1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 27 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሐምሌ 27 2012

የጀርመን ቡድኖች ወደ ሩብ ፍጻሜ እና ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ የሚጠብቃቸውን ውድድር ለማካሔድ ዝግጅቶቻቸውን አጠናቀዋል። የጣሊያን ሴሪኣ ትናንት ተጠናቋል፤ ጁቬንቱስ የዋንጫው ባለቤት ኾኗል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የተሽከርካሪው ጎማ የፈነዳበት ሌዊስ ሐሚልተን ማሸነፍ ችሏል።

https://p.dw.com/p/3gMKx
F1 - GRAND PRIX 2020 Silverstone I Lewis Hamilton
ምስል Getty Images/Pool/A. Boyers

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ መሻገሪያ ኹለተኛ ዙር ግጥሚያዎች የፊታችን ዐርብ እና ቅዳሜ ይከናወናሉ። በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ከሚከናወኑት አራቱ ውድድሮች መካከል ባየር ሙይንሽን ተጋጣሚው ቸልሲን ጥሎ ወደ ሩብ ፍጻሜ የማለፍ ሰፊ ዕድል አለው። ሌላኛው ጀርመንን ወክሎ በሻምፒዮንስ ሊግ የሚወዳደረው ኤር ቤ ላይፕሲሽ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ከስፔኑ ኃያል አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር በሚቀጥለው ሳምንት ይፋለማል። በእንግሊዝ ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም በመጨረሻ ዙር ላይ የመርሴዲሱ የፊት ግራ ጎማ የፈነዳበት ሌዊስ ሐሚልተን እንዲያም ኾኖ በሚደንቅ ኹኔታ አሸንፏል። የኤፍ ኤ ካፕ የፍጻሜ ግጥሚያን እና ፊፋን የሚመለከት ዘገባም አካተናል።

ሻምፒዮንስ ሊግ

በሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ወደ ሩብ ፍጻሜ እና ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ የቡንደስሊጋው ባለድል ባየርሙይንሽን እና ኤር ቤ ላይፕሲሽ ወሳኝ ግጥሚያቸውን ከሰሞኑ ያከናውናሉ። የዛሬ ወር ግድም በወጣው እጣ መሠረት፦ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፋቸውን ያረጋገጡት ተጋጣሚዎች ፓሪ ሴንጀርሜን ከአታላንታ እንዲሁም ላይፕሲሽ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ናቸው። ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ በሚደረጉ ፍልሚያዎች የፊታችን ዐርብ ኦሎምፒክ ሊዮን ከጁቬንቱስ ጋር ይገናኛል። ምሽት በተመሳሳይ ሰአት ማንቸስተር ሲቲ እና ሪያል ማድሪድ ይፋለማሉ። በነጋታው ቅዳሜ ባየር ሙይንሽን ከቸልሲ እንዲሁም ባርሴሎና ከናፖሊ ተጋጥመው የሩብ ፍጻሜ ስምንቱ ተጋጣሚ ቡድኖች ይለያሉ።

DFB Pokal Finale - Bayer Leverkusen vs. Bayern Munich | Tor 0 : 2
ምስል picture-alliance/dpa/J. MacDougal

የጀርመኑ ኃያል ቡድን ባየርሙይንሽን ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ ከእንግሊዙ ቸልሲ ብርቱ ፉክክር ይገጥመዋል ተብሎ አይጠበቅም። ቸልሲ በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ፍጻሜ በአርሰናል 2 ለ1 በተሸነፈበት ግጥሚያ ወሳኝ ተጨዋቾቹ መጎዳታቸው ለቸልሲ ደጋፊዎች አሳዛኝ ቢኾንም፤ ለባየር ሙይንሽን ጥሩ አጋጣሚ ነው። የቸልሲ አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ ትናንት ይፋ እንዳደረገው ከኾነ፦ ጉዳት የደረሰበት ተጨዋች የመሀል እና የክንፍ ተሰላፊው የቀድሞው የዶርትሙንድ ተጨዋች ክርስቲያን ፑሊሲች ብቻ አይደለም።  ስፔናዊው ተከላካይ አምበሉ ሴሳር አፔሊኲዌታ እና አጥቂው ፔድሮም በደረሰባቸው ጉዳት የተነሳ ቅዳሜ ዕለት ሙይንሽን ከተማ አሊያንትስ አሬና ስታዲየም ውስጥ አይሰለፉም።

