1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ መስከረም 20 2015

በኤሌክትሪክ ኃይል በሚሽከረከሩ መኪኖች ላይ የቀረጥ ቅናሽ፤ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም እንዲያበቃ የተደረጉ ጥሪዎችና በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በተለይም ኡሙሩ ወረዳ በሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ታጣቂዎች የሚፈፅሙትን ግፍ መንግስት እንዲያስቆም የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማሳሰቡን የሚጠቅሱ ዘገቦች ናቸዉ-ትኩረታችን።

https://p.dw.com/p/4HbsK
Symbolbild Apps Facebook, Google und Google + Anwendungen
ምስል Imago Images/P. Szyza

የኤሌክትሪክ መኪኖች ታክስ፣ የኢሰመኮ ማሳሰቢያ፣ የሰላም ጥሪ


ጤና ይስጥልኝ እንደን ዋላችሁ።በያዝነዉ ሳምንት በርካታ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተከታታዮች አስተያየት ከሰጡባቸዉ ርዕሶች ሶስቱን መርጠናል።የኢትዮጵያ መንግስት በኤሌክትሪክ ኃይል በሚሽከረከሩ መኪኖች ላይ ያደረገዉ የቀረጥ ቅናሽ፤ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም እንዲያበቃ የተደረጉ ጥሪዎችና በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በተለይም ኡሙሩ ወረዳ በሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ታጣቂዎች የሚፈፅሙትን ግፍ መንግስት እንዲያስቆም የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማሳሰቡን የሚጠቅሱ ዘገቦች ናቸዉ-ትኩረታችን።
እንደተለመደዉ ለከት የለሽ ስድብ፤ዉንጀላና ማኪኪያሶችን ነቅሰን እየጣልን በየርዕሶቹ ላይ የተሰጡ የየሰከኑ አስአስተያየቶችን በየተራ እንቃኛለን ከቻላችሁ አብራችሁን ቆዩ።
የኢትዮጵያ መንግስት በኤልክትሪክ ኃይል በሚሽከረከሩ መኪኖች ላይ የ15 ከመቶና የ5 ከመቶ የቀረጥ ቅናሽ አድርጓል።የገንዘብ ሚንስቴር «የነዳጅ ዋጋ ንረትንና የአየር ንብረት ብክለትን ለመቀነስ» ባለዉ ማሻሻያዉ ሐገር ዉስጥ የተገጣጠሙ የኤሌክትሪክ መኪኖች 15 ከመቶ፣ ከዉጪ የሚገቡ ደግሞ 5 ከመቶ ቀረጥ ይቀነስላቸዋል።
የቀረጥ ቅናሹ ዜና በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታዮች ዘንድ አወንታዊም አሉታዊዉም ምላሽ አግኝቷል።
ኬ አሚ የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ ወይም ያላት አስተያየት ሰጪ ግን ከቀረጡ ቅናሽ ይልቅ ስለቅናሹ አስተያየት የሰጡ ሰዎችን ይተቻል።«በቃለ መጠይቁ የተካተቱ ሰዎች ሁሌም መጥፎዉ ነገር ብቻ የሚናገሩ ጨለምተኞች ናቸዉ» ይላል ወይም ትላለች ኬ አሚ በእንግሊዝኛ-----በመሠረቱ አስተያየት የሰጡት ሰዎች ለዶቼ ቬለ አንዴ እንጂ ሁሌም የሚናገሩትን ዶቼ ቬለ አያዉቅም----ኬ አሚ ግን ቀጠለ ወይም ቀጠለች------«ደሕና፣ ይኽ ለሁሉም አይደለም።---ይሕ ስለወደፊቱ ማሰብ ነዉ» እያለ።
