1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

ገብረ እግዚያብሔር ገብሬ: የሄርማን ጌማይነር አዋርድ ተሸላሚ

ዓርብ፣ ነሐሴ 15 2012

ገብረ እግዚያብሔር ገብሬ በቅርቡ የዓለም አቀፉ የሄርማን ጌማይነር አዋርድ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፣ ገና በህፃንነቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በ 77 ዓ ም በነበረው ረሀብ ወላጆቹን ያጣው ገብረ እግዚያብሔር SOS በሚባለው የበጎ አድራጊው ድርጅት ስር ነው ያደገው። የትምህርት እና የስራ ስኬቱ ዛሬ ለበርካታ ወጣቶች ዓርዓያ ለመሆን አብቅቶታል።

https://p.dw.com/p/3hJQ1
USA Texas | Hermann Gmeiner Award 2020 | Gebre-egziabher
ምስል privat

ገብረ እግዚያብሔር ገብሬ

ገብረ እግዚያብሔር ገብሬ ዛሬ የ 36 ዓመት ወጣት ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ቴክሳስ ግዛት ውስጥ ይኖራል። የሚሰራው ደግሞ በኃይል ማመንጫ ንግድ ዘርፍ ላይ ነው። ዛሬ ተምረው ጥሩ ቦታ ከደረሱ ኢትዮጵያውያን ተርታ ይሰለፋል። ያደገው SOS በሚባለው የበጎ አድራጊው ድርጅት ውስጥ ነው። ታሪኩን መለስ ብሎ ያስታውሰናል። « SOS የገባሁት የአምስት ወር ልጅ እያለሁ ነው። ብዙ ሰው እንደሚያውቀው በ 19 77 ዓ ም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ድርቅ ተከስቶ ስለነበር በዛ ምክንያት አባት እና እናቴን አጥቼ ነበር።» እዛ ከገባ በኋላም ጥሩ አስተዳደግ እንዳገኘ ገብረ እግዚያብሔር ይናገራል።  በትምህርቱ ጥሩ ውጤት በማግኘቱም ጋና ሄዶ እንዲማር እድል ያገኛል። ኃላም በዩናይትድ ስቴትስ ነፃ የትምህርት እድል ያገኝና ከዝነኛው ሀዋርድ ዮንቨርስቲ በክብር ይመረቃል። ስራም ይይዝ እና እዛው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ኑሮውን ይመሰርታል። ይሁንና ሌሎች ልጆችን ለመርዳት ይበልጥ ቆርጦ ይነሳል። « እኔ እዚህ ደረጃ እንድደርስ ያደረገኝ የሌሎች በጎ አድራጎት ነው። እናኔ ምስጋናዬን መስጠት የምችለው ሌሎች ን ሳግዝ ነው።እና ያደኩበት SOS ሁለት ሰዎችን እደግፋለሁ።» ይህንንም ቁጥር ከፍ ለማድረግ እና ያገዘውን ድርጅት መልሶ ማገዝ ይሻል።

Michaela May besucht SOS-Kinderdörfer in Ghana Bildungschancen in der globalisierten Welt
የ SOS የህፃናት መንደር ጋናምስል dpa

አቶ ሳህለ ማርያም አበበ በ SOS ህፃናት መንደሮች ኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳሬክተር ናቸው። ገብረ እግዚያብሔርን ታታሪ ፣ ሰው አክባሪ እና ተወዳጅ ወጣት ነው ሲሉ ይገልፁታል። « ገብሬ የትምህርት እረፍት በሚኖረው ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ወደ አደገበት ህፃናት መንደር ሄዶ ታናናሽ ወንድም እና እህቶቹን በስነ ምግባር ኮትኩቶ ለማሳደግ ይሳተፍ ነበር።» ይላሉ የድርጅቱ ዳሬክተር።

የሄርማን ጌማይነር ሽልማት ምን አይነት ሽልማት ነው?

