1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመልካም ኅሊና በጎ አድራጊዎች

ዓርብ፣ ኅዳር 11 2013

ምስክር ታሪኩ እና ጀማል በንቲ በኮሮና ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተዘጉ በኋላ ይህንን ጊዜያቸውን የተለያዩ በጎ አድራጎት ስራዎችን በማከናወን እያሳለፉ የሚገኙ ሁለት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው።

https://p.dw.com/p/3lYzO
Äthiopien Melkam Hilina charity center
ምስል Melkam Hilina

የመልካም ህሊና በጎ አድራጎት ማህበር ጎጀብ

ጎጀብ ቀበሌ በኦሮምያ እና ደቡብ ክልል አቅራቢያ በከፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ትገኛለች።  የዚህ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ምስክር ታሪኩ እና ጀማል በንቲ ለወትሮው ከየሚማሩበት ዮንቨርስቲዎች ወደ ከተማቸው የሚመለሱት በክረምት ወራት ነበር። ባለፈው ዓመት በኮሮና ምክንያት ትምህርት ከተቋረጠ ጊዜ አንስቶ ግን ውሎ እና አዳራቸው ጎጀብ ቀበሌ ውስጥ እንደበፊቱ ሆኗል።ምስክር በጅማ ዩንቨርስቲ የ 5ኛ ዓመት የኤሌክትሪካል ፓወር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ሲሆን ጀማል ደግሞ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲ የ4ኛ ዓመት ተመራቂ ተማሪ ነው። ለዚህ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት አዲስ ያልሆኑት እነዚህ ተማሪዎች ከዚህ በፊትም በክረምት ወራት ታናናሾቻቸውን በማስተማር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ገልፀውልናል። «የአሁኑ ስራችንን ለየት የሚያደርገው ወቅት የማይገድበው መሆኑ ነው» ይላል ጀማል። « ስንጀምር የሆነ ቤተ መጽሀፍት እንክፈት በሚል ነበር። ከዛ ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመሆን ወደ መዘጋጃ በመሄድ ፕሮፖዛል አስገባን።» ይላል መዘጋጃውም ቦታ በመስጠት ተባብሯቸዋል። ይህንንም ቦታ  አጥር አጥረው እና አሻሽለው የመጀመሪያ እቅዳቸውን አሳክተዋል።
 ከከተማ ቤተ መፅሐፍቱ በተጨማሪ ሌላው የወጣቶቹ ፕሮጀክት የኪነ ጥበብ ስራዎች ላይ የሚያተኩር ነው። ይህም ፕሮጀክት ወጣቶች ከትምህርት ሌላ የሚዝናኑባቸው አጋጣሚዎችን መፍጠር እና ተሰጥዎ ያላቸውን ወጣቶች ለማጎልበት ያለመ እንደሆነ ሌላው የዚህ የበጎ አድራጎት ማህበር መስራች ምስክር ያስረዳል። « ብዙ ድምጽ ያላቸው ልጆች፣ የስነ ፁሁፍ ችሎታ ያላቸው ልጆች አሉ። ነገር ግን ችሎታቸው ከዚህ ሰፈር አልፎ አይሄድም ነበር» ይላል።
በዚህ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ላይ ችሎታቸውን ያሳዩ አንዳንድ ወጣቶችም ወደ አዲስ አበባ ሄደው ትያትር የሚማሩበት አጋጣሚዎች እየተመቻቹላቸው እንደሆነ ወጣቶቹ ገልፀውልናል።  ሌላው ምስክር እና ጀማል ባለፉት ግማሽ አመታት ካከናወኗቸው ስራዎች መካከል ልጆችን ማስጠናት ይገኝበታል። « ከKG ጀምሮ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ ልጆችን ፤ ግብረ ገብ፣ ኮምፒውተር የመሳሰሉትን ትምህርቶች ስናስተምራቸው ነበር» ከዚህም ሌላ የአካባቢ ፅዳት፣ችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ ፣ የመንገድ ውስጥ ለውስጥ ስራ እና ሌሎችም ስራዎች ላይ ወጣቶቹ ተካፍለዋል። ወጣቶቹ መጀመሪያ ላይ የመሠረቱት ማህበር  «የጎጀብ በጎ አድራጎት ወጣቶች ማህበር » ይባል ነበር ። ይህንንም ስም ኋላ ላይ « የመልካም ህሊና በጎ አድራጎት ማህበር ጎጀብ» በሚል» ቀይረውታል። በሀምሌ ወር ላይ የጀመሩት ማህበርም በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ ዘርፎች አሉት። « ለወጣቱ መዝናኛ እና ዋናም አስበናል»ይላል ጀማል።

Äthiopien Melkam Hilina charity center
ምስል Melkam Hilina

የተለያዩ የኪነ ጥበብ ምሽቶችን ያዘጋጁት ወጣቶች እስካሁን ምንም አይነት ክፍያ ሳይቀበሉ መስራታቸውንም ነግረውናል።ዋና አላማቸው ሀሳባቸውን ማስተዋወቅ ነበር።  ስራቸውን ዘለቄታ ያለው እና አስተማማኝ የማድረጉ ጉዳይ «መጀመሪያ ላይ የአብዛኛው የማህበረሰባችንም ጥያቄ ነበር» የሚለው ምስክር ይህንን አስተማማኝ ለማድረግ «ለተለያዩ ወጣቶች በየዘርፉ የስራ ድርሻ ሰጥተናቸው የባለቤትነት ስሜት ለመፍጠር ችለናል» ይላል፣ ሌላው የዘላቂነቱ ሚስጥር ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ነው።  « ፋይናንስ ካለ ስራዎች ይሰራሉ።»አይቆምም ይላል ምስክር።
እነዚህን ወጣቶች በስልክ ለማግኘት ቀላል አልነበረም። በቀጠሮ ኔትወርክ ያለበት ቦታ ሄደው ነው ቃለ መጠይቁን ያደረግነው። የድምፅ ጥራቱም ጥሩ የሚባል አይደለም። ስለሆነም በአካባቢያቸው ያለውን የኔት ወርክ ችግር ለመቅረፍ ቀጣይ አላማቸው አድርገው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ምስክር ገልፆልናል። « ኔትዎርካችን መብራት ሲሄድ አብሮ ይቋረጣል።» ይህ ችግር ስምንት አመት ይሆነዋል የሚለው ምስክር ምርመር አድርገው መፍትሔ የሚሉትን ሀሳብ ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ በቅርቡ ውጤታማ የሚሆኑበት አጋጣሚዎች እንደተመቻቹ ይናገራል። 

ልደት አበበ

Äthiopien Melkam Hilina charity center
ምስል Melkam Hilina

ታምራት ዲንሳ