ባየር ሙይንሽን ለንደን ውስጥ ቸልሲን በመጀመሪያው ዙር ግጥሚያ 3 ለ0 ጉድ ማድረጉም ተጨማሪ ዕድል ይፈጥርለታል። እናም ባየር ሙይንሽን ቅዳሜ እለት አሊያንትስ አሬና ስታዲየሙ ውስጥ በሚያከናውነው የመልሱ ግጥሚያ የማለፍ ሰፊ ዕድል ይዞ ይገባል ማለት ነው።

ብዙዎች እንደገመቱት ባየር ሙይንሽን ቸልሲን አሸንፎ ወደ ሩብ ፍጻሜ ካለፈ ከፊቱ የሚጠብቁት ኹለቱም ቡድኖች በሻምፒዮንስ ሊግ ፉክክር ልምድ ያካበቱ እና ብርቱ የሚባሉ ተጋጣሚዎች ናቸው። ከባርሴሎና እና ከናፖሊ አሸናፊ የኾነው ቡድንን ይገጥማል። ናፖሊ በዚህ የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር እስካኹን ሽንፈት አልገጠመውም። ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት በመጀመሪያው ዙር ባደረገው ግጥሚያ ከባርሴሎና ጋር የተለያየው አንድ እኩል ነው። የመልሱ ግጥሚያ የሚከናወነው ባርሴሎና ውስጥ ነው።

ላይፕሲሽ በበኩሉ በሩብ ፍጻሜው የሚጋጠመው የሻምፒዮንስ ሊግ ባለድል የነበረው ሊቨርፑልን በደርሶ መልስ ማሰናበት ከቻለው አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ነው።

Fußball I Arsenal v Chelsea
ምስል picture-alliance/C. Ivill

ባየር ሙይንሽን ዐርብ ምሽት የሻምፒዮንስ ሊግ የአቋም መለኪያ ግጥሚያ አከናውኖ ኦሎምፒክ ማርሴይን 1 ለ 0 አሸንፏል። ተከላካዮችን በድንቅ ኹኔታ አልፎ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ በግራ እግሩ ያስቆጠረው ሰርጌ ግናብሬ ኹለተኛ ግብ የማግባት ዕድሉንም ለጥቂት ነበር ያጣው። የባየር ሙይንሽን ተጨዋቾች ተጋጣሚያቸው ላይ ግብ የማስቆጠር ተደጋጋሚ ዕድሎችን አግኝተው ነበር። ባየር ሙይንሽን በፈረንሳይ ሊግ አንድ ውስጥ ዘጠኝ ጊዜ ዋንጫ ማንሳት የቻለውን ጠንካራ ቡድን ኦሎምፒክ ማርሴይን ማሸነፉ ለቸልሲ ተጨማሪ ስጋት ሳይኾን አይቀርም።

አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ በቡድናቸው ውጤት መደሰታቸውን ገልጠዋል። «ባደረግነው የጨዋታ ስልት እጅግ በጣም ነው የተደሰትኩት»ም ብለዋል። በተለይ ደግሞ በርካታ ወራት በጉዳት ተለይቶ የቆየው የብሔራዊ ቡድኑ ተሰላፊ ኒክላስ ሱይሌ ዳግም ተሰላፊ መኾኑ ይበልጥ እንዳስደሰታቸው በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል። ኒክላስ ሱይሌ ጥቅምት 9 ቀን፣ 2012 ዓ.ም በቡንደስሊጋ ግጥሚያ ከአውግስቡርግ ጋር ኹለት እኩል በወጡበት ጨዋታ ነበር አደጋ የደረሰበት። በግራ እግሩ የጉልበት መጋጠሚያ ጅማት መላቀቅ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ለበርካታ ወራት ሳይሰለፍ ቆይቶ በዐርቡ ግጥሚያ ለግማሽ ሰአት ያኽል ተጫውቷል።

