1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ጥር 5 2015

የህወሓት ተዋጊዎች ከባድ ጦር መሳሪያቸዉን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ማስረከባቸዉ፣ የኦሮሚያ በጣሙን ምዕራብ ኦሮሚያ ዉስጥ የሚደረገዉ ግጭት፣ጥቃትና ግድያ አሁንም መፍትሔ አለማግኘቱና ኢትዮጵያዉን አትሌቶች በትግራይ ያደረጉት ጉብኝት ሳምንቱንየማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታዮችን ትኩረት የሳቡ መስለዋል

https://p.dw.com/p/4M6Bg
Äthiopien Tigray | Waffenübergabe der Rebellen an Armee
ምስል Ethiopian Broadcasting Corporation

የሕወሓት ትጥቅ መፍታት፣የወለጋዉ ግጭት፣ የአትሌቶች ጉብኝት በመቀሌ

 

ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተዋጊዎች ከባድ ጦር መሳሪያቸዉን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ማስረከባቸዉ፣ የኦሮሚያ በጣሙን  ምዕራብ ኦሮሚያ ዉስጥ የሚደረገዉ ግጭት፣ጥቃትና ግድያ አሁንም መፍትሔ አለማግኘቱና ኢትዮጵያዉን አትሌቶች በትግራይ ያደረጉት ጉብኝት ሳምንቱን የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታዮችን ትኩረት የሳቡ መስለዋል።በሶስቱ ርዕሶች ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች ስድብና ዘለፋዉን ነቅሰን ባጫጭሩ እንቃኛለን።አብራችሁን ቆዩ።

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተዋጊዎች ከባድ ጦር መሳሪያዎቻቸዉን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ባለፈዉ ማክሰኞ አስረክበዋል።የጦር መሳሪያ ርክክቡ ከመቀሌ በቅርብ ርቆት ላይ በምትገኘዉ አጉላዕ ከተማ መደረጉን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣የህወሓት ጦር አዛዦችና የአፍሪቃ ሕብረት ተቆጣጣሪዎች አረጋግጠዋል።

የጦር መሳሪያዉ ዓይነት፣ብዛትና ከእንግዲሕ የሚኖረዉ አገልግሎት አልተነገረም።ይሁንና ርክክቡ  የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስትና ሕወሓት ሁለት ዓመት ያስቆጠረዉን ጦርነት ለማቆም ባለፈዉ ጥቅምት የተፈራረሙትን ስምምነት ገቢር የማድረጉ ሒደት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን እንደሚያመለክት ተረካካቢዎቹና ታዛቢዎቹ አስታዉቀዋል።

የሕወሓት ዋና ተደራዳሪ ጌታቸዉ ረዳ በትዊተር ገፃቸዉ «ትግራይ» ያሉት ፓርቲያቸዉ ጦር መሳሪያዎቹን ማስረከቡ «ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ገቢር ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረዉ ተስፋ እናደርጋለን፣ እንጠብቃለንም።» ብለዋል።«ተስፋ እናደርጋለን።እንጠብቃለን»ደገሙት አቶ ጌታቸዉ በትዊተር።

Äthiopien Sportler aus Tigray in Mekele angekommen
ምስል Million Hailesilassie/DW

አቢሲኒያ የጥቁሮች መነሃሪያ፣ የሚል የፌስ ቡክ መጠሪያ ያለዉ አስተያየት ሰጪ «ሰላም ይሻላል» አለ ባጭሩ። ሁሴይን አፋርም በፌስ ቡክ «ለሀገራችን ከሰላም የተሻለ ነገር የለም።» ባይ ነዉ»ከ2ቱም ወገን ይህንን በጎ ተግባር የፈፀማቹህ አካላት እጅግ በጣም ልተመሰገኑ ይገባል።« አከለ ሁሴይን አፋር።ማሳሰቢያ ብጤም አለዉ-ሑሴይን «በዚህ አጋጣሚ ኤረትራ ና የአማራ ክልል መልሸያ መሳይ ኋይሎች ክልሉን በአሰቸኳይ ለቆዉ እንድወጡ መንግሰታችን ሳይውል-ሳያደር ማድረግ አለበት።ሐሰን ዓሊ ግን እሱም በፌስ ቡክ ህወሓት ጦር መሳሪያ አስረከበ መባሉን የተቀበለ አይመስልም።«70 በመቶዉን ቀብሮ 30 በመቶዉን ርክክብ ይላል» ሐሰን ዓሊ ነዉ እንዲሕ ባዩ።