ናማ ኬንያ እሱም በፌስ ቡክ  ምሳሌ የጠቀሰበት ምፀት መሰል ጥያቄ አለዉ።«ለምሳሌ» ይላል ናማ «ከአዲስ አበባ ሻኪሶ መሔድ ብፈልግ ሻኪሶ ላይ 8 ሰዓት ቆይቼ ቻርጅ ማድረግ አለብኝ ማለት ነዉ?» 
ዑመር ፈድሉም ተቀራራቢ ጥያቄ ለበስ አስተያየት አለዉ።« በየትኛዉ ኤሌክትሪክ ቻርጅ ሊደረግ ነዉ» የሚል።
ላንካሞ ዋይ መሰለ ግን የኤሌክትሪክ እጥረት ወይም የመንገድ መጥፎነት ችግር አይደለም ባይ ነዉ።የመኪና ዋጋ እንጂ «ችግሩ ያለዉ መብራትና መንገድ ላይ ሳይሆን የመኪና ዋጋዎቹ ላይ ነዉ» ላንካሞ ነዉ ይኽን ባዩ።
ሱዳን አል ዋዲ ኡንዱሩማን የሚል በሱዳን የተንቆጠቆጠ የፌስ ቡክ ስም ያለዉ ወይም ያላት አስተያየት ሰጪ «ጉረኞች ይላል» እና ይጠይቃል።«እንዲያዉ እንደ ኢትዮጵያ ጉረኛ ሐገርና ሕዝብ ዓለም ያላት አይመስለኝም» ይልና አከል አድርጎ «ለምን ብትሉ ችግራችን ይኼ ነዉ?» የሱዳን አልዋዲ ኡዱሩማን አስተያየት ነዉ።
የኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥትና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በዋናነት የገጠሙት ጦርነት ዓመት ሊደፍን ሶስት ሳምንታት ቀሩት።በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሕይወት የጠፋበት፣ሚሊዮኖች የተፈናቀሉ፣ ለረሐብ የተጋለጡበት፤ በቢሊዮን ብር የሚገመት ሐብት ንብረት የወደመበት ጦርነት እንዲቆም በተደጋጋሚ የሚደረገዉ ጥሪ እስካሁን ሁነኛ መልስ አላገኘም።ተፋላሚዎች ዉጊያዉን አቁመዉ ጠባቸዉን በድርድር እንዲፈቱ የሚደረገዉ ጥረትና ጥሪ ግን አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።
በአብዛኛዉ ዋና መቀመጫቸዉን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረጉ የተለያዩ ኢትዮጵያ ነክ የሲቢል ማሕበራት በያዝነዉ ሳምንት በሰጡት መግለጫ ደግሞ ሰላም ለማዉረድ በሚደረገዉ ድርድር ከዋንኞቹ ተፋላሚ ኃይላት በተጨማሪ በጦርነቱ የተጎዱት የአማራና የአፋር ክልል ነዋሪዎች ተወካዮች እንዲካፈሉ ጠይቀዋል።
አንዱዓለም ታምሩ፣ የሲቢል ማሕበራቱን ጥያቄ «ጥሩ ነዉ» ብሎታል። ባናና ጆም ከአንዱዓለም ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ አለዉ «አፋርና አማራ ክልል የሌለበት ድርድር ዋጋ የለዉም» የሚል።
አሾ ቱራ ቦኮሬ በበኩሉ ምንም ተደርጎ ቢሆን ብቻ ሰላም ባስቸኳይ ይዉረድ ባይ ነዉ።«የሚደራደረዉ ተደራድሮ እባካችሁ እንደምንም ሰላም አምጡ። እኛ ኑሮ አቅቶናል።ሰዉ በድሕነት ማለቁ ነዉ» የአሾ ቱራ ቦኮሬ አስተያየት ነዉ።----ሹሜ ሰይፉ ግን የድርድር ጥያቄ-የሰላም ጥሪዉም ብዙ ያሳሰበዉ አይምስል።«አፋር ከአማራዉ ጋር ዉሕደት ቢፈጥር ጥሩ  ነበር» ነዉ የሚለዉ-ሹሜ ሰይፉ 

