1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ጥቅምት 19 2014

ከሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ተፈናቅሎ ደሴ ዉስጥ የተጠለለዉ ወይም መጠለያ የሚፈልገዉ ሕዝብ ብቻ 750 ሺሕ እንደሚደርስ የአካባቢዉ ባለስልጣናት ይገምታሉ። ደሴ ለሚገኙት ተፈናቃዮች  ርዳታ መከፋፈሉ ቢዘገብም፣ርዳታዉ ለተፈናቃዮቹ በቂ እንዳልሆነ፣ ጨርሶም ርዳታ ያያልደረሳቸዉ መኖራቸዉን ተፈናቃዮቹ በተደጋጋሚ ይናገራሉ

https://p.dw.com/p/42LWt
Sudan Putsch Protest Ausschreitungen
ምስል AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ ጦርነት፣ የደሴ ተፈናቃዮች፣ የሱዳን ፖለቲካዊ ቀዉስ

ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።በዛሬዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የብዙዎችን ትኩረት በሳቡ  ሶስት ርዕሶች ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች የጎሉትን ቃርመናል።አብራችሁን ቆዩ።
                             
በኢትዮጵያ መንግስት ጦር እና በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ታጣቂዎች መካከል የሚደረገዉ ዉጊያ፣ የኢትዮጵያ ጦር የሕወሓት የጦር መሳሪያ ማምረቻ፤ ማከማቻና የወታደር ማሰልጠኛ ያላቸዉን አካባቢዎች በጦር ጄቶች መደብደቡን የሚያወሱ ዘገቦች ብዙ አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል።በሳምንቱ አጋማሽ የሕወሓት ባለስልጣናት ደሴ፣ኮምቦልቻና አካባቢዎቹ ለሰፈረዉ የኢትዮጵያ ጦርና ለነዋሪዉ ሕዝብ የሰጡት ማስጠንቀቂያም እንደዚሁ የበርካታ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተከታዮችን ትኩረት ስቧል።
በቃኘናቸዉ የፌስ ቡክና የቲዊተር ገፆች ላይ የሰፈሩት አብዛኞቹ መልዕክቶች ግን ከአስተያየት ይልቅ ዉጊያ፣ ግጭት መጠፋፋቱን ይበልጥ የሚያባብሱ ፕሮፓጋንዳዎች፣ ዘርና ጎሳን ነጥለዉ፣ ያንዱ ወይም የሌላዉን ወገን ባለስልጣናት ስም እየጠቀሱ የሚሳደቡ፣ ጉዳዩን የዘገቡ መገናኛ ዘዴዎችን ሳይቀር ካንዱ ወይም ከሌላዉ ጋር እየደበሉ የሚያንቋሽሹ፣የሚራገሙ፣ እንዲጠፉ የሚመኙ በመሆናቸዉ አላቀረብናቸዉም።
በጣም ጥቂቱን ግን እነሆ፣--
ይስ ሐበሻ በፌስ ቡክ «ሰላም ለሁሉም» ይላል ወይም ትላለች፤ ጦርነቱ «በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት።» የይስ ሐበሻ አስተያየት ነዉ።ማራ ናታ ግን ተቃራኒዉን ነዉ የፃፈዉ።«ከዚሕ በኋላ በሰላም መፍታት የለም።» ብሎ።ዓሊ መሐመድ ይስን በመቃወም፣ ማራን በመደገፍ የቆመ ይመስላል።«በሰላም ይፈታ የሚለዉ አለፈ ወዳጄ!» ይላል ዓሊ።
አል ሙዕሚን ያረብ፣ የሁሉም የጣመዉ አይመስልም።እንደስሙ ሁሉ ወደ ፀሎት፣ ዱዓዉ ነዉ ያዘነበለዉ። «አላሕ ንፁሐንን ይጠብቅልን።» ይላል በፌስ ቡክ።
