1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 9 2012

የፕሬዝደንት ትራምፕ እርምጃ የሕግ ጥያቄም አስከትሏል።የሕግ ባለሙያዎችና ፖለቲከኞች እንደሚሉት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለዓለም አቀፉ ድርጅት የምትሰጠዉን የገንዘብ ድጋፍ ያፀደቀዉ የሐገሪቱ ምክር ቤት ነዉ።ድጋፉ መቋረጥ ካለበት እንዲቋረጥ መወሰን ያለበትም የአሜሪካ ምክር ቤት እንጂ ፕሬዝደንቱ መሆን አልነበረባቸዉም

https://p.dw.com/p/3b1qa
Schweiz Genf - Hauptsitz der Weltgesundheitsorganisation (WHO)
ምስል picture-alliance/dpa/S. Di Nolfi

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የትራምፕ ዉሳኔ፣የኢትዮጵያዉያን መባረር

የኮረና ተሕዋሲ አለቅጥ መዛመት፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዉሳኔና  የዓረብ መንግሥታት ኢትዮጵያዉያንን ማባረራቸዉ በሳምንቱ የብዙዎችን የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አስተያየት ሰጪዎች ትኩረት ስበዋል።የጎሉትን ባጫጭሩ እንቃኛለን።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሲፎክሩ ሰንብተዉ በያዝነዉ ሳምንት ሐገራቸዉ ለተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት (WHO) የምታደርገዉን የገንዘብ መዋጮለማቆም ወስነዋል።የትራምፕ ዉሳኔ ከሐገራቸዉ የዴሞክራቲክ ፓርቲ እንደራሴዎች ሳይቀር ከአብዛኛዉን ዓለም መንግሥታትና ድርጅቶች ከፍተኛ ትችትና ተቃዉሞ ገጥሞታል።

ዩናይትድ ስቴትስ  ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት  የምትሰጠዉን ገንዘብ ትራምፕ የከለከሉት ድርጅቱ የኮሮና ተሕዋሲ ቻይና ዉስጥ እንደተከሰተ የተሕዋሲዉን አደገኛነትና የወረርሺኙን ፍጥነት ለዩናይትድ ስቴትስ ፈጥኖ አላስታወቀም በሚል ሰበብ ነዉ።ፕሬዝደንት ትምፕ ከዚሕ ቀደምም ግዙፉን የጤና ድርጅት ለቻይና ይወግናል በማለት ሲወቅሱት ነበር።

የትራምፕን ወቀሳና በያዝነዉ ሳምንት ያሳለፉትን ዉሳኔን የተቃወሙት የዩናይትድ ስቴትስና የአብዛኛዉ ዓለም ፖለቲከኞች እንደሚሉት፣ ትራምፕ ዓለም አቀፉን ድርጅት የሚወቅሱት እራሳቸዉ ትራምፕ በሐገራቸዉ የተሕዋሲዉን ስርጭት ለመገደብ ሁነኛ  መርሕ ባለመቀየሳቸዉ ወይም ጠቃሚ እርምጃ ባለመዉሰዳቸዉ ነዉ ባዮች ናቸዉ።ጥፋታቸዉን በሌላ ለመሸፈን።

የፕሬዝደንት ትራምፕ እርምጃ የሕግ ጥያቄም አስከትሏል።የሕግ ባለሙያዎችና ፖለቲከኞች እንደሚሉት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለዓለም አቀፉ ድርጅት የምትሰጠዉን የገንዘብ ድጋፍ ያፀደቀዉ የሐገሪቱ ምክር ቤት ነዉ።ድጋፉ መቋረጥ ካለበት እንዲቋረጥ መወሰን ያለበትም የአሜሪካ ምክር ቤት እንጂ ፕሬዝደንቱ መሆን አልነበረባቸዉም።ከሁሉም በላይ ዓለም ከድምፅ አልባ፣ ስዉር ገዳይ ጠላቱ ራሱን ለመከላከል በጋራ መቆም በሚገባዉ ባሁኑ ወቅት የዕለ ኃያሊቱ ሐገር የመጨረሻ ባለስልጣን የወሰኑትን መወሰናቸዉ ለብዙ ዓለም አሳዛኝ፣ አስተዛዛቢ፣ አናዳጅም ነዉ የሆነዉ።

ለአፍሪቃዉያን በጣሙን ፣ ለኢትዮጵያዉ ደግሞ የሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዉሳኔ ዘጠረኝነት እና በ«ሐገር ልጅ» ላይ የተቃጣ ጥቃት ዓይነት ነዉ-የሆነዉ። የግዙፉ ጤና ድርጅት የበላይ ኃላፊ አፍሪቃዊዉ-ኢትዮጵያዊዉ ፖለቲከኛ ቴዎድሮስ አድሐኖም ናቸዉና።

