1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጭው ምርጫ ተግዳሮቶች

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 22 2010

በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ የተሟላ እና ፍትሃዊ በማድረግ ሁሉን አቀፍ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለመመሥረት በርካታ ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ እንደሚገባ ተገለጸ።

https://p.dw.com/p/33tHf
Äthiopien Parlamentswahlen
ምስል DW/Y. G. Egziabhare

ከወዲሁ መግባባት እና ሥምምነት ላይ ሊደረስ ይገባል

በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ የተሟላ እና ፍትሃዊ በማድረግ ሁሉን አቀፍ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለመመሥረት በርካታ ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አስናቀ ከፍአለ ለዶቼቨለ ገልጸዋል :: ከምርጫው በፊት ነጻ እና ገለልተኛ የሆኑ የዲሞክራሲያዊ ተቋማት ሊገነቡ ይገባል የሚሉት ባለሙያው ከሥነ ምግባር ብልሹነት እና ሙስና በጸዱ ገለልተኛ ሰዎች ምርጫ ቦርዱን ማደራጀት ቅሬታዎች የሚዳኙበትን ነጻ የፍርድ ሥርዓት መመሥረት እና ለምርጫው አፈጻጸም ዕንቅፋት የሆኑ ድንጋጌዎችንም ከሕገ መንግሥቱ እና ከምርጫ ሕጉ ማሻሻል ተገቢ ነው የሚል ዕምነት አላቸው::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገዥው መንግሥት ኢሕአዲግ ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ የማራዘም ሃሳብ እንደሌለው ገልጸዋል :: በምርጫው ውጤት የሚከሰቱ ውዝግቦችንም ለማስቀረት ያለምንም ኮሮጆ በዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ መንገድ ምርጫው በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንደሚካሄድ ነው ያስታወቁት :: በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አስናቀ ከፍአለ ለዶቼቨለ እንደገለጹት መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋቱ እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አገር ውስጥ እንዲገቡ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ በጎ ጅማሮ ነው :: ያም ቢሆን ይላሉ የፖለቲካ ጠበብቱ ከምርጫው በፊት በሁሉም ዘንድ ቅቡልነት ያላቸው ነጻ እና ገለልተኛ የሆኑ የዲሞክራሲያዊ ተቋማት ከወዲሁ ሊገነቡ ይገባል :: ለዚህም በኬንያ እና በሌሎችም የአፍሪቃ አገራት ውጤት ካመጡ የምርጫ አፈጻጸም ተሞክሮዎች ግንዛቤ እና ልምድ መቅሰም ጥሩ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል :: ለዚህም ተቃዋሚውም ሆነ ገዥው ፓርቲ ዓመኔታ የሚያሳድሩበት ምርጫውን የሚያስተዳድር ተቋም መገንባት አማራጭ የለውም :: ልምሳሌ እ.ኤ.አ በ 2010 ዓ.ም ላይ ኬንያ ሕገ መንግሥታቸውን ካወጡ በኋላ ፍርድ ቤቱን ሲያደራጁ የተከተሉት ሂደት ነበር :: ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚሾሙ ሰዎችን ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ ቀደምት ታሪካቸውን በመመርመር ከዚህ በፊት ከሙስና ወንጀል ጋር ንክኪ የሌላቸውን ሰዎች መርጦ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመሾም ችግሮችን ለመቅረፍ ሞክረዋል :: እንዲህ ዓይነቱን ተሞክሮ በመውሰድ እና ሌሎችም ጠቃሚ ልምዶች ላይ በሰፊው በመነጋገር ሁሉም ፓርቲዎች ዓመኔታ ሊጥሉባቸው የሚችሉ ሰዎችን የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽን ውስጥ ማስገባት የተሻለ እንደሆነ ምንም ጥርጠር አይኖረውም ብለዋል ዶክተር አስናቀ ::