ባየር ሙይንሽን ኦሎምፒክ ማርሴይን ማሸነፉ የዛሬ ወር ባየር ሌቨርኩሰንን በጀርመን እግር ኳስ ማኅበር (DFB-Pokal) ፍጻሜ ግጥሚያ 4 ለ2  ድል ካደረገ በኋላ ያሸነፈው ተጨማሪ ድል ኾኖ ተመዝግቦለታል።

DFB Pokal Finale I Bayer Leverkusen I Bayern
ምስል Imago Images/J. Fromme

ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት በሚደረጉ ግጥሚያዎች ቀሪዎቹ አራቱ የመልስ ጨዋታዎች የፊታችን ዐርብ እና ቅዳሜ (ነሐሴ 2 እና 3) ይከናወናሉ።

ከሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ እስከ ቅዳሜ ድረስ የሚኪያኼዱ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎችም ኾኑ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ላይ ዘንድሮ በኮሮና ምክንያት ደርሶ መልስ ውድድር እንደማይኖር የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) ቀደም ሲል ወስኗል።  ውድድሮቹ በአጠቃላይ በፖርቹጋል ዋና ከተማ ሊዝቦን ውስጥ ይከናወናሉ።

ለሩብ ፍጻሜው እስካሁን ያለፉ ቡድኖች አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ፓሪስ ሳንጀርሜን፣ አትላንታ እና ላይፕሲሽ ናቸው። ፓሪስ ሳንጀርሜን ቦሩስያ ዶርትሙንድን በደርሶ መልስ 3 ለ2 ረትቶ ነው ሩብ ፍጻሜ የገባው። ላይፕሲሽ ቶትንሀምን 4 ለ0፤ አታላንታ ቫለንሺያን 8 ለ4 እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ ሊቨርፑልን በደርሶ መልስ 4 ለ2 አሸንፈው ነው ወደ ሩብ ፍጻሜው ያለፉት።

ኤር ቤ ላይፕሲሽ በበኩሉ በሻምፒዮንስ ሊግ ከተጋጣሚዎቹ የተሻለ ዕድል ላይኖረው ይችላል። ምክንያቱም ሌሎቹ ቡድኖች የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ የሚያከናውኑት በየሀገራቸው ያሉትን የሊግ ግጥሚያዎች ካጠናቀቁ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ነው። በአንጻሩ ኤርቤ ላይፕሲሽ እና ባየር ሙይንሽን በቡንደስሊጋው እና ሌሎች ግጥሚያዎች ካከናወኑ ረዘም ያለ ጊዜ አስቆጥረዋል። 

Fussball Bundesliga FC Augsburg vs. RB Leipzig | Tor Timo Werner
ምስል Imago Images/firo Sportphoto/M. Engelbrecht

የኤርቤ ላይፕሲሽ አሰልጣኝ ዩሊያን ናገልስማን ቡድኖች ከውድድር ሳይርቁ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ መግባታቸው የበለጠ ጥቅም አለው ብለዋል። የጀርመን ቡድኖች ለበጋ ረፍት በወሰዱበት ወቅት ሌሎች የሻምፒዮንስ ሊግ ተጋጣሚ የአውሮጳ ቡድኖች የሊግ ግጥሚያዎቻቸውን በማከናወን ላይ ነበሩ። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የትናንትና ሳምንት እሁድ ነው የተጠናቀቀው።  የስፔን ፕሪሜራ ዲቪዚዮን በበኩሉ ከፕሬሚየር ሊግ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ነው ያበቃው። የጣሊያን ሴሪ ኣ ትናንት ነው የተጠናቀቀው።