አበበ ሮባም እንደ ሐሰን ሁሉ የጦር መሳሪያ ርክክቡን እዉነተኝነት አልተቀበለዉም « የወላለቀ፣ የማይሠራ መሳሪያ አስረክበው ‘አስረከቡ’ ይባላል ወይ ቁማር» እያለ ቀጠለ አበበ ሮባ በፌስ ቡክ።አቡ ፊሊሞንም «የራሳቸዉን ትጥቅ መለሱ» በሚል ይስተካከል» ይላል።እዮብ፣ እዮብ ግን ጥያቄ ብጤ አለዉ ግን ለማን እንደሁ በግልፅ አልጠቀሰም፣ ብቻ ጥያቄዉን እነሆ«የተበተነ ዱቄት አላላችሁም እንዴ?ከየት አመጣችሁት?»እዮብ እዮብ ነዉ ጠያቂዉ።ጥያቄዉ እናንተን ከተመለከተ እባክችሁ መልሱለት።

እሸቱ ፈቃደ ትጋ አጠቃላዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካና ከሱ በፊት የተሰጡ አስተያየቶች ስልችት ያሉት ይመስላል።ግን ላይሰለችም ይችላል።ብቻ እንዲሕ ብሎ ፃፈ በፌስ ቡክ «የኢትዮጵያኖች ፓለቲካ የብሽሽቅ እና መርህ አልባ እየሆነ ነው።»

 

ሁለተኛዉ ርዕስ ከትግራይ ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ይወስደናል።በሐሳብ።የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስትና ሕወሓት ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ ዉጊያ ከመግጠማቸዉ በፊት ምዕራብ ኦሮሚያ በግጭት፣ዘርን መሰረት ባደረገ ጥቃትና ግድያ ስትመሰቃቀል ነበር።ግጭት፣ጥቃት ግድያዉ የጥፋት አድማሱን እያሰፋ አብዛኛዉን የኦሮሚያ አካባቢን አዳርሷል።ለ4ኛ ዓመት እንደቀጠለ ነዉ።

ከየጥቃት ግድያዉ ያመለጡ ተፈናቃዮች፣ የዓይን ምስክሮችና የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት በጥቃቱ የተገደለዉ ሰዉ ቁጥር በብዙ ሺሕ ይቆጠራል።አንዳዱi ስፍራ የሚፈፀመዉ ግድያና ግፍ፣ያዩ እንደሚሉት ለሌሎች ለመናገር እንኳን የሚከብድ ዘግናኝ ነዉ።

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ሰሞኑን ባወጣዉ ዘገባ ደግሞ በምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ዉስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የመንግስት ፀጥታ ኃይላት በ«ኦነግ-ሸኔ ላይ» በከፈቱት ዘመቻ ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል፣ዘርፈዋል፣አንገላተዋልም።

ናኒ የናትዋ ልጅ በፌስ ቡክ ለኢሰመጉ ያለመችዉን መልዕክት ፅፋለች «ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ምንም ሊያመጡ አይችሉም» ብላ።ታምራት ብዙነሕ ቸርቀና ግጭት ግድያዉ የሚቆመዉ «ከዘረኝነት የተላቀቀ መንግስት ሲመጣ ነዉ« ይላል በፌስ ቡክ።«ከዚሕ ሁሉ ግድያ ጀርባ ያለዉ» ይላል ሐይሉ ደነቀ የም፣ ዘለግ ባለ በፌስ ቡክ መልዕክቱ «እኔ ልግዛ የሚል የፖለቲከኞች ቁማር መሆኑ ይታወቅ»።ምሳሌ ጠቅሷልም ኃይሉ ደነቀ የም---አንጠቅሰዉም።

ሸዋ ጌች ካሳ «እራሱም ከኦሮሚያ ተፈናቃለዉ ደብረ ብርሐን ከሰፈሩ አንዱ መሆኑን ይገልጻል።«ከዛሬ ነገ ወደ ቀያችን እንመለሳለን ብለን ስንጓጓ ጭራሽ ቁጥሩ እየጨመረ መጠለያ አንኳ አጥተን ሜዳ ላይ ወድቀናል»----ሸዋ ጌች ካሳ ነዉ ይኽን ባዩ።«ችግራችንን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ብታሳዉቁሉን?» በማለትም ይማፀናል።

ሌሊሳ አብዲሳ---- ተስፋ የቆረጠች ትመስላለች።ያዉ -እሷም በፌስ ቡክ «የአማራ ሸኔና የኦነግ ሸኔ እያለ ምን ይቆሟል ብለክ ነዉ» አለች ግጭትና ጥቃቱን ማለቷ ነዉ።ኦሮሚያን ለፉማ የሌሊሳን ሐሳብ ይጋራል።መፍትሔዉ በሶስት ወገኖች እጅ ነዉ ባይ ነዉ።«በሁለቱ ወገን የተሰለፉ ሸኔዎች ሂሳብ የማወራረድ ስራቸውን አቁመው ወደ ሰላማዊ የጠረጴዛ ንግግር ሲመጡና መንግስት ወደማያዳላ እርምጃ ሲያመራ የሚፈለገው (ሰላም) ይመጣል»  ትዕምርተ አጋኖ አክሎ በታል ኦሮሚያን ለፉማ በፌስ ቡክ አስተያየቱ።!

