1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህዳሴው ግድብና የምርጫ ዝግጅት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 8 2013

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ከወትሮው በተለየ የህዳሴውን ግድብ እና የምርጫ ዝግጅት ላይ በይበልጥ ያተኮሩበት ሰሞን ይመስላል ሳምንቱ። ግብጽና ሱዳን ተባብረው ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ እያሴሩ ነው የሚለው የጋራ ግንዛቤ ብዙኃኑን የግድቡ ሥራ እንዲፋጠን ሙሌቱም እንዲቀጥል የሚያበረታቱ አስተያየቶችን እንዲሰነዝሩ ጋብዟል።

https://p.dw.com/p/3s8Vj
Äthiopien Addis Abeba | Report | Grand Ethiopian Renaissance Dam
ምስል DW/N. Desalegen

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ኢትዮጵያ ስለግድቡ የውኃ ሙሌትና  የሙሌቱን አስተዳደር በተመለከተ ግድቡ ያሰጋናል ከሚሉት ሱዳንና ግብጽ ጋር ለመነጋገር እንደምትሻ አስፈላጊ መረጃዎችንም ለማጋራት ዝግጁነቷን ብትገልጽም ከሁለቱም ሃሳቧ ተቀባይነት አላገኘም። ሆኖም የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በቀጣይ 10 ቀናት ውስጥ የሦስቱን ሃገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች በዝግ ለመወያየት መጋበዛቸውን አስመልክቶ ንጉሤ ፋንታ በፌስቡክ፤ «ዝግ ውይይቱ ከአፍሪቃ አንድነት ማዕቀፍ ውጪ እንዲሆን ለምን ፈለጉ? ለሰላም ነው ወይስ በሌላ ሴራ ማኖ ሊያስነኩ አስበው ይሆን?» የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ፤ ኃይሉ ትካ በትዊተር፤ «ራሳቸውን አፍሪቃዊ አድርገው አያስቡም። ለዚህም ነው ውኃው አፍሪቃ ውስጥ ሆኖ እያለ ራሳቸውን ከአረብ ሊግ ድጋፍ የሚፈልጉት። በዚያም ላይ ተጨማሪ ገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ማግኘት እንዲችሉም ምዕራባውያንን በጉዳዩ ለማስገባት ይፈልጋሉ» የሚል አስተያየት አስፍረዋል።

አህመድ ሰይድ በበኩላቸው፤ «ሱዳን በአሁኑ ወቅት በህዝብ የተመረጠ መንግሥት የሌላት ሀገር ሆና ሳለ እንዲሁም ድንበር ተሻግራ የኢትዮጵያን መሬት በወረር ይዛ በወቅታዊው የህዳሴ ግድቡ ሁኔታ በመሪዎች ደረጃ እንወያይ የሚለው ጥያቄዋ ከሞራል፣ ከፖለቲካና ከማኅበራዊ ጉዳዮች አንጻር በጥርጣሬ ሊታይ፣ ሊፈተሽና ሊመከርበት ይገባል። ምክንያቱም አጀንዳው የራሷ የሱዳን ላይሆን ይችላልና» በማለት ጥርጣሬያቸውን አካፍለዋል። አባነጋ ቶል ደግሞ ጭራሽ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትርን በዝግ እንደራደር ጥያቄ አልተቀበሉትም፤ «ሀምዶክ ያቀረቡትን የዝግ ድርድር ኢትዮጵያ መቀበል የለባትም፤ ከፈለጉ በአፍሪቃ ሕብረት በኩል ብቻ መሆን አለበት። ግብጽና ሱዳን የአፍሪቃ ሕብረትን ከአደራዳሪነት በማውጣት ድርድሩን ወደተመድ ለመውሰድ ነው» ይላሉ። አሜን በል ስሜ ደግሞ፦ «ሱዳን እና ግብጽ የህዳሴውን ግድብ ወይም የአባይ ወንዝን ፕሮጀክት አስመልክቶ የጦርነት ነጋሪት መምታታቸውን ማቆም አለባቸው። የአባይ ተፋሰስ ሃገራት በሙሉ በትብብርና በመረዳዳት ውኃውን ለመጠቀም መብት አላቸው» በማለት ያስጠነቅቃሉ።

