1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመን የእልቂት አብነት

ሰኞ፣ ጥር 16 2014

የሰነዓዉ ለቅሶ ዋይታ፣እልሕ ቁጭት ሲንተከተከተክ  ሰዓዳ ላይ ሌላ ሞት ይዘንብ ገባ።የሪያድ-አቡዳቢ ነገስታት ያዘመቷቸዉ የጦር ጄቶች የሰዓዳ እስር ቤትን አጋዩት።82 እስረኛ (ምናልባት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር የተሰደደ የሶማሌ ወይም የኢትዮጵያ ስደተኛ ጭምር) ተገደሉ።ከሁለት መቶ ስልሳ በላይ ቆሰሉ።

https://p.dw.com/p/461R5
Gefangenenaustausch im Jemen
ምስል Hani Mohammed/AP Photo/picture-alliance

የሪያድ-አቡዳቢ ነገስታት እብሪት መፈንጫ ሆናለች


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሟች ቁስለኞችን ብዛት ይቆጥራል፤አሟሟታቸዉን ያወግዛል።የረሕብተኛ-ተፈናቃይ ብዛትን ያሰላል፤ ዕርዳታ ይማፀናልም።የዓለም ብቸኛ ልዕለ ኃያል ሐገር ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ለሳዑዲ አረቢያና ለተከታዮችዋ በገዘብ የሚቸበችቡትን ጦር መሳሪያ ለዩክሬን በነፃ ያስታጥቃሉ።ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከ2014 ጀምራ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ለኪየቭ ያስታጠቀችዉ ጦር መሳሪያ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ተገምቷል።ምዕራባዉያኑ ዩክሬንን «ልትወርነዉ» እያሉ የሚወነጅሏት የሩሲያ፣ እስራልን ልታጠፋ፣ሳዑዲ አረቢያን ልትመታ፣የመንን ልትቆጣጠር ነዉ የሚሏት የኢራንና የምዕራባዉያኑ የንግድ ተሻሚ ቻይና ወታደሮች የጋራ የባሕር ላይ ዉጊያ ልምምድ ላይ ናቸዉ።ዩክሬን ገናለገና ትወረራለች ብሎ ማዓልት ወሊት የሚጨነቀዉ ምዕራብ ዓለም የየመንን መወረር ካፀደቀ፣ለወራሪዎች ሁለንተናዊ ድጋፍ ማንቆርቀር ከጀመረ ሰባት ዓመት አለፈዉ።የመኖችም በአሜሪካ-ብሪታንያ ቦምብ-ሚሳዬል፣በረሐብ፣ በሽታ በየቀኑ ያልቃሉ።እስከመቼ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
                                             
የቆጣሪዎችን ቁጥር እንጥቀስ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር የመንን ከወረረ ከመጋቢት 2015 እስከ ታሕሳስ 2021 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) 377 ሺሕ የመናዊ አልቋል።
29 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሐገሪቱ ሕዝብ  24.2 ሚሊዮኑ ሕይወቱን ማትረፊያ ምግብ አያገኝም።50ሺዉ ረሐብተኛ ነዉ።የበሽተኛዉም ቁጥር በሚሊዮን ይቆጠራል።በረሐብና በሽታ ከሚሰቃዩት መካከል 400 ሺሕዉ ሕፃናት ናቸዉ።እሷ አንዷ ናት።11 ዓመቷ ነዉ ግን የ4 ዓመት ሕፃን ያክል አትመዝንም።ብዙ አትናገርም።ታቃስታለች።ተርባለች።ዓይኗ ፈጥጧል፣ አጥንቷ ገጥጧል።ቆዳዋ ተሸብሽቧል።
እናት ዛሕራ አል-ኻዉሊኒ ሆስፒታል ይዛት ከገባች የዚያን ቀን አምስተኛ ቀኗ ነበር።
«እዚሕ ከመጣን አምስተኛ ቀናችን ነዉ።አልተሻላትም።መድሐኒትና የሕመም ማስታገሻ ይሰጧታል።ለሕክምናዉ ብዙ ገንዘብ እንከፍላለን።ሌላ ምን እናድርግ።»
የዛሕራ ልጅና የብጤዎቿን ምስል የሚያሳየዉ ቪዲዮ እዚሕ ዶቸ ቬለ የደረሰ ዕለት አብዛኛ የመንን የሚቆጣጠረዉ ሁቲ ወይም አንሳር አላሕ የተባለዉ ቡድን የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶችን ርዕሠ-ከተማ አቡዳቢን በሰዉ አልባ በራሪ በድሮን መደብደቡ ተሰማ።ሶስት ሰዎች ተገደሉ።
የአቡዳቢ፣የሪያድ ገዢዎች፣ የካይሮ፣አማን ኩዌይት ተከታዮቻቸዉ ጥቃቱን ለማዉገዝ፣አጥቂዎችን አሸባሪ ለማለት ጊዜ አልፈጀባቸዉም።የሪያድ አቡዳቢ ደጋፊ አስታጣቂዎችም ጥቃቱን በተተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በኩል ለማዉገዝ ኒዮርክ ላይ ተሰበሰቡ። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አምባሳደር ላና ኑሰቢሕ-ኒዮርክ።ሐሙስ።
                           
«የሁቲ አሸባሪዎች በሐገሬ ላይ ባደረሱት አረመኔያዊ የሽብር ጥቃት ሶስት ሰዎች በመገደላቸዉና ስድስት በመቁሰላቸዉ -(ሁሉም ሰላማዊ ሰዎች ናቸዉ) የዛሬዉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ስብሰባ እንዲደረግ የጠየቀችዉ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ናት።» 
የዓረብ ሊግ ባለስልጣናትም ካይሮ ላይ ተሰበሰቡ።የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ደ ኤታ ኸሊፋ ሻሒን ለተሰብሳቢዎች እንደነገሩት «አሸባሪ» ያሉት ሁቲ በኢራን ባይደገፍ ኖሮ «ወረራዉ»ን ባልቀጠለ ነበር።
«አሸባሪዉ የሁቲ ቡድን፣ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ዉሳኔ በመጣስ ከኢራን የሚላክለት ጦር መሳሪያ ባይቀጥል ኖሮ ወረራዉን ባልቀጠለ ነበር።»
ወራሪዉ ማን ነዉ? አሸባሪዉስ? 
በ1960ዎች ማብቂያ ስልጣን ላይ የነበሩት የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች መንግስታቸዉ ቬትናምን የወረረዉ ኮሚንስቶችን ለማጥፋት ነዉ-ይሉ ነበር።የጦርነቱ መራዘም፣የሚጠፋዉ ሕይወትና ሐብት መብዛት ያሳሰበዉ አሜሪካዊ ግን «ዋንኞቹ ኮሚንስቶች ሞስኮ ላይ እያሉ» ቬትናም ድረስ ምን አዘመታችሁ እያለ ይተች፣ያላግጥ፣ ከልብም ይጠይቅ፣ ይሳለቅ ገባ።
ከአቡዳቢ ቴሕራን የሁለት ሰዓት በረራ ነዉ።አቡዳቢን ያስወረችዉ ኢራን ከሆነች የሪያድ-አቡዳቢ ገዢዎች በቅርብ ርቀት ቴሕራን ላይ የሚገኙ ዋና ጠላቶቻቸዉን ትተዉ ድፍን ሰባት ዓመት የመንን ለምን ያጠፋሉ?
«እናሞኛችሁ» ለሚሉ ዋሾች ሞኝ አለመሆንን ከማረጋገጥ ባለፍ በርእግጥ ጥያቄዉ ፖለቲካዊ አፀፋ ሊሆን አይችልም።ለወታደራዊዉ አፀፋም የሪያድ-አቡዳቢ ተሻራኪዎች ከለንደን ዋሽግተን በገፍ የሚሸምቱት ቦምብ ሚሳዬል የመን ላይ ማዝነቡን ቀጠሉ።
ሰሞኑን በቦምብ ሚሳዬል ለመንደድ ሁዴይዳ ቀደመች።በትንሽ ግምት ሶስት ተገደሉ።ርዕሰ-ከተማ ሰነዓ ቀጠለች።የሁቲዎችን ጄኔራል አብደላ ቃሲም አል ጁኔይድን መኖሪያ ቤትና ባካባቢዉ የሚገኙ ቤቶችን ባወደመዉ ድብደባ ጄኔራሉ፣ባለቤታቸዉ፣ ወንድ ልጃቸዉና ሌሎች 15 መንደርተኞች ተገደሉ።40 ሰዎች ቆስሉ።ጠበቃ አክረም ሐሙንድ ይጠይቃሉ-ለምን እያሉ?
                                      
