1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስቀል በዓል በአዲግራት ከኤርትራዉያን ጋር

ሐሙስ፣ መስከረም 17 2011

የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዝያ ባሻገር ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የያዘ ብዙ ሊባልለት የሚችል ብቻ ሳይሆን በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር የሚቀራረቡበት ፤ ከበአሉ ጋር ተያይዞ የተጣሉ የሚታረቁበት፤ ብዙ ልንዘረዝራቸዉ የምንችል መገለጫዎች ያሉት ክብረ በዓል ነዉ።

https://p.dw.com/p/35bPc
Äthiopien Meskel Feierlichkeiten in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Ayalewaus

መስቀል ማለት ሰላም አንድነት ፍቅር ማለት ነዉ

«ከወድያኛዉ መንደር እዮሃ ሲል ከወዲኛዉ መንደር ያለዉም ተነስቶ እዮሃ ይላል። ከዝያ በየመንደሩ ያለዉ ሰዉ ሁሉ ይወጣል። እንደመጠራራት ድምፅ አሰምቶ አረሪ አረሪ ፤ መረሪ መረሪ፤ መስቀል ጠባ ዛሬ በሸዋ በትግሬ ….. ሲሉ በማዜም ችቦዉን ደመራዉን ይለኩሳሉ።» እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ! ወይዘሮ  ገብያነሽ መንግሥቱ ይባላሉ። በተወለዱበት በጎንደር አካባቢ የደመራን የመስቀልን በዓል እንዴት ያከብሩ እንደነበር ካጫወቱን የወሰድነዉን ነበር ያስደመጥናችሁ። ለረጅም ዓመታት በጀርመን ፍራንክፈርት አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ገብያነሽ ልጃቸዉን ለመጠየቅ ወደ ሰሜን አሜሪካ ሄደዉ ነዉ በስልክ ያገኘናቸዉ፤ ስለ መስቀል ባህላዊ አካበባር ያጫዉቱንን ይዘናል ። ስለመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን የመላዉ አዉሮጳ  ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ድዮናስዮስ ጠይቀናቸዉ ነበር።

« መስቀል የሰላም ምልክት ነዉ መስቀል የአንድነት ምልክት ነዉ። መስቀል የእርቅ ምልክት ነዉ ስለዚህ ይህን ምልክት የያዙ ክርስትያኖች ሁላችንም ሰላማዉያን የእርቅ ሰዎች ፤ የአንድነት ሰዎች ልንሆን ይገባል። የመስቀል በዓል በአገራችን በብሔራዊም ሆነ እንዲሁም በአደባባይ ከሚከበሩ በአላት አንዱ ነዉ። እንግዲህ በዋናነት የጌታችን የመዳሕኒታችን የእየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በአራተኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን በንግስት ኢሌሊ አማካኝነት ተቆፍሮ የተገኘበትን በዓል በማስመልከት ነዉ የምናከብረዉ ይህ በዓል በቤተ-ክርስትያን በድምቀት ከሚከበሩት በዓላትም አንዱ ነዉ። በተለይ በዚህ ዓመት ቤተ-ክርስትያናችን ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በሁለት ሲኖዶስ ተከፋፍላ ትኖር ስለነበረና፤ አሁን ደግሞ የሁለትነት ጠፍቶ ወደ አንድነት የመጣችበት፤ ምዕመናኑም ካህናቱም ጭምር በእጅጉ የተደሰቱበት ወቅት ስለሆነ ፤ ይህ የአንድነት በዓል በመሆኑ በደመቀና በተለየ ሁኔታ ይከበራል። መላ ኢትዮጵያዉያን እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ  አደረሳችሁ።»       

የመስቀል በዓል በመላ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት እየተከበረ ነዉ። የደመራ እና የመስቀል በዓል በብሔራዊ በተለይም በአደባባይ ከሚከበሩ የኢትዮጵያዉያን በዓላት መካከል አንዱ ነዉ። የደመራን በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለማክበር እየሄድኩ ነዉ የደወልሽዉ ሲሉ እንኳን አደረሳችሁ ያሉት በኢትዮጵያ የቅርስና ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዩናስ ደስታ፤ በበኩላቸዉ፤ «መስቀል በዓል የሕዝብ በዓል ነዉ። ኅብረተሰቡ ከዚህ ቀደም በሚከብረዉ መልኩ አዲስ አበባ ላይ እያከበረ ነዉ የአየሩም ሁኔታ ጥሩ ነዉ ። ወደዝያዉ ወደ መስቀል አደባባይ እየሄድኩ ነዉ።»

በ ጎርጎረሳዉያኑ በ 2013 በአዘርባጃን ባኩ መዲና ላይ በተካሄደዉ ስምንተኛዉ የዓለም ህልናዊ ባህላዊ ቅርሶች ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያዉያን የደመራና የመስቀል በዓል የተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት፥ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት «UNESCO» በዓለም ሕሊናዊ ቅርስነት መመዝገቡን ያስታወሱት አቶ ዮናስ ደስታ በመስቀል አደባባይ ብዙ የዉጭ ሃገር ዜጎች የበዓሉን አከባበር ለማየት መምጣታቸዉንም ተናግረዋል።

Äthiopien Meskel Feierlichkeiten in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Ayalewaus

« የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዝያ ባሻገር ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የያዘ ብዙ ሊባልለት የሚችል ብቻ ሳይሆን በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር የሚቀራረቡበት ፤ ከበአሉ ጋር ተያይዞ የተጣሉ የሚታረቁበት፤ ብዙ ልንዘረዝራቸዉ የምንችል መገለጫዎች ያሉት ክብረ በዓል ነዉ። ከኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ጋር ከአዲስ ዓመት ጋር የተያያዘ ስለሆነ፤ ከአዲስ ተስፋ ይዞ መጥቶአል። በዓሉ ከኛ ከባለቤቶቹ ባሻገር እንግዶችንም አሰባስቦ በሌሎች ዘንድ ኢትዮጵያንን ከማስተዋወቅ ባሻገር ኤኮኖሚንም ማግኘት የምንችልበት መንገድ አለ። ያን እድል ለማስፋት የሚመለከታቸዉ አካላት እየተንቀሳቀሰ መጥቶአል። የዝያም ዉጤት ሆኖ ነዉ የመስቀል በዓልን በተመ የቅርስ ጥበቃ መጥገብ ዉስጥ ለማስመዝገብ የቻልነዉ። ስለዚህም ይህን ስራ ነዉ እኛ እንደ ቅርስ ባለስልጣን መስርያ ቤት ለማስተባበር እየሞከርን የመጣነዉ። የሃይማኖት ተቋማትም በስፋት ኅብረተሰቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተሳትፎ ያላቸዉ አካላት  በቅንጅት በየዓመቱ እየሰሩ ዛሬም በሚያምር መልኩ እያየነዉ ነዉ።»          

ከአገር ከወጣሁ ከ 40ዓመት በላይ ሆነኝ ያሉን ገብያነሽ መንግሥቱ፤ በተወለድኩበት አካባቢ የመስቀል አከባበር ልዩ ነበር ሲሉ ነግረዉናል። ወይዘሮ ገብያነሽ ወ/ሮ ገሊላ ወ/ጊዮርጊስ በሚል ስያሜም እንደሚታወቁ ነግረዉኛል ። በተወለድኩበት አካባቢ የመስቀል አከባበር አሉ በመቀጠል።

«በአገር ቤት የተወለድኩት በጎንደር ክፍለሃገር ጠዳ ወረዳ በሚባለዉ ጌራ ጊዮርጊስ አገረ ስብከት መገናኛ መንደር አዲቃ ከምትባል ቦታ ላይ ነዉ የተወለድኩት። እኔ በተወለድኩበት በገጠር አካባቢ መስቀል የሚለኮሰዉ ማለዳ ጠዋት በ17 ነዉ ። እኔ እንደአየሁት ከሆነ በአዲስ አበባ ደመራ የሚለኮሰዉ በ 16 ማታ ነዉ። ማለዳ ላይ ደመራ ለመለኮስ ሽቅድምድም አለ ። መጀመርያ የለኮሰ እንደ አሸናፊ ነዉ የሚታየዉ። ደመራዉን ካነደድን በኋላ ወደ ቤት ሄደን የገንፎ ምቸት ግባ፤ የጎመን ምቸት ዉጣ ይባላል።»

በኢትዮጵያ የደመራ በዓል በደማቅ ተከብሮአል። በዉጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ በተለይ በአዉሮጳና በሰሜን አሜሪካ በአብዛኛዉ ባለፈዉ እሁድ የደመራ በአልን አክብረዋል። ምክንያቱም የሥራ እና የትምህርት ቤት ጉዳይ አመቺ ባለመሆኑ ነዉ። የፊታችን እሁድ በዚሁ በዉጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ደመራን ሊደምሩ የተዘጋጁም ጥቂት አይደሉም። ረዘም ላሉ ዓመታት በቦን ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ላቀች ተገንቸሬ ባለፈዉ እሁድ በኮለኝ የደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን የደመራ በድምቀት መከበሩን ተናግረዋል። የፊታችን እሁድ ደግሞ በፍራንክፈርት በድምቀት ይከበራል።

Äthiopien Meskel Feierlichkeiten in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Ayalewaus

የጎንደር መስቀል አከባበር ዘንድሮ እጥፍ ደማቅ ነበር ያሉን አድማጫችን አቶ የሽዋስ ዋለልኝ የእስልምና እምነት ተከታዮች የደመራን ቦታ ማፅዳታቸዉን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል በአዲግራት ዘንድሮ ለየት ያለ አከባበር ላይ ነን በርካታ ኤርትራዉያን መጥተዉ አብረዉን እያከበሩ ነዉ የኤርትራዉም ጳጳስ ይመጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነዉ ግን እስካሁን የተረጋገጠ ነገር የለም ስትል በአዲግራት ነዋሪ የሆነችዉ ወጣት ፍረወይኒ ገ/ፃድቅ ናት።

በኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶች ላይ ጥናት እና ምርምር ያደረጉት የታሪክ ተመራማሪዉ አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ ፤ የመስቀል በዓል ከሃይማኖት በዓልነቱ ባሻገር በማኅበራዊ ሕይወት ከፍተኛ ሚናን የሚያበረክት በመሆኑ ሊጠበቅ ሊከበር እንደሚገባ ተናግረዋል። አቶ ኃይለመለኮት የኢትዮጵያዉያን የመስቀል በዓል በመንግሥታቱ የቅርስ ማኅደር እንዲካተት ከፍተኛ ጥረት በማድረጋቸዉ የምስክር ወረቀትን አግኝተዋል።

በፍራንክፈርት ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ካህን መሪ ጌታ ብሥራት ካሳሁን በተለይ የዘንድሮዉ በዓል የሚያስደስት ነዉ ሲሉ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶች ላይ ጥናት እና ምርምር ያደረጉት የታሪክ ተመራማሪዉ አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ ፤ የመስቀል በዓል ከሃይማኖት ከበዓልነቱ ባሻገር በማኅበራዊ ሕይወት ከፍተኛ ሚናን የሚጫወት በመሆኑ ሊጠበቅ ሊከበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