Symbolbild Twitter
ምስል Imago/xim.gs

ኦስካር በሽር የሱዳን አቋም ያበሳጫቸው ይመስላል። «ሱዳን ከሀዲ ሆና ነው የቀረበች፤ ስለዚህ ምክረው ምከረው ካልሆነ መከራ ይምከረው የሚለውን የአማርኛ ፈሊጥ ተግባራዊ ማድረግ ነው።» እንደእሳቸው።

በትዊተር አስተያየታቸውን በእንግሊዝኛና በአማርኛ አዛንቀው ያካፈሉት ሶልያና እንዲህ ይላሉ፤ «እና ኢትዮጵያውያን የሀገራችን ኩራት የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ባለቤቶችና ለጋሾች ነን። ግድቡን እየገነባን ነው፤ እናጠናቅቀዋለን።» 

ዳዊት ሚካኤል በበኩላቸው፤ «ለሺህ ዓመታት ግብጽ አባይን ተቆጣጥራ ነበር። ኢትዮጵያ 85 በመቶውን የአባይ ውኃ ታዋጣለች፤ ሆኖም በለውጡ የምታገኘው የለም። ግብጽ ምንም ሳታዋጣ 100 በመቶ ትቀበላለች። 60 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኤሌክትሪክ አያገኙም። ከኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ጎን ቁሙ» በማለት በእንግሊዝኛ በጻፉት አስተያየታቸው ሌሎችንም ጋብዘዋል።

የአባይ ግድብ ጉዳይ በኢትዮጵያውያን ብቻ የሚደገፍ አለመሆኑን ናይጀሪያዊው ኢድሪስ ኤም ሳኒሲ  በትዊተር ያጋሩት አስተያየት ያሳያል። «ግብጽ እና ሱዳን ለአፍሪቃውያን ችግር አፍሪቃዊ መፍትሄ የሚለውን መመሪያ ውድቅ አድርገዋል። ለእነሱ ቀለል ያለ መልእክት አለኝ። የአባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ እናም የህዳሴ ግድቡን እንሞላዋለን።፤ ግድቡ የእኔ ነው፤ ግድቡ ይሞላ፤ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!» ብለዋል ናይጀሪያዊው ኢድሪስ። በርካቶች ይኽን አስተያት በመደገፍ ተቀባብለውታል። ናይጀሪያዊው አስተያየት ሰጪ በአባይ ግድብ ዙሪያ ለበርካታ ጊዜያት በd,ጋጋሚ አስተያየት በመስጠት ይታወቃሉ።

ለናይጀሪያዊው ምላሽ የሰጡት ዳዊት ታደሰ፤ «የአፍሪቃ ሕብረት የኢትዮጵያን አቋም አድንቆ ተመጣጣኝ ምላሽ ይሰጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ያቋቋመችው ተቋም ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ከድቷታል። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያውና የገጠማቸውን ፈተና ብቻቸውን ተጋፍጠው ወጥተዋል። አባት እናቶቻችን እንዳደረጉት አስፈላጊ ከሆነ ብቻችንንም ቢሆን ወደፊት እናመራለን።»

Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance

ዶክተር አበበ ከበደ በትዊተር ይህን መረጃ አጋርተዋል። «ግብጽ በውጭ የሚኖሩ ዜጎቿ የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ የተመለከተ ተቃውሞ እንዲያካሂዱ ጠርታለች። ኢትዮጵያም እንዲህ ማድረግ አለባት። ማን ይሆን ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው? የህዳሴው ግድብ በአንዳንድ ሃገራት የምርጫ መቀስቀሻ ርዕሰ ጉዳይ እየሆነ ነው። ለምርጫው ተዘጋጁ።»

 

