1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

​​​​​​​የመቀሌ መያዝ፤ የተመድ ርዳታና የኬሪያ እጅ መስጠት

ዓርብ፣ ኅዳር 25 2013

መቀሌ ከተማ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር መዋሏ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትግራይ ውስጥ ርዳታ ለመስጠት ከመንግሥት ጋር ስምምነት ማድረጉ እና የቀድሞዋ አፈ ጉባኤ እጃቸውን ለመንግሥት ሰጡ መባሉን በተመለከተም በርካታ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። አስተያየቶችን አሰባስበናል።

https://p.dw.com/p/3mCIT

በዜናው ከተደሰቱት አንስቶ እስከተከፉት ድረስ

የሕወሓት ከመቀሌ ከተማ ሽሽት

በሳምንቱ ዐበይት መነጋገሪያ የነበሩ ሦስት ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል። ሕወሓት ከመቀሌ ከተማ ሸሽቶ መውጣቱ እና የፌዴራል መከላከያ ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን መግለጡ በሳምንቱ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኗል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለትግራይ ክልል ሕዝብ፦ «ያለምንም መሰናክል» ሰብአዊ ርዳታ ማድረስ እንዲችል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መስማማቱን በተመለከተም ዳሰሳ እናደርጋለን። የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈ ጉባኤ እና የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ኬሪያ ኢብራሒም እጃቸውን ለመንግሥት ሰጡ መባሉን በተመለከተም በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። አብራችሁን ቆዩ!  ሙዚቃ፥

ባለፈው ቅዳሜ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ ም አመሻሽ ላይ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የመቀሌ ከተማን መቆጣጠሩን መንግሥት ይፋ ካደረገ በኋላ በርካታ አስተያየቶች ጎርፈዋል። እኛም ዜናውን በዶይቸ ቬለ አማርኛ ማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ላይ ማስፈራችንን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች ደርሶናል። በዜናው ከተደሰቱት አንስቶ እስከተከፉት ድረስ፣ ምስጋና ከሰጡት አንስቶ በመዘገባችን ዘለፋ እስካቀረቡት ድረስ የተሰጡትን አስተያየቶች ቃኝተናል። ስድብ፣ ዘለፋ፣ የብሔር ማንኳሰስ እና ጥላቻን የሚያንጸባርቊትን ወደ ጎን ትተን ለፍሬ የበቊ አስተያየቶችን ብቻ እንዲህ እያሰባጠርን እናሰማችሁ።

Äthiopien Tigray-Provinz Mekele
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP

ኤሊያስ ወርቊ የተባሉ የፌስቡክ ተከታያችን የመቀሌ መያዝን፦ «ታላቅ ዜና» ሲሉ በአጭሩ አወድሰዋል። ጆን ሚቼል የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ ዜናውን እንደሰሙ ለመቀበል የተቸገሩ ይመስላል። «ለምን ግን መቐለ ዉስጥ የሚኖር ሰው ደዉላቹ ወይ የእዉነት ዘገባ ለህዝብ ግልጽ ኣታርጉም» ሲሉ በመጠራጠር ይጠይቃሉ። በትግራይ የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ እንደነበር የተገነዘቡ ግን አይመስሉም። አለበለዚያ ለምን አትደውሉም ባላሉ እና የዜናውን እውነትነት ባልተጠራጠሩም ነበር።

ኢዛና የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ሌላ ቦታ በፌስቡክ ጽሑፍ ላይ፦ «መቀሌ በመከላከያ ቊጥጥር ስር ናት። ይኸ የቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ አይደለምና ከሱዳን ርዳታ የሚባል ነገር የለም። ጁንታው ተበላ» ሲሉ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ አዛንቀው ጽፈዋል።

ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)አመራር የመጨረሻ ምሽጉ አድርጎ ከቆየባት ከመቀሌ ከተማ መውጣቱ እና መከላከያ መግባቱን በተመለከተ ከተሰጡ አስተያየቶች ደግሞ የሚከተሉት ይገኙበታል።

መአዛ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ በትግራይ የግንኙነት መስመር እንዲመለስ ጠይቀዋል። «ህዝባችን ላይ በጨለማ ስለኾነው እንስማ» ሲሉም ጽፈዋል።

«ቋምጠሽ ትቀሪያታለሽ እንጅ በትግራይ ህዝብ ላይም ሆነ በሌላዉ ኢትዮጵያዉያን ላይ የናፈቃችሁት እልቂት ከሽፏል።» አስተያየቱ የዉልሰዉ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ሲኾን ለመአዛ የተሰጠ መልስ ነው። «ኢትዮጵያ የምትገርም አገር ናት። ይህ ጦርነት ወደ እርስበርስ እልቂት (Civil war) ሳያድግ የአማጺ እና የሕግ አስከባሪ ሆኖ ማለቁ ታላቅ ምስጢር ነው።» በትዊተር አስተያየቱን የሰጡት ባዬ ተሻገር የተባሉ ተጠቃሚ ናቸው።

