1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«ሕዳሴ ግድብ» ድርድር ወዴት? 

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 1 2012

የግብጽ፤ የሱዳንና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ከአንድ ወር በኋላ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ዳግም ሲገናኙ የ«ሕዳሴው ግድብ» የውኃ አሞላልን በተመለከተ ቁርጥ ያለ መፍትኄ እንዲያበጁ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይጠበቃል። ግብጽ ንግግሩ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መኪያሄዱ ያስደሰታት ይመስላል። በእርግጥ ከዋሽንግተኑ ንግግር ተጠቃሚው ሀገር የቱ ነው?

https://p.dw.com/p/3UeAn
Grand Ethiopian Renaissance Dam
ምስል picture-alliance/dpa/G. Forster

«ግድብ ሠርቶ እንደ ሐውልት ዐይን ዐይኑን እንደ ማየት»

ግብጽ፤ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በ«ሕዳሴው ግድብ» ዙሪያ ለመስማማት ከዘጠኝ ዓመታት በላይ በተደጋጋሚ ጊዜያት ቢነጋገሩም አኹንም ድረስ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም። ሦስቱ ሃገራት አንዴ አዲስ አበባ፤ ሌላ ግዜ ካርቱም እንደገና ደግሞ ካይሮ ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ተወያይተዋል። የንትርካቸው ሰበቡ ደግሞ ኢትዮጵያ የምታስገነባው ግዙፉ የ«ሕዳሴው ግድብ» ነው። አፍሪቃ ውስጥ አልሳካ ያለው ንግግር ምን ይዞ እንደሚመጣ ባይታወቅም ዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ውስጥ የሦስት ዙር ንግግር ተጀምሯል።

ዶክርተር ያዕቆብ አርሳኖ፦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሣይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምሕር እና የኃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪ ናቸው። ሦስቱ ሃገራት ወደ ዋሽንግተን የሄዱበትን አንድምታ ሲያብራሩ፦ «ወደ ዋሽንግተን የተኬደው ድርድሩን እዛ ለማድረግ አይደለም እኔ እስከሚገባኝ» ብለዋል። «ካኹን ቀደም ለተደጋገሙ ዙሮች እንዳልከው ካይሮም፣ ካርቱምም አዲስ አበባም ስለ ሕዳሴ ግድብ ውኃ ሙሊት እና ስለ ግድቡ ዘላቂ አስተዳደር መግባባት ላይ ለመድረስ ውይይቱ ተካሂዶ አንዳንድ መስመር የያዙ ውሳኔዎች እና መግባባቶች ላይ እንዲደረስ ነበር እነዚህ ውይይቶች ሲደረጉ የነበሩት» ሲሉም አክለዋል። 

Grand Ethiopian Renaissance Dam
ምስል picture-alliance/dpa/G. Forster

እነዚያ ስምምነቶች ላይ መድረስ እና መግባባት ላይ ግን ዛሬም የተደረሰ አይመስልም። የዛሬ ዓመት ግድም የሦስቱ ሃገራት የውኃ እና የግድብ አሞላል ጉዳይ ባለሞያዎቻቸው ጥናት አካሂደዋል። ባቀረቡት የጥናት ውጤት ላይም ተወያይተዋል። በኃይድሮሎጂ እና በውኃ አስተዳደር ልምድ ያላቸው እና ከሞላ ጎደል ዕውቀት ያላቸው ከሦስቱ ሃገራት የተውጣጡ አምስት አምስት ባለሞያዎች ጥናቱን ማካሄዳቸውን የጠቆሙት ዶክተር ያዕቆብ በውኃ ሚንስሮች ደረጃ ውሳኔ ሊሰጥበት ዕቅድ ተይዞ ነበር። 

