1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ኅዳር 23 2015

በያዝነዉ ሳምንት ግጭት ጥቃቱ የባሰዉ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳና አካባቢዉ ነዉ።ከጥቃቱ ያመለጡ ነዋሪዎች እንደሚሉት በተደጋጋሚዉ ግጭትና ጥቃት በመቶ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።በትንሽ ግምት 52 ሺሕ ሕዝብ ከየቀየዉ ተፈናቅሏል።አብዛኞቹ ተፈናቃዮች የአማራ ተወላጆች ናቸዉ

https://p.dw.com/p/4KOP7
Äthiopien Vertriebene aus Wollega in Bahir Dar angekommen | Hauptstadt der Amhara-Region
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የወለጋ ቀዉስ፣የዩኒቨርስቲ መምሕራን አድማ እና እግር ኳስ

በኦሮሚያ ክልል የሚደረገዉ ግጭት፣ጥቃት፣ግድያና ማፈነቃል፣ የኢትዮጵያ የዩኒቨርስቲ መምሕራን ጠሩት የተባለዉ አድማና ዉዝግቡ፣ በዓለም እግር ኳስ የዋንጫ ግጥሚያ የአፍሪቃ ቡድናት ተሳትፎና ዉጤትን በተመለከቱ ከተሰጡ አስተያየች ከስድብና ዘለፋ የፀዱትን ነቅሰን አዉጥተናል።
በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞኖች በሸመቁ ታጣቂዎችና በመንግስት የፀጥታ አስከባሪዎች መካከል የሚደረገዉ ግጭት፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት፣ግድያና ማፈናቀል መሰንበቻዉንም እንደቀጠለ ነዉ።
በያዝነዉ ሳምንት ግጭት ጥቃቱ የባሰዉ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳና አካባቢዉ ነዉ።ከጥቃቱ ያመለጡ ነዋሪዎች እንደሚሉት በተደጋጋሚዉ ግጭትና ጥቃት በመቶ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።በትንሽ ግምት 52 ሺሕ ሕዝብ ከየቀየዉ ተፈናቅሏል።አብዛኞቹ ተፈናቃዮች የአማራ ተወላጆች ናቸዉ።በእግር መጓዝ የቻሉና የተሳካላቸዉ ተፈናቃዮች አማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ ደርሰዋል።እስካለፈዉ ማክሰኞ ድረስ ግን ባሕርዳር ከተማ ዉስጥ  ሜዳ ላይ የፈሰሱት ተፈናቃዮች የሚረዳቸዉ አለማግኘታቸዉን አስታዉቀዋል። 
