1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመኖርያ ፈቃድ ለፈላሻሙራ ቤተ-ዘመዶች

ሐሙስ፣ መስከረም 10 2011

«አይሁድ የሚለዉ በአጠቃላይ በዓለም ላይ የሚገኙ የአይሁድ ሃይማኖትን የሚከተሉ ማለት ነዉ። ግን ቤተ- እስራኤላዉያን፤ ኢትዮጵያዊ አይሁዳዊ ማለት ነዉ። ቤተ- እስራኤል ከግዕዝ የመጣ ቃል ነዉ ቤቱ እስራኤል የሆነ ሰዉ ማለት ነዉ። ፈላሻሙራ ደግሞ የአይሁድ ሃይማኖቱን ቀይሮ የነበረ አልያም የቀየረ ማለት ነዉ»

https://p.dw.com/p/35GR8
Sommer 2017 Programm für äthiopisch-jüdische Kinder in Gondar, Äthiopien
ምስል youtube/G.Metzger

የመኖርያ ፈቃድ ለአንድ ሺህ የፈላሻሙራ ቤተ-ዘመዶች

አይሁዳዉያን «ዮም ኩፐር» ማለትም «የስርየት ቀን» መላው የእስራኤል ሕዝብ በፈጣሪዉ ፊት ጾም ጸሎት የሚያደርግበት፤ ለኃጢያቱ ንስሃ እየገባ የሚዉልበት፤ የተጣላ የሚታረቅበት፤ የበደለ ይቅር የሚባባልበት፤ ቀን ነዉ። ዘንድሮ ያዮም ኩፐር ፆም በያዝነዉ ሳምንት ማክሰኞ ፀሐይ መጥለቅያ ምሽት ላይ ጀምሮ፤ የተጠናቀቀዉ ትናንት ምሽት ላይ ነዉ። በዚህ እለት መኪና አይንቀሳቀስም ሰዎች ስልክ እንኳ ሳይጠቀሙ አጥፍተዉ በጾም ፀሎት እና በእርጋታ የሚያሳልፉበት እለት ነዉ። በዓመት ዉስጥ ካሉት ቀናት ሁሉ ዮም ኩፐር ማለትም «የስርየት ቀን» ለእስራኤላዉያን የተመረጠ ቀናቸዉ እንደሆነ ተመልክቶአል።

Israel gibt Aufenthaltsgenehmigung für Tausende Äthiopier
ምስል DW/Abraham Yohanes

« በእንግሊዘኛዉ  “The day of Atonement ” የስርየት ቀን የሚለዉ ነዉ። በአይሁድ እምነት ልማድ መሰረት ከጥንት ጀምሮ የመጀመርያዎቹ የአይሁድ እምነት መስራቾች እነ ሙሴ፤ የመጀመርያዉ ካህን አሮን ጀምሮ የነበረ መመርያ ነዉ። አይሁዳዉያን የራሳቸዉ የሆነ የቀን መቁጠርያ አላቸዉ። ሰባተኛዉ ወር አስረኛዉ ቀን ላይ ነዉ የሚዉለዉ። በዚህ ቀን በጥንት ጊዜ ሁለት ፍየል ነዉ ለመስዋእትነት የሚቀርበዉ። አንዱ ለአምላክ የሚሰጥ ነዉ አንዱ ደግሞ የሕዝቡን ሃጥያት ማስተሰረያ የሚሆን ተብሎ ሃጥያቱን ተናዞ ፍየሉን ወደ በረሃ የሚለቀዉ ይሆናል። ስለዚህ በዚህ በአንድ ቀን ጾም ማለት ለ 25 ሰዓታት ገደማ ማንም ስራ አይሰራም፤ ማንኛዉም አይነት የስራ እንቅስቃሴ የለም ጋዜጦች እንኳ አይታተሙም፤ ኢንተርኔት ምናምን ባጠቃላይ ያሉት ነገሮች ሁሉ አይጠቀመም ። ጾማቸዉን የሚፈቱት 25 ሰዓታቱ አልፎ በጎርጎረሳዉያኑ መስከረም 19 ሲዉል ፀሐይ ሲጠልቅ ነዉ። 

በማኅበረሰብ ጥናት በተለይም በቤተ-እስራኤላዉያን ማንነት እና ሕይወት ዙርያ በጀርመን በቤለፊልድ ከተማ ዩንቨርስቲ ምርምር ላይ የሚገኘዉ ወጣት አብርሃም ዮናስ ነበር። ጤና ይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ ፤ነገርን ነገር ያነሳዋል  ነዉ እና ነዉ እንጂ፤ የእለቱ ርዕሳችን ወደ እስራኤል በተለይ ከቤተ-እስራኤላዉያን ፤ ከፈላሻሙራዎች ጋር ነዉ የሚያቆየን። በሳምንቱ መጀመርያ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለ 1000 ኢትዮጵያዉያን የፈላሻሙራ ቤተሰብ አባላት እስራኤል ዉስጥ ለመኖርና መስራት የሚያስችል ፈቃድ ለመስጠት መወሰናቸዉን በደስታ አብስርያለሁ ሲሉ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ 1000 ሺህ የፈላሻሙራ ቤተሰብ አባላት የመኖርያ ፈቃድ እሰጣለሁ አሉ እንጂ በኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ለመግባት ፈቃድ እስኪያገኙ የሚጠባበቁት ገና ወደ ስምንት ሺህ የፈላሻሙራ ቤተ-ዘመዶች እንዳሉ ነዉ የተሰማዉ። ግን፤ አይሁድ፤ ቤተ እስራኤል፤ ፈላሻሙራ በተሰኙት ስያሜዎች ላይ ምን ልዩነት ይኖር ይሆን? የኢትዮጵያ አይሁዶች በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ከሄዱ በኋላ ያላቸዉ ሕይወትስ ምን ይመስል ይሆን?

Sommer 2017 Programm für äthiopisch-jüdische Kinder in Gondar, Äthiopien
ምስል youtube/G.Metzger

የኢትዮጵያ ቤተ- እስራኤላዉያን  እስራኤል መኖርያ ፈቃድ አግኝተዉ ለመኖር ለረጅም ዓመታት ታግለዋል። በ 1980 ዎቹ እና 90 ዎቹ  በአስር  ሺህ የሚቆጠሩ ቤተ- እስራኤላዉያንን ወደ ሃገርዋ ስትወስድ የእስራኤል መንግሥት ወነኖቼን አጓጉዤ ጨርሻለሁ ብሎ አስቦ ደምድሞም ነበር። ይሁንና  በጎርጎረሳዉያኑ 2015 ዓ.ም የእስራኤል መንግሥት ከኢትዮጵያ ፈላሻሙራ ቤተሰቦችን ለማገናኘት ባፀደቀዉ አዲስ ሕግ መሰረት 9000 ቤተሰቦችን ወደ እስራኤል ለማስገባትና የመኖርያ ፈቃድ ለመስጠት በመወሰን አዲስ ሕግ ማዉጣቱ  ይታወሳል። እስራኤል ይህን ሕግ ከወጣበችበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ለ 1300 የፈላሻሙራ ኢትዮጵያዉያን ቤተሰቦች የመኖርያ ፈቃድ ሰጥታ በእስራኤል ዉስጥ መኖር ጀምረዋል።  በጀርመን ቤለፌልድ ከተማ በሚገኘዉ ግዙፍ የማኅበረሰብ  እና ታሪክ ጥናት ዩንቨርስቲ ዉስጥ በተለይ ቤተ-እስራኤላዉያን በኢትዮጵያ ሳሉ እና ወደ እስራኤል ከመጡ በኋላ ያላቸዉን ማኅበረሰባዊ ባህላዊ ኑሮና ማንነትን በማጥናት ላይ የሚገኘዉ ወጣት አብርሃም ዮናስ፤ ለዲፕሎም ሥራዬን የምሰራበት ርዕስ ይላል፤ 

„National Identities Verses Cultural identity of Beta Israel communities“ ቤተ-እስራኤሎቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሲኖሩ ያዳበርዋቸዉ ኢትዮጵያዊ ማንነቶች እና እስራኤል ዉስጥ ከሄዱ በኋላ አይሁዳዊ ማንነታቸዉ ነዉ በጥናቴ ለመመልከት የምሞክረዉ። ማለትም ቤተ እስራኤላዉያኑ እስራኤል ሲኖሩ ሃይማኖታቸዉ ከእስራኤል ማኅበረሰብ ጋር እንደ አንድ ያስቆጥራቸዋል። ከእስራኤላዊ ጎረቤታቸዉ ጋር ሲኖሩ ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሲኖሩ ያደበርዋቸዉ ባህሎች ማንነቶች  የሚጋጩባቸዉ ጊዜ አለ እና እኔም የማጠናዉ በዚህ ማሃል ያለዉን አንድነትና ልዩነትን ነዉ። »