የኤሌክትሪክ መኪና
በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ መኪናምስል AP

ኢዮብ ፓዎል በፌስ ቡክ «እራሳቸዉን ችለዉ ነበር እንዴ የተሳተፉት» ይላል ክልሎቾቹን።---የአሰፋ ኢሳያስም አስተያየት ከኢዮብ ጋር ተመሳሳይ-እና በጥያቄ የተዋዛ  ነዉ።«ኢትዮጵያ ወዴት ሄዳ ነዉ አፋርና አማራ የሚወከሉት?»
ዳኒ ጌራ ሚካሌ ግን----- «ኬኬኬኬ» ብሎ ጀመረ ፅሁፉን በፌስ ቡክ ሳቅ-መሆኑ ነዉ።ስላቅ ብጤ። «ድርድሩ ለትግራዋይ እና የኢትዮጵያ፣የኤርትራ፣የዓረብ ኤሚሬት እንጂ ትግራይ ከክሎች አትደራደርም» ብሎ አረፈዉ ዳኒ ጌራ ።ዓለምነዉ ደረሰ  የኢትዮጵያ መንግስትን ይመክራል-በፌስ ቡክ እንዲሕ እያለ።«የ(ጠቅላይ ሚንስትር) ዓብይ መንግስት አካሔዱን ቢያስተዉል ጥሩ ይመስለኛል።» ምክንያትም አለዉ።«ሞቱ፣መፈናቀሉ፣ብልሹ አሰራሩ----- የጥቁር ሸማ ሐገር ሆናለች።» የሚል ምክንያት። 
ስመኘዉ የስላሴ ልጅ እንደሚለዉ እሱ ሌላ ነገር አይፈልግም።«ፍትሕ ለራያ ቆቦ ሕዝብ» ይላል በሶስት ቃለ አጋኖ ባጀበዉ አስተያየቱ-----ቀጠለና  «ወሬ አንፈልግም» ብሎ አሳረገ።ወደ ሶስተኛዉ ርዕሳችን እንለፍ።
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈዉ ሰኞ ባወጣዉ መግለጫ መንግስት በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን የሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎችን ደሕንነት የማስጠበቅ ግዴታዉን እንዲወጣ አሳስቧል።ኮሚሽኑ እንደሚለዉ በሆሩ ጉድሩ ወለጋ ዞን በተለይ ኡሙሩ ወረዳ ዉስጥ ታጣቂዎች በብሔር እየለዩ ሰላማዊ ሰዎችን መግደል፣ማቁሰል መዝረፍና ማፈናቀላቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።ካለፈዉ ነሐሴ 25 ወዲሕ ብቻ ከ100 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸዉን ኮሚሽኑ ገልጧልም።
ዮናስ ሚናሴ---- በፌስ ቡክ የሰላማዊ ሰዎችን ጩኸት የሰማ የለም ይላል።«የድረሱልን ጥሪ ሲያሰሙ ማን ዞር ብሎ አያቸዉ።ሰማቸዉ።» ይላል ይቀጥላልም።ዳንኤል ማኒ በበኩሉ «ይገርማል አማራን ጨረሱት» አለ።ነፃነት ገቢሳ ግን በእንግሊዝኛ ተቃራኒዉን ነዉ የሚለዉ።«የወለጋ ኦሮሞን ከምድረ ገፅ ማጥፋት የብልፅግና እና የነፍጠኛ ምኞት ነዉ ----» የነፃነት ገቢሳ አስተያየት ነዉ።ቀጥሏልም።
በላይ ማሞ «ፊታችንን ከሕወሓት ወረራ እንድንመልስ የተጀመረ ሴራ ነዉ» መግለጫዉን ይሁን፣ ግድያ ማፈናቀሉን  ወይም ለመንግስት የቀረበዉን ጥሪ ይሆን የሚያዉቀዉ ያዉ ፀሐፊዉ ነዉ።ካሳ ምርጫ «በድሮን ሲቪሊያን ሲጨፈጨፉ ግን ትንፍሽ ብሎ እያዉቅም» በማለት ኮሚሽኑን ይወቅሳል። መሐመድ ለገሰ ዓሊ «መፍትሔ ያጣ ጉዳይ ነዉ» አለ ትክት-ስልችት ያለዉ ይመስላል።በርይሁን ደባልቀዉ ደግሞ «እኛ ለዉጥ እንጂ መች መግለጫ ፈለግን» ባይ ነዉ።ብሎ ፃፈ።
ነጋሽ መሐመድ

የወለጋ ተፈናቃዮች
አዲስ አበባ የተጠለሉ የወለጋ ተፈናቃዮችምስል Solomon Muchie/DW

ታምራት ዲንሳ