1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 4 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 4 2013

የጀርመን ቡንደስ ሊጋ የዘንድሮ ውድድር የፊታችን ዐርብ በባየር ሙይንሽን እና ሻልከ ግጥሚያ ይጀምራል። በሳምንቱ መጨረሻ በርካታ ጨዋታዎች ይኖራሉ። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን 90ኛ ድሉን አስመዝግቧል። ኢራናዊው የነጻ ትግል ፍልሚያ ባለድል የሞት ቅጣት ተፈጸመበት። እንዲሁም ተጨማሪ ዘገባዎችን አካተናል።

https://p.dw.com/p/3iSow
Fußball Robert Lewandwoski
ምስል picture-alliance/SvenSimon/F. Hoermann

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ቡንደስሊጋ
የጀርመን ቡንደስሊጋ የፊታችን ዐርብ በተለመደው የመክፈቻ ጨዋታ ይጀመራል።  ዐርብ ምሽት የመጀመሪያው ዙር የቡንደስሊጋ ግጥሚያ በባየር ሙይንሽን እና ሻልከ 04 ጋር አሊያንስ አሬና ስታዲየም ውስጥ የሚደረገው ግጥሚያ ነው። ባየር ሙይንሽን ካለፉት 7 ዓመታት አንስቶ ነጥብ የጣለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ በሌሎቹ በሙሉ አሸንፏል። በመክፈቻው ነጥብ የጣለው ባለፈው የጨዋታ ዘመን ከሔርታ ቤርሊን ጋር 2 እኩል በመውጣት ነው። 

በበነጋታው ቅዳሜ ስድስት ጨዋታዎች እንዲሁም እሁድ ላይፕሲሽ ከማይንትስ እንዲሁም ቮልፍስቡርግ ከባየር ሌቨርኩሰን ጋር ይጋጠማሉ። የቅዳሜ ጨዋታዎች፦ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከአርሚኒያ ቢሌፌልድ፣ ዑኒዮን ቤርሊን ከአውግስቡርግ፣ ኮልን ከሆፈንሃይም፣ ቬርደር ብሬመን ከሔርታ ቤርሊን፣ ሽቱትጋርት ከፍራይቡርግ እንዲሁም ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር ናቸው። 

ከግጥሚያዎቹ መካከልም በተለይ ዴር ክላሲከር (Der Klassiker) የተሰኘው በ7ኛው እና 24ኛው ሳምንት በባየር ሙይንሽን እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ መካከል የሚደረገው ግጥሚያ የሚጠበቅ ነው። ባለፈው ግጥሚያ በአሰልጣን ሐንሲ ፍሊክ የመጀመሪያ ግጥሚያቸው ባየር ሙይንሽን ቦሩስያ ዶርትሙንድን 4 ለ0 ነበር ያሸነፈው። ሌላው የሚጠበቅ ጨዋታ በቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ሻልከ መካከል የሚከናወነው ግጥሚያ ነው።

የቦሩስያ ዶርትሙንድ አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ
የቦሩስያ ዶርትሙንድ አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድምስል picture-alliance/SvenSimon/E. Kremser

ባየር ሙይንሽን
በዐርቡ ግጥሚያ ሌሮይ ሳኔ ከቸልሲ እንዲሁም ግብ ጠባቂው አሌክሳንደር ኑይብል ከሻልከ ለባየር ሙይንሽን ተሰላፊ ይኾናሉ ተብሎ ይጠበቃል። የቀድሞ የሻልከ ተጨዋች የነበረው የቸልሲው ሌሮይ ሳኔ ወደ ቡንደስሊጋው ተመልሶ ወደ ባየር ሙይንሽን ያቀናው በ50 ሚሊዮን ዩሮ ነው።

