1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ጥር 8 2012

ናይጀሪያውያን  እናቶችን በቦኮሃራም የታገቱ  ሴት ተማሪዎች ጉዳት ትኩረት እንዲያገኝ ያካሄዱትን ዘመቻ መሰል «ልጆቻችንን አምጡልን»  የሚል የማኅበራዊ መገናኛ ዘመቻ በዚህ ሳምንት ሲካሄድ ነበር።

https://p.dw.com/p/3WMmN
Symbolbild Apps Facebook, Google und Google + Anwendungen
ምስል Imago Images/P. Szyza

«የሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛው መነጋገሪያ»

Äthiopien | Nil-Staudamm Grand Ethiopian Renaissance Dam
ምስል picture-alliance/dpa/G. Forster

የተፈጠረውን ረብሻ  ሸሽተው  ወደ ቤተሰቦቻቸው  ለመመለስ  በጀመሩት  ጉዞ  መንገድ  ላይ መታገታቸው  የተነገረውን  የደምቢዶሎ  ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ አንዱ ወገን ተለቀዋል፤ የልጆቹ ቤተሰቦች ደግሞ ልጆቻችንን ድምፅ ካልሰማን እንዴት እንመን እያሉ ነው። በዚህ መሃልም በጉዳዩ ላይ  አስተያየታቸውን በፌስቡክ ካጋሩት መካከል፣ ያሬድ ኃይለ ማርያም ዘለግ ባለው ጽሑፋቸው « ተማሪዎቹ ከታፈኑ አንድ ወር አልፏቸዋል፤ ለዚህን ያህል ጊዜ ጉዳይ ለምን ተሸፋፍኖ ቆየ? የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣን፣ የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ሹማምንት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ፣ የደንቢዶሎ ዩንቨርሲቲ አመራሮች እና ሌሎች የመንግስት አካላት ለምን በተለያየ ጊዜ የተለያየ እና እርስ በርሱ የሚጣረስ መግለጫ ሰጡ?» ሲሉ ጠይቀዋል።

ዮናስ ደብሬ ደግሞ በትዊተር« 17 ሴት አማራ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታግተው የኢትዮጵያ መንግሥት ገፅታውን ለመጠበቅ ሆን ብሎ ዝምታን በመምረጡ እነሱን ለማዳን የሚያደርገው ነገር የለም» ሲሉ ተችተዋል። በተከታታይ « ተማሪዎቹ ባስቸኳይ ይለቀቁ» የሚል መልዕክታቸውን በትዊተር የጻፉት ማርታ T በበኩላቸው፤ «ከእገታው መማምለጧን የተናገረችው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ይህን በይፋ በመናገሯ ተገቢው ከለላ እና ጥበቃ ሊደረግላት እሷም ብቻ ሳትሆን ቤተሰቦቿም ከለላ ሊደረግላቸው ይገባል።» ብለዋል።  

ተስፋዬ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ «ያንተ እህት ብትሆንስ? ሴቶች ላይ የሚፈፀምን ጥቃት፣ ከመነሻው እናስቁመው የሚል ፖስተር አክለው፤ «ኢትዮጵያ ውስጥ የታገቱ ልጆቻችንን አምጡልን» የሚል መልእክታቸውን አካፍለዋል። ይልማ ኪዳኔ ደግሞ፤ «መንግሥት ደንቢዶሎ ላይ የታገቱትን 17 የማራ ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባስቸኳይ ያስለቅቅ» ብለዋል። ደቻሳ አንጌቻ ታደሰም በዚሁ በትዊተር፤ «ቡና/ሻሂ አለ ሳይሆን አለች በሉ፤ «ጀግና» ሳይሆን «ጀግኒት» በሉን በሚሉ ኮተት አጀንዳዎች ሲጠምዱን የከረሙ የሴቶች መብት ከእኛ በላይ የሚሉት እህቶቻችን ስለደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ምን ብለው ይሆን? ልክ የሴትነት ተምሳሌት የነበሩት እቴጌ ጣይቱ ሐውልት በአዲስ አበባ እንዳይቆም የተባለ ጊዜ እንዳደረጉት ዝም አሉ ወይስ ተቃወሙ? ብለው ጠየቁ።