ወርቁ አዲሱ «ትክክል» አለ በፌስ ቡክ « ብዙ ሺዎች ተፈናቅለዋል።ሞተዋል። ቆስለዋል። ንብረት ወድሟል፤ተዘርፏል ።» እያለ ቀጠለና « የሚያሳዝነው ደግሞ ከጥቃቱ የተረፉት ሰብአዊ ድጋፍ ማጣታቸው ነው» ብሎ አሳረገ ወርቁ አዲሱ።
Tramp Putin የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ አስተያየት ሰጪ ለጥቃቱ የኢትዮጵያ የፌደራልና የኦሮሚያ መሪዎችን ተጠያቂ ያደርጋል።«ኦነግ ብልፅግና በድብቅ ብዙ ሸኔን አሰልጥኖ ኦሮሞ ያልሆነን ብሄር የማስገደልና የማፈናቀል ስራ እየሰራነው።» የትራምፕ ፑቲን አስተያየት ነዉ።ግን «ማስገደል፣ማፈናቀል» የሚባል ስራ አለ ይሆን? ጥያቄዉ የኛ ነዉ።አስተያየት ሰጪዉ ቀጠለ «ባንኮችንም እያዘረፈ ነው፤እስከ 20/3/2015 ድረስ ኦነግ ሸኔ ሙሉ ወለጋንና አሩሲን በከፊል እየዘረፈ ነው።» 
ያሲን ኢስላም ----አስተያየትን ከጥያቄ በቀየጠ የፌስ ቡክ ፅሁፉ እንዲሕ ይላል «ይኸን ማስቆም ለምን አልተፈለገም? አላማቢስ ኦነግ ንፁሀንን ሲገድል ምን ታስቦ ነው?» የያሲን ኢስላም ጥያቄ ለበስ አስተያየት ነዉ።
ከድር ተገኝ «የኦሮሚያ ግፍ ሞልቶ እየፈሰሰ ነው ...ይሄን አስከፊና አሰቃቂ በደም እየተፃፈ ያለ ጥቁር ታሪክ መንግስት ትኩረት ከመንፈጉም በላይ እጁ ያለበት እስኪመስል ድረስ ህዝብን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል!» ከድር ተገኝ ነዉ እንዲያ ባዩ። 
ወርቅነሕ ጌታዬ «ኦነግ ሸኔም፣ ኦሕዴድም ተጠያቂዎች ናቸዉ» ባይ ነዉ።ከቡልጋሪያ ማ። ይላል አስተያየት ሰጪዉ።ጋራሚ ዳክሳ «የኦሮሚያ አይታያችሁም ግን?» ጠየቀ።
ዘሉሜ ዎል «አልሞት ያሉ ፣ መንግሥት እንደችግር የሚያያቸው፣ ዘራቸው፣ ድህነታቸው ሐጢያት የሆነባቸው» ይላል በፌስ ቡክ። 
ክብር ለሐገሬ  በበኩሉ ከረጅም ርቀት ጉዞ፣ ከብዙ መከራ፣ድካም፣ ብዙ ወዳጅ ዘመዶቻቸዉ በየጫካ ፈፋዉ ቀርተዉባቸዉ ባሕርዳር ለደረሱ ተፈናቃዮች የአማራ ክልል ባለሥልጣናት በቂ እርዳታ አለመስጠታቸዉን ይጠይቃል።«የአማራ ክልል አመራሮች ወገኖቻችን እደዚህ ሲንገላቱ ሜዳ ላይ ፈሰው ስታዩ ምን ተሰማችሁ?፡»
ባለስልጣናቱ በጋራ ወይም በተናጥል የተማቸዉን በርግጥ አናዉቅም።የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን አንዲት ባለስልጣን ግን መስሪያ ቤታቸዉ «ተፈናቃዮችን እየረዳ ነዉ» ማለታቸዉን ባለፈዉ ማክሰኞ ዘግበናል።
አሞራው ምንአለ ባሻ----- በፌስ ቡክ «እንዲሕ ሚዛናዊ መሆን መልካም ነዉ» ይላል ዘገባዉን መሰለን።

Äthiopien Studierende Tigray Universität
ምስል Solomon Muchie/DW

                                               
ለበርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያ በጣሙን ከከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት ብዙም የማይሰማዉ የስራ ማቆም አድማ ዝግጅት ወይም ጥሪ ዜና በያዝነዉ ሳምንት ከወደ አዲስ አበባ  ተሰምቷል።በዘገባዉ መሰረት የኢትዮጵያ የዩኒቨርስቲ መምሕራንና የቴክኒክ ሰራተኞች ረጅም ጊዜ ያስቆጠረዉ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄያቸዉ መልስ እንዲያገኝ  ለፊታችን ሰኞ የስራ ማቆም አድማ ለመምታት አቅድዋል።
የዩኒቨርስቲ መምሕራንና የቴክኒክ ሰራተኞቹ አድማዉን የጠሩት የሐገሪቱ የትምሕርት ሚንስትር ብርሐኑ ነጋ መንግስታቸዉ ለመምሕራን የደሞዝ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችል ለሐገሪቱ ምክር ቤት ባቀረቡት ዘገባ ባስታወቁ ማግስት ነዉ።ይሁንና አድማዉ ገና ከጥሪና ምናልባትም ከዝግጅት ባያልፍም  አድማዉን ለማድረግ የሚሹትና የዩኒቨርስቲ መምሕራን ማሕበር እየተወዛገቡ ነዉ።
የማሕበሩ መሪዎች አድማዉን አልጠራንም፣ ማደምም አያስፈልግም ባይ ናቸዉ።መምሕራኑ ግን ተቃራኒዉን።የቴዎድሮስ ታከለ አስተያየት የማህበሩን አቋም የሚጋራ ይመስላል።«በአግባቡ ጥያቄን ማቅረብ ሲቻል ስራ ማቆም አድማ መጥራት  ውጤቱ ጥሩ አይሆንም !!!» ይላል ቴዎድሮስ አስተያየቱን ያሳረገዉ በሶስት ቃል አጋኖ ነዉ ። አስተዉል ተካበ---- በፌስ ቡክ «ገረመኝ» ይላል «አይ መምህራን ተማርን የምትሉ ሠወች ግን ግርም ነው የምትሉኝ።»
ጋሶ አርካሌ አያኖ---ምርር ያለዉ ይመስላል።«እና ምን ይሁን?» ጠየቀ በእንግሊዝኛ ባሰፈረዉ አስተያየት «እኛ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ተቋማት መምሕራን በሐሰተኛዉ በፌዴሪኢ የትምሕርት ሚንስቴርና በCSC ሐሰተኛ አስተዳደር ተጨቁነናል፤ ሞራላችን ተነክቷል፣ ተጎድተናል----ብዙ ጊዜ ጠይቀናል፣ ሺሕ ጊዜ ጮኸናል ግን ማንም ለኛ ደንታ የለዉም።እና ለጥያቄያችን መልስ ለማግኘት ምን እናድርግ። የመጨረሻዉ አማራጭ የሥራ ማቆም አድማ ነዉ።» አለቀ ረጅሙ የጋሶ አርካሌ አያኖ አስተያየት።
መከተ ላስታ ወሎ- ኢትዮጵያ---- እሱም በፌስ ቡክ «ጥያቄዎቻችን የመኖር ያለመኖር የዳቦ ጥያቄዎች ናችው። ሁሉን ነገር ከፖለቲካ ጋር በማያያዝ ሸፋፍኖ ማለፍ አይቻልም።» ይላል።ይሕኑኑ አስተያየት 14 ጊዜ ለጥፎታል።መሐመድ ሰዒድ «ማህበር ህብረት ምናምን የሚባል ነገር የለም፤አድማ የሚያደርገዉ የህልዉና አደጋ የተጋረጠበትና በመንግሥት ቸልተኝነት እየተጎዳ ያለዉ መምህር እንጅ የማንም ፍርፋሪ እንዳይቀርበት ካልኩሌሽን እየሰራ የሚንቀሳቀሰዉ አካል አይደለም» የመሐመድ ሰዒድ አስተያየት ነዉ።አባትሁን ዋሴ----«በልመና የሚሆን ነገር የለም» ይላል።እንዳለማዉ ክንዴ---ደግሞ «ምንታመጣላችሁ» ዓይነት ባይ ነዉ-በፌስ ቡክ «ጠርተናል።ጠርተናል።መቶ ነጥብ» አለና «በልመና መብት ማስከበር አይቻልም» አከለበት።
ጀስቲስ ኢትዮጵያ ግን ያስፈራራል «ወንድ።አቁሙና እናያለን።» መልካሙ አንተነት ግን በተቃራኒዉ «በርቱ» አለበፌስ ቡክ።
ዉዝግብ፤ክርክር፤ አስተያየቱ ቀጥሏል።አድማ መደረግ አለመደረጉ የሚለየዉ ግን ያዉ የቀጠሮዉ ቀን ነዉ።የፊታችን ሰኞ።
                                         
የመጨረሻዉ ርዕሳችን ላይ ደርሰናል።ቀጠር የተያዘዉ የዓለም እግር ኳስ የዋንጫ ግጥሚያ የምድብ ማጣሪያ እንደቀጠለ ነዉ።ይሕን ዝግጅት እስካጠናቀርንበት እስከ ትናንት ድረስ ለ11 ቀናት ቀናት በተደረጉ ግጥሚያዎች አፍሪቃን የወከሉት 5 ቡድኖች ጥሩ ተፎካካሪ መሆናቸዉን እያስመሰከሩ ነዉ።
በያዝነዉ ሳምንት  ሰኞ ካሜሩን ከሰርቢያ ጋር ገጥሞ 3 አቻ ተለያይተዋል።የዚያኑ ቀን የጋና ብሔራዊ ቡድን የደቡብ ኮሪያ ባላጋራዉን 3-ለ-2 ቀጥቷል።
ዳዉድ አብራር----በፌስ ቡክ «እዉነትም ብላክ ስታር» በማለት ያደንቀዋል።አንተነሕ ተዉኔ ደግሞ-----«የአፍሪቃ አለኝታ» ብሎታል የጋንና ቡድን።
ምድብ ሀ ላይ የሚገኘዉ  የሴናጋል ቡድን ወደ ቀጣዩ ግጥሚያ ማለፉን አረጋግጧል።የአፍሪቃ ዋንጫን አምና የወሰደዉ የምዕራብ አፍሪቃዊቱ የሴኔጋል ቡድን ባለፈዉ ማክሰኞ ደቡብ አሜሪካዊቱ ኤኳዶርን  2-ለ-1 አሸንፏል።
ሀና የናቷ ቀበጥ---- በፌስ ቡክ «እኔ መቼም የሴኔጋል ተጨዋቾችን ሳይ ኢትዮጵያን ነው እሚመስሉኝ» አለች በኢትዮጵያ ባንዲራ ባዥጎረጎረችዉ አስተያየት።  ካሳሁን አማረ «አፍሪቃ» አለ።በቃ  ሌላ አላለም።   ማፊ ሚፊ «ትክክል፣ አደረጋችሁት» በእንግሊዝኛ እና በፌስ ቡክ።
ዘር ለገበሬ ብቻ----የፌስ ቡክ ስም ነዉ።«ክብር ለአፍሪካ።የጀግኖች መፍለቂያ ማሸነፍ ግድ ነው» እያለ አደነቀ።

ሞሮኮዎች ከእግር ኳስ ድል በኋላ
ሞሮኮዎች ከእግር ኳስ ድል በኋላምስል PATRICK T. FALLON/AFP


ማት ኤል ኤም በእንግሊዝኛ በሰጠዉ አስተያየት «አልዩ ሴሴ በኮሪያ-ጃፓን የዓለም ዋንጫ ወቅት እንደተጫዋች ያስመዘገበዉን አሁን በቀጠሩ የዓለም ዋንጫ እንደ አሰልጣኝ ደገመዉ» ይላል ማት ቀጠለም።«ከሁለት አስርታት በኋላ ታሪክ ራሱን ደገመ።ሴኔጋል እንኳን ደስያለሽ።አፍሪቃ እንኳን ደስ ያለሽ» የማት ኤል ኤም መልካም መግለጫ ነዉ።
ባለፈዉ ሮብ በተደረገዉ ግጥሚያ ቱኒዚያ የዓለም ዋንጫ ባለቤቱን ፈረንሳይን 1-ለ-0 ብታሸንፍም ለሚቀጥለዉ  ግጥሚያ ማለፍ አልቻለችም።ሞሮኮ ትናንት ሐሙስ ካናዳን 2-ለ-1 አሸንፎ ወደቀጣዩ ግጥሚያ ባስተማማኝ ዉጤት አልፏል። ይሕን ዘገባ እስካጠናቀርንበት እስከ ሀሙስ (ትናንት) አመሻሽ ድረስ  ጋና ወደቀጣዩ ግጥሚያ የማለፍ ሰፋ ዕድል አለዉ።
የካሜሩን የማለፍ ተስፋ ግን ከጠንካራ ግጥሚያ በላይ ተዓምር ብጤ ሳያስፈልገዉ አይቀርም።ለዛሬ ይብቃል።

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