1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሰላም ጥሪ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 26 2014

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በትግራይ ክልል የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ባለፈው ሳምንት ያስተላለፉት የሰላም ጥሪ እንዳስደሰተው ገልጿል። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዛሬ ባስተላለፈው የሰላም ጥሪ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱት ችግሮች ቀድሞውኑ በሰላምና በውይይት እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካ መቅረቱን ጠቅሷል።

https://p.dw.com/p/4GKHS
Logo | Inter Religious Council of Ethiopia
ምስል Inter Religious Council of Ethiopia

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሰላም ጥሪ

በፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ሕወሓት የተጀመረው ሰላም የማስፈን ሂደት  ተቋርጦ ዳግም ጦርነትና ዉጊያ መቀስቀሱ እንዳሳዘናቸው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ የሃይማኖት መሪዎች ገለፁ። "ለሰላም ቅድመ ሁኔታው ሰላም ብቻ ነው"  ያለው ጉባኤው የፌዴራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመለሱ ተማጽኗል። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በትግራይ ክልል የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ባለፈው ሳምንት ያስተላለፉት የሰላም ጥሪ እንዳስደሰተው ገልጿል። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዛሬ ባስተላለፈው የሰላም ጥሪ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱት ችግሮች ቀድሞውኑ በሰላምና በውይይት እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካ መቅረቱን ጠቅሷል። የሃይማኖት አባቶች መቀሌ ከተማ ድረስ በመሄድ መክረው ዘክረው "ታሪክ የማይዘነጋው" ጥረት ተደርጎ እንደነበርም ገልጿል።የሁሉም የሃይማኖት ተቋማት አቋም የሆነውን የሰላም ጥሪ በንባብ ያቀረቡት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ "ወደ ተሻለ መረጋጋት አድጎ ሁለቱም አካላት ለሰላማዊ ድርድር እየተዘጋጁ የነበረው ሁኔታ ተቀይሮ ዳግም ጦርነት እና ውጊያ በመቀስቀሱ ከልብ አዝነናል፣ ደንግጠናልም" ብለዋል።
ጉባኤው ስምንት ዋና ዋና መልዕክቶችንና ምክሮችን ያስተላለፈ ሲሆን ቀዳሚው ወደ ሰላማዊ ድርድሩ መመለስን የሚጠይቀው ነው። ቀሲስ ታጋይ ታደለ "አሁንም ጦርነቱን ለማቆም ተጀምሮ የነበረው ሰላማዊ የድርድር ጥረት እንዲቀጥል አበክረን እንጠይቃለን" ነው ያሉት። በጦርነት ውጊያ ከወታደራዊ ዒላማ ውጪ የሆኑ የሲቪል አገልግሎት ሰጪ እና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ንፁሀን ዜጎች አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው የጠየቀው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ታዳጊ ሕፃናትን ለወታደራዊ ዘመቻ ማሰለፍ እንዲቆምም አሳስቧል።
በትግራይ ክልል የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ባለፈው ሳምንት ያደረጉት የሰላም ጥሪ እንዳስደሰተውም የጉባኤው ፀሐፊ በተለይም ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። የሀገሪቱ ወቅታዊ ፈተና በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን የገለፀው ጉባኤው "ኢትጵያዊያን ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች ቅስቀሳዎችን እንዲመዝኑ እና ከማንኛውም ፓርቲ እና የፖለቲካ ማሕበር ይልቅ የሀገርን ዘላቂ ጥቅም በማስቀደም የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ" ጠይቋል። ቀሲስ ታጋይ ታደለን በትግራይ ክልል የኦርቶዶክስ እና የእስልምና ሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የራሳቸውን ተቋም ማቋቋማቸውን ከዚህ በፊት መግለፃቸውን በተመለከተ የጉባኤውን አስተያየት ጠይቀናቸዋል። "በአንድ ሀገር ውስጥ እስካለን ድረስ ሁለት 'ላይሰንስ' ሊኖር አይችልም" ብለዋል። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት የተቋረጠው የሰላም ድርድር እንዲቀጥል እና ኢትዮጵያን የገጠማት ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ጥረቱን ማገዛቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