በግንቦት መጨረሻ በሚካሄደው ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ለተመዘገቡ መራጮች ካርድ መሰጠት መጀመሩ ተሰምቷል። የማኅበራዊ መገናኛው ተጠቃሚዎች አስተያየት ሲቃኝ የምርጫው ዝግጅት ሁለት አይነት ስሜትን ያዘለ ይመስላል። ናፍቆት በትዊተር አማርኛና እንግሊዝኛ አዛንቀው በጻፉት አስተያየት፤ «እስቲ በዙሪያችሁ ያሉ ሰዎችን ስለመጪው ምርጫ ያላቸውን ስሜት ጠይቁ። እኔ በአካባቢዬ ካዋራኋቸው እንደተረዳሁት ምን ልዩነት ያመጣል የሚል አስተሳሰብ አለ። ማን አለ የሚመረጥ ብለሽ ነው፤ የሚለው በብዙዎች አእምሮ ውስጥ አለ። ኡፍ,,,» ሲሉ፤ ራህመት ያሲን ደግሞ በፌስቡክ፤ « እኔ የገረመኝ ምርጫ ምርጫ ይባላል። የትኛው ምርጫ ነው? ዘንድሮ ግንቦት ነው ወይስ በሚቀጥለው? አልገባኝም። ምክንያቱም ስለሌላው እንጃ እኔ ባለሁበት ደሴ ላይ ግን እስካሁን ድረስ የምርጫ ካርድ የወሰደ ሰው የለም። አንዳንድ ሰዎች ካርድ ለማውጣት ሲጠይቁ ገና ነው እየተባሉ ይመለሳሉ» ብለዋል። ምርጫው ሰባት ሳምንታት ብቻ እንደቀረው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድረ-ገጽ ያሳያል።

Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Nicolas Economou/NurPhoto/picture alliance

ሰሎሞን ቱራ ደግሞ፤ «የምርጫ ካርድ መስጫ ጣቢያዎችን የሥራ ስርዓትን ከማራዘም ጀምሮ በተሰጠው የሥራ ሰዓት በአግባቡ አገልግሎት መስጠታቸውን በመከታተል መራጩን የሕዝብ ፍላጎትና ቁጥር መጨመር ይቻላል ብዬ አምናለሁ» ነው የሚሉት። የምርጫ ካርድ ለመውሰድ ሞክረው ያጋጠማቸውን የገለጹት ደግሞ ቤተልሔም ነጋሽ ናቸው። «የምርጫ ካርድ ለመውሰድ በየትኛውም ጣቢያ ይቻላል የሚል መረጃ ቢኖርም ሰፈሬ ያለው ይሄ የምርጫ ጣቢያ እዚህ ለመኖርሽ ምስክሮች አምጪ ብሎኛል።» ካሉ በኋላ ለመሆኑ አመቺ ያልሆኑ ነገሮችን መፍጠሩ እንዴት ታይቷል» በማለት ጠይቀዋል። «በአሁኑ ወቅት የመራጮች ምዝገባ በጣም ደካማ ነው» ያሉት ደግሞ ዳኛቸው ዳንጊሶ ናቸው። «የጊዜ ልዩነት እንዲኖር ማድረጉ በጣም ጠቃሚ ነው» ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል። ነብዩ ወርቁ ደግሞ፤ «ምርጫ ቦርድ በአዲስ አበባ ሊከፍታቸው የወሰናቸው የምርጫ ጣቢያዎችን በከፊል ነው የከፈተው። ሌላው የምርጫ ካርድ ለመውሰድ ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲኼድ አብዛኞቹ ማለት ይቻላል ሠራተኛውን ማኅበረሰብ ያማከሉ አይደሉም። ከረፋዱ 4 ሰዓት እንዲሁም ከሰዓት ቀደም ብለው በ10 ሰዓት ነው የሚዘጉት፤ ከላይ በተጠቀሱት የምርጫ ቦርድ ቸልተኝነት ላይ የህዝቡ ዳተኝነት ተጨምሮበት አሁን ላለው ዝቅተኛ ተመዝጋቢ ቁጥር ዳርጎናል» ይላሉ።