ዳህላክ በሚል ስም ትዊተር ላይ የጻፉ ደግሞ፦ «አራት ኪሎ እያሉ ታንኩም፣ አየሩም፣ ባንኩም በእጃቸው እያለ ያልቻሉ፥ ትግራይ ሙሉ በሙሉ ሲያስተዳድርሩ ያልቻሉ፤ አሁን የትበረሃ ገብተው ነው የሚችሉት? በረሃውም እኮ ተዘግተዋል» ሲሉ አጠቃለዋል።

የሕወሓት ከመቀሌ ተሸንፎ መሸሽ ብቻውን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለዘመናት የዘለቀውን ግድያና መፈናቀል ላያስቀር እንደሚችል እና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያሻ አስተያየታቸውን የሰጡም አሉ።

Äthiopien Tigray-Provinz Straße in Mekele | ARCHIV
ምስል Maggie Fick/REUTERS

የአማራ ማስሚዲያ ተቋም በፌስቡ ገጹ፦ «የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርአት ችግር ትህነግና የውንብድና ፖለቲካዊ ቀመሯ ነው» በሚል ርእስ በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም አለኸኝ የተጻፈውን ዘለግ ያለ ጽሑፍ አስነብቧል።

የጽሕፈት ቤት ኃላፊው፦ «የሕግ ማስከበር ሥራው ባልተጠናቀቀበት በዚህ ሰአት የድል ሽምያ ውስጥ ገብተው የሚዋዥቁ የድል አጥቢያ አርበኞችን እየተመለከትን ነው» ሲሉ ይጠቁማሉ። «ትህነግ ከእነእብሪቷ ወደ እንጦሮጦስ እየወረደች በምትገኝበት በመቀሌ ሰማይ ስር የምታስወነጭፋቸው ምትሀታዊ አንደርብ የቤንሻንጉል ክልልን እየረበሸው ይገኛል። በንጹሀን ሞት ላይ እየተረማመደ ከርሱን መሙላት የሚፈልገው የኃይል አሰላለፍ የዘመቻውን አቅጣጫ በመቀልበስ ትህነግን ከጣረሞት እንዳይመልሳትና ተጨማሪ የጥፋት ጊዜ እንዳይሰጣት ያሰጋል» ሲሉም አስጠንቅቀዋል በፌስቡክ ጽሑፋቸው።

«በኦሮምያ ክልል አብዛኛው አካባቢ ሕገወጥነትን ልሱና ቅርሱ ያደረገው» ያሉት እና « የትህነግ የእንግዴ ልጅ» ሲሉ የገለጡት ኦነግ ሽኔ «የንጹሀንን ደም እየመጠጠ እስትንፋሱን ለማቆየት መንደፋደፉ አይቀርም» ብለዋል። ቀጠል አድርገው፦ «ይህ ቡድን የኦሮምያ ሸለቆዎች ሲጫኑት ከጉሙዝ አማፂ ቡድን ጋር በመሆን መተከልን የሚረብሽበት፣ ንጹሀንን የሚገድልበትና ሀብትና ንብረታቸውን የደረሰ ሰብላቸውን ጨምሮ የሚዘርፍበትና የሚያቃጥልበት ስውር ምክንያት እንደሀገር የተጀመረውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ አቅጣጫውን» ለማሳት እንደኾነም ኃላፊው በረዥም ጽሑፋቸው ይዘረዝራሉ።

ለመከላከያ ሠራዊቱ እና ለጦር አመራር ጀነራሎቹ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ውዳሴዎች ቀርበዋል። ካሌብ ታምሩ ትዊተር ገጻቸው ላይ ካሰፈሩት እናሰማችሁ፦ «አበባዉ ታደሰ ምሽግ ደረመሰ፤ ባጫ ደበሌ ገባ መቀሌ» ሲል ይነበባል ለጀነራሎቹ በአጭር ግጥም የቀረበው መወድስ።

ነገሮችን በቀልድ እያዋዙ ያለፉም በርካቶች ናቸው። በቀጣዩ ስላቅ ወደ ቀጣዩ ርእሰ ጉዳይ እንሸጋገር። ኩራተኛዋ ልዕልት በሚል ስም የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው ጽሑፉን ያቀረቡት። «እኔ የምፈራው» አሉ። «እኔ የምፈራው ዐቢይ ችግኝ ለመትከል መቀሌ ላይ ሲቆፍር ደፂን እንዳያገኘው ነው።»

ኬሪያ ኢብራሂም

Keria Ibrahim ehemalige Sprecherin Ethiopia's House of Federation
ምስል DW/M. Hailesialssie

«የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም እጃቸውን ሰጡ» ይኽን የዜና ርእስ በርካቶች በፌስቡክ ተቀባብለውታል። የሕወሐት ከፍተኛ አመራር የኮኑት ወ/ሮ ኬርያ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቅቀው ወደ መቀሌ ከመመለሳቸው አስቀድሞ በመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት የነበራቸው ባለሥልጣን ነበሩ። መቀሌ ከተያዘች በኋላ እጃቸውን ለመንግስት መስጠታቸው የተነገረላቸው ከሕወሓት ከፍተኛ አመራር የመጀመሪያዋ ናቸው። ግለሰቧ እጃቸውን መስጠታቸውን በተመለከተ የተለያዩ አመለካከቶች ተንጸባርቀዋል። ከምስጋና እስከ ትችት፤ ከፍርሃት እስከ ማስመሰል የሚመላለሱ ናቸው አስተያየቶቹ።

ሱሌይማን ሰዒድ ፌስቡክ ገጹ ላይ ቀጣዩን ጽፏል። «በቃ በሰላማዊ መንገድ እጅ መስጠት ይሻላል። ቅጣትንም ያቀላል። ከሁሉ በላይ ግን የሚፈሰውን ደም ያስቀራል። እኔ በበኩሌ አመሰግንሻለሁ» ይላል ጽሑፉ። 

ናፍቆት አስጨናቂ በትዊተር ገጿ፦ «እንኳን ኬሪያ፤ ያ ሰይጣን ጌታቸው አሰፋም ኢሰብአዊ በኾነ መልኩ ሊስተናገዱ አይገባቸውም። እናም አማራጭ ሲያጡ እጅ መስጠት ማንንም ጀግና አያስብልም» ብላለች። «ለእምነታቸው ቀናዒ ሙስሊም፤ ክርስቲያን አለያም የቡድሃ ተከታይ መኾንም» ከተጠያቂነት እንደማያድን በትዊተር ገጿ ላይ ጽፋለች።   

ስለሺ አለባቸው በበኩላቸው፦ «ቀድመውም ሰጡ መጨረሻ ከተጠያቂነት አያስመልጥም። ይልቅ ቶሎ ቶሎ እጅ ቢሰጡ ቶሎ ወደ ልማቱ ተመልሰን ያፈረሱትን እንሰራ ነበር» የሚል አስተያየት አስፍረዋል። ፍቃዱ ቲመርጋ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፦ «እጅ መስጠት ሽንፈት ሳይሆን ለሀገርና ለህዝብ ክብር መስጠት ነው» የሚል አጠር ያለ መልእክት አስፍረዋል።

ሙዚቃ፦

የሰብአዊ ዕርዳታ በትግራይ

UN-Sondersession zum 75. Geburtstag
ምስል Mike Segar/Reuters

ሌላው ሰሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ርእስ የኾነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትግራይ ክልል የሰብአዊ ዕርዳታ ለማድረስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መስማማቱን ማሳወቊ ነው። ይኽን በተመለከተ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ሞሐመድ ከማል፦ «ለትግራይ ሕዝብ በዚህ ጊዜ የሰብአዊ ርዳታ እጅግ ወሳኝ ነው» ሲል ትዊተር ገጹ ላይ ጽፏል። ሔለን የተባለች የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ በአጭሩ፦ «ልቤ ተሰበረ» ብላለች።

አብርሃም ዘለቀ ፌስቡክ ላይ ቀጣዩን ጽፏል። «አንድ ጥያቄ ለተጎዱ ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ ከሆነ በአለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ያ ሁሉ ሰው ሲፈናቀል ለምን እንርዳችሁ አላሉንም?» የዳዊት ኤርሚያስ አስተያየት እንዲህ ይነበባል፦ «ሲገቡና ሲወጡ በደንብ ፈትሿቸው ለጁንታ ማምለጫ እንዳይሆኑ።»

በትግራይ ክልል ከሰሞኑ ውጊያ አስቀድሞም ወደ 600 ሺህ የሚሆኑ በርዳታ እህል አቅርቦት የሚኖሩ ዜጎች መኖራቸው ተጠቅሷል። ከዚህም ባሻገር የመንግሥታቱ ድርጅት ከኤርትራ የተሰደዱ በትግራይ ድንበር ላይ ባሉ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ መቶ ሺህ ለሚገመቱ ሰዎችም የሚታደለው የምግብ አቅርቦት ማለቁን ማመልከቱም ተገልጿል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