1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያ ፖለቲካዊ ጥረት ወዴት?

ቅዳሜ፣ ሰኔ 26 2013

የሊቢያ አዲሱ የሽግግር መንግሥት ካለፈዉ የካቲት ወር ጀምሮ መጭዉ ታህሳስ  15 ለሚካሄደዉ ምርጫ የሃገሪቱን ለማረጋጋት እና አንድነት ለመፍጠር ሙከራ ላይ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3vxEN
Libyen Dbeibah wiedereröffnet die Straße Misrata - Sirte
ምስል Mahmud Turkia/Getty Images/AFP

መረጋጋት ወይስ ዳግም ዉግያ?

የሊቢያ አዲሱ የሽግግር መንግሥት ካለፈዉ የካቲት ወር ጀምሮ መጭዉ ታህሳስ  15 ለሚካሄደዉ ምርጫ የሃገሪቱን ለማረጋጋት እና አንድነት ለመፍጠር ሙከራ ላይ ነዉ። የዶቼ ቬለዉ የሰሜን አፍሪቃ ዘጋቢ ዮርገን ስትሪያክ ከስፍራዉ እንደዘገበዉ፤ የሽግግር መንግሥቱ ሃገሪቱን ለማረጋጋት እየሞከረ ባለዉ ሥራ በምዕራብ እና ምስራቃዊ ሊቢያ የሚገኙትን ተቀናቃኝ ኃይሎችን አሸንፎ  ማቅረብ ስለመቻሉ አጠያያቆ ነዉ።

የሊቢያ ጊዜያዊ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደሃሚድ ዲቢባህ የለበሱትን የጃኬት እጅ ሰብሰብ ሰብሰብ አድርገዉ ፤ ትልቅ ገልባጭ የግንባታ ስራ መኪና ላይ ወጡ። ከዚያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልባጩን መኪና እያሽከረከሩ  አንድ መንገድ የተዘጋበትን አግዳሚ በግንባታ ሥራዉ ተሽከርካሪ ጎትተት አድርገዉ መንገዱን ነጻ አደረጉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያደረጉት የሊቢያ የወደብ ከተሞች በሆኑት በሚስራታ እና በሲርት መካከል ያለውን አገናኝ ጎዳና ዳግም መከፈትን በምሳሌ አይነት ነገር ለማብሰር ነበር። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ርምጃ አገሪቱን ወደ ውህደት የሚወስድ ርምጃም ተደርጎ ተወስዶአል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብደሃሚድ ዲቢባህም ይህንኑ ነዉ ያሉት። 

Abdul Hamid Dbeibeh - Heiko Mass
ምስል byan Prime Ministry Press Office/AA/picture alliance

«መድረሻዉ አንድ እና አንድ ብቻ ነው። እርሱም ሊቢያ ሊቢያ አሁንም ሊቢያ ነው ፡፡ መረጋጋቱን እና ደህንነቱን ለማሳካት መሥራት አለብን ፡፡ ሊቢያ ለሁሉም እና ለሁሉም ትበቃለች።  እግዚአብሔር ሊቢያን ይታደግ። እግዚአብሔር ይባርክህ። እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ሲርት ላይ  እንገናኛለን።»

ጠቅላይ ሚኒስትር አብደሃሚድ ዲቢባህ ይህን የተናገሩት በሊቢያ የወደብ ከተሞች መካከል ለዓመታት የተዘጋ መንገድን ከከፈቱ በኋላ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲርት ላይ እንገናኝ ቢሉም እስካሁን ግን ሲርት ከተማ ላይ የመገናኘቱ ጉዳይ አልተሳካም። በሲርት እና በሚስራታ ከተሞች እንደምሳሌ የተከፈተዉ ጎዳናም፤ ለመንገደኞች ክፍት የሚሆነዉ ከአስር ቀን በፊት እንዳልሆነም ተነግሮአል። መንገዱ ነጻ ሊሆን ያልቻለዉ  በተቃዋሚው የጦር አበጋዝ  መሪ  በጀነራል ካሊፋ ሀፍታር የሚመራዉ አማፂ ሚሊሽያ መንገዱን ነፃ ባለማድረጋቸዉ ነዉ። 