ሐና ሐኒሾ በላይ፣ በትራምፕ ዉሳኔ «አላዘንኩም» ባይነች።የፅሑፏ ማሰረጊያ ግን ትክክለኛ ስሜቷን ይመሰክራል።

 «ለሀገሬ ኢትዮጵያ የሚሰጥ ቢሆን በጣም ነበር የማዝነው ነገር ጊን ለአለም መሆኑ ምንም እንዳላዝን አድርጎኛል።» -----ትላለች በፌስ ቡክ ገፅዋ፤ ትቀጥላለችም።«የመጨረሻ ትንሽ ነው መሆኑን አሳይቶናል ዶማው ዶናንድ ትራንፕ»-----እያለች።

USA Washington | Präsident Trump während Pressekonferenz
ምስል Getty Images/A. Wong

ኢክራም ይመር በፌስ ቡክ ያሰፈረችዉ አስተያየት ግን ከሐና ጠንከር፣ገለጥም ያለ ነዉ።እንዲሕ ይነበባል።«በዚች ምድር ላይ እንደ ትራንፕ ዓይነት የለየለት ዘረኛ የለም ይሄን ሁሉ የሚያደርገው ዶ/ር ቴዎድሮስ ጥቁር ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ለማንኛውም ፈጣሪ ንፁሀንን ትቶ ለሰውየው የእጁን ይስጠው»የፀሐዬ እጁጉ  አስተያየት አጭር ነዉ።«ጎበዝ እንኳን አቆመች» ይላል ፀኃዬ በፌስ ቡክ ገፁ። «ጉዳዩ ይጣራ።»ካላሊ ብርሐኑ  ድግሞ የዩናይትድ ስቴትሱን መሪ ከኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስር ጋር ያመሳስላቸዋል።

«ትራምፕና ኣብይ ኣሕመድ ዓሊ ብዙ የሚያማሳስላቸው ነገር ቢኖር የሚያላያቸው ትራምፕ የራሱን ድክመት ላለመቀበል በጥቁር ኣፍሪካዊ ፡ኢትዮጵያዊዉ ክቡር Dr ቴድሮስ ኣድሓኖም ያሳብባል ።» የካላሊ ብርሐኑ የፌስ ቡክ ትንታኔ።ቀጠለም
«ኣብይ ሓመድ ዓሊ ደግሞ ድክመቱን ላለመቀበል በህወሓት ያሳብባል ።» ተጨማሪ አስተያየትም አለዉ።ግን ይብቃን።
ማሙሽ የሚል ብቻ ስም ያለዉ አስተያየት ሰጪ  ቴሌግራም ካሰፈረዉ ዘለግ ያለ አስተያት የሚከተለዉ ይገኝበታል።«እንደ ባለ-አዕምሮ ሰው ማሰብ ሲሳናቸው ባለ-አዕምሮ ሰዎችን ለመዝለፍ ይሽቀዳደማሉ ። ሰንፍናቸውን   ደብቀው ብርቱ ለመምሰል ሲጥሩ ዳግም እንደገና ይወድቃሉ ----------ጨለማ የሚሸነፈው በብርሃን ጉልበት ነው ። ሰለዚህ ለብርሃኑ ለምትታገሉ ፣ ለተሻለው ቀን ለምትደክሙ ፣ ለሰው ልጅ ፈውስ ለምትታገሉ ....እግዚአብሔር አለሁ ይበላችሁ ። ማሙሽ ረጅም አስተያየት፣ ምስጋና፣ ፀሎት-ርግማኑን-----«ግድ የለም ይህንንም ቀን እናልፈዋል ።-----ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እግዚአብሔር ከእርሶ ጋር ነው ።እኔም ከእርሶ ጋር እቆማለሁ ።  " በሚል ማረጋገጪያ ያስርጋል።

Schweiz Genf | WHO: Adhanom Ghebreyesus, Generaldirektor der Weltgesundheitsorganisation
ምስል picture-alliance/dpa/M. Trezzini

AHM ED የሚል ስም የለጠፈ አስተያየት ሰጪ ግን ትራምፕ ለምን ይወቀሳሉ ባይ ነዉ።«ግድ ስጥ ብለው ነው?» ይጠይቃል።የአብረሐም ኢሻቅ አስተያየት ረጅም ነዉ።የዓለም ጤና ድርጅትን እና ደጋፊዎቹን ይወቅሳል።

