1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙስና እና የመብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች የፍርድ ቤት ውሎ

ሰኞ፣ ኅዳር 10 2011

በሰብዓዊ መብት ጥሰት በሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው  ዛሬ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ልደታ ምድብ 10ኛ  ቀርበው ዋሉ። ፍርድ ቤት የቀረቡት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ወንድማቸው አቶ ኢሳያስ ዳኘው እና የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት የሥራ ባልደረባ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ናቸው።

https://p.dw.com/p/38Xqj
Justitia mit Pendelwaage
ምስል picture-alliance/Ulrich Baumgarten

 

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳያቸዉ የታየዉ የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት የሥራ ባልደረባ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በሰብዓዊ መብት ጥሰት በሙስና ወንጀል መጠርጠራቸዉን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤት መግለፁ ተዘገበ። አቶ ተስፋዬ የደህንነት መምሪያ ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ ሰዎችን በሽብር ተጠርጥራችኋል በሚል በስውር እስር ቤት በማሰርና በማሰቃየት፥ እርቃናቸውን በካቴና አስረው ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ በማቆየት፣ ግለሰቦችን ባልተገባ መልኩ ለስቅየት በመዳረግ መጠርጠራቸዉን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። ከዚህ ሌላ በሽብር ከተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ገንዘብ በመቀበል እና በሀዋላ ከተጠርጣሪዎች ላይ ሕገ ወጥ ገንዘብ በመቀበል በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል መጠርጠራቸዉንም መርማሪ ፖሊስ መናገሩን የሃገር ዉስጥ መገናኛዎች ዘግበዋል። በሌላ በኩል ጠበቃ መያዝ አልችልም ብለዉ የነበሩት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው የግል ጠበቃ ይዘዉ መቅረባቸዉ ተነግሮአል። ሆኖም ተጠርጣሪው ከግል ጠበቃቸው ጋር መገናኘት እንዳልቻሉ እና መርማሪ ባለበት የተገናኘን በመሆኑ ሚስጥር ማውራት አልቻልንምና ለመወያየት ጊዜ ይሰጠኝ ብለው በመጠየቃቸው ፍርድ ቤቱ ሌሎች ጉዳዮች እስከሚታዩ ድረስ ብሎ እንዲወያዩ መፍቀዱ ታዉቋል። ባለፈው ዐርብ መንግሥት ለሜጄር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ያቆመላቸውን ጠበቃ ማንሳቱ ይታወሳል። የሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ወንድም ኢሳያስ ዳኘው በፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባስመዘገቡት ሐብት መሰረት በግል ጠበቃ ለማቆም የሚያስችላቸው በመሆኑ በመንግስት የተመደበው ተከላካይ ጠበቃ እንዲነሳ መደረጉም ታዉቋል። ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ ጠበቆችን ማብራሪያ አድምጦ ለህዳር 13 ቀን፣ 2011 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
መርጋ ዮናስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