«እነሱ (ሳዑዲ መራሹ ጦር) ሁሉንም ነገር ይደበድባሉ።ሰዎችን፣ ሕንፃዎችን ያጠቃሉ።ሁሉንም ያጠፋሉ።እገዳ ጥለዋል።ይገድላሉ፣ይገድላሉ።ምንድነዉ ይኸ? ለምንድ ነዉ ሁሉም  ጉዳዩን ዝም ያለዉ?በየቀኑ ሰዉ ይጨፈጨፋል።ሳምንቱን ሙሉ በአዉሮፕላን እየተደበደብን ነዉ።ሁሉም ሰዉ ሞትን እየተጋፈጠ ነዉ።የመጨረሻዉ ያደረጉት ነገር ደግሞ መገናኛ (ስልክና ኢንተርኔትን)መቁረጥ ነዉ።»
ብዙ ጥያቄ።ዜሮ መልስ።ጠበቃ አክረምና መንደርተኛዉ ከየመኖሪያ ቤቱ ፍርስራሽ፣ ከቤት-ቢሮዉ ቁሳቁስ ስብርባሪ መሐል የቃረሙትን የሰዉ አካል ቁርጥራጭ በከረጢት ቋጥረዉ፣ በሳጥን አሽገዉ ቀበሩ።
የቀድሞዉ የየመን የረጅም ጊዜ ገዢ ዓሊ አብደላ ሳሌሕ «የመንን መግዛት በብእባቦች ጭንቅላት ላይ እንደመደነስ ነዉ» ብለዉ ነበር አሉ።ከሪያድ-ዋሽንግተን፣ ወደ ባግዳድ- ከባግዳድ ተመልሰዉ ወደ ሪያድ-ዋሽግተን፣ ከአል አሕመር ወደ አል-ሁቲ ሲፈናጠሩ ከ30 ዓመታት በላይ የመን ላይ «መደነስ» አልተሳናቸዉም ነበር።
ከሁቲ በአብድ ረቦ መንሱር ሐዲ አናት ላይ ዘለዉ ሪያድ ለመድረስ ሲማረፍ ሲሞክሩ ግን አዳለጣቸዉና በጥይት ተበጠራርቀዉ ላይመጡ ሔዱ።ታሕሳስ 2017።በቀደም በሳዑዲ አረቢያና በተባባሪዎቿ የተገደሉት ጄኔራል ከፕሬዝደንት ከሳሌሕ በተሻለ ክብር ተቀብረዋል።
ሰነዓዎች ደም ካጨቀየዉ ፍርስራሽ፣ አቧራ-ቡናኝ መሐል   የለቀሙትን የሰዉነት ቁርጥራጭ በሐዘን፣ዋይታ፣ በማርሽ፣ወታደራዊ ሥርዓት ቀብረዋልና።
                                    
የሰነዓዉ ለቅሶ ዋይታ፣እልሕ ቁጭት ሲንተከተከተክ  ሰዓዳ ላይ ሌላ ሞት ይዘንብ ገባ።የሪያድ-አቡዳቢ ነገስታት ያዘመቷቸዉ የጦር ጄቶች የሰዓዳ እስር ቤትን አጋዩት።82 እስረኛ (ምናልባት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር የተሰደደ የሶማሌ ወይም የኢትዮጵያ ስደተኛ ጭምር) ተገደሉ።ከሁለት መቶ ስልሳ በላይ ቆሰሉ።
ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር ጄኔራልን ከሲቢል ነዋሪ፣ ሕፃን ካዋቂ፣ እስረኛን ከወታደር፣ በሽተኛን ከጤነኛ፣ ተማሪን ከተዋጊ፣ መኖሪያ ቤትን ከጦር ሰፈር ሳይለይ በቦምብ ሚሳዬል ማርገፍ-ማዉደም ከጀመረ ስምንት ዓመት ሊደፍን ወር ቀረዉ።ለየመን ሕዝብ የዕርዳታ እሕል፣መድሐኒትና ሌሎች ዉሳቁሶች እንኳን እንዳይደርስ አዉሮፕላን ማረፊያዎች፣ ወደቦች፣የመኪና መንገዶች ተዘግተዉበታል።ወይም ፈራርሰዋል።
እስካሁን በየመን ሕዝብ ላይ የደረሰዉን ግፍም ሆነ የሰሞኑን የሰላማዊ ሰዎች እልቂት ለማዉገዝ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት፣ለአረብ ሊግም ሆነ ለሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ከቁብ የሚገባ ርዕሥ አይደለም።ለዓለም አቀፉ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ለአንቶኒዮ ጉተሬሽም ሶስት ሰዉ የተገደለበትም፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ  እስረኞች ጭምር የተጨፈጨፉበትም ድብደባ እኩል ነዉ።                                               
«በአቡዳቢ ላይ የደረሰዉ ጥቃት (ጦርነቱን) የሚያባብስ አሳዛኝና በኔ አስተያየት፣ ተቀባይነት የሌለዉ ከመሆኑም በላይ በጣም ትልቅ ስሕተት ነዉ።ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ ወይም ለሰላማዊ ሰዎች ጥንቃቄ የማያደርግ የአዉሮፕላን ድብደባም ተቀባይነት የለዉም።»

COP26 in Glasgow
ምስል Yves Herman/Pool/REUTERS
Jemen | Sanaa | Drohnen-Modell
ምስል MOHAMMED HUWAIS/AFP/Getty Images
Jemen Nach Luftangriff auf Sanaa
ምስል Khaled Abdullah/REUTERS

ዛሬ ደግሞ የየመን ሁቲዎች የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የንግድ ከተማ አቡዳቢን በሚሳዬልና ድሮን መምታቸዉን አስታዉቀዋል።የአቡዳቢ ገዢዎች ግን ጥቃቱን አክሽፈናል ባዮች ናቸዉ።ብዙ መቶ ሺዎችን የፈጀዉ፣ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለዉ፣ ከዓለም ከፍተኛዉን ሰብአዊ ቀዉስ ያስከተለዉ የየመን ወረራ ፍፃሜ የማግኘቱ ተስፋ ግን ዛሬም እንደ ጨለመ ነዉ።
የዓሊ አብደላ ሳሌኋ «የእባብ ጭንቃላትዋ» የመን ለግሪኩ ጥንታዊ ፈላስፋ ለክላዉዲዮስ ፔቶሎሚ የአረቢያ ዕንቁ ወይም የደስታ ጌጥ ነበረች።ራቅ ባለዉ ዘመን  የማኢን፣የቃጣባን፣የሐድራሞት፣የአዉሳን፣ የሳባ፣ የሒምየር፣ ኋላ ላይ የሙስሊሞች ስልጣኔ ዕምብርት ነበረች።አሁን ግን ለሪያድ-አቡዳቢ ነገስታት የእብሪት መፈንጫ፣ለምዕራባዉያን ቦምብ-ጠመንጃ መፈተሻ እንደሆነች ቀጥላለች።

Jemen Hodeida Rettungsaktion nach Luftangriff
ምስል Ansar Allah Media Office via AP/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