1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመን የጦርነት፣የረሐብ የኮሮና ስጋት ምድር

ሰኞ፣ ሚያዝያ 26 2012

መሐመድ አ- ዘቂር።የ40 ዓመት ጎልማሳ ነዉ።የስድት ልጆች አባት።በጦርነቱ ከቤት ንብረቱ ከተፈናቀለ በኋላ ስምንት ራሱን የሚቀልበዉ ሲገኝ ዕቃ እየተሸከመ፣ ብዙ ጊዜ ግን የተጣሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ለቀሞ በመሸጥ ነዉ።የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለመከላከል «በየቤታችሁ ቆዩ» ብሎ ምክርን «እንዴት አድርጌ?» ይላል መሐመድ።

https://p.dw.com/p/3blRO
Jemen | Corona Händehygiene in Slums
ምስል UNICEF/UNI324899/AlGhabri

ማሕደረ ዜና፦ የመን ኮሮናም ይጨክንባት ይሆን?

የመኖች ሰሜን ደቡብ፣መንግሥት አማፂ፣ አልቃኢዳ፣ አይስል፣ የደቡብ ነፃ አዉጪ፣ መንግሥት ተብለዉ እብዙ ቦታ ተከፍለዉ እርስበርስ ይዋጋሉ።የመኖች፣ የሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችና የተከታዮቻቸዉ መንግስታት የጦር ጄቶች በሚያዘንቡት ቦምብ ሚሳዬል ያልቃሉ።ይፈናቀላሉ።በረሐብ ይሰቃያሉ።ልጆቻቸዉ በምግብ እጥረት ይቀነጭራሉ።የእስካሁኑ እልቂት፣ስቃይ መከራ አልበቃ ያለይመስል ባለፈዉ ወር ከዉጪ የሚገኘዉ ርዳታ ቀነሰ።የኮሮና ተሕዋሲ ስጋትና መከላከያ ርምጃዉ ተጠናከረ።የየመኖች ማብቂያ የለሽ ስቃይ መከራ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።

ረመዳን ለሙስሊሞች የፆም፣ፀሎት፣ደካሞችን የመርጃ የተከበረ ቅዱስ ወር ነዉ።ሐሞድ ርዕሥ ከተማ ሰነዓ የሰፈረ ተፈናቃይ ነዉ።ረመዳን ለሐሞድና ለብዙ ብጤዎቹ ብዙ ዓመታት እንደኖሩበት የሚያደርጉበት ወይም-የሚደረግላቸዉ ወር መሆኑ ከቀረ አራት ዓመት አለፈዉ።ዘንድሮ ጠንቷል።ይሰጣቸዉ የነበረዉ ርዳታ ቀንሷል።የኮሮና ተሕዋሲ ስጋት አይሏል።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት (WFP) የሠራዉ የማስታወቂያ ፊልም ግን ትንሽ ዘግየት ያለ ሳይሆን አይቅርም።ቢሆንም የሐሞድን ኑሮ በጨረፍታ ያሳያል።ከጎዳደፈችዉ ዉሽልሽል  ቤቱ አንድ ጥግ ተቀምጧል።ከጀርባዉ ባዶ የላስቲክ ከረጢቶች፣ከቀረጢቶቹ አጠገብ ትናንሽ የቆርቆሮ ጀሪካኖች ተደርድረዋል።ከረጢትና ቆርቆሮዎቹ ላይ በሰማያዊ ቀለም በእንግሊዝኛ የሰፈረዉ ፅሁፍ፣ ሐሞድ ቤት የገቡት ከየት እንደሆነ በግልፅ ይናገራል። World Food Progeramme (የዓለም ምግብድ ድርጅት) ይላል ፅሁፉ።ሐሞድ ደግሞ፣-

Jemen | Corona Händehygiene in Slums
ምስል UNICEF/UNI324949

«ከድርጅቱ የምናገኘዉ ርዳታ፣ዱቄት፣ ዘይት፣ስኳር፣ ፈሶሊያና የመሳሰሉት የምግብ ሸቀጦች ናቸዉ።ርዳታዉ ለብዙ ተፈናቃዮች ይደርሳል እና በየወሩ የችግረኞቹን መሠረታዊ ፍላጎቶች በከፊልም ቢሆን ያረካል።»

በየወሩ! አይደለም።ወይም እንዳልነዉ የዓለም አቀፉ ድርጅት ማስታወቂያ የከረመ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለየመኖች የሚሰጠዉን ርዳታ ከመጋቢት ጀምሮ በግማሽ ቀንሷል።ችግረኞች ርዳታ የሚያገኙት በየሁለት ወሩ አንዴ ነዉ።ምክንያት? በየመን ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ አስተባባሪ ሊዘ ግራንዴ «እንዳንረዳ የሚረዳን አጣን» ዓይነት ይላሉ።

«በዚሕ ዓመት፣ እንዳለ መታደል ሆኖ፣ለርዳታ የሚያስፈልገንን ገንዘብ አላገኘንም።ይሕ ማለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሐገሪቱ ከሚያከናዉናቸዉ 41 መርሐ-ግብሮች 31ዱ አንድም ይቀነሳሉ፣ አለያም ሙሉ በሙሉ ይዘጋሉ።ለጋሾች የሚያስፈልገንን ገንዘብ አልሰጡንም።»

የጥንቷ የመንን አብዛኛ ግዛት ለብዙ ዘመናት የገዙት እኒያ የዛይዲ ሐራጥቃ መሪዎች በ1990ዎቹ ማብቂያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ያነሱት ጥያቄ አጉዞ አጉዞ የጥንት ስልጣኔ፣የልምላሜ፣ የንግድ ማዕከሊቱን ስልታዊት ሐገር ዛሬ ከገባችበት የጥፋት አዘቅት ይዶላታል ብሎ ያሰበ አልነበረም።ከነበረም አልተናገረም።

ሑሴይን ባዳርኢዲን አል-ሁቲ የመሯቸዉ የዛይዲ ተወላጆች ጥያቄ በሙስና የጠነጠኑት ፕሬዝደንት ዓሊ አብደላሕ ሳሌሕ፣ ቤተሰቦቻቸዉና ባለሟሎቻቸዉ በየመኖች ሐብትና ንብረት እየተንደላቀቁ የመኖች የዕድሜ ልክ «ለማኝ» ሆነዉ መቅረት የለባቸዉም የሚል ነበር።

ፕሬዝደንት ዓሊ አብደላ ሳላሕ ራሳቸዉ የዛይዲ ሐራጥቃ አማኝ ናቸዉ።ከዛይዲዎች ጠንከር፤ጠጠር ያለዉ ጥያቄ በቀረበላቸዉ ወቅት ግን ከወገኖቻቸዉ ይልቅ ለሳቸዉ የወገኑት የሳዑዲ አረቢያና የዩናይትድ ስቴትስ መንግስታት ነበሩ።በቱጃር-ኃያላኑ ድጋፍ የልብ ልብ የተሰማቸዉ አምባገነኑ ገዢ   የዘረፉትን ገንዘብ ለሕዝብ ጥቅም እንዲያዉሉ አለያም ሥልጣናቸዉን እንዲለቁ የቀረባላቸዉን ሁለት አማራጮች ንቀዉ የራሳቸዉን ሶስተኛ አማራጭ ገቢር ያደርጉ ገቡ።አል-ሁቲና ተከታዮቻቸዉን በጦር ኃይል ለማንበርከክ ወታደራዊ ዘመቻ ከፈቱ።

Überschwemmung im Jemen
ምስል pictue-alliance/dpa/H. Al-Ansi

ከ1993 ጀምሮ አል-ሐቅ የተሰኘዉን  ፓርቲ ወክለዉ የየመን ምክር ቤት እንደራሴ የነበሩት አል ሁቲ ወታደራዊ ዘመቻዉን ለመመከት በ1997 የምክር ቤት እንደራሴነቱንም ሰነዓንም ጥለዉ ከትዉልድ ግዛታቸዉ ከሰዓዳ ጉጥ ስርጓጉጥ መሸጉ።ከ7 ዓመት በላይ ግን አልቆዩም።የፕሬዝደንት ዓሊ አብደላ ሳሌሕ ጦር ከብዙ ተከታዮቻቸዉ ጋር ገደላቸዉ።መስከረም 2004።