አምና ትግራይ ዉስጥ የተጀመረዉ ጦርነት  ወደ አማራና አፋር ክልላዊ መስተዳድሮች ከተስፋፋ ወዲሕ የሚሞት፣የሚቆስልና የሚፈናቀለዉ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UHCR) እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር መስከረም 6፣2021 ባወጣዉ ዘገባ ጦርነቱ ትግራይ ዉስጥ 2.1 ሚሊዮን፣ አማራ ክልል 250 ሺሕ፣ አፋር ክልል ደግሞ 112ሺሕ ሕዝብ ማፈናቃሉን ዘግቦ ነበር።
ዘገባዉ ከተሰራጨ በኋላ በተለይ በአማራና አፋር ክልሎች የቀጠለዉን ዉጊያ በመሸሽ ወደተለያዩ አካባቢዎች የተጓዘዉ ተፈናቃይ ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን እንደሚበልጥ የተለያዩ የርዳታ ድርጅቶች ይናገሩ።ከሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ተፈናቅሎ ደሴ ዉስጥ የተጠለለዉ ወይም መጠለያ የሚፈልገዉ ሕዝብ ብቻ 750 ሺሕ እንደሚደርስ የአካባቢዉ ባለስልጣናት ይገምታሉ።
ደሴ ለሚገኙት ተፈናቃዮች  ርዳታ መከፋፈሉ ቢዘገብም፣ርዳታዉ ለተፈናቃዮቹ በቂ እንዳልሆነ፣ ጨርሶም ርዳታ ያያልደረሳቸዉ መኖራቸዉን ተፈናቃዮቹ በተደጋጋሚ ይናገራሉ።የሰሜንና የደቡብ ወሎ የርዳታ ጉዳይ ባለስልጣናትም ተፈናቃዩ ቢያስ እስከዚሕ ሳምንት አጋማሽ ድረስ  በቂ ርዳታ እንዳላገኘ አረጋግጠዋል።
ለዚሕ ዛይሆን አይቀርም፣ ሴ ንግ የተባለ የፌስ ቡክ ተከታታይ ተፈናቃዩን «መጥታችሁ እዩት» የሚለዉ።ቀጠለ ሴ፣  «እባካችሁ  ደሴ ገራዶ ያለው ተፈናቃይ በረሀብ ማለቁ ነው። ሲረዳው የነበረው የደሴ ህዝብ ከተማውን ለቅቆ ወጥቷል። መንግስት አላየንም» የሴ ንግ አስተያየት ነዉ።
ሰለሞን ዳኜ ደግሞ አሁንም በፌስ ቡክ «ከየቤታቸዉ ሳይወጡ የቀሩት ይበዛሉ።» ይላል ጠየቀም «ማን ይድረስላቸዉ?» ብሎ።
ጌታቸዉ ዓሊም ይጠይቃል።«የእናት እምባ ዋጋዉ ስንት ነዉ?» እያለ።ሌላም ጥያቄ አለዉ ጌታቸዉ። «ስለምንስ የወሎ ህዝብ ይሄ ሁሉ መከራ እና ስቃይ እንዲደርስበት ተፈለገ?» አንዱ ጥያቄ ነዉ።«ዝምታውስ እስከ መቼ?» ሁለተኛዉ።«የሐይማኖት አባቶች ዝምታ፣ የፖለቲከኞች ዝምታ። ኧረ ምንድ ነው ጉዱ ? የሰሚ ያለህ ???» በሶስት የጥያቄ ምልክት አሳረገ-ብዙ ጥያቄዉን።
ናንቺ አንዋር የተፈናቃዩን ችግር ከቁብ የጣፈዉ አይመስልም።እንዲያዉም «የአዉሮጳን ርዳታ ከመዉሰድ መሞት ይሻላል» ብሎ አረፈዉ ናንቺ በፌስቡክ።
ብሩክ ዘ ዋሲ የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ አስተያየት ሰጪም የናንቺ አንዋርን አቋም በከፊል ይጋራል።ግን እርዳታ ከመቀበል ሞትን አልመረጠም።«የአሜሪካ ርዳታ ቢቀር የተሻለ ነው» ይላል ብሩክ።
«ካልሆነ ግን የሚሰጠዉን ርዳታ የክልሉ መንግሥት መቀበል አለበት። ከዚያም እነሱን አሳይቶ ለተፈናቀሉት መርዳት ቢቻል እንጂ ሰሜን ወሎና ዋግ በእርዳታ ስም አሜሪካኖች ከገቡ በቀጥታ ለወያኔ ድጋፍ የሚያደርጉበትን ስልት ቀይሰው ነው የሚመለሱት።» ይላል።
የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አንዳድ ስሞች አስቸጋሪ ናቸዉ።ያአይ ሌንሳ ይላል አንዱ።የአዉሮጳ አሜሪካኖች ርዳታ ይቅርብን ባዮችን ይቃወማል።«የአሜሪካ እርዳታ ይቅር የምትሉት» ይልናል--- እዚሕ በማንደግመዉ ቃል ይሳደባል።«የኢትዮጵያን ዓመታዊ በጀት 40% የምትሸፍነው አሜሪካ መሆኗን አታውቁማ...» እያለ ቀጠለ።