አሰልጣኝ ዩሊያን ናገልስማን ቡድናቸው ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ የመድረስ እድል እንዳለው ተጠይቀው ሐቁን ተናግረዋል። ኤርቤ ላይፕሲሽ እና አታላንታ ካሉት ቡድኖች ለዋንጫ ይደርሳሉ ተብለው ከተገመቱት ውስጥ እንደማይመደቡ አልሸሸጉም። ኾኖም «ቢልድ አም ሶንታግ» ለታበለው ጋዜጣ፦ «ዋንጫ አሸንፋለኹ ብዬ አላሰብኩበትም፤ ኾኖም ፍጹም ያልተጠበቀ ነገር ላደርግም እችል ይኾናል» ብለዋል። የሀገራቸው ቡድን ባየር ሙይንሽን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ሊያነሳ እንደሚችልም ግምታቸውን ሰጥተዋል።

ተጋጣሚው አትሌቲኮ ማድሪድ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ የወሰደው ባለፈውም የሻምፒዮንስ ሊግ ባለድል የነበረው ሊቨርፑልን ያሰናበተ ቡድን ነው። አትሌቲኮ ማድሪድ ቅዳሜ ዕለት እና የፊታችን ሐሙስ የአቋም መለኪያ ውድድር ማድረግ ነበረበት። ኾኖም ግን የስፔን ቡድኖች ለበጋ ረፍት ስለተበተኑ ተጋጣሚ ቡድን ማግኘት አልቻለም ሲል «ሙንዶ ዴፖርቲቮ» የተሰኘው የስፖርት ጋዜጣ ዘግቧል። እናም አትሌቲኮ ማድሪድ ለሻምፒዮንስ ሊግ ቀጣይ ጨዋታ አቋሙን መለካት አልቻለም። እናም አሰልጣኝ ዲዬጎ ሲሞኔ ቡድናቸውን ከማድሪድ በስተምዕራብ ወደሚገኘው ሲውዳድ ዴፖርቲቮ ወስደው ቅዳሜ ዕለት ልምምድ አከናውነዋል።

ኤርቤ ላይፕሲሽ ሐሙስ ዕለት የአቋም መለኪያ ግጥሚያ ከቮልፍስቡርግ ጋር አከናውኖ አንድ እኩል ተለያይቷል። አሰልጣኙ ቡድናቸው ከጥሩ ተጋጣሚ ጋር ጥሩ ፉክክክር ማድረጉን ተናግረዋል። ቮልፍስቡርግ በቡንደስሊጋው 7ኛ ኾኖ ነው ያጠናቀቀው። ኤርቤ ላይፕሲሽ ተጨማሪ የአቋም መለኪያ ለማድረግ ዕቅድ የለውም።

Champions League 2018 | Atletico Madrid v Borussia Dortmund
ምስል Reuters/J. Medina

የአውሮጳ ሊግ ግጥሚያዎችም ከነገ በስተያ ረቡዕ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ይከናወናሉ። ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ በሚደረጉት ኹለተኛ ዙር ስምንት ግጥሚያዎች ውስጥ ከጀርመን ቡድኖች፦ ቮልፍስቡርግ፣ ባየር ሌቨርኩሰን እና አይንራኅት ፍራንክፉርት ተካፋይ ናቸው።