«WHO እና ቢል ጌትስ በሰብአዊ መብት ላይ ለተፈጸሙት ወንጀሎች ተጠያቂ መሆን አለባቸው ፡፡ ለጠፋው ለእያንዳንዱ ህይወት ተጠያቂ WHO ነው? !! የዓለም ጤና ድርጅት በእጆቻቸው ላይ ብዙ ደም አላቸው-----»እንዳልነዉ አብረሐም ኢሻቅ በፌስ ቡክ ያሰፈረዉ አስተያየት ሰፊ ነዉ።ለዛሬ ከዚሕ በላይ መጥቀስ አልቻልንም።

አቡዘር መሐመድም እንደ አብረሐም ሁሉ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ዉሳኔ ደጋፊ፣ ዓለም አቀፉን ድርጅት ወቃሽ ነዉ።«ኮቪዲ በዩናይትድ ስቴት እያደረሰ ላለው ጥፍት ..... አሜሪካ ድርጅቱን በብዛት ከመደገፍ ጋ ሲነፃፀር የወሰደችው እርምጃ ትክክል ነው... የአለም የጤና ድርጅትን 40 በመቶ ድጋፍ አድራጊዋ ብቸኛዋ ሀገር ናትና .. እንዲያም ሆኖ በድርጅቱ እንዝላልነት ዬ .ኤስ .ኤ. ጉዳቱ የከፍ ሁኖባታል So Donald Right

ዩናይትድ ስቴትስ ለዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ ባጠቃላይ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛዉን ገንዘብ የምታዋጣ ሐገር ነዉ።ሐገራት ለየድርጅቶቹ የሚያዋጡት የገንዘብ መጠን በየገቢያቸዉ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ከዓለም ከፍተኛዉን ገቢ የምታገኘዉ አሜሪካ ለዓለም አቀፎቹ ድርጅቶች የምስጠዉ ከምታጋብሰዉ ብዙ ጋር ሲነፃፀር ኢምንት ነዉ ባዮች ጥቂት አይደሉም።ወደ ሌላኛዉ ርዕስ እንለፍ።

የሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስታት የኮረና ስርጭትን ለመግታት በሚል ሰበብ በርካታ ኢትዮጵያዉያንን ወደ ሐገራቸዉ መላካቸዉን የሚመለከት ነዉ።

አፍሪካግሎብ የተሰኘዉ የዜና ምንጭ በያዝነዉ ሳምንት በአምደ-ረብ ያሰራጨዉ ዘገባ ከኢትዮጵያ አልፎ የብዙዎቹን የእንግሊዝኛ አምባቢ አፍሪቃዉያን የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተከታታዮችን ትኩረት ሳይስብ አልቀረም።

«አረቦች በኮሮና ተሕዋሲ ሥርጭት መከላከል ሰበብ በጥቁሮች ላይ የተጀመረዉን  ዓለም አቀፍ ዘመቻ ተቀየጡ» ይላል የዘገባዉ ርዕሠ።ዘገባዉ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች  በሺሕ የሚቆጠሩ  ኢትዮጵያዉያንን ማባረራቸዉን በዝርዝር ያስረዳል።

ባለፉት ሳምንት ወደ 3ሺሕ የሚጠጉ ኢትዮጵያዉያን ከሳዑዲ አረቢያ፤ ከአረብ ኤሚሬቶችና ከጁቡቲ ወደ ሐገራቸዉ ተግዘዋል።ሌሎች 3 ሺሕ የሚሆኑ ደግሞ በሚቀጥሉት ሳምንታት ኢትዮጵያ ይገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነዉ።አረቦቹ የኢትዮጵያዉያንን ሥራ እያቋረጡ የሚያባርሩት የኮሮና ተሕዋሲን ያሰራራጫሉ በሚል ሰበብ ነዉ።

ፋርሲ ሲራጅ የአረቦቹ በጣሙን የሳዑዲ አረቢያ እርምጃ ስሜቱን ክፉኛ ሳይነካዉ አልቀረም።

«የሳውዲ መንግስት ለስውልጆች ከብር የሌለው የማህይማን ስብስብ ነው ስለዝህምነው በዚህ ወቅት ዓለም በተጨነቀችበት ስዓት ስዎችን በጅምላ ስብስባ ከሐገሬ ውጡ እያለች የምታስቃየው---»ፋርሲ በፌስቡክ የሰጠዉ አስተያየት በዚሕ አያበቃም።ይቀጥላል እንዲሕ እያለ።«በተለይ ኢትዮዽያዉያን ላይ ያላት አመለካከት ጥሩ አይደለም። አንድ ስው፣ ስው የሚያስኛው ሌላዉን  እንደራሱ ሲያከብር ብቻ ነው፣» አስተያየቱ በርግማን ነዉ የሚያሳርገዉ።ትተነዋል።

ፌለ ሞን በሰነዘረዉ ጭር አስተያየት ደግሞ «ምንም ማድረግ አይቻልም» ባይ ነዉ ።ሙሉዉን እነሆ።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