1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያ ጎረቤቶች ጥሪ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 26 2013

በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ይታገዙ የነበሩት የሊቢያ አማፂያን የሐገሪቱን የረጅም ጊዜ ገዢ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ከስልጣን ካስወገዱ ከ2003 ወዲሕ ሊቢያ የተለያዩ የዉጪ ታጣቂ ኃይላት መፈንጪያ ሆናለች

https://p.dw.com/p/3zn5I
Libyen Fahne
ምስል Costas Baltas/REUTERS

ሊቢያ የሚዋጉ የዉጪ ታጣቂ ኃያላት በሙሉ ሰሜን አፍሪቃዊቱን ሐገር ለቅቀዉ እንዲወጡ የሊቢያ አጎራባቾች ጠየቁ።አልጀርስ-አልጄሪያ ዉስጥ የተሰበሰቡት የሊቢያ አጎራባችና የተለያዩ ማሕበራት ተወካዮች እንዳሉት ሊቢያ ዉስጥ ሠላም ለማስፈን የዉጪ ተዋጊዎች ከሐገሪቱ ለቅቀዉ መዉጣት አለባቸዉ።እስከ ትናንት ማታ ድረስ ለሁለት ቀን በተነጋገረዉ ስብሰባ ላይ የግብፅ፣የቱኒዚያ፣የሱዳን፣የቻድ፣የኒዠር፣ የሊቢያና የአስተናጋጅዋ የአልጄሪያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች፣በሊቢያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ፣የአፍሪቃ ሕብረትና የአረብ ሊግ ተወካዮች ተገኝተዋል።ተሰብሳቢዎቹ የሊቢያ ተቀናቃኝ ኃይላት በሐገራቸዉ ሰላም ለማስፈን ያደረጉትን ስምምነትና የቀየሱትን የጉዞ ካርታ እንዲያከብሩ አደራ ብለዋልም።የሊቢያ ተፋላሚ ኃይላት ባደረጉት ስምምነት መሠረት በመጪዉ ታሕሳስ የምክር ቤት እንደራሴዎችና ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ይደረጋል።የስብሰባዉ አስተናጋጅ የአልጄሪያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ራምታነ ላማምራ ከሊቢያዋ አቻቸዉ ነጂላ ኤል ማንጉስ ጋር ሆነዉ በስጡት መግለጫ እንዳሉት የዉጪ ኃይላት ከምርጫዉ በፊት ከሊቢያ መዉጣት አለባቸዉ።«የዉጪ ቅጥረኛ ወታደሮች፣አሸባሪዎችና መደበኛ ያልሆኑ ኃይላት የመዉጣታቸዉ ጉዳይ በጣም መሰረታዊ ጥያቄ ነዉ።ምርጫዉ ጥሩ ዉጤትና የሚያመጣዉና ሒደቱ የተሰካና አስተማማኝ የሚሆነዉም የዉጪ ኃይላት ሊቢያን ለቅቀዉ ሲወጡ ነዉ።ሊቢያ የነዚሕ ሕገ-ወጥ ኃይላት የመጀመሪያ ሰለባ ናት።እነዚሕ ኃይላት ግልፅና በተደረጃ መልኩ ካልወጡ በጎረቤት ሐገራት ላይ የሚያሳድሩት ስጋትም ከፍተኛ ነዉ።»
በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ይታገዙ የነበሩት የሊቢያ አማፂያን የሐገሪቱን የረጅም ጊዜ ገዢ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ከስልጣን ካስወገዱ ከ2003 ወዲሕ ሊቢያ የተለያዩ የዉጪ ታጣቂ ኃይላት መፈንጪያ ሆናለች።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈዉ ታሕስ እንዳስታወቀዉ ከ20 ሺሕ የሚበልጡ የዉጪ ቅጥረኛ ወታደሮችና ተዋጊዎች ሠፍረዋል።አብዛኞቹ የሶሪያ፣የሩሲያ፣የሱዳንና የቻድ ዜጎች ናቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