በኤፍ ኤ ካፕ የፍጻሜ ግጥሚያ አርሰናል በፒየር ኤመሪክ ኦባማያንግ ኹለት ግቦች ቸልሲን 2 ለ 1 ድል አድርጓል። ዌምብሌ ስታዲየም ውስጥ በተከናወነው በቅዳሜው ዕለት የፍጻሜ ግጥሚያ ጨዋታው በተጀመረ አምስተኛው ደቂቃ ላይ ለቸልሲ ግብ ያስቆጠረው ጉዳት የደረሰበት ክርስቲያን ፑሊሲች ነው። በርካታ ቢጫ ካርዶች በታዩበት ግጥሚያ 73ኛው ደቂቃ ላይ ማቴዎ ኮቫቺች በኹለት ቢጫ (ቀይ ካርድ) ከሜዳ ተሰናብቷል።

ትናንት በተጠናቀቀው የጣሊያን ሴሪ ኣ 83 ነጥብ መሰብሰብ የቻለው ጁቬንቱስ ከኢንተር ሚላን በአንድ ነጥብ ልዩነት በልጦ ዋንጫውን ወስዷል። 78 ነጥብ ያለው አታላንታ እንዲሁም ተመሳሳይ ነጥብ ይዞ በግብ የተበለጠው ላትሲዮ በቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተሳታፊዎች መኾናቸውን አረጋግጠዋል። ኤኤስ ሮም ለአውሮጳ ሊግ ሲያልፍ ኤስ ሚላን  ወደ ማጣሪያው ይገባል። ኡኤስ ሌቼ፤ ብሬሲካ ካልቺዮ እና ፌራራ ወራጅ ኾነዋል።

ፎርሙላ አንድ

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን የመርሴዲሱ የፊት ግራ ጎማ ፈንድቶም ቢኾን በአስደናቂ ኹኔታ አሸናፊ ኾኗል። ሐሚልተን በመጨረሻዎቹ ዙሮች የተሽከርካሪው ጎማ ከመቦትረፉም ባሻገር በፍጥነት ሲያሽከረክር ተሽከርካሪው ከመሬቱ ጋር በሚፈጥረው ሰበቃ የእሳት ብልጭታዎችም ታይተው ነበር። በታላቋ ብሪታንያ ግራንድ ፕሪ ውድድር ላይም ያስመዘገበው ድል ሰባተኛ ኾኖ ተቆጥሮለታል። የሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፓን ኹለተኛ ሲወጣ፤ የፌራሪው ቻርለስ ሌክሌርክ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል። ጀርመናዊው የፌራሪ አሽከርካሪ ሰባስቲያን ፌትል በ10ኛ ደረጃ አጠናቋል።

F1 - GRAND PRIX 2020 Silverstone I Lewis Hamilton
ምስል Getty Images/Pool/B. Stansall

ስዊትዘርላንድ በፊፋ ፕሬዚደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ላይ ምርመራ ጀምራለች። የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA) ኃላፊ፦ «የወንጀል ተግባር ምልክቶች»ን አስመልክቶ ከስዊትዘርላንድ አቃቤ-ሕግ ሚካኤል ላውበር ጋር ምሥጢራዊ ግንኙነት አድርገዋል በሚል ነው ክስ የተከፈተባቸው። አቃቤ ሕጉ ከፊፋ ጋር በነበራቸው ግንኙነት የተነሳ ባለፈው ሐሙስ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ዐስታውቀዋል።

ክስ የተከፈተባቸው የፊፋው ፕሬዚደንት ከሳቸው ቀደም ብለው ፊፋን ይመሩ የነበሩት ሴፕ ብላተር በሙስና ቅሌት ሥልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ነው እሳቸውን የተኩት። የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA)ፕሬዚደንት ሚሼል ፕላቲንም ወዲያው ነበር ሥልጣናቸውን የለቀቁት። እናም የፊፋው ፕሬዚደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የሚመሩት ተቋምን ስም ለማደስ የዛሬ አራት እና ሦስት ዓመት ከአቃቤ ሕጉ ጋር በተደጋጋሚ ግንኙነት ፈጥረዋል በሚል ነው የተከሰሱት። ኹለቱም ክሱን አስተባብለዋል።   

ማንተጋፍቶት ስለሺ