የባየር ሙይንሽን የክብር ፕሬዚደንት ዑሊ ሆኔስ፦ በሳምንቱ መጨረሻ ለቡድናቸው ሊፈርሙ እና በቡድኑ ላይቆዩ ስለሚችሉ ተጨዋቾችም ጥቁምታ ሰጥተዋል። የ29 ዓመቱ ስፔናዊ አማካይ ቲያጎ አልካንታራ እና የ32 ዓመቱ ጃቪ ማርቲኔዝ ውላቸው የሚጠናቀቀው ከአንድ ዓመት በኋላ ነው። ቲያጎ የአራት ዓመት ውል ለባየር እንደፈረመ ዑሊ ሆኔስ ቅዳሜ ዕለት ተናግረዋል። 

የ28 ዓመቱ ዳቪድ አላባ በባየር ሙይንሽን እንዲቆይ ብዙዎች እንደሚፈልጉ ኾኖም ግን «ቆጥቋጣ አማካሪ» እንዳለው ዑሊ ኾኔስ በቃለ መጠይቁ ገልጠዋል። ዳቪድ አላባ ምናልባት ባየር ሙይንሽንን ሊለቅ ይችላል እየተባለ ነው።

ኢቫን ፔሪሲች የሐንሲ ፍሊክ ቡድን ላይ ባለፈው ረቡዕ ለልምምድ ዐልታየም። የ31 ዓመቱን ክሮሺያዊው ልክ እንደ ፊሊፕ ኮቲንሆ እና አልቫሮ ኦድሪዞላ ወደ ተዋሰበት ቡድን አቅንቷል።  ወደ ኢንተር ሚላን እንዲመለስ የተደረገው ስምምነት አልተሳካም። ኢቫን በቀጣዩ የጨዋታ ዘመን ወደ አትሌቲኮ ማድሪድ ሊያቀና እንደሚችል ተዘግቧል። የ24 ዓመቱ ተከላካይ ሉቃስ ሔርናንዴዝ በበኩሉ የቊርጭምጭሚት እና የጉልበት ጉዳት በተደጋጋሚ ስለገጠመው በባየር ቆይታው አስተማማኝ አይደለም። 

የቀድሞ የሻልከ ተጨዋች የነበረው የቸልሲው ሌሮይ ሳኔ ለባየር ሙይንሽን የፈረመው በ50 ሚሊዮን ዩሮ ነው
የቀድሞ የሻልከ ተጨዋች የነበረው የቸልሲው ሌሮይ ሳኔ ለባየር ሙይንሽን የፈረመው በ50 ሚሊዮን ዩሮ ነውምስል imago images/Chai v.d. Laage

ፈረንሳዊው ተከላካይ የአራት ዓመት ውል ገና ቢቀረውም የባየርን ቆይታው የሚወሰነው በቀጣይ በሚያሳየው እንቅስቃሴ ነው። እሱም ቢኾን ወደ ሌላ ቡድን ቢያቀና ይመርጣል። ወደ ሌላ ቡድን ካቀናም አልፎንሶ ዳቪስ የግራ ክንፍ ተከላካይ ስለኾነ እና ዳቪድ አላባም ባየርን ውስጥ የሚቆይ ከኾነ እንደ ግራ ተከላካይነቱ ሊሰለፍ ይችላል። የቀድሞው የአትሌቲኮ ኮከብ በቀጣይ የውድድር ዘመን በባየር ሙይንሽን ለመቆየት የቻለውን ኹሉ እንደሚጥር ዐስታውቋል።

ሌዎን ጎሬቴሳካ በኩሉ ከባየር ሙይንሽን ጋር የገባው ውል ሊጠናቀቅ ኹለት ዓመት ይቀረዋል።  በሐንሲ ፍሊክ ቡድን ውስጥ ቀዳሚ ተሰላፊም ነው። የ25 ዓመቱ የባየርን አማካይ ከስፖርት 1 ከተሰኘ ማሠራጫ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ የዛሬ ኹለት ዓመት ቡድኑን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ «ጥሩ ስሜት እንደሚሰማው» ገልጧል።  

የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር የመጀመሪያ ዙር ውድድር ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ተጀምሯል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሦስተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ ከሚገኘው MSV ዱይስቡርግ ጋር ዛሬ ማታ ይጋጠማሉ። ደርቢ ነው። ባየር ሙይንሽን ከዱረን ጋር የነገ ወር ይጋጠማል። ለአዲስ ዓመት ነበር የታቀደው። ጨዋታው ለሌላ ጊዜ ተዘዋውሮ ነው።

ነፃ ትግል
ኢራን የነጻ ትግል ስፖርት ባለድል የነበረው ናቪድ አፍካሪን ቅዳሜ ዕለት በሞት ቀጥታለች። የ27 ዓመቱ ሪስሊንግ ተጋጣሚ ኢራናዊ የሞት ቅጣት የተፈጸመበት የዛሬ ኹለት ዓመት በሀገሪቱ በነበረው ተቃውሞ ወቅት ግድያ ፈጽሟል በሚል ነው። የኢራን መንግስት በወቅቱ የውኃ አቅርቦት ኩባንያ ጥበቃ የነበረ ሰውን ናቪድ ወግቶ ገድሏል ቢልም፤ የናቪድ ቤተሰቦች ግን አስተባብለዋል። 

በኢራን መንግስት የሞት ቅጣት የተፈጸመበት የነፃ ትግል ስፖርት ባለድል የነበረው ናቪድ አፍካሪ
በኢራን መንግስት የሞት ቅጣት የተፈጸመበት የነፃ ትግል ስፖርት ባለድል የነበረው ናቪድ አፍካሪምስል mashreghnews

የኢራን መንግስት ማሠራጪያ ጣቢያ የናቪድን ኑዛዜ አስተላልፏል። የናቪድ ጠበቃ እና ቤተሰቦች ኑዛዜው በማስገደድ የተፈጸመ ነው፤ ናቪድ ወንጀሉን ለመፈጸሙ ማስረጃ የለም ብለዋል። ናቪድ ወግቶ ገድሎታል የተባለው ጥበቃ ሐሰን ቱርክማን ቤተሰቦች ባቀረቡት ጥብቅ ጥያቄ እና በፍርድ ሒደት የሞት ቅጣቱ ተፈጻሚ መኾኑም ተዘግቧል። 

ኢራን የሞት ቅጣቱን ተፈጻሚ እንዳታደርግ በዓለም ዙሪያ በርካቶች ድምፃቸውን አሰምተው ነበር። ቀደም ሲል የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የናቪድ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው በትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ ገጻቸው ጽፈው ነበር። «ለኢራን መሪዎች፤ ይኽን ወጣት በሞት ከመቅጣት ሕይወቱን ብትታደጉ እጅግ በጣም ነው የማመሰግናችሁ» በማለት የሚነበበው የባለፈው ሳምንት የትራምፕ የትዊተር መልእክት፥ «አመሠግናለሁ!» ሲል ይጠናቀቃል። የኢራን መሪዎች የትራምፕንም ኾነ በዓለም ዙሪያ የበረታውን ጥያቄ ወደ ጎን ብለው የሞት ፍርዱን ተፈጻሚ አድርገዋል። 

Formel 1 | Grand Prix Toskana | Boxengasse
ምስል Getty Images/P. Fox

ፎርሙላ አንድ
እሁድ ዕለት በተከናወነው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን 90ኛ ድሉን አስመዝግቧል። ጣሊያን ውስጥ በተከናወነው የቱስካን ፉክክር በርካታ መኪናዎች እርስ በእርስ ተላትመው ነበር። ሌዎስ ሐሚልተን በመርሴዲስ የቡድን አጋሩ ቫልተሪ ቦታስ መጀመሪያ ላይ ቢቀደምም ከ7ኛው ዙር በኋላ ግን መሪነቱን በመያዝ በአሸናፊነት አጠናቋል። ቫለሪ ቦታስ የኹለተኛ ደረጃን ሲያገኝ፤ በሶስተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው የሬድ ቡል ሬሲንጉ አሽከርካሪ አሌክሳንደር አልቦን ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

አዜብ ታደሰ