 «የሄርማን ጌማይነር ሽልማት በየሁለት ዓመቱ የሚመጣ ሽልማት ሆኖ በSOS መንደሮች ውስጥ ያደጉ እና ራሳቸውን የቻሉ ልጆች የህይወት ስኬትን፣ የድርጅቱን አላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ልጆችን እውቅና የምንሰጥበት መንገድ ነው። » ይላሉ አቶ ሳህለ ማርያም።

ከግል ስኬቱ ባሻገር ገብረ እግዚያብሔርን የሄርማን ጌማይነር አዋርድ ተሸላሚ ለመሆን ያበቃው ሌላው ስራው ልዑል ግርማይ ፋውንዴሽን ውስጥ ያለው ተሳትፎ ነው። ወጣቱ የፋውንዴሽኑ ፕሬዚዳንትም ነው። « የኮምፒውተር ማዕከል እና ቤተ መፅሐፍት ስራዎች ላይ እስካሁን ጋና ፣ ጋምቢያ እና  መቀሌ ከተማ ውስጥ ሰርተናል ይላል ወጣቱ። ልኡል ግርማይ ደግሞ አብሮት SOS ውስጥ ያደገ እና ታላቁ የነበረ ተማሪ ሲሆን በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበር ይላል። «በአጋጣሚ በሞት ሲለየን በጣም አዝነን ነበር ። ስለሆነም እሱን ለማስታወስ ስንል አብረን ያደግን እና ቤተሰቦቹ ሆነን ያቋቋምነው ነው።»

70 Jahre SOS-Kinderdörfer - SOS-Kinderdorf in Thailand
ሄርማን ጌማይነር ታይላንድ ውስጥምስል picture-alliance/dpa/SOS-Kinderdörfer

በጎ አድራጊው SOS ድርጅት በ 136 ሀገራት የሚንቀሳቀስ ድርጅት እንደሆነ አቶ ሳህለ ማርያም  ገልፀውልናል። በድርጅቱ ስር ኢትዮጵያ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናት እና ወጣቶች በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ድጋፍ ያገኛሉ። « ለምሳሌ ገብሬ ያደገበት የSOS ህፃናት መንደሮች ውስጥ ወደ 3000 የሚሆኑ ህፃናት እና ወጣቶች ይገኛሉ። ከዛ ውጪ ደግሞ  በተለያዩ ተቋማት ውስጥ እንዲያድጉ የምናደርጋቸው ወደ 26000 የሚጠጉ ህፃናት እና ወጣቶች አሉ» ይላሉ።  ገብረ እግዚያብሔር ባደገበት ተቋማት ውስጥ ድርጅቱ የሚመሰርተው ቤተሰብ የሚኖር ሲሆን ለልጆቹም  የSOS እናት የምትባል እናት ያገኛሉ። «እሷም አንድ ቤት ውስጥ ስምንት ልጆችን ታሳድጋለች። ስለዚህ ፍቅር እየሰጠች ታሳድጋቸዋለች። እናት ትሆናቸዋለች » ይላሉ አቶ ሳህለ ማርያም። ገብረ እግዚያብሔርም በዚህ ይስማማል። ምንም እንኳን ወላጅ እናትና አባቱን ገና በህፃንነቱ ቢያጣም በድርጅቱ ስር ሆነው ያሳደጉት እናቱ ፍቅር ሰጥተው ማሳደጋቸው ጥሩ ቦታ እንዲደርስ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን በሙሉ ልብ  ይናገራል። «  የእናት ፍቅር ሰጥታ ነው ያሳደገችኝ። በጣም ጥሩ አክብሮት አለኝ። በጣም ጥሩ ግኝኑነት አለኝ። በየሳምንቱ ነው በስልክ የምናወራው።  በህይወቴ ትልቅ የሚባሉ ክስተቶች ላይ ስመረቅ፣ ሳገባ፤ ልጅ ተወልዶ ክርስትና ላይ ትመጣለች።» ይላል ገብረ እግዚያብሔር ገብሬ።

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