1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 05 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ መጋቢት 5 2014

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ ዛሬ ማታ ወሳኝ ግጥሚያ ያከናውናል። ትናንት አርሰናል እና ቸልሲ ድል ቀንቷቸዋል። ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ዩናይትድ ፖርቹጋላዊ አጥቂው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ወሳኝ ተጨዋችነቱን ባስመሰከረበት ግጥሚያ ዋነኛ ተፎካካሪው ቶትንሃም ሆትስፐርን ድል አድርጓል። በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ መሪው ባየርን ሙይንሽን ነጥብ ጥሏል።

https://p.dw.com/p/48TDf
BdTD | UK, Londen - Premier League - Arsenal v Crystal Palace
ምስል Hannah Mckay/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ ዛሬ ማታ ወሳኝ ግጥሚያውን ያከናውናል። የዛሬው ውጤት በተለይ እግር በእግር በሚከተለው ሊቨርፑል ደጋፊዎች ዘንድ በልዩ ኹኔታ ነው የሚታየው። ማንቸስተር ሲቲ የደረጃ ሰንጠረዡን የሚመራው በአንድ ጨዋታ ውጤት 3 ነጥብ ልዩነት ብቻ ነው። ትናንት አርሰናል እና ቸልሲ ድል ቀንቷቸዋል። ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ዩናይትድ ፖርቹጋላዊ አጥቂው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ወሳኝ ተጨዋችነቱን ባስመሰከረበት ግጥሚያ ዋነኛ ተፎካካሪው ቶትንሃም ሆትስፐርን ድል አድርጓል።  በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ መሪው ባየርን ሙይንሽን ነጥብ ጥሏል። ላይፕትሲሽ ትናንት ተጋጣሚውን የግብ ጎተራ አድርጓል። በስፔን ላሊጋ መሪው ሪያል ማድሪድ ዛሬ ማታ ማዮካን ይገጥማል። 10ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች እና 3ኛው ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ውድድሮች በትናንትናው ዕለት ተጠናቋል። ለዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድን ዛሬ ማታ አሸኛኘት ይደረግለታል።  

አትሌቲክስ

Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

ወደ ዓለም ዋንጫ ውድድር ለመግባት ብርቱ ተፎካካሪ ኾኖ ወደ መጨረሻ የደርሶ መልስ ዙር ግጥሚያ የደረሰው የኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ቡድን በጋና አቻው በሜዳው 3 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ብሔራዊ ቡድኑ ወደ መጨረሻው ዙር ለመድረስ ባደረጋቸው ውድድሮች የተለያዩ ጠንካራ ቡድኖችን አስተማማኝ በኾነው ውጤት እያሸነፈ ነበር የተጓዘው። ኾኖም በመጨረሻው ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያ ሀገር ውስጥ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ባደረገው ውድድር አሸናፊ የኾነው የጋና ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ፉክክሮች ከፍተኛ ልምድ ያለው ቡድን ነው።

የሚደርሳትን ኳስ ለግብ በማብቃት ብቃቷን ያስመሰከረችው አጥቂ ረድኤት አስረሳኸኝ በትናንትናው ግጥሚያ ተሰላፊ አለመኾኗ ቡድኑ ላይ ተጽዕኖ አሳርፏል። ረድኤት በትናንትናው ውድድር ያልተሰለፈችው ቀደም ሲል በደረሰባት ጉዳት መኾኑም ተገልጧል። ኮስታሪካ በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ፉክክር አፍሪቃን ወክለው ከሚሳተፉ ሁለት ሃገራት አንዱ ለመሆን የመጨረሻ አንድ ዙር ግጥሚያ የቀረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋና ውስጥ አራት ለዜሮ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ወደ መለያ ምት ለመግባት ደግሞ ጋናን ሦስት ለዜሮ ማሸነፍ ይኖርበታል።

ፕሬሚየር ሊግ

በፕሬሚየር ሊጉ እስካሁን 28 ጨዋታዎችን አከናውኖ 69 ነጥብ መሰብሰብ የቻለው ማንቸስተር ሲቲ ዛሬ ማታ ከክሪስታል ፓላስ ጋር ይጋጠማል። ክሪስታል ፓላስ እስካሁን የሰበሰበው ነጥብ ከተጋጣሚው ማንቸስተር ሲቲ ከግማሽ በታች ነው። ክሪስታል ፓላስ 33 ነጥብ ይዞ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