በጀነራል ካሊፋ ሀፍጣር የሚመራዉ ሚሊሽያ የሊቢያን ምሥራቃዊ  ክፍል ተቆጣጥሮ ይዞአል። ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ጀምሮ ወዲህ ደግሞ ሚሊሽያዉ የመዲና ትሪፑሊን ምዕራባዊ ክፍል ተቆጣጥሮ መያዙ ተሳክቶለታል ማለት ይቻላል።  ቀደም ሲል በዚህ ቦታ ላይ በዓለም አቀፍ እዉቅናን ያገኘዉ የሊቢያ የሽግግር መንግሥት መኖርያ አካባቢ ነበር። በትሪፑሊ የሀፍታር ሽምቅ ተዋጊ ጦር እያጠቃ በመምጣቱ፤ የሊቢያ የሽግግር መንግሥት በጎርጎረሳዉያኑ 2020 ከቱርክ ወታደራዊ ርዳታ አግኝቶ ለመመከት መቻሉም ይታወሳል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በሊቢያ የሽግግር መንግሥት እና በሽምቅ ተዋጊዉ ሀፍጣር ኃይል መካከል  የኃይል ሚዛኑ እኩል ማለትም አንድ አይነት ሆነ። ከዝያም ነዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጎርጎረሳዉያኑ ጥቅምት ወር 2020 ዓመት በተወዛጋቢዎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲካሄድ ያደረገዉ። ሁለቱ ተወዛጋቢ ኃይላት ለአራት ወራቶች ምንም አይነት የተኩስ ድምጽን አላሰሙም። ከአራት ወራት በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደልሃሚድ ዲቢባህ የሚመራ የሊቢያ አዲስ የሽግግር መንግሥት ተመሰረተ። አዲሱ ዲቢባህ የሽግግር መንግሥት ደግሞ አሁን በመጭዉ ታህሳስ ወር በሊቢያ ነፃ ፣ ብሔራዊ ምርጫን ማረጋገጥ ይኖርበታል። በሊቢያ የሚካሄደዉ ምርጫ ሃገሪቱ ለዓመታት ከተዘፈቀችበት ጦርነት አዉጥቶ አንድነት እንዲመጣ ለማድረግ የሚካሄድ ሙከራ ነው ተብሎአል፡፡

የሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናጅላ ኧል ማንጎሽ ሁሉም የሊቢያ ኃይላት የአንድነትን ፍላጎት እንዲሁም ለወደፊቱ ብሔራዊ ራዕይ ማሳየት እንዳሚጠበቅባቸዉ አሳስበዋል ፡፡

Abdul Hamid Mohammed Dbeibah
ምስል Mohammed El Shaikhy/AFP/Getty Images

ግን የዉጭ ጉዳይ ኧል ማንጎሽ ማሳሰብያ ተፈፃሚ ይሆን? የሚታይ ይሆናል።  በሊቢያ የጦር አበጋዝ መሪ  በጀነራል ካሊፋ ሀፍታር ሚሊሽያዎች ወደ ወደብ ከተሞቹ የሚወስደዉ ጎዳና መዘጋት፤ ጦረኛዉ ኃይል ለጊዜያዊዉ የሊቢያ አስተዳደር ፖለቲካ ሂደት በቀላሉ መገዛትን አለመፈለጉን የሚያሳይ ነዉ ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ።   

ሊቢያ ወደ ሰላም እና አንድነት እንዳታገኝ ከተጋረጡባት ታላላቅ እንቅፋቶች መካከል በሊቢያ ያሉ የውጭ ኃይሎች ዋንኞቹ ናቸው፡፡ በምስራቅ የሃገሪቱ ክፍል ካሊፋ ሀፍታር ኃይል በሩስያ ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በግብፅ ይደገፋል፡፡ ቱርክ አሁንም ወታደራዊ ርዳታን በማድረግ  በምዕራብ ሊቢያ ከሚገኙ የታጠቁ ኃይላት ጎን ቆማለች። ጠቅላይ ሚኒስትር አብደሃሚድ ዲቢባህ እዚህ ላይ አንድ ዋንኛ የሚሉት ችግር ይታያቸዋል።

«ክልሉን ለማተራመስ የሚፈልጉ ኃይሎች ከአሁን በኋላ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ቦታ አንሰጥም። የሊቢያ መሬት እና የአየር ክልል ከሊቢያ መንግሥት በስተቀ ለማንኛውም ሀገር መጠቀምያ አይሆንም» 

Symbolbild Libyenkonferenz in Berlin
ምስል Suhaib Salem/REUTERS

ሊቢያ ራስዋ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ሚሊሻዎች፣ በጎሳ በማህበራት እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ነን በሚሉ ቡድኖች እየተዘወረች ነዉ። እነዚህ ኃይላት የሚረድዋቸዉን የዉጭ ኃይላት አሁን አንፈልጋችሁም ብለዉ ሊተዋቸዉ ዝግጁ ስለመሆናቸዉ ማንም እርግጠኛ አይደለም። ምክንያቱም እነዚህ ተደጋፊ እና ደጋፊ ኃይላት በሊቢያ ዉስጥ የራሳቸዉ ፍላጎቶች ስላላዋቸዉ ነዉ። በዚህም ምክንያት በሊቢያ ምርጫ ይደረጋል እስከተባለበት ቀን ድረስ ማለትም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሊቢያ ዉስጥ  ዳግም  ውጊያ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ተቀስቅሶአል፡፡

 

አዜብ ታደሰ / ዮርገን ስትሪያክ

ነጋሽ መሐመድ