1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕጻናት ሀኪሞች የልምድ ልውውጥ በቦን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2015

የጨቅላ ሕጻናትና የእናቶች ሞት ምጣኔ የአንድን ሀገር የህክምና ደረጃ እንደሚያሳይ ይነገራል። በበለጸጉት ሃገራት የህክምና አገልግሎቱ ዘመኑን ተከትሎ እያደገ ከመሄዱም በላይ ለሁሉም ዜጋ ስለሚዳረስ ከህክምና ጉድለት ጋር በተገናኘ የጨቅላ ሕጻናትና ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ሞት አይሰማም። እንደኢትዮጵያ ባሉት ሃገራት ግን ትልቅ ችግር ነው።

https://p.dw.com/p/4Qo9X
Austauschprogramm UKB Universitätsklinikum Bonn
ምስል Shewaye Legesse/DW

የሕጻናት ሀኪሞች የልምድ ልውውጥ በቦን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል

በጥቁር አንበሳ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እና በቦን ዩኒቨርሲቲ ክሊኒክ የጨቅላ ሕጻናት ህክምና ክፍል መካከል ትብብር እና የልምድ ልውውጥ የማድረጉ መርሃግብር የጀመረው በቅርቡ ነው። በግለሰቦች ተነሳሽነት የተጠነሰሰው ዕቅድ ወደ ተግባር የተለወጠው ባለፈው ሳምንት ሁለት የሕጻናት ህክምና ባለሙያዎች ከጥቁር አንበሳ ወደ ጀርመኗ ቦን ከተማ ለሙያዊ ልምድ ልውውጥ ሲመጡ ነው። የህክምና ሙያው መሠረታዊ እውቀት አንድ አይነት ቢሆንም ህክምናውን ለመስጠት የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችም ሆኑ መድኃኒቶች አቅርቦት ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። የልጆች እና የጨቅላ ሕጻናቶች ሀኪም የሆኑት ዶክተር አስራት ደምፀ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሕጻናት ክፍል ሲያገለግሉ ከ10 ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል። ለሕጻናት ለየት ያለ ፍቅር ያላቸው እኚህ የሕጻናት ሀኪም በቦን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የሕጻናት ክፍል በህክምና ጉድለት የሚከሰት ሞት አለመኖሩ ስሜታቸውን ነክቶታል። «ያለው የህክምና ደረጃ የት እንደደረሰ ለማየት ችለናል፤ ለሕጻናቱ የሚደረገው ክብካቤ በነርሶችም በዶክተሮችም ምን ያህል እንደሆነ እና ሞት የሌለበት የጨቅላ ሕጻናት ህክምና ክፍል ማየት ለእኛ በጣም ትልቅ ነገር ነው።» ነው ያሉት።

ሌላኛዋ የልምድ ልውውጡ ተሳታፊ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በጨቅላ ሕጻናት ጽኑ ሕሙማን ክፍል አስተባባሪ ነርስ የሆኑት ሲስተር ጠጄ ቱፋም እንዲሁ በተለይ በንጽሕና ጉድለት ሊመጡ የሚችሉ ጉዳቶችን ማስወገድ የሚቻልበትን ስልት ኢትዮጵያ ውስጥም ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ብለው ያስባሉ።  እንደ እሳቸውም በአካል መጥተው በቀላሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ አሠራሮችን ለማየት እንዲችሉ ሌሎች ባልደረቦቻቸውም የዚህ የልምድ ልውውጥ ተሳታፊ እንዲሆኑም ነው የሚመኙት። በነገራችን ላይ ሁለቱም የሕጻናት ህክምና ባለሙያዎች እነሱ በሚሠሩበት ስፍራ በየጊዜ የሚያጋጥማቸው የጨቅላ ሕጻናት ሞት ያንገበግባቸዋል። አቅም ዕውቀትን አለመደገፉም አስቆጭቷቸዋል። በጉዳዩ ላይ ስንወያይም የህክምና ሙያ ምን ያህል ሰብአዊነትን የሚጠይቅ እንደሆነ ባገኘሁት አጋጣሚ ከእነዚህ ሁለት የሕጻናት ሀኪሞች ታዘብኩ።

Austauschprogramm UKB Universitätsklinikum Bonn
ዶክተር አስራት እና ሲስተር ጠጄ ከቦን ዩኒቨርሲቲ ክሊኒክ ባልደረቦች ጋር ምስል Shewaye Legesse/DW

የዓለም የጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው በመላው ዓለም እየቀነሰ የነበረው የሕጻናት እና የእናቶች ሞት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባስከተለው ተጽዕኖ ምክንያት ዳግም ከፍ የማለት አዝማሚያ እያሳየ ነው። ዶክተር አስራት በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለጨቅላ ሕጻናት ሞት ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ያነሳሉ። «በዓለም ላይ ሦስት ነገሮች ናቸው ጨቅላ ሕጻናትን የሚገድሉት፤ አንዱ ኢንፌክሽን ነው፤ ሁለተኛው ያለ ቀናቸው መወለዳቸው ነው ሦስተኛው ደግሞ የመታፈን ችግር ነው።»

እሳቸው እንደሚሉት የሞቱ መንስኤ ከታወቀ በዚያ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ቢቻል የሞት ምጣኔውን መቀነስ ይቻላል ነው።

Austauschprogramm UKB Universitätsklinikum Bonn
ዶክተር አስራት እና ሲስተር ጠጄ በዶቼ ቬለምስል Shewaye Legesse/DW

የሕጻናት ህክምናን ለማሻሻል በጤና ጥበቃ በኩል የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸውንም ዶክተር አስራት ይናገራሉ። «በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሠራ ያለ ነገር አለ፤ 80 ሆስፒታሎችን ደረጃ ሦስት ለማድረግ ጥረቶች አሉ።» ብለዋል። ይኽን መሰሉ የማሻሻያ እንቅስቃሴ በዘርፉ የሚሰጠው የህክምና ደረጃ ላይ ለውጥ እያመጣ እንደሆነም ገልጸዋል። የህክምናው ባለሙያዎች በዘርፉ ያሉትን ችግሮች በቅርበት አይተው የሚረዱበት እና ለችግሩ መፍትሄ የሚፈለግበት የተግባር ዕቅዶችን አውጥቶ ሥራ ላይ ማዋልን እንደሚጨምርም አመልክተዋል። ግን እንዲህ ያለው የሀኪም ቤቶችን ደረጃ የማሳደጉ ሥራ በ80 ሀኪም ቤቶች ብቻ መወሰን እንደሌለበት፤ ባሉት ከ200 በላይ የሚሆኑ የጨቅላ ሕጻናት ህክምና ክፍሎችም ተመሳሳይ ሥራ መሠራት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል። ለማብራሪያው ባለሙያዎቹን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር