1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕክምና ባለሞያዎች ጥያቄ በኢትዮጵያ

እሑድ፣ ሰኔ 2 2011

በኢትዮጵያ የተለያዩ ሥፍራዎች ካለፉት ሦስት እና አራት ወራት አንስቶ በዋናነት እጩ (ኢንተርን) ሐኪሞች በአደባባይ ሰልፍም በአዳራሽም ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን አሰምተዋል። እጩ ሐኪሞች በዋናነት ያነሱትን ጥያቄ መንደርደሪያ በማድረግ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ላይ የተነሱ ጥያቄዎች፣ ተግዳሮታቸውንና መፍትኄዎቻቸውን ለመዳሰስ ሞክረናል።

https://p.dw.com/p/3K2rc
Äthiopien - Krankenhausmitabeiter protestieren in Addis Abeba
ምስል DW/S. Muchie

ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሞያዎችና የጤና ሥርዓቱ

በኢትዮጵያ የተለያዩ ሥፍራዎች ካለፉት ሦስት እና አራት ወራት አንስቶ በዋናነት እጩ ሐኪሞች (ኢንተርን የሚባሉት) በአደባባይ ሰልፍም በአዳራሽም ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን አሰምተዋል። የሕክምና አገልግሎት አሰጣጡ ያለበት ኹኔታ፤ የሥራ ዋስትና፣ ደሞዝን ጨምሮ የጥቅማጥቅም ጉዳይ እንዲሁም የጤና ስርዓቱን የሚመለከቱ ጥያቄዎች አንስተዋል። ጤና ጥበቃ ሚንሥቴር መልስ ያለውን ተናግሯል፤ ባለሞያዎቹንም ጠርቶ አነጋግሯል። ይኹንና የሕክምና ባለሞያዎቹ ጥያቄዎቻቸው በአግባቡ አለመመለሳቸውን እየገለጡ ነው። ጥያቄዎቹ የሕክምና አገልግሎት ጥራት፣ ለሞያ ሥነ-ምግባር መገዛት የሚሉ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችንም አስከትለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) አንድ ሀገር ካሏት ሐኪሞች ቢያንስ አንድ ሐኪም ለአንድ ሺህ ሰዎች መዳረስ አለበት ሲል ይመክራል። ኢትዮጵያ ያሏት አጠቃላይ ሐኪሞች ብዛት እና የሕዝብ ቊጥሩ ሲሰላ የዓለም ጤና ድርጅቱ ዝቅተኛው ካለው መሥፈርት እጅግ በርቀት የሚገኝ ነው። ይህም በኢትዮጵያ የሕክምና ባለሞያዎች በከፍተኛ ኹኔታ እጥረት እንዳለ አመላካች ነው።

WHO erklärt Schweinegrippe zur Pandemie
ምስል AP

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2001 ሚያዝያ ወር ላይ የአፍሪቃ ኅብረት ሃገራት ያጸደቁት የአቡጃው ስምምነት አባል ሃገራቱ ከዓመታዊ በጀታቸው ለጤናው ዘርፍ 15 በመቶ እንዲያውሉ ይጠይቃል። ኢትዮጵያ ይኽን ስምምነት ከፈረሙ ሃገራት አንዷ ናት። ኾኖም ለጤናው ዘርፍ ከዓመታዊ በጀቷ ከአምስት በመቶ ያልዘለለ አለመመደቧ በሕክምናው ዘርፍ ለሚነሱ የጥራት ጉድለቶች መሠረታዊ ሰበብ ተደርጎ ይጠቀሳል። 

በዛሬው ውይይት፦ እጩ ሐኪሞች በዋናነት ያነሱትን ጥያቄ መንደርደሪያ በማድረግ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ላይ የተነሱ ጥያቄዎች፣ ተግዳሮታቸውን እና መፍትኄዎቻቸውን ለመዳሰስ ተሞክሯል።  

ሙሉ ውይይቱን ታች ካለው የድምጽ ማዕቀፍ ውስጥ ማድመጥ ይቻላል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