1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የመን ጦርነትና ግራ አጋቢዉ የኃይል አሰላለፍ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 23 2011

ጦርነቱ አሁን አደን ባሕረ ሰላጤን በረገጠችዉ አደን ዉስጥ ነዉ። አቶ የሱፍ እንደሚሉት የአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት በተለይም እስካሁን ድረስ ባንፃራዊ መመዘኛ ገለልተኛ አቋም ይዛለች የምትባለዉ ኢትዮጵያ ሁነኛ መፍትሔ ካልፈለገች ከወላፈኑ ግርፋት አታመልጥም።

https://p.dw.com/p/3OiGG
Jemen Aden Soldaten des Southern Transitional Council (STC)
ምስል picture-alliance/Photoshot/M. Abdo

 የመን ጦርነት፣ ግራ አጋቢዉ የኃል አሰላለፍ እና የአፍሪቃ ቀንድ አስተጋብኦቱ

የየመን ሁቲ አማፂዎችን በጋራ የሚወጉት የሐገሪቱ መንግስትና ደቡብ የመንን ከተቀረዉ የሐገሪቱ ክፍል ነፃ ለማዉጣት የሚፋለሙት ኃይላት የሐገሪቱን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ አደንን ለመቆጣጠር እየተዋጉ ነዉ።ሕጋዊ እዉቅና አለዉ የሚባለዉ መንግሥት ጦር ትናንት የከተማይቱን አዉሮፕላን ማረፊያ ጨምሮ ሥልታዊ አካባቢዎችን መቆጣጠሩን ባለስልጣናቱና የከተማይቱ ነዋሪዎች አስታዉቀዉ ነበር።ትናንት ማምሻዉን የተገንጣዮቹ ኃይላት የተያዘባቸዉን ሥፍራ አስለቅቀዉ አደንን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል።የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት የየመን ጦርነት መራዘም፣የተፋላሚ ኃይላት አሰላለፍ መቀያየርና ዓላማቸዉ በግልፅ አለመታወቁ ጦርነቱ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ የአፍሪቃ ቀንድን እንዳያዳርስ ያሰጋል።
ኢትዮጵያዊዉ የፖለቲካ ተንታኝና ደራሲ ዩሱፍ ያሲን የጦርነት ዉስጥ ትንሽ ጦርነት ይሉታል።የአደኑን ዉጊያ።በርግጥም ትልቁ ጦርነት ያካባቢዉን ታላላቆች በቀጥታ፣ የዓለም ኃያላንን በተዘዋዋሪ ያሰለፈ፣ ከሪያድ እስከ ቴሕራን፣ ከለንደን አስከ ዋሽግተን ያነካካ ነዉ።የሪያድ፣ አቡ-ዳቢ ነገስታት እንደ አዛዥ ናዛዥ የበላይ፣ የካይሮ፣የካርቱም፣ የጅቡቲ፣ የአስመራና የዳካር ገዢዎች እንደ ጥቅም ጠባቂ ከመሐል የቆሙበት፤የመኖች የመንግሥት፣የተገንጣዮች፣ የእስልምና እምነት አራማጆች እየተባሉ ባንድ አብረዉ፣ ሁቲ ከሚባሉ ወገኖቻቸዉ ጋር የሚጋደሉበት ጦርነት ነዉ።
አምስተኛ ዓመቱ።ብዙ ሺዎች አልቀዋል።መቶ ሺዎች ቆስለዋል።ሚሊዮኖች ተርበዋል።አሸናፊም ተሸናፊም የለም።
                          
ዘንድሮ የሳዑዲ አረቢያ ነገስታት የሚደግፏቸዉ «የመንግስት» የሚባሉት ኃይላት፣ የሳዑዲ አረቢያ ወዳጅ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያደረጀች-ያስታጠቀቻቸዉ ተገንጣይ ኃይላት ዉጊያ መግጠማቸዉ ነዉ ወትሮም አሳማኝ ምክንያት ያጣዉን ጦርነት፣ ቅጥ ያሳጣዉ ።
                                    
በሪያድና አቡዳቢ  ገዢዎች የሚገፋዉ ቅጥ ያጣ ጦርነት ከዉድመት የተረፈችዉን የመንን እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ከ1990 በፊት እንደነበረችዉ እሁለት መግመሱ አይቀርም።ወዳጅ የሚመስሉ የአረብ መንግስታትን በተቃራኖ ጎራ ያቆመዉ፣ ደጋፊዎቻቸዉን የሚያፋጀዉ በተለይ የአደንኑና የአካባቢዉ ዉጊያ በየመን ብቻ ተገድቦ መቅረቱ አጠራጣሪ ነዉ።
የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲን እንደሚሉት የዉክልና የሚመስለዉ ጦርነትና ሽኩቻ የመጨረሻ-መጨረሻ ግቡ የአካባቢዉን ሥልታዊ የባሕር መተላለፊዎች መቆጣጠር ሳይሆን አይቀርም።
                                             
ምሥራቅና ምዕራብ ቀይ ባሕር።የአደን ባሕረ ሰላጤ፣ ሕንድ ዉቅያኖስ።ባንድ በኩል የመንን ራሷን፣ ሳዑዲ አረቢያን፣ እያለ ሽቅብ የሚወጣዉ መስመር በተቃራኒዉ አቅጣጫ ግብፅን ይዞ፣ ሱዳን፣ ኤርትራን፣ ሶማሊያን እያለ ቁርቁል ይወርዳል።ጦርነቱ አሁን አደን ባሕረ ሰላጤን በረገጠችዉ አደን ዉስጥ ነዉ።አቶ የሱፍ እንደሚሉት የአፍሪቃ ቀንድ ሐገራት በተለይም እስካሁን ድረስ ባንፃራዊ መመዘኛ ገለልተኛ አቋም ይዛለች የምትባለዉ ኢትዮጵያ ሁነኛ መፍትሔ ካልፈለገች ከወላፈኑ ግርፋት አታመልጥም።

Jemen: Regierungstruppen dringen nach Aden vor
ምስል picture-alliance/AP
Jemen Separatisten aus dem Südjemen erobern Präsidentenpalast in Aden
ምስል picture-alliance/AP Photo

ነጋሽ መሐመድ

ተስፋአለም