የሑሴይን ባዳርኢዲን አል-ሁቲ «ወንጀል» የየመን ግፉዓንን ጥያቄ ከአብዛኛዉ የመናዊ ብዙ ዓመታት ቀድመዉ ማንሳታቸዉ ነበር።ርዕይ፣ዓላማ፣ ትግላቸዉም በስማቸዉ ተሰይሞ ተጠናክሮ ቀጠለ።በ2011 ቱኒዞች ጀምረዉት ግብፆች ያጠናከሩት የዓረብ ሕዝባዊ አመፅ ጥንታዊቱን ሐገር ሲያነቃንቅ የ33 ዓመቱን ገዢ፣ የየመኖችን አዋሐጅ፣ የአል ሁቲን አስገዳይ፤ ያጋበሱት ገንዘብ፣ ያደረጁት ጦር፣ የሪያድ ዋሽግተኖች ወዳጆቻቸዉም ሊያጥሏቸዉ አልቻሉም።ዓሊ አብደላ ሳሌሕ። ሰላሳ ዘመን የገዙ፣ያዘዙ፣የተንደላቀቁበትን ሥልጣን ቤተ-መንግስት በግድ ለቀቁ።

ሳሌሕ ከስልጣን ከለቀቁ በኋላም ዘመናት እንደኖሩበት አንዱን ኃይል ክደዉ ሌላዉን ሲወዳጁ በሁቲዎች ተገደሉ።ታሕሳስ 2017።

አንሳር አላሕ (የፈጣሪ ደጋፊ) ወይም ሁቲ ተብለዉ የሚጠሩት አማፂያን የትግላቸዉን መስራች ደም ሰነዓ ላይ ከመበቀላቸዉ ከ5 ዓመት በፊት የዓሊ አብደላ ሳሌሕን ስልጣን የወረሱት አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ ፍትሐዊ ምርጫ እንዲያደርጉ መክረዉ፣ አስመክረዉ አስጠንቅቀዉም ነበር።የሰማ እንጂ የተቀበላቸዉ የለም።

ሐዲ በዉርስ ያገኙትን ሥልጣን «ምርጫ» ባሉት ድምፅ ሲያጠናክሩ፣ ሁቲዎች የቀድሞዉን የደቡብ የመን ጄኔራል ጦርን ባጭር ጊዜ ዉጊያ መነቃቅረዉ ርዕሠ ከተማ ሰነዓን ተቆጣጠሩ።2014።ዓሊ አብደላ ሳሌሕ በ2004 የሁቲዎችን አመፅ መስራች አል ሁቲን ሲያስገድሉ፣ የሪያድና የዋሽግተን ደጋፊዎቻቸዉ «አበጀሕ» ብለዋቸዉ እንደሁ እንጂ «ተሳሳትክ» አላሏቸዉም።የየመን ሕዝብ በዓሊ አብደላ ሳሌሕ ላይ ሲያምፅ ግን ሪያዶች እንደ ሩቅ ታዛቢ ዝምታን ሲመርጡ ዋሽግተኖች እንደዴሞክራሲ ጠበቃ «የሕዝብ ጥያቄ» ይከበር ባዮች ነበሩ።

Überschwemmung im Jemen
ምስል pictue-alliance/dpa/H. Al-Ansi

ሁቲዎች በ2014 ሰነዓን ሲቆጣጠሩ ግን «የኢራን ተላላኪነታቸዉ»፣ለሳዑዲ አረቢያና ለአካባቢዉ ሰላም አስጊነታቸዉ፣ የዛይዲ ሐራጥቃ ሺዓነት፣የአብድ ረቦ መንሱር ሐዲ  ሕጋዊነት በዓለም ግዙፍ መገናኛ ጠዴዎች ይተነተን፣ በፖለቲካ ተንታኞች ይከካ፣ይከረተስ፣ይሰለቅ ያዘ።በዚሕ አለበቃም።

