1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

የምስገና ቀን

ዓርብ፣ ግንቦት 6 2013

ሰሞኑን ኢትዮጵያ ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተማሪዎች ወላጆቻቸውን እና መምህራንን የሚያመሠግኑበት አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ያነጋገርናቸው ተማሪዎች እንደገለፁልን በተለይ ለመምህራኖቻቸው ግጥም እና  ሙዚቃ በማቅረብ እንዲሁም የምስክር ወረቀት እና ስጦታ በማበርከት ምስጋናቸውን ገልፀዋል። 

https://p.dw.com/p/3tLaY
Äthiopien Sprachschülerinnen und Schüler im Goethe-Institut in Addis Abeba
ምስል Goethe-Institut Addis Abeba

በትምህርት ቤት ዘመናችን ፤ አርዓያ የሆኑን ወይም የምናደንቃቸው መምህራን አይጠፉም። ግን ምን ያህሎቻችን አጋጣሚውን ተጠቅመን ይህንን ለእነዚህ መምህራኖች ገልጸንላቸዋል?  ሰሞኑን በትምህርት  ሚኒስቴር እና ቅን ኢትዮጵያ በሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት አነሳሽነት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መምህራኖቻቸውን እና ወላጆቻቸውን ያመሰገኑበት መርሀ-ግብር ተካሂደዋል። ለምስጋናው የተያዘው ቀን ግንቦት ሶስት የነበረ ሲሆን አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ቀደም ብለው ሌሎች ደግሞ በተቆረጠለት ቀን እና ከዚያም በኋላ ማካሄዳቸውን ለመረዳት ችለናል። ሱመያ ሳሙኤል አዲስ አበባ የሚገኘው የ « ኪድስ ኒው ፍላወር ትምህርት ቤት » የ6ኛ ክፍል ተማሪ ናት። በትምህርት ቤታቸው ግንቦት አራት በተካሄደው የምስጋና ሥነ ሥርዓት በመድረክ ላይ ምስጋና ካቀረቡት ተማሪዎች አንዷ ናት።  « እኔና እና ጓደኛዬ ተባብረን ለሁሉም የግቢው መምህራን የምስክር ወረቀት አዘጋጅተናል።» ከዚህም ባሻገር ግጥሞች እና ሙዚቃ ሳይቀር በደማቅ ሁኔታ መከበሩን የ 12ኛ ክፍል ተማሪዋ ትናገራለች።

Flüchtlingslager in Afar, Äthiopien
በአፋር አንድ የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ምስል DW/T. Haile-Giorgis

ወይዘሮ ሂሩት አሰፋ ሱመያ የምትማርበት የ ኪድስ ኒው ፍላወር ትምህርት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ናቸው። ትምህርት ቤቱ ከጀማሪ አንስቶ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን እንደሚያስተምር ነግረውናል። « ዝግጅቱ የተካሄደው የጠዋት ሰልፍ ላይ ነው። የተለያዩ ተማሪዎች ግጥም እና የተለያዩ የምስጋና ፁሁፎችን ለመምህራኖቻቸው አቅርበዋል» ይህም ቀደም ብሎ ታቅዶ እንደነበር ወይዘሮ ሂሩት ይናገራሉ።  አብይ ሽባባው ምስጋና ከቀረበላቸው ወንድ መምህራን አንዱ ናቸው። ከ  1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን የተፈጥሮ ሳይንስ ያስተምራሉ። ተማሪዎቹ ያደረጉት ነገር « ያስደስታል። ሞራል የሚሰጥ ነገር ነው» ይላሉ። እንደዛም ሆኖ ሱመያ ለመምህራኖቻችን ያቀረብነው የምስጋና ፕሮግራም በቂ አይደለም ትላለች። ስለሆነም ተማሪዎች ክፍል ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ ባይረብሹ እና መምህራንን ቢረዷቸው ጥሩ ነው ትላለች። ከዚህ ቀደም በዚህ መልኩ ባይሆንም ተማሪዎች አንዳንድ ነገሮችን ገዝተው መምህራኖቻቸውን እንዳመሠገኑ ለዶይቸ ቬለ ገልፃለች።

