1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሊ ፖለቲካዊ ቀውስ እና ድንበር ተጋሪው የውጭ ኃይላት ሽኩቻ

ቅዳሜ፣ ጥር 7 2014

ከአስር ዓመታት በፊት በሰሜናዊ ማሊና ኒጀር ነዋሪ የሆኑ የቱዋሬግ ነባር ሕዝቦች የበርካታ ምዕራባዋያን ሀገራት ዓይን ባረፈበት አካባቢያቸው ከሚገኘው ከፍተኛ የዩራንየምና ዕምቅ ሃብትና ሌሎችም ውድ ማዕድናት ፍትሃዊ ክፍፍልን በመጠየቅ የትጥቅ ትግል ማቀጣጠላቸው የሳህል ቀጣና አካባቢ ሃገራትን ታላቅ የነውጥ ማዕበል ውስጥ ከተተው::

https://p.dw.com/p/45ZmL
Französischen Marine-Spezialeinheiten bildet in Mali aus
ምስል Thomas Coex/AFP/Getty Images

የማሊ ፖለቲካዊ ቀውስ እና የውጭ ኃይላት ሹክቻ

ከአስር ዓመታት በፊት በሰሜናዊ ማሊና ኒጀር ነዋሪ የሆኑ የቱዋሬግ ነባር ሕዝቦች የበርካታ ምዕራባዋያን ሀገራት ዓይን ባረፈበት አካባቢያቸው ከሚገኘው ከፍተኛ የዩራንየምና ዕምቅ ሃብትና ሌሎችም ውድ ማዕድናት ፍትሃዊ ክፍፍልን በመጠየቅ የትጥቅ ትግል ማቀጣጠላቸው የሳህል ቀጣና አካባቢ ሃገራትን ታላቅ የነውጥ ማዕበል ውስጥ ከተተው:: "ከሞኝ መንደር ሞፈር ይቆረጣል" እንደሚባለው ብሂል ከ 59 የሚልቁ የኒውክለር ማብላያ ተቋማትን ገንብታ ከአፍሪቃ በሚዛቅ የዩራንየም ማዕድን እንደ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ስዊትዘርላንድ፣ ስፔይንና ሉክሰምበርግን ለመሳሰሉ የተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭታ ለምትቸበችበው የቀድሞ የሃገራቱ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ይህ በሳህል አካባቢ ሃገራት የተጀመረ የተፈጥሮ ሃብት ፍትሃዊ ፍትሃዊ ክፍፍል ያለም አመጽ ፈጽሞ ምቾት የሚሰጣት አልነበረም:: እናም "የኒጀርና ማሊ የዩራንየም ማዕድን በአክራሪ አማጽያን ለጥቃትና ለአደጋ ተጋልጧል" በማለት ከዛሬ ስምንት ዓመታት በፊት ልዩ የጦር ኃይሏን በፀረ-ሽብር ዘመቻ ስም ወደ ማሊና ኒጀር በይፋ ላከች:: እርምጃዋም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክርቤት ዕውቅና የተሰጠው ሲሆን ሰላም አስከባሪ ጦሩንም ወደ አካባቢው ልኳል:: ዛሬ የማሊ ሕዝብ የፈረንሳይን ጦር በሕዝባዊ አመጽ አባሮ በአሜሪካና ሸሪኮቿ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአውሪጳ ሕብረት ጭምር በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሃገራት የመንግሥት ግልበጣ ወንጀሎች በጥቁር መዝገብ ስሙ ሰፍሮ ዓለማቀፍ ማዕቀብ የተጣለበትን የሩሲያውን ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን የዋግነር ግሩፕ ሰራዊት ሃገሩ አስገብቷል:: ምዕራባዋያን በዚህ ያልተተበቀ እርምጃ በእጅጉ ታምሰዋል የሚይዙትን የሚጨብጡትን አጥተዋል:: ላለፉት አያሌ ዓመታት እንዲህ በቀውስ የምትናጥው ማሊ አሁንም ድረስ በተደጋጋሚ የወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት በአክራሪ ጽንፈኞች ጥቃትና በምዕራባውያን የጥቅም ሹክቻ ሰላሟ ከድጡ ወደማጡ እያመራ ይገኛል:: የዛሬው ትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችንም ይህንኑ የማሊን ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት በወፍ በረር ይቃኛል::

