1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የማርቲን ግሪፊትስ የኢትዮጵያ ጉብኝት ውጤት

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 30 2014

ለአንድ ዓመት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ለርዳታ ለተዳረጉ ሰባት ሚሊየን ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ ማድረግ እንዲቻል እንቅፋቶች እንዲወገዱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጠየቀ።

https://p.dw.com/p/42mgg
Schweiz Glion | Treffen zu Gefangenenaustausch mit der Schweiz
ምስል Denis Balibouse/Reuters

ለ7 ሚሊየን ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ ማድረግ እንዲቻል

ለአንድ ዓመት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ለርዳታ ለተዳረጉ ሰባት ሚሊየን ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ ማድረግ እንዲቻል እንቅፋቶች እንዲወገዱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጠየቀ። የድርጅቱ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ባደረጉት የአራት ቀናት ቆይታ በግጭቱ ተሳታፊ ከኾኑ አካላት እና አጋር ካሏቸው ድርጅቶች ጋር ፍሬያማ ያሉትን ውይይት ማድርጋቸውን ገልጠዋል። ማርቲን ግሪፊትስ የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በኢትዮጵያ የሚደረግ ጦርነት ያለቅድመ ሁኔታ እንዲቆም ያቀረቡትን ጥሪ በመድገም ተመድ የቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ለጀመሩት የሰላም ጥረት ሙሉ ድጋፍ እንዳለውም ገልጠዋል። 

በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የአስቸኳይ ርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ ከባለፈው አርብ ጀምሮ በኢትዮጵያ የነበራቸውን የአራት ቀናት ቆይታ ትናንት አጠናቀዋል። ኃላፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨመሮ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በኢትዮጵያ ስላለው የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት እና ፈተናዎቹ ላይ ገንቢ የተባለውን ውይይት ማድረጋቸውን ድርጅቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ዐስታውቋል። ግሪፊትስ በኢትዮጵያ ለድርድር ሀሳብ ጥረት እያደረጉ የሚገኙትን የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጎን ኦባሳንጆን ጨምሮ ከመንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ድጋፍ ለሚሹ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለመድረስ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መምከራቸውም ተነግሯል። በድርጅቱ የደቡብና ምስራቅ አፍሪካ ሪጅን ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አድሪያኖ አብሪዩ ለዶይቼ ቬለ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በጦርነቱ ሳቢያ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው ቀውስ አስከፊ ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ ነው፡፡ ጦርነቱ በተስፋፋባቸው አማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች በጣም አስቸኳይ እርዳታ የሚሹ 13 ሚሊየን ዜጎች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 5 ሚሊየኑ በትግራይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ የተፈናቀሉ ሲሆን ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው የመጣው፡፡ እናም የርቲን ግሪፊትዝ ሰሞኑን በግጭቱ ከተሳተፉት አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት የርዳታ ድርጅቶች ያለፈተና ለተጎጂዎች መድረስ እንዲችሉ ነው፡፡

ማርቲን ግሪፊትስ ትግራይ ክልል መዲና መቀሌ በነበራቸው የአንድ ቀን ጉብኝትም አሁን ላይ ክልሉን ከሚያስተዳድሩትና የሰብዓዊ ድጋፍ አጋሮች ካሏቸው ጋር የሰብዓዊነት መርህ ተከብሮ ለጉዳት የተዳረጉ ዜጎች የሚደገፉበት አግባብ ላይ መምከራቸውም ተገልጿል፡፡ በመቀሌ ቆይታቸው በጦርነቱ በተለይም ለጾታዊ ጥቃት የተዳረጉ ሴቶችን ጎብኝተው ተጨማሪ የምግብና መድሃኒት ድጋፍ የሚደረግበት ሁኔታ እንዲመቻች መጠየቃቸውም እንዲሁ።

ማርቲን ግሪፊትስ በቆይታቸው በአዲስ አበባ እና በመቀሌ ከባለስልጣናት ጋር ገንቢ ውይይት አድርገዋል። በዚህም ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የተሰማሩ ተቋማትና ግለሰቦች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ በግጭቱ ውስጥ ካሉ አካላት ጋር መክረዋል። አሁን ማንኛውም አይነት ሰብዓዊ ድጋፍ መዘግየቶች የህይወት ዋጋን ያስከፍላሉ፡፡ እናም ለአንድ ዓመት ያህል እና ከዚያም በታች በጦርነት ውስጥ ለቆዩት መድረስ ይጠበቅብናል፡፡  

ግሪፊትስ እሁድ መቀሌን በሚጎበኙበት ወቅት የተመድ ሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ዶ/ር ካትሪነ ሶዚ፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ስቴቨን ኦማሞ እና የተመድ ሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ሣራህ ሒዲንግ ባህርዳር ከተማ ውስጥ ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ጋር በክልሉ በደረሰው ሰብዓዊ ቀውስና ተደራሽ ማድረግ በሚቻልባቸው አግባብ ላይ መምከራቸውም በድርጅቱ የዛሬ መግለጫ ተጠቅሷል። 

ማርቲን ግሪፊትዝ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከባለስልጣናቱ ጋር ባደረጉት ውይይት በመንግስት በኩል ስለተሰጣቸው ማብራሪያም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽ/ቤት ከፍተኛ ባለሙያ ኃይለሚካኤል ዴቢሳን ጠይቀናቸው። መንግስት ከየትኛውም ረጂ ተቋማት ጋር ለመስራት አሁንም ቁርጠኛ አቋም አለው ያሉን አቶ ኃይለሚካኤል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንንም መንግሰታቸው በተቋማቱ ላይ ያላቸውን ጥያቄ ግልጽ እርገውላቸዋል ብለዋል።

እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ መረጃ ባሁን ወቅት በኢትዮጵያ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክኒያት 20 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ድጋፍን ይሻሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ 7 ሚሊየኑ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ ለቀውስ የተዳረጉ ናቸው። በኢትዮጵያ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ለእርዳታ ከተመደበው በጀት በተጨማሪነት ከ1.3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ያስፈልጋልም ተብሏል።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