Champions League - Young Boys Berne v Manchester United - Christiano Ronaldo
ምስል Lairys Laurent/ABACA/picture alliance

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከተከናወኑ ግጥሚያዎች ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሦስት ግቦች በማስቆጠር ሔትትሪክ የሠራበት ሳይጠቀስ አይታለፍም። ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሬሚየር ሊጉ ቅዳሜ ዕለት ባደረገው ግጥሚያ በአጥቂው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሦስት ግቦች ቶትንሀም ሆትስፐርን 3 ለ2 ድል አድርጓል። ማንቸስተር ዩናይትድ ባለፈው ሳምንት በማንቸስተር ሲቲ 4 ለ1 በተሸነፈበት ግጥሚያ ሳይሰለፍ የቀረው እና ወደ ሀገሩ ፖርቹጋል አቅንቶ የነበረው አጥቂ በ12ኛው፣ 38ኛው እና 81ኛው ደቂቃዎች ነበር ሦስቱን ግቦች ያስቆጠረው። በዚህም ክርስቲያኖ ለቡድኑ ወሳኝ አጥቂ መሆኑን ሲያስመሰክር አሰልጣኙ ራልፍ ራንኚች እና የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎችን አስፈንጥዟል።  ለቶትንሀም ሆትስፐር ሐሪ ኬን በፍጹም ቅጣት ምት 35ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።  72ኛው ደቂቃ ላይ የማንቸስተር ዩናይትዱ ተከላካይ ሐሪ ማጉዬር ኳሷን ለማጨናገፍ ሲሞክር የገዛ መረቡ ላይ አሳርፏል። በዕለቱ ሊቨርፑል በሉዊስ ዲያዝ እና ሞሐመድ ሣላኅ ግቦች ብራይተንን 2 ለ0 ድል አድርጓል።

ረቡዕ ማታ ሁለት የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች በሚደረጉበት ተመሳሳይ ሰአት በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ወሳኝ ፍልሚያ ሊቨርፑል ከአርሰናል ጋር ይጋጠማል። 66 ነጥብ ሰብስቦ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል በ3 ነጥብ ከሚበልጠው መሪው ማንቸስተር ሲቲ ላለመራቅ ረቡዕ ማታ የሞት ሽረት ማድረጉ አይቀርም። በተመሳሳይ መልኩ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት በ51 ነጥቡ አራተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው አርሰናልም የረቡዕ ግጥሚያ እጅግ ወሳኝ ነው። አርሰናል ትናንት ላይስተር ሲቲን 2 ለ0 ድል አድርጓል። አርሰናል ቀሪ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎቹን የሚያሸንፍ ከኾነ በ57 ነጥቡ ቸልሲን እጅግ መጠጋት ይችላል ማለት ነው። ቸልሲ እስካሁን ባደረጋቸው 28 የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች 59 ነጥብ ሰብስቦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  

ቸልሲና ሩስያዊው ቢሊዬነር ሮማን አብራሞቪች

ቸልሲ በጀርመናዊው አጥቂ ካይ ሐቫርትስ ብቸኛ ግብ ትናንት ኒውካስል ዩናይትድን 1 ለ0 ድል ቢያደርግም ቡድን ግን የዓለም ፖለቲካዊ ምስቅልቅል አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። የሩስያ ዩክሬን ጦርነት የቸልሲ ቡድንን ብርቱ ተጽእኖ እያዳሳደረበት እንደኾነም እየተነገረ ነው። በጦርነቱ የተነሳ የሩስያ መንግሥት እና ባለሐብቶች ላይ የሚጣለው ማዕቀብ ቸልሲ ቡድን ላይ ጎልቶ ታይቷል። ሩስያ ዩክሬንን በመውረሯ የተነሳ በርካታ ኃያላን ሃገራት በሩስያ መንግሥት እና ንብረቶች ላይ ማዕቀባቸውን ማጠናከራቸው በቸልሲ ቡድን ላይ ግዙፍ ጥላውን አሳርፏል።

