1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሽግግር ፍትሕ፣ድርቅ፣ የኦሮሚያ አስተዳደር ማሻሻያ

ዓርብ፣ መጋቢት 1 2015

የኢትዮጵያ መንግስት የፍትሕ ሚንስቴር ባዘጋጀዉ የሽግግር ፍትሕ ሰነድ ላይ የሚደረገዉ ዉይይት፣ ኢትዮጵያን በመታዉ ድርቅ የደረሰዉ ጉዳትና የኦሮሚያ ክልል ባንዳድ አካባቢዎች የጀመረዉ አስተዳደራዊ የመዋቅር ማሻሻያና የገጠመዉ ተቃዉሞ የብዙዎችን ቀልብ የሳቡ መስለዋል

https://p.dw.com/p/4OWv3
Worst drought in Borena
ምስል Seyoum Getu/DW

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ለዛሬዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ቅኝታችን ባገባደድነዉ ሳምንት የብዙዎቹን የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተከታታዮችን ትኩረት በሳቡ በ3 ርዕሶች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ቃርመናል።
የኢትዮጵያ መንግስት  የፍትሕ ሚንስቴር ባዘጋጀዉ የሽግግር ፍትሕ ሰነድ ላይ የሚደረገዉ ዉይይት፣ ኢትዮጵያን በመታዉ ድርቅ የደረሰዉ ጉዳትና የኦሮሚያ ክልል ባንዳድ አካባቢዎች የጀመረዉ አስተዳደራዊ የመዋቅር ማሻሻያና የገጠመዉ ተቃዉሞ የብዙዎችን ቀልብ የሳቡ መስለዋል።ሁሌም እንደምናደርገዉ በየርዕሶቹ ላይ ከተሰጡት አስተያየቶች ከስድብና ዘለፋ ራቅ ያሉትን ነቅሰናል። 
የኢትዮጵያ መንግስት ያረቀቀዉ «የሽግግር ፍትሕ የመርሕ ወይም የፖሊሲ አማራጮች» ያለዉ ሰነድ ባለፈዉ ሰኞ ለዉይይት ቀርቧል።የሽግግር ፍትሕ የሚለዉ ሐሳብ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉና በሚደረጉ ጦርነቶች፣ግጭቶችና ጥቃቶች የደረሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር፣ ተጠያቂዎችን ለፍርድ ለማቅረብና ተበዳዮችን ለመካስ በዉጤቱም በሐገሪቱ ዕርቅ ለማዉረድ ያለመ ነዉ።
በሰነዱ ላይ የሚደረገዉ ዉይይትና ሒደቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ትብብር እንደሚደረግ ኮሚሽኑ አስታዉቋል።Ensaro Times ግን የኢትዮጵያ መንግስትን ይወቅሳል።
«ከኢትዮጵያ መንግስት ፍትህን የሚጠብቅ ካለ እሱ የመጨረሻ ሞኝ ነው።» ይላል እንሳሮ በፌስ ቡክ። «ማስመሰል እንጅ ፍትህ የለም ።አይኖርምም።» እያለ ቀጠለም እንሳሮ።ካሳ ምርጫ ደግሞ «ኢትዮጵያ ዉስጥ የኃይማኖትን ጨምሮ ገለልተኛ ተቋም የለም።» ባይ ነዉ። እሱ የፌስ ቡክ ስሙን----የልብ አድራሽነኝ ብሎታል።አስተያየቱ ግን በተደጋጋሚ ጥያቄ የተሞላ ከይዘቱ ይልቅ በጋዜጠኞች ላይ ያነጣጠረ ነዉ።
«አሁን ደሞ የሽግግሩ ፍትህ እዛው ትግራይ ነው ዛሬም?» ብሎ ጀመረ፣ «የኢትዮጵያ ሌላው ህዝብ የሚያልቀው ዶሮ ነው? በግ ነው? ወይስ መጫወቻ ነው?» ማወቅ ያለባችሁ---- ትግራይ በውጊያ ነው ሌላው የኦነግ ጥቃትና ግጭት ለይታቹ አውሩ።» ይላል ለጋዜጠኞች ትዕዛዝ በመሰለ መልዕክቱ።
የልብ አድራሽ ነኝ፣ ለትክክለኛ መረጃ እባክሕ ዶቸ ቬለን እድምጥ።ብለነ አለሙ በፌስ ቡክ ረዘም ያለ አስተያየት ነዉ የሰጠዉ።ገሚሱን እነሆ።----«ከማን አገዛዝ ወደማን ነውየተሸጋገርነው?» ጠየቀ ብለነ ዓለሙ---በዚሕ አላበቃም።«የተጓደለውስ ፍትህ የሚታየው በህውሃት አገዛዝ ዘመን የተፈፀመው ነው? ወይስ ኦሮሙማ የፈፀመው ህውሀትን ያስናቀውን ግፍና በደል ነው?» የብለነ ጥያቄ አዘል አስተያየት ነዉ።
ልዑል አለማየሁ ደግሞ ለኢትዮጵያ ፖለቲከኞችም በሰነዱ ላይ ለተወያዩት ለሲቪል ማሕበራትም ምሕረት ያለዉ አይመስልም«ኢትዮጵያ ውስጥ አፋኝና ጨፍጫፊ ስርአት እንጂ ዴሞክራሲያዊ ሰርአት የለም።» አለ ልዑል በፌስቡክ «ያሉት ሲቪክ መሀበራትም  ቁራ ናቸው።» እያለ ቀጠለ።
                               