የማሊ ቀውስ እና የውጭ ኃይላት ጣልቃ ገብነት

ከ 60 ዓመታት በፊት እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 1959 ዓ.ም በመላው የአፍሪቃ አህጉር የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ሲቀጣጠል ዛሬ ማሊ በሚባለው አካባቢ ሰፍረው ይኖሩ የነበሩ የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች ፍሬንች ሱዳን የሚባለው የሱዳናውያን ሪፐብሊክ እና ሴኔጋል የአሁኗን የማሊ ሪፐብሊክ መመስረታቸውን በይፋ አወጁ:: የቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይም ወዲያውኑ ስምምነቱን የተቀበለች ሲሆን በዓመቱ ሰኔ 13, 1952 ዓ.ም ማሊ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ መውጣቷን በመጀመሪያው ፕሬዝዳንቷ ሞዲቦ ኬይታ አማካኝነት ለዓለም አበሰረች:: ምንም እንኳ ማሊን ጨምሮ አስራ አራት አፍሪቃውያን የፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ ግዛት ሃገራት እንደ ኮንጎ ኮትዲቯር ቡርኪናፋሶ ኒጀር ሴንትራል አፍሪቃን ሪፐብሊክ ካሜሩንና ሌሎቹም ለይስሙላ ነጻነታቸውን ቢያውጁም፤ በቅኝ ግዛት በተገዙበት ወቅት ያገኙትን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ አሁንም ድረስ ግብር እንዲከፍሉና የውጭ ምንዛሪያቸውን በፈረንሳይ ማዕከላዊ ባንክ በማስቀመጥ ለፈረንሳይ 65 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሪያቸውን ለመስጠት የሚያስችል አስገዳጅ ስምምነት በመፈረማቸው ሃገራቱ ዛሬም ድረስ ከፈረንሳይ የእጅ አዙር ባርነትና ቅኝ አገዛዝ መዳፍ አለመላቀቃቸው እሙን ነው:: ዛሬ ምዕራባውያን ሀገራት ለኒውክለር የጦር መሳሪያ ምርት፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፣ ለሕክምና መስጫ አገልግሎትና ለተለያዩ ምርቶች ግብዓት እጅግ በጥብቅ የሚፈልጉትን ከፍተኛ የዩራንየም ክምችት በከርሰምድሯ የያዘችው የምዕራብ አፍሪቃዊቷ የሳህል ቀጣና ሃገር ማሊ፤ በእርስ በእርስ ግጭት፣ በአክራሪ ጽንፈኞች መጠናከር፣ የተፈጥሮ ሃብቷን ለመቀራመት ባሰፈሰፉ ኃይላት ሹክቻና በተደጋጋሚ በተፈታተናት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሳቢያ ከዓመታት በላይ መረጋጋት ተስኗት ቆይታለች:: ከ 19 ሚልዮን የሚልቅ ሕዝብ ያላት  ወደብ አልባዋ ሃገር ማሊ በቆዳ ስፋቷ ትንሽ ትሁን እንጂ በአፍሪቃ አራተኛዋ ግንባር ቀደም የወርቅ አምራች፣ ጥራት ባለው ከፍተኛ የጨው ክምችት ምርቷ የምትታወቅ እንዲሁም ለጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን ብዛት ያለውን የጥጥ ምርት ለዓለም ገበያ የምታቀርብ መሆኗም ይጠቀሳል:: ዛሬ ማሊ በተለይም በማዕከላዊና ሰሜናዊ ክፍሏ ታኦዴኒን በመሳሰሉ ገጠራማ ከተሞቿ እንደ ፈረንሳይ፣ አውስትራሊያ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ ቃጣርና ስፔይንን የመሳሰሉ ከ 15 የሚልቁ የዓለም ሃገራት ግዙፍ ካምፓኒዎች የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ምርቶቿን በማሰስና አጣርቶ ለገበያ በማቅረብ የኢንቨስትመንት ንግዶቻቸውን የሚያጧጡፉባት ብትሆንም፤ ሃገሪቱ ግን ለዓመታት በግጭትና በአሸባሪዎች ጥቃት እየታመሰች በምጣኔ ሃብት ደቃ የዜጎቿን ሕይወት ከድህነት አረንቋ ማላቀቅ ተስኗት ቆይታለች:: ዓለማቀፉ የንግድ ድርጅት ካውንስል ከዓመት በፊት ባወጣው መረጃ እንደጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ከ 2006-2019 ዓ.ም ባሉት ዓመታ በዓለም ከፍተኛው የተባለ አዲስ የወርቅ ክምችት ከ 79 ሚልዪን አውንስ በላይ በምዕራብ አፍሪቃ መገኘቱን ጠቅሶ ሃገራቱም ቡርኪናፋሶ ጋና ማሊና አይቮሪኮስት መሆናቸውን ይፋ አድርጓል:: ሆኖም ዛሬ በተለይም በሰሜናዊ ምስራቅ የኪዳል ግዛት ይህን ግዙፍ የወርቅና አያሌ የተፈጥሮ ኃብት ለመበዝበዝ ፍላጎት ያላቸው ታጣቂ የማፊያ ቡድኖችና አክራሪ የሽብር ኃይላት እየተጠናከሩ መምጣት፣ በአካባቢው ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በሳህል ቀጣና የሰፈረው የፈረንሳይ ጦር ተጨባጭ የሆነ አንጻራዊ ሰላምን ለማስፈን ባለመቻሉና ሃገሪቱም በተደጋጋሚ በመፈንቅለ መንግስት እየተኛጠች ከመሆኗ ጋር ተዳምሮ የተረጋጋ አስተዳደርን መፍጠር ባለመቻሉ የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠባት እየተነገረ ይገኛል:: እንደ ቲምቡክቱ ሁሉ በተመሳሳይ በከርሰ ምድር የተፈጥሮ ሃብት የበለጸገችው የኪዳል ግዛት አብዛኛው ክፍልም መንግስት ከቁጥጥሩ ውጪ ወጥተው ዛሬ ላይ በታጣቂዎች እጅ መውደቃቸው እየተነገረ ነው::