የታገቱት ተማሪዎች ተለቅቀዋል በሚል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የፕረስ  ሴክረታሪ  ኃላፊ በመገናኛ ብዙሃን የሰጡትን መግለጫ ተከትሎም ምሥጋናው ታደሰ በፌስቡክ፤

« ተደብቆ  ቆይቶ ህዝብ እንዳወቀ ሲታወቅ መግለጫ መሰጠቱ ይበልጥ ያናድዳል ። ለምን? እንደታገቱ በወቅቱ ለህዝብ ይፋ መደረግ ነበረበት ። የሚያሳዝነዉ አማራ ክልል ሆኖ ቢሆን እንኳን በሚኒስተር ደረጃ ይቅርና የቀበሌ አመራር መግለጫ በኢቲቪ ይቀርብ ነበር ። ሆኖም ግን መለቀቃቸዉ ደስ ይላል ።» ሲሉ፤ እድገቱ በዛብህ በበኩላቸው፤ «በመለቀቃቸው  ትልቅ  ደስታ ነው  የተሰማኝ። ነገርግን ያለምንም ጉዳት አይባልም  የስነልቦና  ጉዳት ይኖራል ቢያንስ፥  ከዛ ውጭ ስለ አካላዊ ጉዳት ደግሞ የባለሙያ እና የህክምና መረጃ ያረጋግጣል።» ብለዋል። ሂክማ ሀሰን ይጠይቃሉ፤ « ታድያ የት አሉ? ከተለቀቁ ተማሪዎቹን ማየት እንፈልጋለን። ምንስ ጉዳት ደርሶባቸው ይሆን? መቸም ለጌጥ አይደለም ያገቷቸው።» አበበ ንጋቱ እንዳለው ደግሞ፤ «እኔም መቸም ከገታ ስለወጡ ወጣቶች ደስታየ ወደር የለውም:: በእነርሱ ስቃይ ፕሮፖጋንዳ ከመስራት ሰው ቢቆጠብ ጥሩ ነው::  ክፉ ጊዜ ማለት ይኸው ነው::  በዘውግ ብቻ የሚታሰብበት::  ይህን ድርጊት ያላወገዘ አክቲቪስትም ሆነ ፖለቲከኛ በሽተኛ ብቻ ነው።» መስከረም አበራም በፌስቡክ፤ የመንግሥት ሹማምንት በወንበዴ የታገቱት እነዛ የሚፈርጡ የሚመስሉ ፣በቪ8 ከትምህርት ቤት የምታመላልሷቸው፣ በየምዕራብ ሃገሩ የምታስተምሯቸው፣ የእንጀራ ጠርዝ የሚቆርጣቸው ልጆቻችሁ ቢሆኑስ ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ይህ በእናንተ ቢደርስ ተኝታችሁ የምታድሩ ይመስላችኋል???? እነዚህን የታገቱ ልጆች እዚህ ለማድረስ ወላጆቻቸው ስንቱን የኑሮ መስቀል ተሸክመው ስንቴ "ኤሎሄ!" እንዳሉ ታጡታላችሁ? ሌላው ቀርቶ "አስለቅቀናል" ብላችሁ ባታፌዙ ምናችሁ ይጎዳል?» ብለዋል።

Symbolbild Twitter Konto
ምስል picture-alliance/dpa/A. Gombert

 

ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር በአባይ ላይ በምትገነባው ግድብ ምክንያት የጀመረችው ድርድር እና ከካይሮ ጋር የገባችበት ውዝግብም በዚህ ሳምንት የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ርዕሰ ጉዳይ መሆኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚታዩት አስተያየቶች ያመለክታሉ። ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ግብፅ እና ኢትዮጵያ በግድቡ ውኃ አሞላል መግባባት አለመቻላቸው እና ግብፅም ጉዳዩ በዓለም አቀፍ አደራዳሪ ይታይልኝ በማለት ስትወተውት የቆየችውን በመጥቀስ ብዙዎች በስሜት እና ትኩረት ያገኙትን መረጃ ሲለዋወጡ ነው የሰነበቱት። በዚህ ሳምንት ዋሽንግተን ላይ ውይይቱ ከተካሄደ በኋላ የወጡ መረጃዎች ላይ በመመርኮዝ አስተያየታቸውን በፌስ ቡክ ካካፈሉት መካከል፤ የከዳሽ ይከዳ በሚል ስም፤ «ይገርማል! ለምን የ ASWAN ግድብ አጠቃቀማቸው ድርድሩ ውስጥ እንዲካተት አልሆነም? ለምን እኛብቻ ስለድርቅ ጊዜ አጠቃቀም እንጠየቃለን?» ሲሉ ጠይቀዋል። ኡርሚያስ ሽፈራው በበኩላቸው፤ «በሌላ ሀገር የተፈጥሮ ሀብት/ብሄራዊ ጥቅም ላይ ተደራድሮ እና እጂ ጠምዝዞ በአሸናፊነት መውጣት እንደሚቻል ግብፅ አሳይታለች ማለት ይቻላል።» ነው ያሉት።

 የዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛው በሰፊው  መነጋገሪያ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮው ምርጫ የሚካሄድበትን የጊዜ ሰሌዳ ነው። ሀሰን አብዲ ሀሰን በፌስቡክ፤« ህዝባችን (ጨዋ) ህዝብነው። ስለዚህ ፕሮግራሙን ያመነ ባት ይመርጣል። ሳናይ ምሽት!» በአጭሩ ሲሰናበቱ፤ ቴድሮቪች ተስፋዬ፤

" መልስ ካልተሠጠ ምርጫ ምን ያደርጋል ? " ዋናው ነገር የምርጫው ጊዜ በበጋ ወይም በክረምት መሆኑ አይደለም :: ምርጫ ምረጡ ይሉናል አንመርጣለን,  ይሉናል እንመርጣለን,..... ቁም ነገሩ የምርጫው ጥያቄ መልስ ላይ ነው ።  ምክንያቱም ያለፉት ምርጫዎች መልስ =  መልስ አልተሠጠም ነው፤ ታደያ መልስ ካልተሠጠ ምርጫ ምን ያደርጋል ? ምንአልባት ምንአልባት የዘንድሮው ከምርጫ ይልቅ አብራራ ይሻል ይሆን ?» ብለዋል። ሮቤል ሮባ ደግሞ በዚሁ በፌስቡክ፤ «ዝርዝር ማቅረባችሁ ያስመሰግናል። ነሐሴ? አስተያየቴ፣ በክረምት 1) ገበሬ በሥራ ይወጠራል  2) መንገዶች ለተሽከርካሪ ያስቸግራሉ። 80% በላይ የሆነዉ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ "ሕዝብ"፣ ፓርቲ አላልኩም የቅኝት ጥናት በማድረግ ሃሳቡ በሳምፕል ደረጃ ተጠንቷል??» ሲሉ ጠይቀዋል።

ነጋሽ ረጉ ደምሴም ዘለግ ያለ ጥያቄ ያካተተ አስተያየት ነው በፌስቡክ ያቀረቡት፤ «ለአንድ ሀገር ህዝብ ምርጫ አስፈላጊ እና ወሳኝ መሆኑን የሚክድ የለም ። ይሁንና የኢትዮጲያ ምርጫ ቦርድ ያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ተገቢ ያልሆነና ግልጽነት የጎደለው ነው 1ኛ ነሐሴ ማለት በአብዛኛው የሀገራችን ክልሎች ከባድ የዝናብ መጠን የሚታይበት ወክት ነው። ይህ በእንዲ እያለ የመንገድ መሠረተ ልማት እንኳ በሌለበት በምን አይነት ሁኔታ ነው የተሳካ ምርጫ ተደረገ የሚባለው? የትኛው ገለልተኛ ታዛቢ ነው የሚታዘበውስ በዚህ በማይመች ሠአት? 2ኛ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ወደየቤተሠባቸው የሚመለሱበት ሠአት ነው የመራጭ ካርድ ካልወሰዱ በምን ይመርጣሉ? ይህንና ሌሎች ምክኒያቶችን ያላገናዘበ በመሆኑ ይህን ነገር የሚመለከተው የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ የሲቪክ ማሕበራት ከቦርዱ ጋር መነጋገር አለባቸው።»

