1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ዉይይት 

ሐሙስ፣ ጥር 7 2012

የኢትዮጵያ የግብጽ እና የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ታዛቢነት ያደረጉት አግባቢ ዉጤት ያመጣ መስሏል።የሶስቱ ሐገራት ባለስልጣንት ከሶስት ቀናት ድርድር በኋላ ዉዝግቡን በስምምነት ለመጨረስ ቃል ገብተዋል።ባለስልጣናቱ የተግባቡባቸዉ   ዝርዝር ሃሳቦች ግን አልተገለጹም።

https://p.dw.com/p/3WKFT
USA Washington | Treffen Fitsum Arega, Botschafter Äthiopien & Präsident Donald Trump
ምስል Fitsum Arega - Ethiopian ambassador to the United States

ከሁለት ሳምንት በኋላ ተደራዳሪዎቹ ዳግም ይገናኛሉ

የኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮችን በድጋሚ በዋሽንግተን ያገናኘው የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ከአዲስ አበባው ውጤት አልባ የሶስትዮሽ ድርድር በኋላ ተስፋ ሰጪ የተባለለትን ስምምነት በማድረግ መጠናቀቁ ተገልጿል።

ዋሽግተን ዉስጥ የተነጋገሩት የሶስቱ ሐገራት ባለስልጣናት ከስምምነት ላይ ስለደረሱባቸው ዝርዝር ጉዳዮች የተባለነገር ባይኖርም ዉዝግቡን ለመቋጨት ከሁለት ሳምንት በኋላ እዚያው አሜሪካ ተመልሰው ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው መለያየታቸውም ተሰምቷል።

የኢትዮጵያ የግብጽ እና የሱዳንን ባለስልጣናት የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ፊት ለፊት እያገናኙ አንዴ የተስማሙ እየመሰለ፣ ሌላ ጊዜ ውጤት እያጣ አመታትን ተሻግሮ ታላቋን ሀገር አሜሪካንን አደራዳሪነት አስገብቷል።

ተደራዳሪዎቹ ቀደም ሲል ጥቅማቸውን ለማስከበር ያራምዱት ከነበረው አቋማቸው ማን ምን አግኝቶ፣ ምን አጣ፤ ማንስ ጥቅሙ እንዴት ተጠብቆለት ከስምምነት ተደረሰ ለጊዜው «የነበሩትን ልዩነቶች በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ መፍታት » በሚል መርህ ከስምምነት መደረሱ ነው የታወቀው።

ዝርዝር ስምምነት ምንም ሆነ ምን፣ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዓመታት ወደ ግድቡ የሚገባዉ የውሃ መጠን የሚፈለገውን ኃይል የማመንጨት መጠን የሚወስን በመሆኑ ኢትዮጵያ በዚህ በኩል ትኩረት አድርጋለች የሚሉት ከኢትዮጵያ ወገን አባል ተደራዳሪ የሆኑት ዶ/ር ይልማ ስለሺ ናቸው።

ግድቡ ውኃ የሚሞላዉ በዝናባማ ወቅት ማለትም በሐምሌ እና በነሐሴ እንደ ሁኔታውም በመስከረም ወራት እንደሚኾን ተጠቅሷል። የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የውኃ መጠን ከባሕር ጠለል በላይ 595 ሜትር እስኪደርስ እና ለመጀመሪያ ደረጃ የኃይል ማመንጨት እስኪበቃ ግድቡ ውኃ እንዲሞላ ሦስቱ ሃገራት ተስማምተዋል። ከከፍታ ሙሌቱ ለመድረስ የሚያስፈልገዉ ጊዜን በተመለከተ ግን የተባለ ነገር የለም።ኢትዮጵያ ያስቀመጠችዉ ረዥሙ የሙሌት ጊዜ 7 ዓመትን ፈቀቅ ሊያደርገው የሚችለው ተፈጥሯዊ ክስተት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው በማለት ዶክተር ይልማ ያክላሉ።

የስምምነቱ ማዕቀፍ የግድቡን ዉሃ የመያዝ ጊዜ በአመታት ወደ ፊት እንዲገፋ የማድረግ ዝንባሌ ከፈጠረ ከፈሰሰው የመዋዕለ ንዋይ አንጻር ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ሳያጋጥማት እንደማይቀር የሚናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውስጥ በተመራማሪነት የሚሰሩት አቶ አሜን አብደላ ናቸው።

ተደራዳሪዎቹ የህዳሴውን ግድብ የውሃ ሙሌት መጠን እና የቀን ገደብን ዋነኛ የመደራደሪያ ነጥብ የማድረጋቸውን ያህል የተፈጥሮ አካባቢ ልማት እና ጥበቃውም የማዕቀፉ አካል ሊሆን ይገባል ብለው ይከራከራሉ አቶ አሜን። በዚህ ረገድ ደግሞ ግብጽ ኃላፊነት አለባት በማለት ያስረዳሉ።

ስምምነቱ በተለይ የተራዘመ ድርቅ ሲኖር ለመከላከል ይቻል ዘንድ ሦስቱም ሃገራት ተቀራርበው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያሳስባል። እንደ ዶ/ር ይልማ ግን ዘመናትን ቆጥሮ ለሚመጣ ድርቅ ይህን ያህል ከመጨነቅ ይልቅ ኢትዮጵያ በፍጥነት ግድቡን ሞልታ አስከፊውን ጊዜ አስቀድሞ ማስቀረት ይቻላል ባይ ናቸው።

በግብጽ ጫና ለግድቡ ማስገንቢያ ዓለም ዓቀፍ ብድር እና ድጋፍ ተነፍጓት የቆየችው ኢትዮጵያ፣ አሁን የምትሻዉን ብድርና ድጋፍ ለማግኘት አለማቀፉ ኅብረተሰብ በሩን ይከፍትላት ይሆናል? ማን ምን አተረፈ ምንስ ከሰረ የሚለዉ ጥያቄም ከሁለት ሳምንት በኋላ ተደራዳሪዎቹ ዳግም ሲገናኙ የምንሰማው ይሆናል። 

USA Treffen über die äthiopische GERD-Delegation in Washington
ምስል Fitsum Arega, Ethiopian ambassador to the United States

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