ተደጋጋሚ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባት ማሊ

ማሊ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣች በኋላ ባሉት 60 ዓመታት ውስጥ አምስት ያህል መፈንቅለ መንግስት የተካሄዱባት ሲሆን በታሪኳ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ያደረገችው አንድ ጊዜ ብቻ ነው:: አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ በቅርቡ የተካሄዱት ሁለቱ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች በ 9 ወራት ልዩነት ውስጥ መፈጸማቸው ነው::  እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2018 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ በምርጫ ማሸነፋቸውን ያወጁት የ 75 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ የማሊው ፕሬዝዳንት ኢብራሒም ቡባካር ኬይታ ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ በነሃሴ ወር 2020 ዓ.ም በማሊ ከአክራሪ ጀሃዲስቶች ጋር ለረጅም ዓመታት የዘለቀው ፍልሚያ ውጤት አልባ መሆኑ የኑሮ ውድነትና የምጣኔ ሃብት ድቀት ሕዝባዊ ተቃውሞ በማቀጣጠሉና የሃገሪቱ ወታደሮች ክፍያም መዘግየት በቀሰቀሰው ቁጣ ምክንያት የገዛ ወታደሮቻቸው የፕሬዝዳንቱን ቤተመንግሥት በመክበብ መፈንቅለ መንግስት ማካሄዳቸውን በይፋ አወጁ:: ድርጊቱን የዓለም መንግሥታት የአውሮጵያ ሕብረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪቃ ሕብረትና የምዕራብ አፍሪካ መንግስታት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) በጽኑ በማውገዝ የመንግሥት ግልበጣው እንዲቀለበስ አያሌ ጥረቶችን አድርገው ነበር:: እኔን በስልጣን ለማቆየት ተብሎ የንጹሃን ደም መፍሰስ የለበትም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ግን ፓርላማውን መበተናቸውንና ስልጣናቸውንም መልቀቃቸውን በይፋ አሳወቁ:: ታህሳስ 2020 ዓ.ም ወታደራዊ ጁንታው የመፈንቅለ መንግስቱ ዋና ጠንሳሽ ከሆኑት መኮንኖች መካከል ኮሎኔል ማሊክ ዳያውን የማሊ ህግ አውጪ አካል የሆነው የሀገሪቱ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አድርጎ ሲመርጥ፣ ኮሎኔል ባህ ዳዋ እና ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ ደግሞ ሃገሪቱን በ 18 ወራት ወራት ውስጥ ወደ ሲቭል አስተዳደር እንዲያሸጋግሩ የሃገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው 121 አባላት ባሉት የብሔራዊ የሽግግር ምክርቤት ተመርጠዋል:: ይሁናን ከዘጠኝ ወራት ቆይታ በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የአገሪቱን ጦር ሠራዊት ሁለት ከፍተኛ መኮንኖችን ከሥልጣናቸው አንስቶ በሌላ መተካቱ ቅሬታ ያሳደረባቸው ኮሎኔል ጎይታ ባልተጠበቀ ሁኔታ ፕሬዝዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩን "ኃላፊነታቸውን አልተወጡም" በሚል እንዲታሰሩ ካደረጉ በኋላ የማሊው ሕገመንግሥታዊ ፍርድ ቤት ባሳለፈው ውሳኔ ኮሎኔል ጎይታ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው "የአገሪቱን የሽግግር ሂደት አስከፍጻሜው እንዲመሩ" ኃላፊነት እንደሰጣቸው ይፋ አድርጓል። ኮሎኔሉ ሥልጣን በኃይል ከያዙ በኋላ ለሕዝቡ በአገሪቱ መንግሥታዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው "በጦር ሠራዊቱና በጸጥታ ኃይሉ መካከል ሊከሰት ከሚችለው ሥርዓት አልበኝነት ይልቅ የሃገሪቱን ዘርፈ ብዙ ቀውስና ችግር ለመፍታት መተባበርን መርጣናል" በማለት ሁለተኛውን መፈንቅለ-መንግሥት ያካሄዱበትን ምክንያት አስረድተዋል።

