዉን ተችተዋል።ብርቱካን ኢያሱ በበኩላቸዉ «መንግስት ሆይ በነካ እጅህ በዚህ ንግግር ሰበብ ከዚያኛዉ መንደር የሚሰበከዉን ጥላቻም አስቁምልን ብለዋል።» ናማፍ ጋማቴ «ባጋጣሚው ተጠቅማችሁ የፖለቲካ ሸር ለመተግበር ካልሆነ በስተቀር ትዳር የግል እንጂ መንግስትን አይመለከተውም። ያን ያህል አሳሳቢና መግለጫ የሚያስወጣ ነገር አይደለም።»ሲሉ።« ወንድሜ ነገሩን አታቃለዉ ቤተሰብ የሀገር መሰረት ነዉ» ያሉት ደግሞ»ሽኩሪ መሀመድ ናቸዉ።
ቆይቶም የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ከፍተኛ አመራር አቶ በቀለ ገርባ በምክክር መድረኩ  በአንዲት ተሳታፊ የተላለፈው መልዕክት እኛን ወይም ፖርቲያችንን አይወክልም ሲሉ ለሀገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልፀዋል።አቶ በቀለ የእርሷን ሀሳብ ደግፈን አላጨበጨብንም ያም ሆኖ ግን ከእኛ ቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ለተፈጠረው ነገር በማህበራዊ  መገናኛ ዘዴዎችና በግለሰቦች  ተከፈተብን ያሉትን ዘመቻም አግባብ አይደለም ሲሉ መተቸታቸዉን በዚሁ በፌስቡክ ተመልክተናል።
 የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ያወጣዉ ጠቅላይ ሚንስትሩና ባለቤታቸዉ መኝታ መለየታቸዉን የሚያሳይ የተቀነባበረና  ከተፃፈዉ ታሪክ ጋር አብሮ የማይሄድ የተሳሳተ ምስል ደግሞ ለማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሳምንቱ  ሌላ አዲስ የመነጋገሪያ ክስተት ነበር።ድርጅቱ ለተፈጠረዉ ስህተት ይቅርታ ቢጠይቅም ጉዳዩ ግን ማነጋገሩ ቀጥሏል።
ይህንን ተከትሎ ማርታ አሰፋ «በእርግጥ  ድርጅቱ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ጠይቋል። ይህ ግን ተራ ስህተት አይደለም። የለየለት እብደት እና ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያፈነገጠ ነዉ።»ሲሉ « ጠቅላይ ሚንስትሩን ሳይሆን የሚመሯትን ሀገር ጭምር ያዋረደ ነዉ»ያሉት ደግሞ ዲቦራ ታመነ ናቸዉ። አብዲ ከድር ደግሞ «ስናሳዝን በቃ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የብሽሽቅ ሜዳ ሆነ ማለት ነዉ።»ብለዋል።አባ ባህሬ በሚል የፌስቡክ ስም «ምንም የጠቅለዩ አካሄደ ባይመቸኝም እንዲህ ክብረ ነክ ድርጊት ግን ፈፅሞ ነዉርና የተወገዘ ነዉ።»ብለዋል።
ፍቅርተ መንግስቴ ደግሞ« በፈጣሪም በማህበረሰቡ ታላቅ ክብር ያለውን ትዳርን ያህል ነገር እንዲህ  ሰዎች ሲያፌዙበት ማየት ያሳፍራል።ጉዳዩ ያለንበትን የአስተሳሰብ ዝቅጠት በግልፅ ያሣያል።»ብለዋል።ሀመረ ሚካኤል«ይሄ ለውጥ ግን ስንቱን ባለጌ አስተዋወቀን።»ሲሉ ገልጸዋል።« ይህ በጣም ትልቅ ጥፋት ነው። አንድ የሀገር መሪ የሚወክለው የሚመራውን ሀገርና ህዝብ ነው። እንደእኔ ይህ ድርጊት ሀገርን መስደብ ነው።»ያሉት ደግሞ ሀብታሙ ጉዲሳ ናቸዉ። አለሙ ወልዴ «ነፃነት ሲበዛ ባርነት ነው ይሉት እሄ ነው ከምር በዝቷል» ሲሉ ሀዋ አደም«ድርጊቱ የዝቅጠታችን ልክ ነው ያሳየን። ያሳዝናል !በቃ ነውር የሚባል ነገር ነውር ሆነ ማለት ነው ?»
ያለፈዉ ረቡዕ በአማራ ክልል ሞረትና ጅሩ ወረዳ፣ እነዋሪ ከተማ ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ  የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ላይ በህክምና ሰበብ የሌላ ሀይማኖት ተከታዮችን ሰብከዋል በሚል ጥቃት ደረሰባቸዉ መባሉ፤ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ያነጋገረ ሌላዉ ጉዳይ ነበር።በጥቃቱ የቤተክርስቲያኒቱ ማምለኪያ አዳራሽና ለቢሮነት የሚያገለግሉ ክፍሎች መውደማቸውም ተሰምቷል። ይህንን ተከትሎ፤ ፍሬሰንበት ባህሩ «ስንቱን ነውር ሰማን፥ በስንቱ አዘንን።ቤተ እምነትን በማቃጠል መቼም ፅድቅ አይገኝም።»ሲሉ ሮቤል ረጋሳ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ«ነፃ ህክምና እሠጣለሁ ብሎ እምነትህን ቀይር ማለትሥ  ህጋዊ ነዉ ?ሲሉ ጠይቀዋል።«ሰዎቹ ይህንን ድሪጊት የፈጸሙት  ለመፅደቅ አይደለም። መታለላቸው በችግራቸው መዘበቻ መሆናቸው። መናቃቸው  በማይገባ መብል ሊያታልሏቸው በመሞከራቸው ነዉ። መብል ከክብር ይበልጣል።ያም ቢሆን ጥቃቱን ትክክል ነዉ ብዩ አልወስደዉም።»ያሉት ሸዋነሽ ሀይሉ ናቸዉ።
«አይ! ኢትዮጵያ ማምለኪያ ቦታዎችን ማቃጠል ሆነ ምዕመናኑን ማሳደድ ጀብድ የሆነባት የጉድ ህገር» ያሉት ደግሞ አበራ መከተ ናቸዉ።ዲሜጥሮስ ሙላቱ «ጉዳዩን በደንብ አጣራ በመንግስት ተቋም ውስጥ ድንኳን ተክለው ነው ስብከት የጀመሩት ይህ አግባብ ነው?  ማምለኪያ ቦታቸውን የነካ የለም የተቃጠለውም በመንግስት ተቋም ውስጥ የተከሉት ድንኳን ነው።»ሲሉ
ሶሎሞን ታፈረ ደግሞ  «ለማንኛውም  የፀሎት ቤትም ይሁን የህክምና ድንኳን መቃጠሉ መልካም ዜና አይደለም።ጉዳዩ ተጣርቶ በአፋጣኝ መፍትሄ ቢሠጠው መልካም ነው። ድርጊቱን የፈፀሙት በህግ ሊጠየቁ ይገባል።»ብለዋል።ቢኒ ሶኒክስ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረዉ መልዕክት ደግሞ« የህክምና ባለሙያዎቹም ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። ከህክምና ስነምግባር ውጪ ሙያቸውን በመጠቀም የግል ሀሳባቸውን ሰዎች ላይ ለመጫን ያደረጉት በመሆኑ በዚህ ተግባራቸው መወገዝ አለባቸው።» ብለዋል።
ፋሲካ መኮነን «ያም ሆነ ይህ ቤተ እምነትም ሆነ ድንኳን ማቃጠል መፍትሄ አይሆንም። መጀመሪያ ይሄንን ክፉ ተግባር እንቃወም። እንኮንን። ከዚያ ለችግሩ መፍትሄ መፈለግ ይሻላል።»ብለዋል።ደጀኔ ስዩም ደግሞ « ምንም ይበሉ ምንም ያድርጉ ማቃጠል ተገቢ አይደለም።»ሲሉ ሞግተዋል።አበበች መገርሳ ደግሞ «መስጊድና ቤተክርስቲያን ሲቃጠል ህዝቡ አዋጥቶ በመስራት አብሮነቱን አሳይቷል።ይህ አልሆን ሲል ደግሞ ወደ ሌላ አቅጣጫ ዞረ ማለት ነዉ? ወገን ሀገር ከማጣታችን በፊት ችግራችንን በፍቅር እንለፍ።»በማለት ፅፈዋል።«ህዝቡ እርዳታና ስብከት ሲቀላቀል ተቃዉሞ ከነበር የአካባቢዉ አመራር በጊዜ መፍትሄ መስጠት ነበረበት።ያ ባለመሆኑ የአካባቢዉ ባለስልጣናትም ተጠያቂ መሆን አለባቸዉ።»ያሉት ደግሞ ህብስት ጥላሁን ናቸዉ።

Symbolbild Facebook
ምስል Getty Images/AFP/L. Bonaventure
Pro Merera Gudina vorsitzender OFECO
ምስል DW/S. Wegayehu


ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