Roman Abramowitsch | russischer Oligarch
ምስል Glyn Kirk/AFP/Getty Images

ላለፉት 19 ዓመታት በሩስያዊው የ55 ዓመቱ ቢሊዬኔር ሮማን አብራሞቪች ንብረትነት የሚተዳደረው የእንግሊዙ ቸልሲ ቡድን አስተዳደራዊ እንቅስቃሴው በማዕቀቡ የተነሳ በከፍተኛ ኹኔታ ተገትቷል። የእንግሊዝ መንግሥት እና ፕሬሚየር ሊግ በጣሉት ገደብ ቸልሲ የተጨዋቾች ዝውውርን መፈጸም አይችልም። በፕሬሚየር ሊጉ የሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ የቲኬት ሽያጭ እንዳያከናውንም ታግዷል። ቡድኑ የተለያዩ የስፖርት ትጥቆችን እና መሰል ጉዳዮችን የሚሸጥበት የንግድ እንቅስቃሴ ላይም ማዕቀቡ አሉታዊ ተጽእኖውን አሳርፏል። ይህ ሁሉ የኾነው ቸልሲን ለሁለት ዐሥርተ ዓመታት ግድም በባለቤትነት የያዙት ባለሐብት ሩስያዊው ቢሊዬነር ሮማን አብራሞቪች ለሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ድጋፋቸውን ዐሳይተዋል በሚል ነው።

የሩስያ ባለሐብቶች ንብረት የሆኑ ተቋማት ላይ በተጣለው ማዕቀብ የተነሳ የእንግሊዝ፤ የጀርመን እና ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት ዜጎች ላይ ጫናው በርትቷል። የእንግሊዙ ቸልሲ ቡድን አሰልጣኝ ቶማስ ቱኹል ቡድናቸው ከሩስያ ባለሐብት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ እና በማዕቀቡ የተነሳ ከአሰልጣኝነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው ይነሱ እንደሆን ተጠይቀው ነበር። ጀርመናዊው አሰልጣኝ ግን፦ «የውድድር ዘመኑ እስኪጠናቀቅ ድረስ መቆየቴ አንዳችም ጥርጥር የለው» ብለዋል። ትናንት ቸልሲን ለድል ያበቃችውን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው ሌላኛው ጀርመናዊ አጥቂ ካይ ሐቫርትስ በበኩሉ፦ የቡድኑ ሠራተኞች እና ደጋፊዎች ላይ የማቅቀብ ተጽእኖው መበርታቱን ገልጧል። «እኛ ተጨዋቾች የተለየ ነው የሚደረግልን። መሰልጠን እንችላለን፤ ወደፊትም ስልጠናችንን እንቀጥላለን» ሲል ማእቀቡ በቀጥታ የተጨዋቾች ስልጠና ላይ ተጽእኖ እንደሌለው የ22 ዓመቱ አጥቂ ተናግሯል።

ቡድናቸውን ለመሸጥ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር የተነጋገሩት የቸልሲ ባለቤት ሩስያዊው ቢሊዬኔር ሮማን አብራሞቪች በበኩላቸው፦ «እያንዳንዱ ነገር በእየቀኑ ስለሚቀያየር ከቀን ቀን መጠበቅ ይኖርብናል» ብለዋል።

ሻምፒዮንስ ሊግ

Fußball Logo UEFA Champions League | RB Leipzig
ምስል motivio/dpa/picture alliance

ቸልሲ በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት ከፈረንሳዩ ሊል ጋር የመልስ ግጥሚያ ይጠብቀዋል። የመጀመሪያውን ጨዋታ 2 ለ0 ነው ያሸነፈው። ረቡዕ እለት ለሻምፒዮንስ ሊግ ለሚደረገው ሌላ ግጥሚያ ቀደም ሲል አንድ እኩል የተለያዩት የጣሊያኑ ጁቬንቱስ እና የስፔኑ ቪላሪያል ተቀጣጥረዋል። ነገ ማታ በተመሳሳይ ሰአት የሻምፒዮንስ ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ይኖራሉ። በመጀመሪያ ግጥሚያቸው ሁለት እኩል የተለያዩት የሆላንዱ አያክስ አምስተርዳም እና የፖርቹጋሉ ቤኔፊካ የመልስ ግጥሚያቸውን ሆላንድ አምስተርዳም ከተማ በሚገኘው ዮሐን ክሩፍ ስታዲየም ውስጥ ያከናውናሉ። ማድሪድ ውስጥ አንድ እኩል ተለያይቶ የመጣው ማንቸስተር ዩናይትድ በበኩሉ በሜዳው ኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም አትሌቲኮ ማድሪድን ያስተናግዳል።