Äthiopien Sportler aus Tigray in Mekele angekommen
ምስል Million Hailesilassie/DW

መስፍን ተካ  የናፈቀዉ ሌላ ነዉ።ሳቁ።«አረ ሳቄ ናልኝ»----መጥሎት ይሆን?

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት ደራርቱ ቱሉ የተመራ የፌዴሬሽኑ ባለስልጣናትና ታወቂ አትሌቶች የሚገኙበት ቡድን ሰሞኑን መቀሌ-ትግራይን ጎብኝቷል።የቀድሞዋ የኦሎምፒክ አሸናፊና የዓለም ሻምፒዮን ደራርቱ ቱሉ የመራችዉ ቡድን ካስተናበራቸዉ አባላቱ መከከል በተለያየ ርዕሰት በተደጋጋሚ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊና ክብረ-ወሰንን የያዙት እትሌት ለተሰንበት ግደይ፣ ጎተይቶም ገብረሥላሴ እና ጉዳፍ ፀጋይ ይገኙበታል።

የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ አትሌቶች በሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት ምክንያት ወደ ትዉልድ አካባቢያቸዉ መጓዝ አልቻሉም ነበር።አትሌቶቹ ሁለት ዓመታት ግድም ከተለዩአቸዉ ከወላጅ፣ወዳጅ፣ ዘመዶቻቸዉ ጋር ሲገናኛ የሰሞኑ የመጀመሪያቸዉ ነዉ።አንዳዶቹ አትሌቶች ከወላጆቻቸዉ ጋር ሲገናኙ የሚያሳየዉ የዶቸ ቬለ ቪዲዮ ባጭር ጊዜ ዉስጥ በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ተመልክቶታል።አብዛኛዉ አስተያየት ሰጪም የአትሌቶቹንና የቤተሰቦቻቸዉን ደስታ ተጋርቷል፤ ቡድኑን ለመራችዉ ለአትሌት ደራርቱም አክብሮትና አድናቆቱን ዘርግፎታል።

 

ሙባረክ መሐመድ በፌስ ቡክ ባሰፈረዉ አጭር መልዕክት « የብሔራዊ ቡድኑን መለያ ለብሳችሁ በመሔዳችሁ ደስ ብሎናል» አለ እና  «ሀገር ማለት ይህ ነው። ያምራል» ብሎ ቀጠለ።እምባዬ ወልደማርያምም --«ፍቅርና አንድነትን የሚያጠናክር ተግባር» ይለዋል ጉብኝቱን።አይቼዉ BN በለጠ አትሌት ደራርቱን ያደንቃል በፌስ ቡክ «ጀግና አትሌት ደራርቱ ፖለቲካ ያማያናዉጣት ምርጥ ኢትዮጵያዊት ሴት» እያለ።ኢብሮ ድሬዳዋ ደግሞ ደራርቱን «የሁሉም እናት» አላት።በኮኮብ ባሸቀረቀረዉ አጭር የፌስ ቡክ ፅሁፉ።

ሰኚኮ ረብራ «ብቻዋን ሀገር የሆነች ሴት« ይላታል ደራርቱን።

Äthiopien | Oromiya Region
ምስል Fischer/Bildagentur-online/picture alliance

የሕወሓት ዋና ተደራዳሪ አቶ ጌታቸዉ ረዳም በትዊተር በእንግሊዝኛ ባሰፈሩት ፅሁፍ «ጀግኖቻችን እንኳን ወደ ሐገራችሁ መጣችሁ።» ብለዋል ከአትሌቶቹ ጋር የተነሱትን ፎግ ግራፍ አስደግፈዉ ባሰፈሩት ፅሁፍ »አትሌቶቹ ትግራይን እንዲጎበኙ ሁኔታዉን ያመቻቹትን አትሌት ደራርቱ ቱሉንና የፌደራሉ መንግስትን ያመሰግናሉም።

ሲሳይ ፈለቀ በተደራራቢ ትዕምረተ-ቃል አጋኖ በሳረገዉ ፅሑፉ «ፍቅር የአንድነት ኃይል ነዉ» ይላል በፌስ ቡክና በእንግሊዝኛ ቋንቋ።ፍልስፍና ብጤ አስተያየቱን ቀጠለ ሲሳይ ፈለቀ «አንድ ፍቅር ብዙ ጥላቻዎችን  ያጠፋል» እያለ።በዚሕ አላበቃም።ወደ ሳሚ ዓይናለም አስተያየት እንለፍ ኮምጨጭ ያለች ጥያቄ፣ ትችት ምናልባት ምክር ብጤም ናት።«ዝም ብሎ ለይስሙላ ድቤ ከመምታት እውነተኛ እና ዘላቂ ሰላም የሚመጣበትን መፍትሄ መፈለግ አይሻልም ?» ሌላም ብሏል እኛ እንለዉም።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