Mali I Unruhen I Konflikt
ምስል Michele Cattani/AFP/Getty Images

በካቲ ወታደራዊ ካምፕ መኮንኖች ተጠንስሶ ሃገሪቱን ከሲቭል ወደ ወታደራዊ አስተዳደር ያሸጋገረው አዲሱ ሥርዓት ቀደም ሲል አያሌ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን በማደራጀት ለፕሬዝዳንት ኬይታ ስልጣን ማጣት ቁልፍ ሚና ከነበረው ዋንኛው የተቃዋሚ ድርጅት የሰኔ 5 ንቅናቄም ተቃውሞ ገጥሞታል:: ድርጅቱ "የዓመታት ዴሞክራሲያዊ ትግላችን በሃገሪቱ ሥር ነቀል ለውጥን ለማምጣት እንጂ ወታደራዊ ጁንታው ስልጣንን ጠቅልሎ እንዲወስድ አይደለም" በሚል ራሱን ከሽግግር መንግሥቱ አግልሏል:: የ 38 ዓመቱ ኮሎኔል ጎይታ ጊዜያዊ አስተዳደሩን በማፍረስ ራሳቸውን የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር አድርገው መሾማቸው ብቻ ሳይሆን ስልጣኑንም ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለማራዘም ፍላጎት እንዳለው ካሳወቀ በኋላ አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ "ኢኮዋስ"ማሊን ከአባልነት ማገዱንም ጭምር የሚታወቅ ነው። ኢኮዋስ ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ ማዕቀብ እጥላለሁ የሚል ውሳኔ ካሳለፈና የትብብሩ አባል ሃገራት ከማሊ ጋር የሚያገናኛቸውን ድንበሮቻቸውን ከዘጉ በኋላ ወታደራዊ አመራሩ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት ቢገደድም ማሊን ወደ ሲቭል አስተዳደር ይመልሰዋል የተባለው የጊዜያዊ አመራሩ አባላት መወገድና እስከ 2026 ዓ.ም ወታደራዊው ኃይል ስልጣኑን ለማራዘም የጀመረውን እንቅስቃሴ በጽኑ በመቃወም 15 አባል ሃገራት ያሉት ኢኮዋስ ማሊን ወደ ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሥርዓት ይመራታል የተባለውንና በመጪው የካቲት ወር ማብቂያ ለማካሄድ ቀጠሮ የተያዘለትን ሃገራዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ እንዲያከብር ይህ ተፈጻሚ ካልሆነ ግን በወታደራዊ አመራሩና ቤተሰቦቻቸው ላይ በአባል ሃገራቱ ውስጥ የጉዞ እገዳን ጨምሮ በባንክ ያስቀመጡት ገንዘብና ንብረት ላይ እገዳን እስከመጣል የሚደርስ እርምጃ እንዲወሰድ ያስተላለፈውን ውሳኔ ገቢራዊ እንደሚያደርገው አስታውቋል:: የማሊ አጎራባች ድንበሮች መዘጋት የሃገር አቋራጭ ትራንስፖርት እንቅስቃሴው እንዲገታና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲገደብ በማድረጉ ገና ከአሁኑ ሃገሪቱን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከቷታል:: ሕዝቡም በፕሬዝዳንት ኬይታ መወገድ የመደሰቱን ያህል ከዓመት በላይ በዘለቀው የሽግግር ሂደት ሲናፍቀው የኖረው ለውጥ ጠብ አለማለቱ ተስፋው እንዲሟጠጥ እያደረገው ይገኛል:: ባለፈው እሁድ ኤኮዋስ ያሳለፈውን ውሳኔው የሽግግር መንግስቱ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ጎይታ አጥብቀው ቢቃወሙም አስቸኳይ ውይይት እንደሚሹ ግን አልሸሸጉም::

"ምንም እንኳን የትብብሩ ውሳኔ ህገወጥና ሰብዓዊነት የጎደለው በመሆኑ እጅግ ቢያሳዝነንም ለሕዝባችን ዋስትናና ጥቅም ስንል ከቀጣናው ጋር ያለንን ሕብረት ለማጠናከርና የትብብሩን መሰረታዊ መርህዎች በማክበር አስቸኳይ ድርድር እና ውይይት ለማድረግ እንሻለን" ብለዋል ጎይታ::

Mali I Unruhen I Konflikt
ምስል Annie Risemberg/AFP/Getty Images

የማሊያውያን የበቃ ንቅናቄና የፈረንሳይ የጦሩ ከቲምቡክቱ ለቆ መውጣት

እንደ ጎርጎሮዋዊ አቆጣጠር ታህሳስ 2012 ዓ.ም በሳህል ቀጣና አካባቢ እየተስፋፋ በመጣው የሽብርተኞች ጥቃት በተለይም ደግሞ በማሊ ሰሜናዊ ግዛት በአይ.ኤስ የሚደገፉ አክራሪ ጽንፈኛ ቡድኖች መጠናከርና ማዕከላዊ መንግሥቱን ለመገልበጥ የጀመሩትን ግስጋሴ ለመግታት ፈረንሳይ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ጥበቃ ም/ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት "ኦፕሬሽን ሰርቫል" የተሰኘ ወታደራዊ ተልዕኮዋን ማሊ ውስጥ በይፋ ጀመረች:: ፈረንሳይ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከ 5,100 በላይ ለማሊ ብሔራዊ ጦር ወታደራዊ ስልጠና የሚሰጥና ሰላም በማስከበር ተልዕኮ ላይ የተሰማራ ሰራዊቷን በሳህል አካባቢ አስፍራ ቆይታለች:: ሰላምን ያረጋግጣል ተብሎ የዚህ ጦር በአካባቢው መስፈር ያልተዋጠላቸው አንዳንድ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ግን ገና ከጅምሩ "ሃብት ለማስጠበቅ ፈረንሳይ በማሊ ጦርነት ከፈተች" ሲሉ ስላቃዊ ዘገባ በወቅቱ እስከማውጣት ደርሰው ነበር:: ለዚህም አንዱ ምክንያት ከ 59 የሚልቁት የፈረንሳይ የኒውክለር ማመንጫ ጣቢያዎች ለሚያመርቱት የኤሌክትሪክ ኃይል ግብዓት የሚውለውን የዩራንየም ማዕድን የሚያገኙት ከኒጀርና ማሊ በመሆኑ ነው:: በማሊ የሽብር ጥቃትን ለመከላከልና በሰላም ማስከበር ስም የሰፈሩት አንዳንድ የፈረንሳይ ወታደሮች በሃገሪቱ ሕገወጥ የወርቅ ምዝበራ ሽያጭ ላይ ተሰማርተዋል ተብለው በተደጋጋሚ የወጡ ከገለልተኛ ወገን ያልተረጋገጡ አወዛጋቢ ቪድዮዎችና ምስሎችም ብዙሃኑ ማሊያውያንን ከ 9 ዓመታት በላይ ተጨባጭ ውጤት ሊያመጣ ያልቻለውን የፈረንሳይ የሳህል ቀጣና ሃገራት ወታደራዊ ተልዕኮ በከፍተኛ ጥርጣሬና ቁጭት እንዲመለከቱት አድርጓቸው ቆይቷል:: ሰላም አስከባሪው ጦር እንዲህ ምስጋናና ቅሬታን ለዓመታት ሲያስተናግድ ከቆየ በኋላ አምና በፈረንጆቹ ዓመት ማብቂያ ላይ ፈረንሳይ ዋና የጦር ሰፈሯ የሚገኝበትን ታሪካዊቷንና በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገችውን የቲምቡክቱ ክፍለግዛት "ሙሉ ለሙሉ ከጀሃዲስቶች ነጻ አድርጌያለሁ" በማለት ሰራዊቷ ከአካባቢው እንዲወጣ አድርጋለች:: አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ግን ለጦሩ ከማሊ መልቀቅ ዋናው ምክንያት ማሊያውያን የፈረንሳይ ጦር አካባቢውን ከታጣቂዎች ነጻ ከማድረግ ይልቅ እንዲጠናከሩ አድርጓል አንዳንድ የተልዕኮው አባላትም በሕገወጥ የማዕድን ዘረፋና ሕገወጥ ሽያጭ ላይ ተሰማርተዋል በሚል የበቃ ወይም ኖ ሞር ንቅናቄንና የአደባባይ ተቃውሞ በሃገሪቱ ማቀጣጠላቸውን ተከትሎ ነው ይላሉ:: ፈረንሳይ እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ከ 2013 ዓ.ም ጦሯን በይፋ በማሊ ካሰፈረች ጀምሮ የ 7 ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት በተልዕኮው ስህተት እንደተቀጠፈ ብታምንም ገለለተኛ ወገኖች ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች በአውሮፕላን የቦምብ ጥቃትና ከአሸባሪ ኃይላት ጋር በተደረገ ፍልሚያ በፈረንሳይ ወታደሮች መገደላቸውን ነው የሚገልጹት:: የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰየመው መርማሪ ቡድንም ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በማሊ ቦንቲ በምትባል መንደር የሰርግ ሥነ ስርዓት ታዳሚ በነበሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈረንሳይ ጦር በሄሊኮፕተር በከፈተው ጥቃት 19 ሰዎች መገደላቸውን ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል:: የፈረንሳይ ጦር በማሊና ሳህል ቀጣና በቆየባቸው ዓመታት ከ 55 በላይ ወታደሮቹ በአጥፍቶ ጠፊ ጽንፈኛ ኃይሎችና በተጠመዱ ቦምቦች ጥቃት የተገደሉበት ሲሆን ጥቂት የማይባሉም የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል::