ይዲድያ ምሥጋና በበኩላቸው፤  " በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ " አሉ ..  ሕዝቡን ያቺኑ እርሻውን ልጆቹን የሚያስተዳድርበትን ሊታሳጡት ነው ??? ምንድነው ዓላማችሁ ??» ሲሉ ጠይቀዋል። አዲስ አለማየሁ ደግሞ፤ «ምርጫ በዝናብ ወቅት አጋማሽ» ሲሉ በበርካታ የጥያቄ ምልክቶች አስተያየታቸውን አጅበዋል። ብርሃኑ ገ፤ ለማ በትዊተር፤ «በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የዘነበው ከባድ ዝናብ የምርጫ ቁሳቁሶችን በጎርፍ ወስዷል የEBC የነሐሴ ዜና» ካሉ በኋላ «የምርጫ ቦርድ በነሐሴ ምርጫ ሊካሄድ ይችላል የሚል ዕቅዱን ይፋ ካደረገ በኋላ ፌስቡክን ካጥለቀለቁ ቀልዶች አንዱ  ነው» ሲሉ ለሌሎች አጋርተዋል። 

Nationales Wahlgremium Äthiopiens
ምስል DW/S. Muchie

 ዘማስክ ካሳ ደግሞ፤ « እኔ ምርጫው ከሚፈለጉት ወገን ነኝ።  በዚህ ሁኔታ እንድንቀጥል አልፈልግም ። ያለው መንግሥት ጠንካራ ሊሆን የሚችለው በምርጫ አሸንፎ ቅቡልነት ሲኖረው ነው ። ለስጋቱ እንደሆነ አሁን ካለው በላይ ልንሰጋ አንችልም ባይሆን ይለይለትና አንዱን እንይዛለን ።» ሲሉ፤ ማቲ በቀለ፤ « ወንድሜ ሰለ ምርጫው ገጣሚ ታገል ሰይፉ ጨረሰልን አኮ «አማራ አማራን ከመረጠ ኦሮሞው እሮሞን ከመረጠ ትግሬውም ትግሬን ከመረጠ ይሄ ምርጫ አይደለም አዛምድ ነው»" በቃ ከዚህ በላይ ምን መልስ አለህ አሁን ከባድ ነው ሰው ከእንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል መንቀሳቀሰ ካልቻለ ሁሌ ከእንቅልፍህ ሰትነሳ ዛሬ ሰላም ይሆን አያልክ የምትሰጋበት ሀገር ላይ ከምርጫ ምን ትጠብቃለህ አኔ ለምሳሌ ያደኩት አዲሰ አበባ ነው አሁን የምኖረው አገብቼ በኑሮ ምክንያት ሱሉሉታ ነው ሁሌ በሰጋት ተኖራለህ  ምክንያቱም  በኔ  ኢኮኖሚ  አዲሰ አበባ  መኖሮ  ከባድ  ነው። ነገ  ምርጫ  ሲደረገ ወንድሜ  ምናለ  ባላደረግን  የምንልበት  ግዜ  ይመጣል።  ሰው  በሚያየው  ነገር  ያምናል  እኔ  ምርጫ በዚህ ግዜ አልደግፍም።» «ሀገርን ለማፍረስ መዶሻ የምትሰጡ ሚስማር ጨምሩና ለልማት ሩጡ» ያሉት ደግሞ አቡዲ ነው በሚል ስም የፌስቡክ ገፅ ያላቸው አስተያየት ሰጪ ናቸው።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