Israel gibt Aufenthaltsgenehmigung für Tausende Äthiopier
ምስል DW/Abraham Yohanes

«አይሁድ የሚለዉ በአጠቃላይ በዓለም ላይ ያሉ የአይሁድ ሃይማኖትን የሚከተሉ ማለት ነዉ። ግን ቤተ- እስራኤላዉያን፤ ኢትዮጵያዊ አይሁዳዊ ማለት ነዉ። ቤተ- እስራኤል ከግዕዝ የመጣ ቃል ነዉ ቤቱ እስራኤል የሆነ ሰዉ ማለት ነዉ።»

ግን ቤተ-እስራኤላዉያን ወይም ፈላሻሙራ አልያም ደግሚ አይሁድ የሚለዉ መጠርያ ልዩነቱ ምንድ ነዉ ልዩነት አላቸዉ?

በሳምንቱ መጀመርያ በወጣዉ አንድ ዘገባ መሰረት አይሁዳዉያን ነን ብለዉ ወደ እስራኤል የገቡ ፈላሻሙራዎች የእስራኤል መንግሥት እንደ አይሁዳዊ እዉቅና አልሰጣቸዉም ይላል፤ እና ቤተ-እስራኤልና ፈላሻ ሙር በእስራኤል ዉስጥ ልዩነት አላቸዉ ማለት ነዉ?

«ትክክል ነዉ። ፈላሻ ሙራ የሚባሉት ሃይማኖታቸዉን ከአይሁዴነት ወደ ክርስትና ለዉጠዋል። ስለዚህ ወደ አይሁድ ሃይማኖt መለለስ የሚለዉ ሕግ«አልያ» የሚባለዉ ደግሞ ከተለያዩ የዓለም ሃገራት እንደሚመጡት አይሁዳዉያን ቤተ -እስራኤላዉያንም አይሁዳዊ እንደሆኑ ያስቆጥራቸዋእል። የፈላሻሙር ሁኔታ ግን በህጉ መሰረት ችግር ይፈጥራል። በአይሁድ ሕግ መሰረት አንድ አይሁድ ሃይማኖቱን ከቀየረ አይሁዳዊ አይደለም ስለዚህ በመመለስ ሕግ ዉስጥ አይካተትም ማለት ነዉ። ነገር ግን በግዴታ ሃይማኖቱን የቀየረ ሰዉ ዳግም ሃይማኖቱን ተምሮ በሕጉ መሰረት አይሁዳዊነትን መቀበል ይችላል። በእስራኤል አብዛኛዉን ችግር የፈጠረዉ ነገር የቤተ እስራኤላዉያኑ ዘመዶች ወንድሞች እህቶች ፈላሻ ሙራ ሆነዉ ኢትዮጵያ የቀሩ አሉ። ይህን ቤተሰብ ለሁለት የከፈለዉ ሕጉ ነዉ የአይሁድ እምነትን ያልተዉት ወደ እስራኤል ሲመጡ፤ ሃይማኖቱን የተዉት ግን ፈላሻ ሙራ ተብለዉ ብዙዎች ቀርተዋል። »   

በአንዳንድ መረጃዎች መሰረት እስራኤል ዉስጥ በአሁኑ ወቅት ወደ 140 ሺህ ቤተ- እስራኤላዉያን ይኖራሉ፤  ከነዚህ መካከል ወደ 50 ሺህ የሚሆኑት እስራኤል ዉስጥ የተወለዱ ናቸዉ። እንደ ማኅበረሰብ ጥናት ተመራማሪዉ አቶ አብርሃም፤ በእስራኤል ፈላሻሙራዎች ብቻ ሳይሆኑ ቤተ-እስራኤሎቹም ቢሆኑ የይሁዲ ሃይማኖትን በከተል ረገድ ችግር ገጥሞአቸዋል።   

«ቤተ እስራኤላዉያኑም ቢሆኑ ወደ እስራኤል ሲመጡ ሃይማኖቱን እንደ አገሪዉ ሰዉ ለማካሄድ ችግር ገጥሞአቸዋል። እነሱም የሃይማኖት ስርዓታቸዉን መቀየር እንዳለባቸዉ ተነግሮአቸዉ ነበር። የተለያዩ የስርዓት ፀሎቶችን እንዲከተሉ ተደርገዋል። በተለያዩ የእስራኤል ረቢዎች አማካኝነት ሃይማኖቱን እንዲማሩ ስማቸዉን እንዲቀይሩ የተለያዩ ነገሮች እንዲያደርጉ ጫና ተደርጎባቸዋል። የፈላሻሙራን ጉዳይ ስናይ ግን በሕግ የሰፈረ ነገር ስለሆነ ክፍተት አይታይበትም። »