«እነዚህ ሞዴሎች ተሠርተው ቀርበው ውይይቶች በባለሞያዎች ደረጃ ተካሂደዋል። ከዚያም ደግሞ ኤክስፐርቶቹ ስምምነት ላይ ለመድረስ ስላልቻሉ።  እያንዳንዱ ሀገር የራሱን ሞዴል የተሻለ ነው ብሎ እያቀረበ ጉዳዩ ስላስቸገረ ጉዳዩ ከዓመት በፊት ለሚንስትሮች ቀርቦ ሚንስትሮቹ በጉዳዩ ላይ ተነጋግረው ሞዴሉን መምረጥ ላይ እያሉ ግብጽ ውይይቱን በደንብ ተሳትፋበት ነገር ግን ስምምነቱን አለቆቼን አስፈቅጄ ነው በሚል የግብጽ ሚንስትር ቃለ-ጉባኤው ላይ ሳይፈርሙበት ሔዱ። ይኼ እንግዲህ ዓመት ከቆየ በኋላ እንደገና ጉዳዩ ተቀስቅሶ አኹን ውይይቱ በፍጥነት እየተካሄደበት ነው ያለው።»

ግብጽ አጠናሁት ባለችው ሞዴል መሰረት ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውኃ እንድትለቅ በኢትዮጵያ የግድብ አሞላል ሒደት የግብጽ አስዋን ግድብ ከባሕር ጠለል በላይ ከ165 ሜትር እንዳይቀንስ ትፈልጋለች። በዚህ ኹኔታ ኢትዮጵያ ብትስማማ ግድቡን ለሙላት ብዙ ጊዜ ማስጠበቁ አይቀርም። ከዚያ በላይ ደግሞ ይላሉ ዶክተር ያዕቆብ፦ በግብጽ ሐሳብ ከተኬደ «ግድብ ሠርቶ እንደ ሐውልት ዐይን ዐይኑን እንደ ማየት» ይኾናል ብለዋል።  ግብጽ ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት እንዲገባ ገና ከመነሻው አንስቶ ትፈልግ እንደነበረም ተናግረዋል። በዋሽንግተኑ ስብሰባ ምን መጠበቅ ይቻላል? «አንደምታው ወደፊት ስንመለከተው ግብጽ እምቢ የምትል ነገር ይመስላል» የዶክተር ያዕቆብ አስተያየት ነው።  ግብጽ «ከፍ ብሎ አደራዳሪ ገብቶበት የተሻለ አገኛለሁ፤ ሐሳቤን በተሻለ መንገድ አጸናለሁ፤ አደራዳሪዎቹም ሊረዱኝ ይችላሉ የሚል ግምት ይኖራትና እስከ ጃንዋሪ 15 እስካሁን ድረስ ባለው፤ በተጠናው፤ በቀረበው መንገድ ላትስማማ ትችላለች የሚል ጥርጣሬ አለ እንደዛ ይመስለኛል»ም ብለዋል። 

Grand Ethiopian Renaissance Dam
ምስል picture-alliance/dpa/G. Forster

ጥቅምት 26 ቀን፤ 2012 ዓ.ም የሦስቱ ሃገራት ተወካዮች የዩናይትድ ስቴትስ እና የዓለም ባንክ ባለሥልጣናት ባሉበት ዋሽንግተን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ በሦስት ዙር ንግግር አንዳች ውሳኔ ላይ ለመድረስ ተስማምተዋል። ግብጽ የውኃ አሞላሉ ለኅልውናዬ ስጋት ነው ስትል ኢትዮጵያ የግብጽ የውኃ ድርሻ ተጽዕኖ አይደረግበትም ስትል በተደጋጋሚ ተደመጣለች።  

ዋሽንግተን ውስጥ በነበረው ውይይት እንዲደረግ የታቀደው ንግግር ከኅዳር 5 ቀን እስከ ኅዳር 6 ቀን፤ 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ሲከናወን ትኩረቱን ያደረገው የተራዘመ ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት ስለሚኖረው የግድቡ የሙሊት ጊዜ ነው።  ኹለተኛው ዙር ንግግር በካይሮ መዲና ኅዳር 22 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ሲከናወንም የዩናይትድ ስቴትስ እና የዓለም ባንክ ተወካዮች ተገኝተዋል። ያኔም የሃገራቱ ዐቢይ መነጋገሪ የግድቡ አሞላል ነበር። በሦስተኛው እና ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ሊካሄድ በታቀደው ውይይት ሦስቱ ሃገራት እስከ ጥር 6 ቀን ቀን፤ 2012 ዓ.ም ድረስ አንድ ውሳኔ እና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ይጠበቃል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