ሳዑዲ አረቢያ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን፣ ኩዌትን፣ ግብፅን፤ ቀጠር (ኋላ ብትወጣም)፣ ሱዳንን፣ ዮርዳኖስን፣ሞሮኮን፣ ሴኔጋልን፣ ብላክ ዎተር ወይም አካዳሚ የተባለዉን የአሜሪካ የቅጥረኛ ወታደሮች ድርጅትን አስከትላ ሁቲዎችን ለማጥፋት ዘመተች። መጋቢት 2015።የሪያድ ገዢዎች «ዘመቻ ወሳኝ ማዕበል» ያሉትን ወረራ ሲያዉጁ፣ የዘመኑን ምርጥ  ጦር መሳሪያ የታጠቀ ጦራቸዉ እኒያን « ኋለቀር ወንበዴዎች» ግፋ ቢል በ3 ወር እድሜ እንደሚያደባይ ፎክረዉ ነበር።

የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ ሰላዮች፣የጦር አሰልጣኝ፤ አማካሪዎች፣ ዓየር ላየር ነዳጅ የሚሞሉ አዉሮፕላኖች የሚደግፉት ጦር ከ250 ሺሕ በላይ ወታደር፣ ከ250 የሚበልጡ ተዋጊ ጄቶች አዝምቷል።የኤርትራ፣ የጅቡቲና የሶማሊያን የዓየር፣ የባሕርና የበበስ ግዛቶች እንዳሻዉ ተጠቅሞባቸዋል።በብዙ መቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ተከስክሶበታል።ሁሉ ነገር ሞልቶ የተረፈዉ ጦር የመንን በቦምብ ሚሳዬል ማንደድ ከጀመረ ዘንድሮ መጋቢት አምስት ዓመቱን ደፈነ።ዉጤት? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚገምተዉ 13 ሺሕ የሚሆኑ የመናዉያን አልቀዋል።500 የሳዑዲ አረቢያ ዜጎች ተገድለዋል።እስካሁን ከሞተና ከቆሰለዉ ሕዝብ በተጨማሪ የመን ተተኪ ትዉልድ አልባ እንዳትቀር ማስፈራቱ ነዉ-ከዘመን ማለፍ ጋር የማያልፈዉ አበሳ።

«የመን ዉስጥ 3 ሚሊዮን ሕፃናት በምግብ እጥረት ይሰቃያሉ።አስር ሚሊዮን ልጆች ደግሞ ተገቢዉን ሕክምና አያገኙም።እስካሁን እንዲሕ ነዉ።ከዚሕ ሁሉ ጦርነት በኋላ የነዚሕ ሕፃናትና ልጆች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ይከብደኛል።እነዚሕ ሕፃናትና ልጆች እንደ ጤነኛ ሰዉ ለማደግ የሚያስፈልጋቸዉን ምግብና ሕክምና አያገኙም።»

በጀርመን የሴቭ ዘ ችልድረን ተጠሪ ሱዛና ክሩገር።

የየመኑ አመፅ፣ ግጭትና ዉጊያ ጦርነት ከተጀመረ ከ2011 ጀምሮ ከ91 ሺሕ በላይ ሰዉ ተገድሏል።ዛሬ በሕይወት ከሚገኘዉ የመናዊ 80 በመቶዉ ተመፅዋች ነዉ።24 ሚሊዮን ሕዝብ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመንን የዓለም «ታላቅ የሰብአዊ ድቀት» ሐገር ብሎ የሰየማትም ለዚህ ነዉ።አሁን ደግሞ ገዳዩ የኮሮና ተሕዋሲ ታከለበት።

Jemen Kinder im Flüchtlingslager in der Provinz Hajjah
ምስል picture-alliance/Photoshot/M. Al Wafi

ሙዉቶቻቸዉን ቀብረዉ መሞቻ-አሟሟታቸዉን ከሚያሰላስሉት የመኖች ጥቂቶቹ «ኮሮና እናኛ ጋ ማንን ሊገድል ይመጣል» እያሉ በመከራቸዉ የሚቀልዱ አሉ።ጨካኙ ተሕዋሲ ግን ቀልድም፤ምሕረትም አያዉቅም።ትናንት ዕሁድ ይፋ በሆነዉ ዘገባ መሠረት በኮቪድ19 ሁለት ሰዎች ሞተዋል።10 ተለክፈዋል።