ቤተ-እስራኤላዉያን በተለይ በጥንት ጊዜ በጎንደር አካባቢ ይኖሩ እንደነበር ይነገራል። የማኅበረሰብ ጥናት ተመራማሪዉ አቶ አብርሃም እንደሚሉት ቤተ-እስራኤላዉያን በኢትዮጵያ ብዙ ታሪክን የሰሩ ናቸዉ።

Israel gibt Aufenthaltsgenehmigung für Tausende Äthiopier
ምስል DW/Abraham Yohanes

«ቤተ-እስራራኤላዉያን በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ ትልቅ ታሪክን ፅፈዋል። ምክንያቱm የኢትዮጵያ የነገስታት ታሪክ ወደ ሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል በነበረበት ወቅት በፖለቲካዉ፤ በታሪክ፤ በማኅበረሰብ መስተጋብር ትልቅ ትልቅ ሚናን ተጫዉተዋል።  ግን በቁጥር ትንሽ ስለነበሩ ብዙም ጎልተዉ እንዳይታዩ አድርጎአቸዋል። ከዝያ በኋላ ግን በ14ኛዉ ክፍለ ዘመን ትልቅ ጦርነት አድርገዉ ነበር ። በግብርና ይተዳደሩ የነበሩት እነዚህ ቡድኖች በጦርነቱ ወቅት መሪታቸዉን ተቀሙ። አንድ ሰዉ የእርሻ መሪት እንዲኖረዉ ከፈለገ ክርስትያን መሆን አለበት። ስለዚህ ነዉ ከዚህ በኋላ እራሱን የቻለ አንድ የማኅበረሰብ ቡድን ተፈጠረ። በአካባቢያቸዉ ላይ በኤኮኖሚ እንቅስቃሴዉ ላይ ገበሪየሚያመርትበትን ሞፈር የሚያመርቱ ቀጥቃጭ ሸክላ ሰሪ ሆኑ ማለት ነዉ። እነዚህ ማኅበረሰቦች እስከ 1980 ዎቹ አልያም እስከ 1990 ዎቹ  በቀጥቃጭነትና በሸክላ ሰሪነት ተሰማርተዉ ይተዳደሩ ነበር። ወደ እስራኤል እስኪሄዱ ድረስ ማለት ነዉ። »         

ቤተ-እስራኤላዉያን በ 1980 ዎቹ እና 90 ዎቹ ወደ እስራኤል ከሄዱ በኋላ ወደ 50 ሺህ የሚሆኑ ሁለተኛ ትዉልዶች መፈጠራቸዉ ተነግሮአል።  በምሁራን ጥናት ወደ እስራኤል የገቡት ቤተ-እስራኤላዉያን ሕይወትስ እንዴት ይገመገም ይሆን?

« ወደ እስራኤል የሄዱት ቤተ- እስራኤላዉያን ሁለተኛ ትዉልድ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰዋል እዉነት ነዉ። የመጀመርያዎቹ የባህል ቀዉስ የቋንቋ ችግር አጋጥሞአቸዋል። አሁንም ችግር አለባቸዉ። ሁለተኛዉ ትዉልድ ግን እዝያዉ ተምሮ ስላደገ የትምህርትም ሆነ የቋንቋ ችግር የለበትም ። አሁንም ግን በማኅበረሰቡ ተቀባይ የመሆኑ እድል ጎልቶ አይታይም። »  

በቤተ -እስራኤሎች አይሁድ አዲስ ዓመት ሮሽ ሃሻና 5779 ዓመተ ዓለም ገብቷል።  አይሁዳዊ​​​​​​​ የሚለዉን ጽንሰ ሃሳብ ለመተንተን እጅግ ከባድ ነዉ ያሉት የማኅበረሰብ ጥናት ተመራማሪዉ አቶ አብርሃም ዮሃንስ በምሳሌነት ኢትዮጵያዊ የሚለዉን ፅንሰ ሃሳብ በምሳሌነት ያስቀምጣሉ።

Israel gibt Aufenthaltsgenehmigung für Tausende Äthiopier
ምስል DW/Abraham Yohanes

ለዝግጅቱ መሳካት ቃለምልልስ የሰጡንን በጀርመን ቤለፈልድ ከተማ የማኅበረሰብ ጥናት ተቋም በቤተ- እስራኤላዉያን እና ፈላሻሙራ ላይ ጥናት እያካሄደ ያለዉን ወጣቱን ተመራማሪ አብርሃም ዮሃንስን በ «DW » እያመሰገንን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