ሙዚቃ፦

በስፔን ላሊጋ የደረጃ ሰንጠረዡን በ63 ነጥብ የሚመራው ሪያል ማድሪድ ዛሬ ማታ ከማዮካ ጋር ይጋጠማል። ማዮካ 26 ነጥብ ይዞ በላሊጋው ደረጃው 16ኛ ነው። ትናንት በነበሩ ግጥሚያዎች አትሌቲኮ ቢልባዊ በቤቲስ 1 ለ0 ተሸንፏል። የቤቲሱ አጥቂ ናቢል ፌኪር በ80ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ለቤቲስ የማሸነፊያ ብቸኛዋን ግብ 20ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ቦርጃ ኢግሌዚያስ ነው። ትናንት ሪያል ሶሴዳድ አላቬስን 1 ለ0 ሲያሸንፍ፤ ሴቪያ ከራዮ ቫሌካኖ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ባርሴሎና በሰፊ የግብ ልዩነት ኦሳሱናን 4 ለ0 አንኮታኩቷል። ፌራን ቶሬዝ በ14ኛው እና 21ኛው ደቂቃ ላይ ለባርሴሎና ሲያስቆጥር፤ ቀሪዎቹ ሁለት ግቦች የፒዬር ኤመሪክ አውባሜያንግ እና ሪኩዊ ፑዪግ ናቸው።

ቡንደስሊጋ

1. Bundesliga | 1899 Hoffenheim - Arminia Bielefeld
ምስል Uwe Anspach/dpa/picture alliance

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት አርሚኒያ ቢሌፌልድን 1 ለ0 ሲያሸንፍ፤ ላይፕትሲሽ ግሮይተር ፊዩርትስን 6 ለ1 የግብ ጎተራ አድርጎታል። መሪው ባየርን ሙይንሽን በአንጻሩ ቅዳሜ ዕለት ከሆፈንሀይም ጋር ተጋጥሞ አንድ እኩል በመለያየት ነጥብ ጥሏል። በዚህም መሠረት ቦሩስያ ዶርትሙንድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በባየር ሙይንሽን የሚበለጠው በ7 ነጥብ ነው። መሪው ባየር ሙይንሽን 60 ነጥብ አለው። ላይፕትሲሽ 44ነጥብ በመሰብሰብ ከባየርን ሌቨርኩሰን ቀጥሎ በ4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት በኮይልን የ1 ለ0 ሽንፈት የገጠመው ባዬር ሌቨርኩሰን በ45 ነጥቡ በቡንደስሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ ሦስተኛ ነው። ሽቱትጋርት፤ ሔርታ ቤርሊን እና ግሮይተር ፊዩርት ከ16ኛ እስከ 18ኛ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ይገኛሉ።

አትሌቲክስ

ሰርቢያ ቤልግሬድ ከተማ ውስጥ ለሚከናወነው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድን ዛሬ ማታ አሸኛኘት እንደሚደረግለት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዐስታውቋል። የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሰርቢያ ዋና ከተማ ቤልግሬድ ሽታርክ አሬና ስታዲየም ውስጥ የሚጀምረው የፊታችን ዐርብ ነው። ለሁለት ቀናት የሚከናወነው ውድድር እሁድ ዕለት ይጠናቀቃል።

በሀገር ውስጥ ደግሞ 10ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች እና 3ኛው ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ውድድሮች በትናንትናው ዕለት ተጠናቋል። በኦሮሚያ ክልል፤ አሰላ ከተማ ውስጥ ለ7 ተከታታይ ቀናት ሲካኼድ በቆየው ፉክክር ረዥም እና አጭር ርቀት ሩጫ፣ ዝላይ፣ መሰናክል እና ጦር ውርወራን የመሳሰሉ የተለያዩ አይነት የአትሌቲክስ ውድድሮች ተከናውነዋል። በዚህ ፉክክር ብርታታቸውን ዐሳይተው አሸናፊ የኾኑ ጠንካራ አትሌቶች ለአፍሪቃ ውድድር እንደሚመረጡ ቀደም ሲል ተገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