1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐዋሳ ሐይቅን ከብክለት ለማደን

ማክሰኞ፣ የካቲት 17 2012

በሐይቅ ዳርቻዎች ላይ የተሰፋፋው የእርሻ ሥራ እያስከተለ በሚገኘው ጉዳት ዙሪያ የሀዋሣ ሐይቅ በቀዳሚነት ቢጠቀስም በደቡብ ስምጥ ሸለቆ የሚገኙ ሌሎች ሐይቆችም የዚሁ ችግር ተጠቂ መሆናቸው ይታመናል፡፡

https://p.dw.com/p/3YOEA
Äthiopien Umweltschutz Awasasee
ምስል DW/S. Wegayehu

የሐዋሳ ሐይቅ የተጋረጠበት አደጋና መፍትሔዉ

በሐዋሳ ሐይቅ አካባቢ የነበሩ ደኖች መመናመን እና የእርሻ ማሳ መስፋፋት ሐይቁን ለብክለት ምናልባትም በዉስጡ የሚገኙ ዕፅዋትና እንስሳት ለጥፋት ማጋለጡ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።ችግሩ ያሳሰባቸዉ የተፈጥሮ ሐብት ተሟጋቾችና የሐይቁ ተጠቃሚዎች አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠዉ በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ።የየስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ልማት ፅሕፈት ቤት እና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ለረጅም ጊዜዉ ጥያቄ መልስ ለመስጠት መዘጋጀታቸዉን ይናገራሉ።

 

የሀዋሣ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተድላ ወ/ሚካኤል ከሀዋሣ ሀይቅ ጋር ያላቸው ትውውቅ አራት አስር ዓመታትን ይሻገራል፡፡ የግብርና ባለሙያውና በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የበጎ ፈቃድ አገልጋይ የሆኑት አቶ ተድላ የሀዋሣ ሀይቅ ቀደምት የነበረው ገጽታ ዛሬ ከሚታየው ጋር በእጅጉ የተለየ ሥለመሆኑ ይናገራሉ፡፡
በወቅቱ የሐይቁ ዳርቻ ጥቅጥቅ ባለደን የተሸፈነ በመሆኑ  ሰዎች በቅርበት ካልተጠጉ በቀር እንዳአሁኑ ከርቀት ለማየት ይቸገሩ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሀይቁን ዙሪያ መለስ የከበበው ደን ለማገዶ ፣ መሬቱን ደግሞ ለእርሻ ሥራ በመዋሉ ዛሬ ላይ ያኔ የነበረውን ውበቱን ማጣቱን ይናገራሉ፡፡ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀይቁ ዳርቻዎች ላይ እየተስፋፋ የመጣው የእርሻ ሥራ ለቀጣይ ህልውና ላይ አሉታዊ ተዕእኖ እያሳደረ እንደሚገኝ አቶ ተድላ ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በሐይቁ ዙሪያ የሚከናወኑ የእርሻ ሥራዎች በአፈር መሸርሸር ከሚፈጥሩት ደለል በተጨማሪ ለእርሻ ግብአትነት የሚውሉ ጉጂ ንጥረ ነገሮችም ሥጋት መሆናቸውን የአካባቢ ተቆርቆሪው አቶ ተድላ ይናገራሉ፡፡
በእርግጥ በሐይቅ ዳርቻዎች ላይ የተሰፋፋው የእርሻ ሥራ እያስከተለ በሚገኘው ጉዳት ዙሪያ የሀዋሣ ሐይቅ በቀዳሚነት ቢጠቀስም በደቡብ ስምጥ ሸለቆ የሚገኙ ሌሎች ሐይቆችም የዚሁ ችግር ተጠቂ መሆናቸው ይታመናል፡፡ እነኚህ ሐይቆችንና ወንዞችን የመጠበቅና የማልማት ሃላፊነት የተሰጠው የሥምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ልማት ጽ/ቤት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለጉዳዩ ትኩረት የሰጠ ይመስላል፡፡ የጽ/ቤቱ ሃላፊ አቶ ክፍሌ ደግፌ በደቡብ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙ ሐይቆችና ወንዞች ለጉዳት የተዳረገበትን መሠረታዊ ምክንያቶችንና ከመፍትሔ አማራጮችን በጥናት የመለየት ሥራ መከናወኑን ይናገራሉ፡፡
የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ልማት ባካሄደው ጥናት የሐይቆቹን ጥበቃ በዘላቂነት ለማከናወን በዙሪያቸው የሚገኙ የጥንቃቄ አጠቃቀም ሥፍራ ወይንም በፈር ዞን ከሰዎችና ከእንስሳት ንክኪ መራቅ እንዳለበት ይጠቁማል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ይህንን ሥፍራ ለመጠበቅ የሚያስችል የህግ ረቂቅ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ የሚገለፁት የጽ/ቤቱ ሀላፊ አቶ ክፍሌ የህጉ ማእቀፍ በሀይቆቹ ዙሪያ የሚካሄዱ ሕገ ወጥ የእርሻ ሥራዎችን ለመግታት ያግዛሉ ይላሉ፡፡
ከስምጥ ሸለቆ ሀይቆች አንዱ የሆነው የሀዋሣ ሀይቅ ሕገ ወጥ የእርሻ ሥራዎች ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ የሀዋሣ ከተማ አስተዳደር ሀይቁ የተጋረጠበትን አደጋ ከትምህርታዊ ግንዛቤ ባሻገር በሕግ ማዕቀፍ ለመደገፍ ያስችላል ያለው የራሱን የጥንቃቄ አጠቃቀም ሥፍራ ወይም የበፈር ዞን ሕግ በማውጣት ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
በአስተዳደሩ የተዘጋጀው የጥንቃቄ ሥፍራ ሕጉ በሐይቁ ዙሪያ የሚገኙ ዳርቻዎችን በአግባቡ ለመጠበቅና ለመንከባከብ እንደሚያግዝ በአስተዳደሩ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ጽ/ቤት የአካባቢ ጥበቃ ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አመለወርቅ ገብሩ ይናገራሉ፡፡
በጽ/ቤት አዘጋጅነት በፀደቀው ሕግ መሠረትም ቀደም ሲል በሐይቁ ዳርቻዎች ላይ የእርሻ ሥራዎችን ሲያከናውኑ ለቆዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ጋር ተስማሚ የሆኑ አማራጮች መዘጋጀታቸውን ነው ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪው አቶ አመለወርቅ የጠቆሙት ፡፡
በእርግጥ የተፈጥሮ ሀብቶች ለሰው ልጅ ጠቀሜታ መዋል አለባቸው የሚሉት የተፈጥሮ ሀብት ተቆርቋሪው አቶ ተድላ ወ/ሚካኤል ይሁን እንጂ አጠቃቀማችንን ለትውልድ ሊሻገር በሚችል መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

Lake Hawassa
ምስል DW/Y. Gebreegziabher
Äthiopien Umweltschutz Awasasee
ምስል DW/S. Wegayehu

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