በሶማሌ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች እስከ አራት ዓመታት ለሚደረስ ተከታታይ ዓመት ዝናብ በመሳቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት አልቀዋል።እስከ 25 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ለምግብ እጥረት ተጋልጧል።
የኢትዮጵያ የፌደራልና የክልል መንግስታት የተባበሩት መንግስታትና ሌሎች ግብረሰ ሰናይ ድርጅቶች እንዳስታወቁት ቦረና፣ጉጂ፣ ሐረርጌ፣ ኦሞ ዞኖችንና አብዛኛዉን የሶማሌ ክልልን ባዳረሰዉ ድርቅ ከ3 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት አልቀዋል።ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት እተሰቃዩ ነዉ።
ችግረኛዉን ሕዝብ ለመርዳት የኢትዮጵያ መንግስት፣የዉጪ ድርጅቶችና ኢትዮጵያዉያን በግልም፣በቡድንም የሚያደርጉት ድጋፍ እንደቀጠለ ነዉ።ይሁንና ለአደጋ ለተጋለጠዉ  ሕዝብ በሙሉ ርዳታ ማድረስ እስካሁን አልተቻለም።ድርቁ የደረሰበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ትኩረት የተነፈገበት ምክንያትም እያነጋገረ ነዉ።
ክብረት ሞገስ ከድርቁ ይበልጥ የሚያሳስበዉ የኢትዮጵያ መንግስት «ሥራና አሰራር ነዉ» ባይ ነዉ።«ከድርቁ በላይ የመንግሰታዊ ሸፍጥ፣ የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ እየጣለ ነው።» ክብረት ሞገስ በፌስ ቡክ የሰጠዉ አስተያየት ነዉ።Kevin Toro-------ረዘም ያለ ትችት ነዉ የሰነዘረዉ።
«የ27ት የጭለማ ዘመንን ስታማርሩ እግዜር የ3 አመት የጭለማ፣ የረሃብ፣ የግድያ፣ ሰው መጥለፍ ሌላም ሌላም።» እያለ ቀጥሏል።ከዚሕ በላይ ያለዉን አንደግመዉም።
ሙሉጌታ ኃይሌ፣-በድርቅ ለተጎዱት ጊዚያዊም ቢሆን ርዳታ መሰጠቱ ጥሩ ነዉ ባይ ነዉ።ግን ይሁንና ብሎ ቀጠለ «አሁን ያለው የብልጽግና መንግስት በሀይማኖትና በብሔር በሽታ ከመጠመድ በስተቀር ህዝቡ በረሃብም በጦርነትም ቢያልቅ ምንም የማይሰማውና አፌ ቅቤ ብቻ ነው።»ይልና መፍትሔ ብጤም ይጠቁማል « በእውነቱ ምናለበት አድስ አበባ ዙርያ በየቀኑ አበባዎችን ተከልን ከሚሉት ፉከራ ለቦረና ህዝብ የጉድጓድ ውሃ ቢያስቆፍር ባይ ነኝ።» 