ያአይ በመቶኛ የጠቀሰዉት ድጋፍ አሜሪካ ስለመስጠት አለመስጠቷ ግን ማረጋገጪያ የለንም።
ሳምንቱን የዓለምን መገናኛ ዘዴዎች ትኩረት ከሰባቡ ርዕሶች አንዱ የሱዳን ፖለቲካዊ ቀዉስ ነዉ።የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አልቡርሐን ወትሮም በሕዝባዊ ተቃዉሞ ግፊት፣በዓለም አቀፉ ጫና፣ በኢትዮጵያና በአፍሪቃ ሕብረት ሽምግልና ለሲቢሎች ያጋሩትን ሥልጣን ባለፈዉ ሰኞ በጉልበት ጠቅልለዉ ይዘዉታል።
ጄኔራሉ የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት የተባለዉን ከጦር ሐይሉ ና ከሲቢሉ የተዉጣጡ ፖለቲከኞች የሚመሩትን ምክር ቤት አፍርሰዉ፣ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ የሚመሩትን ካቢኔ በትነዉ የመሪነቱን ሥልጣን ጠቅልለዉ ይዘዉታል።በብዙዎች ዘንድ እንደመፈንቅለ መንሥት የተቆጠረዉ የጄኔራል አል ቡርሐን ርምጃ ከዉጥም ከዉጪም ተቃዉሞ ገጥሞታል።
ከዉስጥ ሕዝባዊ ተቃዉሞዉ ሲቀጥል ከዉጪ ደግሞ የአፍሪቃ ሕብረት ሱዳንን ከአባልነት አግዷል።ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረትና የዓለም ባንክም ለሱዳን የሚሰጡትን ርዳታ አቁመዋል ወይም ለማቆም እየዛቱ ነዉ። 
አበበ ታሪኩ ግን «ግብፅና አሜሪካ የተሳካላቸዉ ይመስላል» ባይ ነዉ።ስመኘዉ በየነ በበኩሉ «የአፍሪቃ መሪዎች ስልጣን ስለምትወዱ ሥራችሁ ሁሉ አይጥመኝም።»ይላል።በዶሬ ታምራት ደግሞ የሱዳን ፖለቲካዊ ቀዉስን «ለኢትዮጵያ የመጣ የፈጣሪ ክንድ ይለዋል።ምክንያት አልጠቀሰም።ግን የፌስ ቡክ አስተያየቱን ቀጠለ «ሚሊተሪው ስልጣኑን ቢቆጣጠር ለኛ ምን ማለት እንደሆነ ማሰብ ይከብዳል የኢትዮጵያ አምላክ ቅን ፈራጅ ነው» ጨረሰ።
ዱሜሪ ዳሞስ፣ 55 ሐገራትን የሚያስተናብረዉን የአፍሪቃ ሕብረትን ይተቻል «የአፍሪቃ ሕብረት ራሱ ምን ይጠቅማል?» እያለ ቀጠለ።«ፖለቲከኞች ወደ እነሱም እንዳይዛመት ነው የፈጠኑት።» የዱሜሪ አስተያየት ነዉ።መረብ ዓደቦይ በእንግሊዝኛ በፃፈዉ አስተያየት «የአፍሪቃ ሕብረት ጥርስ የሌለዉ የአምባገነኖች ስብስብ ነዉ።» ይለዋል።
የፌስ ቡክ ስሙን ፌር ፕሌይ ያለዉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ምዕራባዉያንን ይወቅሳል።በጥያቄ እያዋዛ።«አሜሪካ እና አውሮፓ ግን ምንድን ነው እንደዚህ የአፍሪቃ ጉዳይ የሚያንገበግባቸው? ኢትዮጵያ ላይ መፈንቅለ መንግስት ካልተካሔደ ብለው በገሃድ እየፎከሩ በተቃራኒው ሱዳን ላይ ደግሞ መፈንቅለ መንግስት ለምን ተካሔደ ብለው እዬዬ፣ ኧረ ምን ጉድ ናቸው በፈጣሪ?» መልስ የለንም።መስፍን ቢ ማሞ ግን የኢትዮጵያ ጉዳይ ነዉ ያሳሰበዉ «የኛ ዕጣ ፈንታ ገና አለየም።» ይላል መስፍን በፌስ ቡክ።በዚሁ አበቃን።
ነጋሽ መሐመድ 
እሸቴ በቀለ

Äthiopien I Kriegsvertriebene in Dessie
ምስል T. Abebe
Äthiopien Luftangriff Mekelle Tigray
ምስል Million Haileselassie /DW