ተማሪ ሜሮን ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስዳለች። ዝዋይ ከተማ ሼር የሚባል ትምህርት ቤት ትማር የነበረችው ሜሮን ይህ የምስጋና ቀን እስከሚደርስ በጉጉት እየተጠባበቅን ነበር ትላለች። « በተለይ ደግሞ አሁን ወደ ዮንቨርስቲ የሚገቡት ተማሪዎች» ትላለች። እሷም በምትማርበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለመምህራን በግጥም ምስጋናቸውን ገልፀዋል። የእቃ ሽልማት ያገኙም መምህራን ነበሩ።  ትምህርት ቤት ድረስ 7 ኪሎ ሜትር በታክሲ እየተጓዘች የተማረችው ሜሮን ከመምህራኖቿ በሙሉ በጣም የምታደንቃቸው የ 11ኛ ክፍል የታሪክ መምህሯን ነው። ይህም« ሌሎች መፅሀፎችንም እያመጡ ያስተምሩን፤ ያስጠኑን ስለነበር ነው» ትላለች። ትምህርት ቤት መልሶ ከተከፈተ በኋላ በተለይ መልቀቂያ ፈተና የሚፈተኑ ተማሪዎን መምህራን ከተመደበው ጊዜ በላይ ሰዓታቸውን እየወሰዱ ተማሪዎችን ያስተምሩ እና ያስጠኑ ስለነበር ሜሮን ለነዚህ መምህራን ያላት ምስጋና ከፍ ያለ ነው። 

Schüler in einem Dorf in Äthiopien
ምስል picture-alliance/ dpa

ወይዘሮ ሰርካለም በሪሁን አዲስ አበባ የሚገኘው የቤተሰብ አካዳሚ 1ኛ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው። እሳቸው በሚያስተዳድሩት ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ይማራሉ። በዚህ ትምህርት ቤትም የምስጋናው ሥነ ስርዓት ተካሂዷል። ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመቱ ነው። « መምህራኖቻችንን አበረታተዋል» የሚሉት ወይዘሮ ሰርካለም ሚያዚያ 19 በተካሄደው የምስጋና ሥነ ሥርዓት ላይ ዘንድሮ ወላጆች « እኔም ባለቤት ነኝ፤ ልጆቼን የሚያስተምሩትን መምህራን ማመስገን አለብኝ በሚል» ተገኝተው እንደነበር ገልፀውልናል። ቢታንያ ዐብይ ፣ ወ/ሮ ሰርካለም ርዕሰ መምህር የሆኑበት የቤተሰብ አካዳሚ ትምህርት ቤት የ 6ኛ ክፍል ተማሪ ናት።  መምህር እና ወላጆቿን ያመሠገነችው መዝሙር እና ፉከራ በማቅረብ ነው።

ፍኖት በድሬደዋ ከተማ የሚገኘው አዲስ ህይወት ትምህርት ቤት ተማሪ ናት። እንደ ሌሎቹ ተማሪዎች ምንም አይነት የምስጋና ስነ ስርዓት በትምህርት ቤቷ ሰሞኑን ሲካሄድ አልታዘበችም። እንደ ሌሎቹ ተማሪዎች እድሉን አግኝታ ቢሆን ኖሮ  የቀድሞ የሂሳብ መምህሯን ማመስገን ትወዳለች። ከዚህም ባሻገር ወላጆቿን።

በትምህርት ሚኒስቴር እና ቅን ኢትዮጵያ ግብረ ሰናይ በኩል ግንቦት ሶስት ቀን በተካሄደው መርሀ ግብር ላይ ይህ ወላጆችን እና መምህራንን የማመስገን ቀን በየአመቱ ግንቦት በገባ የመጀመሪያው ሳምንት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚከበር ተገልጿል። 

ልደት አበበ 

ሂሩት መለሰ