Mali Symbolbild UN
ምስል Nicolas Remene/Le Pictorium/imago images

ከመንፈቅ በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላም አስከባሪ ጦሯን ወደ ማሊ የላከችው ጀርመን በሰሜናዊ ምስራቅ ማሊ ጋኦ አጥፍቶ ጠፊዎች በተሽከርካሪ ላይ በፈጸሙት የቦምብ ጥቃት 12 ወታደሮቿ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተሰናብቿ የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር አንግሬት ክራምፕ ካረንባወር መግለጻቸውም የሚታወስ ነው:: ከጥቃቱ በኋላ የማሊ ማህበራዊ አንቂዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ማሊያውያን "ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት አያሌ አሻጥር በሃገሪቱ ፈጽማለች፤ ሕዝባችንንም ለማያባራ ሰቆቃና እልቂት ዳርጋለች" ያሏትን ፈረንሳይ በጽኑ በማውገዝና ሰንደቅ ዓላማዋን በአደባባይ በማቃጠል ጭምር ቁጣቸን በመዲናዋ ባማኮና በተለያዩ ከተሞች የገለጹ ሲሆን የሩሲያን ባንዲራ በመያዝ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞችም በመፈክሮቻቸው "ባይ ባይ ፈረንሳይ, ዌልካም ራሽያ! "ቫግነር ማሊን ነጻ ያወጣታል!" የሚሉና የሩሲያውን ቅጥረኛ ወታደራዊ ድርጅት ቫግነው ወደ ማሊ መምጣት በይፋ የሚደግፉ መልዕክቶች ሲያንጸባርቁ ታይተዋል:: አንድ የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪ "ቫግነር ሶሪያን ነጻ አውጥቷል:: ቫግነር ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክን ከሰቆቃ ገላግሏታል:: እኛም ማሊን ከሽብርተኞች ጥቃት ስለሚታደጋት በባማኮ መዲና እንኳን ደህና መጣህ ብለን እንቀበለዋለን:: ዛሬ የፈረንሳይና አፍሪቃ ግንኙነት ያበቃል" ሲል ለጋዜጠኞች ገልጿል::

የክረምቱ ዶፍ ዝናብና የፈረንሳይ ወታደሮች ጭና ያልበገራቸው በርካታ ማሊያውያን ለዓመታት ዋና የጦር ቤዙን ማሊ ቲምቡክቱ ግዛት አድርጎ አክራሪ "ጅሃዲስቶችን ከሳህል ቀጣና አካባቢ ሃገራት ጠራርጌ አጠፋለሁ" የሚል ዘመቻ የከፈተው የፈረንሳይን ጦር ችግሩን ይበልጥ አባብሶትና አወሳስቦት ቆይቷል በማለት ከፍተኛ ትችትና ቅሬታቸውን በአደባባይ ሲያንጸባርቁ ቆይተዋል:: እናም ከሶስት ሳምንታት በፊት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ማብቂያ ላይ ዳግም በተቀጣጠለው አመጽ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎቹ ጭምር ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ በሕዝብ የተቃውሞ ማዕበል ከተገታ በኋላ በተፈጠረው ግጭት ሁለት ሰላማዊ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተው ከ 18 በላይ ከቆሰሉ በኋላ ዳር እስከዳር የተቀጣጠለው ፀረ-ፈረንሳይ የበቃ ንቅናቄ ስጋት ውስጥ የከተታት ፈረንሳይ ጦሯን ከሃገሪቱ ለማስወጣት ተገዳለች:: ውሳኔውን ደግሞ ማሊያውያን እንደ ታላቅ እፎይታ ቆጥረውታል:: ለበርካታ ቀናትም ደስታቸውን በአደባባይ በጭፈራ በሆታ ሲገልጹ ታይተዋል:: ከፈረንሳይ ጦር መውጣት በኋላ ደስታውን አደባባይ ለመግለጽ የወጣ መሃመድ ሙሳ የተባለ ሌላው የባማኮ ነዋሪም "የፈረንሳይ ጦር መውጣቱን ሳይ ልክ በደስታ ነው የጨፈርኩት:: ምክንያቱም ሰላምና ደህንነታችንን ያረጋግጣሉ ብለን ከፍተኛ ዕምነት ብንጥልባቸውም ችግሩን የበለጠ አስከፊና ውስብስብ አድርገውታል" ሲል ቅሬታውንም ደስታውንም ገልጿል::

Mali I französische Soldaten in Timbuktu
ምስል Thomas Coex/AFP/Getty Images

የሩሲያው የዋግነር ግሩፕ ጦር ማሊ መግባትና የምዕራባውያን ድንጋጤ

የሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ ጦር ማነው?

