1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ በትር ማን ላይ ያርፋል?

ረቡዕ፣ ነሐሴ 11 2014

የኢትዮጵያ መንግሥት "የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በማስፋፋት በመጠገን እና በማሻሻል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ" በገቢ ዕቃዎች ላይ አዲስ ቀረጥ ጥሏል። በአዲሱ ደንብ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዕቃዎች 3% የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ይከፈልባቸዋል። በዚህ ቀረጥ መንግሥት በዓመት 20 ቢሊዮን ብር ገደማ ሊሰበስብ እንደሚችል እምነት አለው

https://p.dw.com/p/4FcgK
Äthiopien Bürgerkrieg, Reportage aus Abaala, an der Grenze zwischen Tigray und Afar
ምስል Mariel Müller/John Irungu/DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ በትር ማን ላይ ያርፋል?

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 30 ቀን 2014 ባደረገው ስብሰባ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ለማስከፈል የወጣ ደንብ አጽድቆ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል። በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው ደንብ በአገሪቱ የጉምሩክ ደንብ የተዘረዘሩ እቃዎች ወደ አገር በሚገቡበት ጊዜ 3 በመቶ ቀረጥ እንዲከፈልባቸው የሚደነግግ ነው። በደንቡ እንደሰፈረው የቀረጡ መጠን የእቃው ዋጋ፣ ኢንሹራንስ እና የማጓጓዣ ወጪ ተደምሮ የሚሰላ ይሆናል።

በደንቡ መሠረት ሱር ታክስ የሚከፈልባቸው እቃዎች ላይ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ መጣል "የእቃዎቹን ዋጋ የሚያንር በመሆኑ ከታክሱ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።" ከዚህ በተጨማሪ የዲፕሎማቲክ ልዩ መብት ያላቸው ሰዎች እና ድርጅቶች ይኸ ቀረጥ አይመለከታቸውም። የሚሰበሰበው የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ መንግሥት የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎችንም የማኅበራዊ መሠረተ ልማቶች ለማቅረብ እና ወጪያቸውን ለመሸፈን ለሚያከናውነው ተግባር የሚል ነው።

ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሸቀጦች አምስት ዓይነት ቀረጦች ይከፈልባቸዋል። እነርሱም የጉምሩክ ቀረጥ፣ ኤክሳይዝ ታክስ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ሱር ታክስ እና ዊዝሆልዲንግ ታክስ ናቸው። በኢትዮጵያ የአዋጪነት እና የገበያ ጥናት በማከናወን እንዲሁም በታክስ ጉዳዮች ላይ የማማከር አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ የተሰማራው የመልቲሊንክ አማካሪ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ጸደቀ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ስሌት እንደሌሎቹ "ተደማማሪ" እንዳልሆነ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

BG Äthiopien Tigray | Camp
በማኅበራዊ ልማት ቀረጥ የሚሰበሰበው ገንዘብ በጦርነት እና በግጭት የወደሙ የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን መልሶ ለመገንባት እንደሚውል መንግሥት ገልጿል። የሰሜን ኢትዮጵያ ባዳረሳቸው የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት የደረሰባቸው ጉዳት ከፍተኛ ነው። ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

የኢትዮጵያ መንግሥት ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ በዓመት እስከ 20 ቢሊዮን ብር ድረስ ሊሰበሰብ እንደሚችል ተስፋ አድርጓል። ለዚህም በጎርጎሮሳዊው 2019 እና 2020 ኢትዮጵያ ከውጭ ገበያ የሸመተቻቸው እቃዎችን ዋጋ መሰረት በማድረግ ሲሰላ በዓመት እስከ 19.6 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ ሊገኝ እንደሚችል ለማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ደንብ በተዘጋጀው ማብራሪያ ላይ በማሳየነት አቅርቧል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ ግን ይኸ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ "የተወሰኑ ቢሊዮን ብሮች ሊያመጣ ይችላል። ነገር ግን የበጀት ጉድለትን በመድፈን ደረጃ የሚደርስ ነገር አይደለም። የተወነሰ ብር ይገኝበት ይሆናል። አገሪቱ ከምትፈልገው የገንዘብ መጠን አኳያ ብዙም አይደለም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ በትር ማን ላይ ያርፋል?

የኢትዮጵያ መንግሥት የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ "ምጣኔ 3 በመቶ ብቻ መሆኑ አስመጪዎች ጫናው ሳይሰማቸው ቀረጡን እንዲከፍሉ" ያበረታታቸዋል የሚል እምነት አድሮበታል። ከዚህ በተጨማሪ "የቀረጡ ማስከፈያ መሰረት የእቃው ዋጋ፣ የኢንሹራንስ እና የማጓጓዣ ወጪ ብቻ መሆኑ የቀረጡ መጠን እንዳይንር ያደርገዋል።"

"የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የሸቀጥ እጥረት ያለበት ነው። በዚያ ላይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ" የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን "ነጋዴውን ቀጥታ አይነካውም። የታክሱ በትር የሚያርፈው ተጠቃሚው ላይ ነው" ሲሉ 3 በመቶው የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ወደ ሸማቹ እንደሚሸጋገር ያስረዳሉ። አቶ አብዱልመናን "እጥረት ያለበት ኤኮኖሚ ባይሆን ኖሮ እቃዎቹ ሲወደዱ ነጋዴው ገዢ ላይኖረው ይችላል። በዚህም ነጋዴውን ሊነካው ይችላል። እጥረት ባለበት ኤኮኖሚ ግን ተጠቃሚው ነው ዋና ተጎጂ የሚሆነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በግንቦት 1999 በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ ነዳጅ ተጨማሪ ወይም ሱር ታክስ ከማይመለከታቸው ሸቀጦች ጎራ ተመድቦ ነበር። ከነዳጅ በተጨማሪ የመሬት ማዳበሪያ፣ የብረታ ብረት ቅባቶች፣ የጭነት እና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ አውሮፕላን እና የካፒታል (ኢንቨስትመንት) ዕቃዎች ሱር ታክስ ከማይከፈልባቸው መካከል ናቸው።

"ሕጉ እንደወጣ የተለያየ ስሜት ነው የተንጸባረቀው። በተለይ በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ የዕቃ ዋጋ ሊጨምር ነው። ካለው የዋጋ ግሽበት ሁኔታ፤ ካለው የኤኮኖሚ ሁኔታ አንጻር ይኸ የታክስ አይነት መምጣቱ ተጨማሪ የዋጋ ግሽበት ያመጣል የሚል አስተሳሰብ ነው ያለው" ሲሉ በገበያው የታዘቡትን አቶ ሳምሶን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

"ነገር ግን ግልጽ መሆን ያለበት ይኸ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ተግባራዊ የሚሆነው ሱር ታክስ የማይከፈልባቸው ዕቃዎች ላይ ነው እንጂ፤ ሱር ታክስ የሚከፈልባቸው ዕቃዎች ላይ እንዳልሆነ በሕጉ ተቀምጧል" የሚሉት አቶ ሳምሶን በቅርቡ የዋጋ ጭማሪ ባሳየው ነዳጅ ላይ ይኸ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ከተጣለ ተጽዕኖው ወደ ዋጋ ግሽበት ሊለወጥ እንደሚችል ጠቁመዋል። "ህብረተሰቡ ለለት ተለት ፍጆታ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ንረት ያመጣል የሚል እምነት የለኝም። ነገር ግን ምን አልባት ነዳጅ ላይ ይኸ የታክስ ዓይነት የሚጣል ከሆነ የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር ይችላል። በተዘዋዋሪ ደግሞ የዕቃዎች ዋጋ ላይ ንረት ሊኖር ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል።

Äthiopien Konsso | Wassermangel
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ የአንበጣ መንጋ በሰብሎች ላይ ያደረሰው ጉዳት እንዲሁም በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው ድርቅ ከኮቪድ ወረርሽኝ ዳፋ ጋር ተዳምሮ በኤኮኖሚው ላይ ብርቱ ጉዳት ማስከተሉን የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል።ምስል Konso Development Association

የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ለምን አስፈለገ?

ለማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ደንብ በኢትዮጵያ መንግሥት የተዘጋጀው ማብራሪያ "መንግሥት በታክስ አማካኝነት የሚሰበስበው ገቢ በመጠን ደረጃ ካለፉት ዓመታት አንጻር ሲታይ እድገት እሳያየ ቢሆንም ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ጋር ሲነጻጸር እየቀሰነ በመሔዱ መንግሥት ከወጪው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ገቢን መሰብሰብ" እንዳልቻለ ያትታል። ከዚህ በተጨማሪ በ2013 የበጀት ዓመት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ የአንበጣ መንጋ በሰብሎች ላይ ያደረሰው ጉዳት እንዲሁም በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው ድርቅ ከኮቪድ ወረርሽኝ ዳፋ ጋር ተዳምሮ በኤኮኖሚው እድገት ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድረዋል። በግጭት የወደሙ የትምህርት እና የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እና መሰል አዳዲስ ተቋማት ለመገንባት የሚያስፈልገው ወጪ መናር በመንግሥት የወጪ ፍላጎት ላይ ከፍተኛ ጫናን አሳድሯል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የማኅበራዊ ልማት ቀረጥን ሥራ ላይ ሲያውል "በቀረጥ አማካኝነት የሚሰበሰበው ገቢ በህብረተሰቡ ላይ ጫናን በማያሳድር መልኩ ከፍ የሚልበትን መንገድ" ለማመቻቸት መሆኑን ገልጿል። ከዚህ ቀረጥ የሚሰበሰበው ገቢ "የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመጠገን፤ በማስፋፋት እና በማሻሻል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲቻል" ታቅዶ ነው።

በኢትዮጵያ የነዳጅ፣ ኤሌክትሪክ እና ውኃ የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ዋጋ መጨመሩን የዋጋ ግሽበትም መበርታቱን የሚያናገሩት አቶ አብዱልመናን ግን መጪው ጊዜ "ለገበያው በጣም ፈታኝ" እንደሚሆን ያስጠነቅቃሉ። ቀረጥ የሚከፍለው የማኅበረሰብ ክፍል ቁጥር አነስተኛ መሆን እና የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱ ደካማነት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው የሚጠቅሷቸው ተጨማሪ የኢትዮጵያ ገበያ ፈተናዎች ናቸው።

ጉድለት የተጫነው የ2015 የኢትዮጵያ በጀት

"ባለፈው ሁለት ዓመት ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና ከውጪ መንግሥታት ጋር ያለን ግንኙነት ብዙም የሚያስደስት አይደለም። በዚያ የተነሳ ዕርዳታ ቀንሰውብናል። ያን ያክል ተስፋ አናደርግም" የሚሉት አቶ አብዱልመናን መሐመድ የኢትዮጵያ መንግሥት ወጪ ቆጣቢ እንዲሆን ይመክራሉ። "ወደ አገር ውስጥ ስናማትር  በጣም የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ጫና ከማብዛት ወጪ ቅነሳው ላይ ማተኮሩ ነው የሚሻለው" የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው "አሁን የሚሰሩ ፕሮጀክቶች እውነት ሁሉም አስፈላጊዎች ናቸው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።  "አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አኳያ አስፈላጊ ለሆኑት ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል። በጦርነቱ በወደሙ አካባቢዎች ህይወት የማዳን ጉዳይ ስለሆነ እሱ ላይ ትኩረት ማድረግ ነው። ገቢ መጨመሩ ላይ ብቻ ሳይሆን ወጪ መቀነሱም ላይ ነው ብዙ መሥራት ያለብን" ሲሉ አቶ አብዱልመናን ተናግረዋል።

በ2015 የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት 231 ቢሊዮን ብር የተጣራ የበጀት ጉድለት ያጋጥመዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ባለፈው ሰኔ ተናግረው ነበር። ይኸን የበጀት ጉድለት ለመሙላት የኢትዮጵያ መንግሥት 224.5 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ፤ 6.9 ቢሊዮን ብር ከውጪ አገር ብድር በመውሰድ ሊሸፍን እቅድ አለው።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