የፖለቲካ ተንታኙ ዶክተር አስናቀ የምርጫው ሕግ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን በጊዜ ማረም በተለይም ከውጭ ሃገራት የገቡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ ማካሄድ ምርጫውን ከሁከት እና ግርግር ነጻ እንዲሆን ሥልት መንደፍ እንዲሁም የምርጫውን ሂደት ተአማኒነት የተሟላ ለማድረግ ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ፍትሃዊ የሚድያ አጠቃቀም የሚያገኙበትን መንገድ ገቢራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል :: ምርጫው ካለቀ በኋላም ቢሆን የሚነሱ ቅሬታዎች በምን ዓይነት የፍትሕ ሥርዓት እንደሚዳኙ ከወዲሁ መግባባት እና ሥምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚገባም ጠቁመዋል :: የፖለቲካ ተንታኙ ዶክተር አስናቀ ይህን ሲያብራሩ የምርጫ ቅሬታ እና ውዝግብ ሲነሳ ባለፈው ሁለት እና ሶስት ዓመታት ያየነው የፍርድቤትን በከፍተኛ በከፍተኛ ሁኔታ መዳከም ነው ሲሉ ነው የጠቀሱት :: እናም አሁን ያለው የፍርድ ቤት ተቋም እንዴት ነው ? ምን ምን ማሻሻያዎች ሊደረጉ ይገባል? ከዚሁ ጎን ለጎንም ራሱን የቻለ የምርጫ ፍርድ ቤት መመስረት ያስፈልጋል ወይስ አሁን ያለው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው የምርጫ ውዝግብን ጉዳይ ይገባል? ምን ዓይነት ችሎቶችስ መቋቋም አለባቸው እነማንስ ናቸው በችሎቱ የሚታቀፉት የሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች ተወያይቶ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል :: በአጠቃላይ በዋንኛነት ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል እንደመሆኑ መጠን ከአሁኑ በምርጫው የሚሳተፉ ድርጅቶች በሙሉ ዕምነት ሊያሳድሩበት የሚችል ብሎም የምርጫ ውዝግቦችን እና ቅሬታዎችን በአግባቡ የሚያስተናግድ ፍትህ ተቋም እና ፍርግ ቤት ማቋቋም እና ማሻሻል አስፈላጊ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ባለሙያው አስረድተዋል :: ሃገራዊ ጥቅም እና አንድነትን በማስቀደም ፍርድ ቤቱ ለሚሰጠው ውሳኔም መቻቻል እንደሚገባ መክረዋል:: 
በቅርቡ ፓርቲዎች በሚያገኙት ድምጽ መሰረት በምክር ቤት ውስጥ የተወሰነ ውክልና ብንሰጣቸው በሚል ርዕስ እየተካሄደበት ያለው ውይይት በመንግሥትም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩል የጋራ ሥምነት የሚደረስበት ከሆነ የሕገ-መንግሥቱን ማሻሻያ ቢጠይቅም በአገሪቱ ሁሉን አቀፍ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለመገንባት አጋዥ መሆኑን ነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አስናቀ የጠቆሙት :: የኢትዮጵያ ሕግ መንግሥት ጥምር ዜግነትን ፈጽሞ እንደማይፈቅድ የሚገልጹት የፖለቲካ ተንታኙ ከውጭ የገቡ አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን በተመለከተ በተለይም ጥምር ዜግነትን ይዘው በውድድር የሚሳተፉበት ሂደት ሌላው የሕገመንግሥቱ ድንጋጌ ዳግም እንዲጤን የሚያደርጉ አነጋጋሪ ጉዳዮች መሆናቸውን ነው ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ ዶክተር አስናቀ :: ለአብነት ኢትዮጵያ በሕገመንግሥቷ ጥምር ዜግነትን አትፈቅድም :: አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ከውጭ የገቡ የተወሰኑ ፓርቲ አመራሮች ጥምር ዜግነትን ይዘው መተዋል :: በመሰረቱ ጥምር ዜግነትን መቀበል ጥቅምም ጉዳትም ስለሚኖረው የትኛው ውንደሚያመዝን ለመለየት ሰፊ የምሁራንን ጥናት ምርምር እና ውይይት ይጠይቃል :: ከዚህ ውጭ የተወሰኑ ሰዎች የውጭ ፓስፖርት ስላላቸው በምርጫው እንዲሳተፉ ማድረግ አለብን የሚል ዕሳቤ ውስጥ መግባት ውሎ አድሮ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው :: ባይሆን እንሱ ከደፈሩ የውጭ ፓስፖርታቸውን መልሰው በግልጽ ወደ ምርጫው ውስጥ መግባት አንድ አማራጭ ነው የሚል ምክራቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር አስናቀ ለግሰዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በሰሞኑ ጋዜጣዊ መግለጫቸው በኢትዮጵያ ከ 2 ዓመታት በኋላ የሚካሄደው ምርጫ ተቀባይነት እንዲኖረው ሁሉንም ወገን የሚያግባባ ነጻ እና ገለልተኛ የምርጫ ተቋም እንፈጠራለን ማለታቸው ይታወሳል :: 

Büro des National Electoral Board of Ethiopia NEBE
ምስል DW

እንዳልካቸው ፈቃደ 

አርያም ተክሌ