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን የቅርብ ወዳጅ መሆናቸው የሚነገረውና በ 2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሩሲያ ከፍተኛ የሳይበር ጥቃቶችንና የመረጃ ቅስቀሳዎችን ጭምር በማድረግ ዶናልድ ትራምፕ ለስልጣን እንዲበቁ አድርጋለች ከሚለው ውዝግብ ጀርባም ምርጫውን ለማዛባት እጃቸውን አስገብተው ነበር ተብለው የሚወነጀሉት ቱጃሩ ይቭጊኒሽ ፕሪጎዥን አወዛጋቢውን የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ድርጅት ዋግነርን በገንዘብ የሚደጉሙና በዋናነት የሚዘውሩት መሆናቸውንም የአሜሪካው ፎሪን ፖሊሲ መጽሔት በ 2020 ዓ.ም የሩሲያውን ገለልተኛ የዜና ምንጭ ናቫልያ ጋዜጣ በምንጭነት ጠቅሶ ለመጀመሪያ ጊዜ መዘገቡ የሚታወስ ነው:: ከመደበኛው የሩሲያ ወታደሮች 10 እጥፍ ክፍያ ያገኛሉ የሚባሉት የቫግነር ቅጥረኛ ወታደሮች ድርጅት የጦርነት ስትራቴጂ በመንደፍ፣ ወታደራዊ የቴክኒክ እገዛና የጦር መሳሪ አቅርቦት በማድረግ እንዲሁም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ልዩ ስልጠና የወሰዱ ተዋጊዎቹን ጭምር በማሰለፍ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያጋብስ ህገወጥ ድርጅት መሆኑን በመጥቀስ የተለያየ ተቃውሞና ውግዘት እየቀረበበት ይገኛል:: በዩክሬን ሩሲያ አፍቃሪ ተገንጣይ ቡድኖች ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጉ የሚጠቀሰው ዋግነር ከ 2019-2020 ባለው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ከአንድ ሺህ የሚልቁ ተዋጊዎቹን ወደ ሊቢያ ልኮ ከተቀናቃኙ የሊቢያው የጦር አበጋዝ ጄኔራል ኻሊፋ ኻፍጣር ጎን በመሰለፍ በማዕከላዊ መንግሥቱ ላይ ውጊያ ማድረጉን አንድ የቀድሞው የድርጅቱ ተዋጊ ለመገናኛ ብዙሃን አጋልጧል:: ከአሁን ቀደምም ዋግነር በሶሪያ፣ በሞዛምቢክ፣ በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክና በቬንዙዌላ ጭምር በእርስ በእርስ ግጭቶች ቅጥረኛ ወታደሮቹን ማሰማራቱ ሲጠቀስ የዛሬ ወር በማሊ የፈረንሳይ ወታደሮች የዘጠኝ ዓመታት ተልዕኮዋቸውን አጠናቀው ከወጡ በኋላ የጸረ ሽብር ዘመቻ በሚል ሽፋን ቫግነር ግሩፕ በሃገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት ጥሪ ቀርቦለት ከቀናት በፊት በቀድሞ የፈረንሳይ ጦር ማዘዣ ከተማ ቲምቡክቱ ታጣቂዎቹን ማስፈሩ ይፋ ሆኗል:: ስልጣን በሚጨብጡ ኃይላት ሹክቻ በጽንፈኛ ኃይሎች የማያባራ ጥቃትና በምዕራባውያን መንግሥታት ጣልቃ ገብነት ዛሬም ድረስ የምትናጠው ማሊ በቅርቡ ከሃገሪቱ ለቆ የወጣውን የፈረንሳይ ጦር እግር ተከትሎ የሩሲያው ቫግነር ቅጥረኛ ሰራዊት በአካባቢው መስፈሩም በአሜሪካናና ምዕራባውያን ሸሪኮቿ ዘንድ ድንጋጤና ኃይለኛ አቧራን አስነስቷል:: አሜርካ ካናዳ ጀርመንና ብሪታንያን ጨምሮ 15 የምዕራባውያን ሃገራት የአውሮጳ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከስሰሞኑ ባወጡት መግለጫ የቫግነር ተዋጊ ኃይላት በማሊ መስፈር በሳህል ቀጣና የተጀመረውን ሰላም የማስከበር ተልዕኮ የሚያደናቅፍ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈፀም የሚያደርግና አካባቢውን ለማያባራ ግጭት የሚዳርግ ነው ሲሉ ክፉኛ ኮንነውታል::

Europäische Soldaten in Mali
ምስል Blondet Eliot/ABACA/picture alliance
Mali I 900 archäologischen Objekte aus den USA nach Mali zurückgeführt
ምስል Annie Risemberg/AFP

ባለፈው ወር አጋማሽ የሩሲያውን ቅጥረኛ ዋግነር ግሩፕ ስም በጥቁር መዝገብ ሊስት ውስጥ በማስፈር ማዕቀብ የጣለበት የአውሮጳ ሕብረት ይህ እርምጃ የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በህብረቱ የማዕቀብ ማዕቀፎች ላይ ማሻሻያ በማከል "የአውሮፓ ህብረት የማሊ ሰላም፣ ደህንነት ወይም መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥሉ ወይም የፖለቲካ ሽግግሩን ትግበራ ለማደናቀፍ ተጠያቂ በሆኑ ግለሰቦች እና አካላት ላይ ገዳቢ እርምጃዎችን እንዲወስድ ያስችለዋል" ብሏል:: በዚህ በዓይነቱ ልዩ ነው በተባለለት ውሳኔም የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በማሊ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የተሳተፉ ግለሰቦችን የንብረትና የጉዞ እገዳን ለመጣል የሚያስችላቸውን ሰነድ አጽድቀዋል:: የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንትና የውጭና የደህንነት ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል የዋግነር ድርጅት በበርካታ ሃገራት ሰብዓዊ ጥሰትን በመፈፀሙ ማዕቀቡ እንደተጣለበት ተናግረዋል::"የሩሲያው ዋግነር በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ሃገራት ግጭቶች ውስጥ እጁን በማስገባት ጥቃትን በማቀነባበር የሚፈጽም፣ ተልዕኮ ወስዶ አመራሮችን የሚገድል፣  የጦር ወንጀልን የሚያቀነባበር፣  መንግሥታትን ላይ መፈንቅለ መንግስት ኩዴታ እንዲካሄድ እገዛ የሚያደርግ፣ ግለሰቦች ላይ አካልን የሚያሰቃዩ ቶርቸሮችንና ግድያዎችን የሚፈጽምና በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም የሚወነጀል ነው" ብለዋል ቦሬል::