Äthiopien Addis Ababa | Nationales Konsultationsprogramm
ምስል Solomon Muche/DW
Äthiopien | Ein Hirt geht mit einem Kamel spazieren
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images

ተሾመ ክብሩ የሚተች፣የሚወቅሰዉ ምድራዊ ኃይል የለም።ፈጣሪዉን ግን ይጠይቃል።በፌስ ቡክ 
«በእውነት አምላክ ፈጣሪ የለም?» ጠየቀ ተሾመ።መልስ የለንም።በ1977 ድርቅ ክፉኛ የተጎዳ የሰሜን ሸዋ ገበሬ «ጣዩ የልሕ የልሕ፣ ጥናቡ የልሕ የልሕ----ታርስበትም እንደሁ ቅብቅቡ ያዉልሕ» ብሎ ነበር አሉ።በምሬት።
ሶስተኛዉና የመጨረሻዉ ርዕሳችን ላይ ደርሰናል።የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኘዉን የክልሉን የቀድሞዉን ልዩ ዞን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የአስተዳደር መዋቅራዊ ለዉጥ አድርጓል።ለዉጡ ለአስተዳደርና ከተሞችን ለማገናኘት ጠቃሚ ነዉ ቢባልም በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖረዉ ሕዝብ አልተቀበለዉም።
የአንዳድ አካባቢ ነዋሪዎች ቅሬታቸዉን በአደባባይ ሰልፍ ሲገልጡ ነዉ የሰነበቱት።በተለይ በጉጂ ዞን በተለያዩ ከተሞች ለተቃዉሞ አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ተጋጭቶ በትንሹ አራት ሰዎች ተገድለዋል።
ተስፋዓለም መሓሪ ወልደሩፋኤል በፌስቡክ ምክር ብጤ ይለግሳል።«ነገሮች ቶሎ ካልተስተካከሉ በስተቀር የከፋው ቀጥሎ ሊመጣ ይችላል ብዬ አስባለሁ።» ይላል።«ሰላም አማራጭ የለውም-----ሰላም ከሌለ ሰው ምንም ማድረግ አይችልም» 
ሕይወት ታደሰ በተቃዉሞዉ ሰበብ መንገዶች መዘጋታቸዉን ትቃወማለች።«ብትዘጉት የራሳችሁን ሰው ነው ምትጎድት፤ ኣብይ (ጠቅላይ ሚንስትር) የሚጎዳ እንዳይመስላችሁ። የራሳችሁ ህዝብ ነው የምጎዳዉ» ባይ ናት።ሸዋ ጌች ካሳ በተለይ አዲስ አበባ አጠገብ ሸገር ከተማ መቆርቆሩን ይተቻል።«ድሮም ሲታቀድ ከኦሮሞ ውጭ ያሉትን ህዝቦች ከሸገር ከተማ ለማስወጣት ስለሆነ ሰው መቸገር አይደለም ቢያልቅም አይገደዉም» ይላል። 
መሐመድ አብደላ «የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ-መስተዳድር «ሽመልስ አብድሳ ጉጂን ኦሮሞ አይደለም።ኦሮሞ አሩሲና ባሌ ነው ብለዉ የተናገሩትን የጉጂ ኦሮሞ መቼም አይረሳውም።» ይላል።ሐብታሙ ያዴ ብሩ ግን ለመሐመድ አብደላ መልስ ብጤ አለዉ።«እሺ ሌላስ» ይላል ሐብታሙ መሐመድን---ለጠቅ አድርጎ «አያልቅበት» የሚል አከለበት።
ጌታቸዉ ማሞ ደግሞ «የመንግስታችን ልዩ ችሎታ» ብሎ ጀመረ «ኢንተርኔትን መዝጋት ነው። ሌላ ብዙ የሚታይ ነገር የለም ሲሉ ሰማሁ» እያለ ይሸረድዳል።  

Äthiopien Flüchtlinge in Oromia Region
ምስል Seyoum Getu/DW

ነጋሽ መሐመድ ነኝ

ሸዋዬ ለገሰ