ጠበቆቻቸው ሊፈቱ ይችላሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል
ረቡዕ፣ ጥር 30 2010ማስታወቂያ
አራት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በሥር ፍርድ ቤት የተወሰነባቸው ቅጣት የሕግ ስሕተት አለበት በማለት ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለዋል። በጠበቆቻቸው በኩል ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን ያቀረቡት አሕመዲን ጀበል፣ ካሊድ ኢብራሒም፣ አሕመድ ሙስጠፋ እና መሐመድ አባተ ናቸው። ጠበቃ መሐመድ አብደላ ከችሎቱ በኋላ እንደተናገሩት "ደንበኞቻችን ይግባኝ የማቅረብ ፍላጎታቸውን ከገለጹ ከሶስት አመታት በላይ ሆኗቸዋል" ሲሉ ተናግረዋል። ጠበቃ መሐመድ ደንበኞቻቸው የተፋጠነ ፍትኅ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል። አሕመዲን ጀበል፣ ካሊድ ኢብራሒም፣ አሕመድ ሙስጠፋ እና መሐመድ አባተ ከ7-22 አመታት ተፈርዶባቸው ማረሚያ ቤት ይገኛሉ። ጉዳዩን ያዳመጠው ፍርድ ቤት ለመጋቢት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል። ጠበቃ አዲስ አሕመድ እና ጠበቃ መሐመድ አብደላ ግን ደንበኞቻቸው ከዚያ በፊት ሊፈቱ ይችላሉ የሚል ተስፋ አሳድረዋል።
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር
እሸቴ በቀለ