በማሊ ወታደራዊ አስተዳደር ወደ ዴሞክራሲያዊ የሚያሸጋግር ምርጫ በቅርቡ ለማካሄድ ፍላጎት አላሳየም ሰብዓዊ መብትንም እያከበረ አይደለም ያለችው አሜሪካ ወታደራዊው ጁንታ ምዕራባውያንን ገሸሽ አድርጎ በሃገሪቱ የሩሲያ ቅጥረኛ ጦር እንዲሰማራ መፍቀዱም ክፉኛ እራስ ምታት እንደሆነባት ስሜቷን ያንጸባረቀችባቸው የተለያዩ መግለጫዎቿ ዋቢ ናቸው:: ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በያዝነው አዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት መግቢያ ላይ ማሊን ጨምሮ ኢትዮጵያንና ጊኒን ለአፍሪቃ ሀገራት ከሰጠችው የቀረጥና ታሪፍ ነፃ መብት /AGOA/ መሰረዟን በይፋ አስታውቃለች:: ከሰሞኑም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው ተጨማሪ መግለጫም በአሜሪካ መንግስት በብሪታንያና በአውሮጳ ሕብረት ጭምር በሩሲያ መንግሥት የሚደገፈው የቫግነር ዋና አመራር ይቭጊኒሽ ፕሪጎዥን እና ድርጅቱ ማ ዕቀብ እንደተጣለባቸው አውስቷል::ይህ እንደ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ ዩክሬንና ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክን በመሳሰሉ ሃገራት አሰቃቂ ተግባራትን እና ከፍተኛ የመብት ጥሰት ሲፈጽም የነበረ ድርጅት አሁንም በማሊ ለሚያካሂደው ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሕዝብ አገልግሎቶችን ለመደገፍና የማሊን የጦር ኃይሎች ለማጠናከር ይውል የነበረ ገንዘብ በወር 10 ሚልዮን ዶላር ወጪ እየተደረገ እንደሚከፈለው መረጃው ደርሶናል በማለት ድርጊቱን አውግዞታል:: ድርጅቱ በማሊ ሰላምን ከማስፈን ይልቅ በሂደት ሃገሪቱ እንድትፈርስ ሊያደርግ ይችላል ሲልም አስጠንቅቋል:: በሌላ በኩል የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቫሮቭ በቀጥታ የዋግነርን ስም ባይጠቅሱም የማሊ መንግሥት የሽብር ጥቃትን ለመከላከል የሩሲያ ወታደራዊ ድርጅቶችንና ተቋማትን እርዳታ መጠየቁን በማውሳት ያ ማለት ግን ከሩሲያ መንግሥት ጋር ምንም ቀጥታ ግንኙነት የለውም በማለት በደፈናው ለመገኛ ብዙሃን ገልጸዋል::

"የማሊ መንግሥት የፈረንሳይ ሰላም አስከባሪ ጦር ለቆ ከወጣ በኋላ የሩሲያ ወታደራዊ ተቋማት በጸረ ሽብር ዘመቻው እገዛ እንዲያደርጉ ጥያቄ አቅርቧል:: ይህ ደግሞ ከእኛ መንግስት ጋር ምንም ቀጥታ ግንኙነት የለውም::  አፍሪቃውያን የውስጥ ችግሮቻቸውን በራሳቸው የመፍታት አቅምና ችሎታ እንዳላቸው እናምናለን:: ሆኖም በእኛ በኩል ማሊ መከላከያ ጦሯን በወታደራዊ ቴክኒክ ለማጠናከርና ቀደም ሲል የነበሩንን ስምምነቶች በሙሉ ለማክበር በተለይም ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ለሚደረገው ጥረት ተጨማሪ እርዳታና ድጋፍ የመስጠት ፍላጎት አለን" በማለት ላቫሮቭ በአሁኑ ወቅት ዓለምን በሚያወዛግበው ዋግነር ዙሪያ ምላሻቸውን ሰጥተዋል:: እስካሁን በማሊው ግጭትና የአሸባሪዎች ጥቃት ለቁጥር የሚታክቱ ንጹሃን ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይነገራል::የወርልድ ቪዥን ጥናት እንደጠቆመው እስካሁን በማሊ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ 112 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ጎረቤት ቡርኪናፋሶ ሞሪታንያና ኒጀር ሲሰደዱ ከእሩብ ሚልዮን የሚልቁ ሰዎችም ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል:: ለመሆኑ እንዲህ በሰላም እጦትና በውጭ ኃይላት ጫና ስር የወደቀችው ማሊ አሁን ከገጠማት ውስብስብ ቀውስ በፍጥነት ትላቀቅ ይሆን? በጊዜ ሂደት አብረን የምናየው ይሆናል::

Mali I Bamako
ምስል Nicolas Remene/Le Pictorium/imago images

እንዳልካቸው ፈቃደ

ታምራት ዲንሳ