ረሐብም የመኖችን ለመዉሰድ መድሕኒት አልባዉን ተሕዋሲ የሚሽቀዳደም መስሏል። ለአብዛኛዉ የመናዊ እሕል የሚያቃምሰዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ርዳታ የጫኑ መርከቦቹም ሆኑ ሌሎች የንግድ መርከቦች ሸቀጦቻቸዉን ከማራገፋቸዉ በፊት 14 ቀናት በየወደቡ እንዲቆዩ ወደቦቹን የሚቆጣጠሩት ኃይላት ያስገድዷቸዋል።በየብስ ወደየመምን የሚገባ ርዳታም ሆነ የንግድ የምግብ ሸቀጥ የለም።እንደገና ክሩገር

«ወረሺኙ እና ወረርሺኙን ለመከላከል እንቅስቃሴ መታገዱ፣ ወትሮም ጦርነት ለከፋ ችግር ያጋለጣቸዉ ሰዎች የሚቀምሱት እንኳ እንዳያገኙ እያደረገ ነዉ።የመን በፊትም ቢሆን ከዉጪ የሚገባ ምግብ ጥገኛ ናት።አሁን የዉጪ ንግድ ቆሟል።»

መሐመድ አ- ዘቂር።የ40 ዓመት ጎልማሳ ነዉ።የስድት ልጆች አባት።በጦርነቱ ከቤት ንብረቱ ከተፈናቀለ በኋላ ስምንት ራሱን የሚቀልበዉ ሲገኝ ዕቃ እየተሸከመ፣ ብዙ ጊዜ ግን የተጣሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ለቀሞ በመሸጥ ነዉ።የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለመከላከል «በየቤታችሁ ቆዩ» ብሎ ምክርን «እንዴት አድርጌ?» ይላል መሐመድ።

«ስለ ኮሮና በሽታ እየሰማን ነዉ።ከየቤታችን እንዳንወጣ ይነግሩናል።ያለስራ፣ እቤት መቀመጥ የምንችለዉ እንዴት ነዉ።ሊሆን አይችልም።ትንሽም ቢሆን ለመሸቀል መዉጣት አለብን።»

አብዛኛዉ የመናዊ ከመሐመድ ዘቂር ብዙም አይሻል።የቀን ሰራተኛ ነዉ።ሥራ ወትሮም ቀዝቅዞ ነበር አሁን ቆሟል።ንግድ የለም።ከሁሉም በላይ አንድ ሰዉ የኮሮና ተሕዋሲ ከለከፈዉ መታከሚያ ስፍራ ማግኘት መቻሉ አጠራጣሪ ነዉ።ድንበር የለሽ ሐኪሞች የተባለዉ ግብረ ሠናይ ድርጅት የየመን ተጠሪ ጄና ብራንዲት እንደሚሉት ለኮቪድ 19ኝ ዓይደለም ሌላዉንም በሽታ በተገቢዉ ሁኔታ መታከሚያ ቤት፣አካሚምም መድሐኒትም የለም።

Symbolbild Armut im Jemen
ምስል picture-alliance/dpa/XinHua/M. Mohammed

«ባንድ በኩል አጠቃላይ የሕዝቡ የጤና ይዞታ አለ።በብዙ የሐገሪቱ ክፍል የሚኖረዉ ህዝብ መሰረታዊ የዜና አገልግሎት አያገኝም።በሌላ በኩል ደግሞ በምግብ እጥረት የሚሰቃዩ ሰዎች በተለይም ብዙ ሕፃናት አሉ።ከዚሕ ቀደም በበሽታ የሚሰቃዩ ሰዎች አሉ።ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ አሉ።»

የተባበሩት መንግስታት ድጅርት ይሁን ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የየመኖችን የስቃይ ዓይነቶች «መፈናቀል፣ ረሐብ፣ የሕክምና እጦት፣ ኮሌራ፣ አሁን ደግሞ ኮሮና።» እያሉ ይዘረዝራሉ።የሚሰቃይ፣የሞተዉን ቁጥር ይደረድራሉ።ስቃዩን ለማቃለል የሚዉል ርዳታ ይማፀናሉ።የሁሉም ምንጭ ጦርነት ነዉ።ጦርነቱ ቀጥሏል። ርዳታ የሚለመኑት የጦር መሳሪያ ይቸበችባሉ።

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