ኤፍሬም ሀብተወልድ ደግሞ በትዊተር ጥያቄ ነው ያቀረቡት፤ «ማንኛውም ሰው አዲስ አበባ ላይ መወዳደር ይችላል እየተባለ ነገር ግን ወደ ክልሎች ስትሄዱ ግን የአካባቢው ተወላጅ መሆን አለባችሁ፤ ወይም ቋንቋውን ማወቅ አለባችሁ መባሉ እንዴት ነው? አሁንስ ምርጫ ልመርጥ ነው?» በማለት ይጠይቃሉ።

Äthiopien Birtukan Mideksa UDJ Partei
ምስል Yohannes Geberegziabher/DW

በጸጥታ ችግር ምክንያት 4126 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደባቸው እንዳልሆኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳወቀውም በዚህ ሳምንት ነው፤ አብዲ ማን በፌስቡክ፤ «ከ50 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች 25151 ማለትም 50 በመቶ ብቻ ሥራ በጀመሩበት፤ በተጀመረባቸውም አነስተኛ ሰው ብቻ መመዝገቡ ከቀረው የመራጮች ምዝገባ ቀናት አንጻር የተለየ ስትራቴጂ ካልተተገበረ ምርጫውን ማካሄድ አስቸጋሪ ይመስለኛል» ነው የሚሉት።

«ለመሆኑ ጥያቄውን ወደ መንግሥት ከማዞር ይልቅ የምርጫ ቦርዱ ምርጫውን ለማካሄድ የጸጥታ ይዞታን ቀዳሚ ጉዳይ አድርጎ ያላቀረበው ለምድነው?» የሚሉት ደግሞ አቤል አስራት ናቸው በትዊተር። ሳሚያ ሳሚያም የጸጥታ ጉዳይ ነው ያሳሰባቸው። «መጀመሪያ ሰላምና ጸጥታ ይስፈን ለመምረጥ እንዲችል ህዝብ» ይላሉ በፌስቡክ። ማሪ ማሪ በበኩላቸው ወደጸሎቱ አድልተዋል። «ይኼን ምርጫ በሰላም አሳልፍልን ፈጣሪ ሆይ!»

ዜጎች የመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማኅበራዊ መገናኛ ገጾቻቸው መጠየቃቸውን አስመልክቶ፤ መሐመድ ሁሴን፤ «አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ወይም አባላት ታስረውና ጽሕፈት ቤቶቻቸው ተዘግተው፤ ደጋፊዎቻቸውም እየተሳደዱ፣ እየተሰቃዩ ወይም ታስረው ወይም ተገድለው ማንን እንምረጥ? ለአንድ ዜጋ መምረጥ መብት ነው ወይንስ ግዴታ?» በማለት ሲጠይቁ፤ ጌች ድሪባ ለታም፤ «ከአንድ ነገር ምኑን ነው የምመርጠው?» ብለዋል።

Symbolbild Facebook Ausfall 27.01.2015
ምስል Reuters/D. Ruvic

ጥላሁን ፀጋ በበኩላቸው፤ «ሲመስለኝ የምርጫ ካርድ ወስጃለው እያሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ፎቶ ከለጠፉ እና ፎቶዎቹን ላይክ ካደረጉ ሰዎች ውጭ ሌላው ሕዝብ የምርጫ ካርድ አልወሰደም። ምርጫ ካርድ አውጡ እያሉ ከመወትወት ይልቅ ህዝቡ ለምን ዝም አለ ብሎ መጠየቅ ይሻላል» ብለዋል። ፍሰሀ አስመላሽ ደግሞ፤ «ሄጄ ተመዘገብኩና ካርድ ወሰድኩ። መዝጋቢውን የሚወዳደሩት ፓርቲዎች የትኞቹ ናቸው? በዚህ ጣቢያ የሚወዳደሩትን አስቀድሜ ባውቅ የምመርጠውን ፓርቲ ከወዲሁ መለየት እችላለሁ አልኩት። መዝጋቢው ቢያንስ ብልጽግና ፓርቲ አለ ሲል መለሰልኝ» በማለት ገጠመኛቸውን አጋርተዋል። ቆሱ ካቤራ ቆሴ ካቤራ የሚል የፌስቡክ ስም ያላቸው ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ የሚያሳስባቸው ሌላ ነው። «እናንተ ሰዎች ያማችኋል እንዴ? የወሰንና የማንነት ጥያቄ ሳይመለስ እኛ ጋር ድርሽ የለም። ቆሴ፣ ዴያስ፣ ባራዋ፣ ቡጫ ወደ ሀድያ ዞን ሳይካለል ምንም ምርጫ አያስፈልግም» ይላሉ።

ሰሎሞን አንበሳውም በፌስቡክ፤ «እንኳን ለምርጫ ህዝባችን አንድ ቀን እንኳን ሰላም ማደር አልቻለም፤ ወለጋ ህዝብ እያለቀ ነው ምርጫ ቅንጦት ነው። ጠቅላላ ህዝባችን የሀገር ውስጥ ስደተኛ ሆኗል። ሕግ የለም መንግሥት በተለይ በኦሮሚያ ላይ ወለጋና ጉምዝ ሕግ ማስከበር አልቻለም። ሰላም ያለው ከአፋር ግጭት ውጭ ሶማሌና አማራ ክልል፤ ደቡብ በከፊል አንጻራዊ ሰላም አለው። ኦሮሚያ የደም መሬት ሆኗል። ወለጋ ላይ ህጻናት እያለቁ ነው ኦነግ በሚል ሽፋን፤ ያሳዝናል» ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተዋል። የልኩ ታየ ሃሳብ ግን ይለያል። «መቸም ምርጫው አይካሄድም ማለት ሌላ ዓመት በህዝብ ያልተመረጠ ሥርዓት ሊቀጥል ነው። ይኽ ደግሞ ችግሩን አይቀርፍም ቢያብሰው እንጂ፤ እናም ምን ልጅ ነው የሰጡትን ይዞ ,,, እንዲሉ ያለችዋን ምርጫ ጣቢያ ላይ የሚቻለውን አድርጎ ሀገር ማዳን ከተቻለ እሰየው ነው ጎበዝ!» ሲሉ አግባቢ ያሉትን ሃሳብ ሰንዝረዋል። አብራር ሱሉማን በትዊተር፤ «በ97 ምርጫ ኢህኣዴግ ባይደናበር ኖሮ ያሸንፍ ነበር? ብዬ እጠይቃለሁ። ብልጽግና ተመሣሣይ ስህተት እንዳይፈጽም ካድሬዎቹን ማረጋጋት ኣለበት። ሰላምና መረጋጋት ከሌለ እውነት ቢያሸንፍም የሚያምነው የለም፡፡ በተለይ የማንነት ተኮር ጥቃት ማስቆም አለበት! በኣንዳንድ ሸገር ዙሪያ ባሉ የምርጫ ወረዳዎች ካድሬዎች 'ምንም እንዳታጭበርብሩ ተብሎ ተነግሮናል' የሚል መረጃ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ መበረታታት ያለበት ነገር ነው፡፡ ጥያቄው ካዲሳባ ውጭስ የሚለው ነው?»

ኢትዮጵያዊ ነኝ በሚል ስም ለእሳቸው መልስ የሰጡት ሌላኛው የትዊተር ተጠቃሚ፤ «ብልጽግና ቢሸነፍም ቢያሸንፍም የማንነት ጥቃት በቀላል ይቆማል ብሎ ማሰብ ይቸግራል፤ የተዘራው እስኪነቀል የካድሬዎች መረጋጋት አስፈላጊነቱ እንዳለ ሆኖ።» ብለዋል። እኛም በዚህ የዕለቱን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት እናብቃ።